2ኛ ጢሞቴዎስ,  Articles,  Blog,  ምጋቤ መልእክታት,  አዲስ-ኪዳን,  የመጽሐፍ-ጥናት,  የአዲስ ኪዳን ሐቲት

የዐደራ ኑዛዜ ክፍል አንድ፡ በወንጌል ዙሪያ የተደራጀ ሕይወትና ማንነት

[ይህ መጣጥፍ አስቀድሞ በታርጌት መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ ያለ ፈቃድ በወረቀት ላይ ማሳተም ክልክል ነው]

“ባሮክ ሆይ…ታዲያ፣ ለራስህ ታላቅ ነገር ትሻለህን?”
ይህ ጥያቄ ከሞላ ጎደል የዛሬ 2,600 ዓመት በፊት እጅግ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ ይኖር ለነበረ ለአንድ አገልጋይ፣ ያህዌህ ያቀረበለት ጥያቄ ነበር (ኤር 45)። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የታላቁ የናቡከደነዖር ሠራዊት ቅድስቲቱን ከተማ ይከባል። የጦር ጀነራል ፈረሶች በንጉሥ ከተማ ሲፋንኑ ይደመጣሉ። አሕዛብ የተቀደሰውን ርስት ያረክሳሉ። ይሁዳም ትሞታለች። እናስ፣ እንዲህ ዓይነት የፍርድ ትንቢት በገዛ እጆችህ በብራና ላይ እየከተብኽ፣ በልብህ የሞላው መሻት ግን “ለራስህ ታላቅ ነገርን” መመኘት ነውን? በሌላ አባባል፣ “በውኑ ሕይወትህ በቅደም ተከተል ተደራጅቷልን?” የሚል ይመስላል። ልክ ዴማስ ከጳውሎስ ጋር እንደ ተነጻጸረ ሁሉ፤ ባሮክንም ከኤርሚያስ ጋር በማነጻጸር “ለራስህ ታላቅ ነገር” አትሻ ይለዋል፣ ይህ ወቅት ከአንድ ታማኝ አገልጋይ መስዋዕትነት የሚጠበቅበት ዘመን ነውና።

በተመሳሳይ መልኩ፣ የይሁዳ ዕጣ ፈንታ ሞት መሆኑ የተወሰነው በ586\87.ል.ክ ላይ የናቡከደነጾር ሠራዊት ኢየሩሳሌምን በመሸገበት ቀን፣ አሊያም ከ4 ወር በኋላ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች አፈራርሶ፣ የቃል ኪዳኑን ሕዝብ በማረከበትም ቀን አልነበረም (2ኛ ነገ 25:17)። ነገሮች ላይስተካከሉ መበላሸት የጀመሩት ከመቶ ዓመት በፊት በዘመነ ምናሴ ነበር (697–687 ቅ.ል.ክ.)። የመጽሐፈ ነገሥት ጸሐፊ፣ “ይህ ሁሉ ጥፋት በይሁዳ ላይ ለምን ደረሰ?” ብሎ አንባቢው እንደሚጠይቅ ተረድቶ፣ “ምናሴ ስላደረገው ኃጢአት ሁሉ…በይሁዳ ላይ ሆነ” ይላል። ይህም የምናሴ ባቡር (የይሁዳ ሕዝብ) ላለፈው አንድ መቶ ዓመት ግምባሩን ወደ ጥፋት አዙሮ እየገሰገሰ ነበር ማለት ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን አርቀው የሚያዩ ነቢያት “ኧረ ኪዳን ፈረሰ” ብለው ደረት ሲደቁ፣ ሙሾ ሲያወርዱ፣ ጆሮ ያለው አድማጭ ቢኖር በማለት አንዳንዴ እንደ እብድ እርቃናቸው ሲሆኑና አንዳንዴም እንደ ጉበኛ ሲያስጠነቅቁ አድማጭ አልነበራቸውም። ነቢዩ ኤርሚያስ ታዲግ ወጣት ሳለ፣ ሕዝቅኤልም እንዲሁ ገና ጨቅላ እያለ በመሃል የተነሳው የኢዮስያስ (640609 ቅ.ል.ክ.) ታላቅ መንፈሳዊ ተሓድሶ እንኳ የምናሴን ባቡር መቀየስ አልቻለም። ምናልባት ይህ “የብሉይ ታሪክ ነው” በማለት ራሳችንን ልናጽናና እንሞክር ይሆናል። ሆኖም ግን የወንጌል ባለ አደራዎች ትውልድን የሚያጠፋ መራራ ሥር በቅሎ ብዙውን ሳይመርዝ አስቀድመው የሚያዩ መሆን አለባቸው። ሞት ፊት ለፊት የተጋረጠ ዕለት፣ “ሞት መጣ” ማለት ምን ፋይዳ አለው? ዓይንና ግንባር የሌለው ክህደት፣ የእውነት ዐምድና መሠረት ቤት ውስጥ ተንሰራፍቶ ሲቆም “አበስኩ ገበርኩ…ኑፋቄ! ኑፋቄ!” ብንል “አስተዋይ” አያስብለንም። ባለ ዐደራዎችማ፣ ፈጽሞ አይደለንም። ነገር ላይጠገን ከመበላሸቱ በፊት አስቀድሞ ማስተዋል፣ በትንሹ ከባለ ዐደራዎች የሚጠበቅ ግዴታ ነው። የቆምንበት ጎዳና የት እየወሰደን እንደሆነ ቆም ብለን ካልተገነዘብን፣ ዐደራን በከንቱ ተቀብለናል። ይህ የይሁዳ አቅጣጫ ወደ ሞት እና ወደ ሞት ብቻ እንደሚገሰግስ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረው የምናሴ ወላጅ አባት ሕዝቅያስ ሲመልስ፡ “የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው” ሲል ይደመጣል (ኢሳ 39:8)። ይህን ምላሽ የሚያደምጥ ሁሉ መቼም በግራ መጋባት ፊቱ የማይጨማደድበት ሰው አይኖርም። ይህ ንጉሥ በ722 ቅ.ል.ክ. እሥራኤል በሰልመናዘር ተመሽጋ በዳግማዊ ሳርጎ (2 ነገ. 17:6-23) ድምጥማጧ ሲጠፋ የተመለከተ ሰው ነበር። “ንጉሥ ሆይ እንዴት?” ብንለው ምላሹ “በዘመኔ ሰላምና ጸጥታ ከኖረ ዘንድ!” ምን ቸግሮኝ ማለቱ ይመስላል። አንዱ “ለራሱ ታላቅ” ነገር ይመኛል። ሌላው ደግሞ “በገዛ ዘመኔ ሰላም ከሆነ” ምን ገዶኝ ይላል። የወንጌል ባለዐደራ ማኅበርተኞች ግን እይታቸውና ሕይወታቸው፣ ትምህርታቸውና ኑሯቸው በወንጌል የተቃኘ ከመሆኑ የተነሳ፣ በየትኛው ሰዓት ዝግጁ ናቸው። “ከራስ በላይ ንፋስ” በሚለው ብሂል ግድ-የለሽ ሆነው ሊመላለሱ አይችሉም። ወደድንም ይሁን ጠላን የተቀበልነው ዐደራ በጌታ ዙፋን ፊት ይሁን በታሪክ ያስጠይቀናል።
 

ሕይወትን የሚቃኝና በቅደም ተከተል የሚያደራጅ መልዕክት

2 ጢሞቴዎስ ሕይወትን የሚቃኝና ሕይወታችንን በቅደም ተከተል የሚያደራጅ መልዕክት ነው። መጽሐፉ ነገሮችን በጥቁርና በነጭ ቁልጭ አድርጎ የሚያስቀምጥ መልዕክት ነው። ለግራጫ ሥፍራ የለውም። “የሚቃኝ” ስንል ወደ ዋነኛ ጥሪያችን እንድንመለስ፣ ትኩረታችንን እንድናስተካክል፣ ዋነኛውን ዋነኛ እንድናደርግ፣ የከበረውን ከተዋረደው እንድንለይ የሚያደርገን መልዕክት ነው ማለታችን ነው። ዴማስ ወደ ተሰሎንቄ ምን ሊሰራ እንደሄደ አልተነገረንም። በአንድ ወቅት ግን እንደ ጢሞቴዎስ አብሮ የወንጌል ሰራተኛ ነበር (ቆላ 414; ፊል 24)። ነገር ግን በዚህ ወሳኝ ሰዓት ላይ እንደ ክርስቶስ በጎ ወታደር፣ ተሸላሚ ተወዳዳሪ ወይም ትጉህ ገበሬ (2 ጢሞ. 2:3-7)፣ ሳይፈራና ሳያፍር ከጳውሎስ ጋር በመቆም የወንጌል ርክክብ ሊያደርግ ይገባው ነበር። የሄደበት ዓላማ ምንም ይሁን ምን፣ ግን ሕይወቱ በወንጌል ዙርያ የተደራጀ እንዳልነበር ሲገልጥልን “ይህን ዓለም ወዶ” ተወኝ ይለዋል። እንዲያውም 416 ላይ “ሁሉ ትተውኝ ሄዱ” ይላል። በተለይ ወንጌል በይዘትና በቅርጽ አደጋ ላይ ባለበት ዘመን ባለ ዐደራዎች ሊያሳዩት የሚገባ ታማኝነትና ማንነት አለ። 2ኛ ጢሞቴዎስ ይኽንን ማንነትና ጥሪ አጉልቶ ያሳየናል። ወንጌል አደጋ ላይ ባለበት ዘመን፣ እንዴት ዓይነት ሰዎችና ምን ዓይነት ባሕሪ ልናንጸባርቅ ይገባል? ይህንንና የመሳሰሉትን በጥልቀት በመዳሰስ ሰዎችን ለወንጌል አደራ ማኅበርተኝነት ይመለምላል። ይህ ማኅበር የወንጌልን ዐደራ ተቀብሎ፣ ዐደራውን እየተወጣ፣ ሌሎችም እንዲሁ ዐደራቸውን እንዲወጡ የሚያሰለጥን ማኅበር ነው። በአጭሩ ክርስቶስ ኢየሱስን የሚከተል ሁሉ የዚህ የወንጌል ዐደራ ማኅበር አባል ሊሆን ይገባዋል። በዚህች ተግዳሮተ-ብዙ በሆነች ዓለም ውስጥ ስንኖር፣ ሕይወታችን ብዥታ ውስጥ እንድትገባ የሚዳርጓት አያሌ ተግዳሮታት አሉ። ከዚህ የተነሳ ባለ ዐደራዎች ሕይወታችንን በየጊዜው በወንጌል መቃኘትና የተሰጠንን ዐደራ እንድንጠብቅ ሕይወታችን በቅደም ተከትል ማደራጀት ይጠበቅብናል።
 

2ኛ ጢሞቴዎስ ግብዣ ነው

2 ጢሞቴዎስ ለወንጌል ዐደራ-ማህበር አባላት ሁሉ የቀረበ አስቸኳይ ‘የስንብትና ዐደራን የመረከብ ግብዣ’ ነው ብለንም ማጠቃለል እንችላለን። ዐደራ ተረካቢዎች ግልጽ የሆነ የሥራ ድርሻ ተሰጥቷቸዋል (2 ጢሞ 4:46; 220-26)

41በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፣ መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፤ 2ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም።

ስለ አገልግሎታቸው አውድም ሲናገር

3ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል…[እነርሱም]…4:4እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ።

በአንጻሩ፣ ባለ ዐደራዎች ለተቀበሉት ዐደራ መጣኝ የሆነ ማንነትን ገንዘባቸው ማድረግ፣ ክርስቶሳዊ ባሕርይን መላበስና የነጠረ መንፈሳዊ ሕይወትን ማዳበር እንዳለባቸው ሲናገር

5አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።

ይህ ሁሉ ለምን? ቁ. 6 ያብራራዋል። ልክ ጌታ ኢየሱስ የአባቱን ዐደራ ተወጥቶ ወደ ክብር እንደሄደ (ራዕ 3:21)፣ ጳውሎስም ዐደራውን ተወጥቶ ወደ ጌታው ሊሔድ ነው። ጥያቄው ‘ተረካቢ ሊሆን የሚችል ማነው?’

6እኔ እንደ መጠጥ ቊርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁተለይቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል [ደርሶአልና] 7መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ። 8ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።

በዚህ ወሳኝ ሰዓት ከጳውሎስ ጋር በአንድ ወቅት አብረውት ቆመው የነበሩ እንደ ዴማስ ያሉ አገልጋዮች እንኳ ሽታቸው አልተገኘም (2 ጢሞ. 49)። ጠንቃቃ ባለ ዐደራዎች እየመነመኑ ሲመጡ ወንጌል በአደጋ ላይ እየወደቀ ይመጣል። ይህ ጥሪ የሁላችንም ነው። ባለ ዐደራዎች በቆራጥነት ዐደራውን እንዲወጡ፣ የተቀበሉትን ዐደራ ይዘት ምን እንደሚመስል አስቀድመው በጥልቀት መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

2ኛ ጢሞቴዎስ የዐደራ ጥሪ ነው

ዐደራ | ፓራቴኬ የሚለው ቃል በጳውሎስ የምጋቤ ደብዳቤያት ውስጥ ሦስት ሥፍራ ላይ ብቻ ይገኛል (አዲስ ኪዳንንም ጨምሮ)። በዐደራ የተቀበልከውን በታማኝነት ጠብቅ” (1 ጢሞ. 6:20)የተሰጠህን መልካሙን ዐደራ፣ በእኛ ውስጥ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ (2 ጢሞ. 114; 1:12)፤ በተጨማሪም ዐደራን የሚያንጸባርቁ ተመሳሳይ ግሦችንም [ፓራቲቴሚ፤ ፉላሶ፣ ቴረዖ] ይጠቀማል፦ በብዙ ምስክር ፊት ከእኔ የሰማኸውን፣ ሌሎችን ለማስተማር ብቃት ላላቸው ለታመኑ ሰዎች ዐደራ [ፓራቱ] ስጥ” (2 ጢሞ. 2:2) “ይህን ትእዛዝ [ዐደራ] እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም እርሱን በመከተል መልካሙን ገድል እንድትጋደል ነው” (1ጢሞ 1:18; 2 ጢሞ. 61215) “ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ (2 ጢሞ. 4:7)። እነዚህ ክፍሎች የሚያስረዱን ታማኝ ባለ ዐደራ የሚቀበለውና የሚያስተላልፈው ‘ይዘት’ እንዳለ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት፣ “ዐደራ” ከሚለው ቃል ጋር “ጠብቅ | ፉላሶ” የሚል ትዕዛዝ በሦስቱም ክፍሎች ውስጥ አብሮ ይደረባል። ይህ አስምሮ የሚያሳየን፣ ባለዐደራነት የታማኝነት ውጤት እንደሆነ ነው። ባለ “ዐደራ” በይዘት የተቀበለውን በታማኝነት እንደተቀበለው የሚጠብቅ ሰው ነው። ይህ ከላይ ካየነው የቃሉ ቋንቋዊ ትርጉም ወደ ቃሉ አውዳዊ ፍቺ እንድንሸጋገር ይረዳናል።

እንደ ሐሙራቢ ደንብ (17921750 ቅ.ክ.) ወይም እንደ ሙሴ ሕግ ያሉ (ዘሌ 6:27) ጥንታዌ የኅበረተሰብ መተዳደሪያ ሕግጋት፣ ዐደራ በሕግ የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነበር። ዐደራ ማለት “እምነት ለተጣለበት ለአንድ ሰው የተሰጠ ንብረት” ማለት ነው። አጽንዖቱ የሚያርፈው ንብረቱ ላይ እና በታማኝነት መጠበቁ ላይ ነው። ዊልያም ባርክሌ ስለ ዐደራ/ፓራቴኬ አውዳዊ ፍቺ ሲጽፍ እንዲህ ይላል፦

በጳውሎስ ዘመን የዚህ ቃል ዐውዳዊ ትርጉም፣ ልክ አንድ ሰው ወደ ሩቅ አገር ለመጓዝ ሲል ለሚያምነው ባልንጀራው “እባክህ ወዳጄ ይህንን የከበረውን ንብረቴን እስክመለስ ድረስ ዐደራህን ጠብቅልኝ” እንደሚለው ነው። በጥንታዌው ዓለም ይህንን ዐደራ በጥንቃቄ ጠብቆ ንብረቱን እንደተቀበለው ለባለቤቱ መልሶ መስጠት፣ ከአንድ ወዳጅ የሚጠበቅ ማኅበራዊ ግዴታው ብቻ ሳይሆን በሕግ የሚያስጠይቀውና በሐይማኖቱም የሚያስነቅፈውም ጉዳይ ነበር። (William Barclay, Expository Times 69 (1958))

በተመሳሳይ መልኩ ወደ 112 ዓ.ም. አካባቢ፣ በቢታንያ-ጳንጦስ አውራጃ አገረ ገዢ የነበረው ወጣቱ-ፕሊንይ በአስተዳደሩ ሥር ይኖሩ ስለ ነበሩ ክርስቲያኖች ወደ ሮሙ ንጉሥ ወደ ትሬጃን እንዲህ ብሎ ይጽፋል፦ “[እነዚህ ክርስቲያኖች] በሳምንት አንድ ቀን ጎህ ሳይቀድ በማለዳ እየተገናኙ፣ ክርስቶስ ለተባለው እንደ አምላክ ይዘምሩለታል፣ አመጽ የሆነን ነገር ላለማድረግ፤ ማንንም ሰው ላለማጭበርበር፣ ላለመስረቅ፣ ዝሙት ላለመፈጸም፣ ቃል አባይ ዋሾ ላለመሆንና በዐደራ አንድ ነገር ቢቀበሉ ታማኝነትን ላለማጓደል፣ በመሃላ እርስ በእርስ ይተሳሰራሉ” እያለ ይመሰክርላቸዋል (Pliny, Letters, x. 96) ስለዚህ ጳውሎስ እነዚህን ሁለት ቃሎች ሲጠቀም (ዐደራ…ጠብቅ) ይህ ማኅበራዊ፣ ሕጋዊና ሐይማኖታዊ ዐውድ በጀርባው ይስተጋባል። ክርስቲያኖች ዐደራ ጠባቂዎች ነበሩ። ቃል አባይ አልነበሩም። ይልቁንም ለተቀበሉት የወንጌል ዐደራ እስከ ሞት የታመኑ ነበሩ። ወጣቱ ፕሊንይ ራሱ መከራ እያደረሰባቸው እነርሱ ግን በእምነታቸው ችክ ያሉ ስለ መሆናቸው የጻፈው ደብዳቤ ይመስክራል።

ስለዚህ ዐደራ የሚለው ቃል ቋንቃዊና አውዳዊ ፍቺው የሚያስረዳን፣ ወንጌል በይዘትም ይሁን በቅርጽ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዳስረከበው ሳይጨምርበትና ሳይቀነስበት ወይም ሳይሻሻል፣ በታማኝነት ለመጪው ትውልድ መተላለፍ ያለበት “ወግ” እንደሆነ ነው (በአዲስ ኪዳን ላይ ወግ የሚለው ዕሳቤ እንዴት እንዳደገ በሚቀጥለው ክፍሎች የምንዳሠው ይሆናል)። እንደማይሽር ቁስል በኤፌሶን እየተስፋፋ ያለው እንግዳ ትምህርት የሚቆመው፣ ባለዐደራዎች የተቀበሉትን የወንጌል እውነት እንደ ተቀበሉት ወደ ሌሎች በማስተላለፍ ረገድ ታማኞች የሆኑ ዘንድ ነው (1 ጢሞ. 1:3; 6:320)። በአጭሩ፣ የጳውሎስ ዐደራ አማኞች ለወንጌል ቅርጽና ይዘት ታማኝ መሆን እንዳለብን ሊያስገነዝበን ነው። ታዲያ የወንጌል “ቅርጽና ይዘት” ስንል ምን ማለታችን ነው?

ወንጌልን በቅርጽና በይዘት የመጠበቅ ዐደራ

“ለዚህ ወንጌል የምሥራች ነጋሪና ሐዋርያ፣ አስተማሪም ሆኜ ተሾምሁ…ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ የእኔም ወንጌል ይኸው ነው” (2 ጢሞ. 1:11; 2:8)

ወንጌል በይዘት ቅርጽ አለው። ከተሐድሶ በኋላ ይኖሩ የነበሩ መሪዎችና ክርስቲያኖች፣ ለነገረ-መለኮትና ለክርስቲያናዊ አስተምህሮ መሠረታዊ የሆኑ “ቅርጽና ይዘት” የሚሏቸው መርሆች (The Formal and Material Principles) ነበሯቸው። እነዚህ መርሆች የአንድን አስተምህሮ ጤናማነት እንደ ቴርሞሜትር እንዲለኩ አስችለዋል። ተሐድሶአውያን ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ያቀረቡት ተቃውሞ ይኸው የቅርጽና የይዘት ተቃውሞ ነበር። ለምሳሌ ያህል “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ!” የሚለው የተሐድሶ መርህ የቅርጽ ጥያቄ ነበር። ቅርጽ ሲሉ፣ በሰፊው ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል ወይም በጠባቡ ለወንጌል ይዘትና ምንነት መሠረት ሊሆን የሚገባው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ብቻ ነው ማለታቸው ነበር። ቅርጽ የምንጭ ጥያቄ ነው። የሥልጣን ጥያቄ ነው። ለምን የጋብቻ “ቅርጽ” “በአንድ ወንድና በአንድ ሴት መካከል ብቻ ሆነ?” ለሚለው ጥያቄ መሠረታዊ መልሱ “የእግዚአብሔር ሥልጣን” ብቻ ነው። እግዚአብሔር ትዳርን ሲመሠርት እንዲያ እንዲሆን በሥልጣኑ ስለወሰነ። ሆኖም ግን፣ ለዚህ ጥያቄ አግባብነት ያላቸው የተለያዩ አሳማኝ ምካቴዎች ማቅረብ ይቻላል። ሆኖም ግን የጥያዌው ጭርስታዊ መልስ (ultimate authority) የእግዚአብሔር ሥልጣን ነው። ከእግዚአብሔር በላይ የሆነ ሌላ ሥልጣን ባለመኖሩ። መጽሐፍ ቅዱስም ከእግዚአብሔር አንደበት የወጣ ቃል እንደመሆኑ፤ የእርሱን ሥልጣን ይሸከማል። ስለዚህ ተሐድሶአውያን እንደሞገቱት፣ የቤተ ክርስቲያን ወግና የአበው ትምህርት፤ አሊያም የጳጳሳት ሥልጣንና አተረጓጎም “ለወንጌል ይዘት” መሠረት አይደለም። “ወንጌል ምንድር ነው?” ለሚለው ‘የይዘት’ ጥያቄ መልሱን የምናገኘው “ከቅዱስ ቃሉ ብቻ” በሚለው ‘የቅርጽ’ መልስ ውስጥ ብቻ ነው። ለዚህ ነው የወንጌላውያን አማኞች ሁሉ መሠረት፣ ቃሉና ቃሉ ብቻ የሆነው። ይኽ ማለት ግን፣ ኋላ ተሐድሶአውያን ግልጽ ለማድረግ እንደሞከሩት፣ ከቅዱስ ቃሉ ውጪ ያሉት ሥልጣናት ሁሉ ዋጋ ቢሶች ናቸው ማለት አይደለም። ንጉሥ ሥልጣን አለው። አባትና እናት በልጆቻቸው ላይ ሥልጣን አሏቸው። መጋቢያን በመንጋው ላይ ለመንጋው ጥቅም የሆነ ሥልጣን አሏቸው። “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው መርሆ ሌሎች ሥልጣናትን አይፎርሽም። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ከሌሎች የሥልጣን ምንጮች ጋር ያለውን “መስተጋብር” ምን እንደሚመስል ከተሓድሶ በኋላ የነበሩት መጪዎቹ ወንጌላውያን አማኞችና መሪዎች ጠለቅ አድርገው ያሰቡበት ጉዳይ ነበር። ለምሳሌ ያህል ጆን ዌዝሊ አራት የሥልጣን ደረጃዎችን (Wesleyan Quadrilateral) ያበጃል፡- (1) መጽሐፍ ቅዱስ፤ (2) የቤተ ክርስቲያን ወግ፤ (3) መንፈሳዊ ልምምድ እና (4) አመክንዮ (Albert C. Outler. “The Wesleyan Quadrilateral in John Wesley)። ለዌዝሊ፣ የአንድ ሰው የግል መንፈሳዊ ልምምድ ሥልጣን ተደርጎ መታየት ፈጽሞ የለበትም። የትኛውም ልምምድ በቅዱስ ቃሉ መዳኘት አለበት። ወይም የሰው አመክንዮ በቅዱስ ቃሉ ላይ አይሠለጥንም። አመክኖዮ ይሁን መንፈሳዊ ልምምድ፣ አሊያም የቤተክርስቲያን ወግ ከቅዱስ ቃሉ ሥልጣን ሥር በታች ናቸው። ይህ የቅርጽ ጥያቄ ነው። የሥልጣን ጥያቄ ነው። የዌዝሊ ሙግት ምን ያህሉ <አሳማኝ ነው ወይስ አይደለም?> የሚለው ጥያቄ የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ አይደለም። ሆኖም ግን ሊሰመርበት የሚገባው፣ ወንጌልን በዐደራ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ማለት፣ ወንጌልን በቅርጽም በይዘትም እንደተጠበቀ መሆኑን ግን አበክሮ ለማስገንዘብ ነው።

ከዚህ የተነሳ፣ የቅርጽ ጥያቄ በየትውልዱ እየተነሳ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። በየትኛውም ትውልድ ውስጥ የእግዚአብሔር ቤት በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ታልፋለች። ቤተ ክርስቲያን የትውልዷን ጥያቄ ለመመለስ ስትል ወጓ እና ልምምዷ እየሰፋ ይመጣል። ከቤተ ክርስቲያን ጎንም በግራና በቀኟ የቆሙ የተለያየ መጠሪያ ስሞችንና አጀንዳዎችን ያነገቡ አገልግሎቶችና እንቅስቃሴዎች እየደሩ ይመጣሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ወንጌልን ‘በቅርጽንና በይዘት’ ምን እንደሚመስል ጠይቆ ለመመለስ እድሉና ጊዜው የሌላቸው፣ ግን የአማኞችን ሕይወትና እምነት በትምህርታቸው እና በልምምዶቻቸው የሚቀርጹ እየበዙ ይመጣሉ። ሳይታወቀን፣ “እንዲህ ይሆንን?” እያሉ ቅዱሳት መጽሐፍትን ለመመርመር እንቅልፍ ያልነሳቸው፣ ነገር ግን “አንደበተ ርቱዕ” ተናጋሪዎች ተደማጭ እየሆኑ ይመጣሉ። ይኽ ሁሉ ሲሆን፣ ወንጌል እየተንሸራተተ፣ ቅርጹ እየተለጠጠና ይዘቱ እንግዳ መልክ እየያዘ ይመጣል። ይህን ጊዜ ነው ጳውሎስ “የንግግር ችሎታ ባይኖረኝም እንኳ፣ ዕውቀት ግን አለኝ” ሲል የሚደመጠው። ዕውቀት አለኝ ሲል “የተማርኹ ነኝ” እያለ እየሸለለ ሳይሆን— የንግግር ብቃት መሠረታዊ ሆኖ እንዳለ— ብቃቱ ለወንጌል ይዘት ታማኝ ከመሆን ጋር ካቀረበ አደገኛ መሆኑን አስምሮ ሊያስተምረን ነው (2 ቆሮ. 11:6)። የአንድ ሰው ማዕረግ (“ሐዋሪያ ነኝ” ቢል) ወይም አንደበተ-ርቱዕነቱ (በግሪክ ሪቶሪክ የተኻነ መሆኑ) ስለ ወንጌል ቅርጽና ይዘት ጥንቃቄ እንዳያደርግ መብት አይሰጡትም።

ቅርጽ ያለ ይዘት

ለምሳሌ ያህል፣ “ኢየሱስ ጌታ ነው፣” “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣” “ኢየሱስ ያድናል…ወዘተ” በሚሉት መፎክሮች ብንስማማ፣ የተስማማነው “በቅርጽ” ብቻ መሆኑን መገንዘብ አለብን። በርግጥ ይህ ስምምነት መሠረታዊ ነው። ሆኖም ግን ቅርጹ ያዘለው ይዘት፣ ይኽም “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” ብሎ አንድ ሰው ሲመሰክር “ምን ማለቱ እንደሆነ” ‘ይዘቱን’ ካላብራራልን፣ በቅርጽ ብቻ ላይ የተመሰረተ አንድነት ውሎ አድሮ መፍረሱ አይቀርም። ምክንያቱም ስምምነታችን በቅርጹ ላይ (በመፈክሩ ላይ) ብቻ የተመሠረተ በመሆኑ። ቅርጹን ብቻ በማየት (መፈክሩን) ‘በአንድ ዓይነት ኢየሱስ እያመንን ነው’ ብለን እንድንደመድም አያስችለንም። እንዲያ ከሆነ፣ የሞርሞንም እምነት ተከታይ በዚሁ ቅርጽ (መፎክር) ይስማማል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያምናል። ሆኖም በቅርጽ ተስማምተን፤ በይዘት ስንለይ፣ ልዩነቱ የሞትና የሕይወት ያህል ነው። “እኛ ከሰበክንላችሁ ኢየሱስ ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ፣ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ መንፈስ ብትቀበሉ ወይም ከተቀበላችሁት ወንጌል የተለየ ወንጌል ብትቀበሉ፣ ነገሩን በዝምታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው (2 ቆሮ 11:4) ይላል። ወንጌል በቅርጽና በይዘት በዐደራ ካልተጠበቀ፦ በቅርጽ “ኢየሱስ” የሚባል እየተሰበከ፤ በይዘት ግን “ሌላ” ኢየሱስ፤ በቅርጽ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሥራ የሚሰራ፣ ነገር ግን በይዘት የክርስቶስ መንፈስ ያልሆነ “ሌላ መንፈስ፣” እንዲሁም በቅርጽ ተመሳሳይ የሆነ ወንጌል እየሰበክን (‘ኢየሱስ ያድናል’) ግን በይዘቱ ሌላ ወንጌል መስበክ ይቻላል ማለት ነው። እውነተኛውን ከተጭበረበረው ለመለየት ቅርጽ ብቻውን ሊያታልለን ይችላል። ይመስላልና። በዚሁ በ2ኛ ጢሞ. ላይ ጳውሎስ አበክሮ ሲናገር “ሃይማኖታዊ መልክ አላቸውኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ” (2 ጢሞ. 3:5) ይለዋል። በመልክ ይመስላል። ቅርጹ ተመሳሳይ ነው፣ ይዘቱ ግን ሌላ ነው። ባለ ዐደራዎች ከዚህ ይርቃሉ። አንድ ሥሉስ የሆነ ፈጣሪና አዳኝ እንዳለ ሁሉ “አንድ ሐይማኖት” “አንድ ተስፋ” አንዲት ጥምቀት ወዘተ..አለ። በዚህ መፈክር ተስማማን ማለት ግን “ሕብረት” አለን ማለት አይደለም። ምክንያቱም የዚህ እምነት ይዘት፤ የዚህ ተስፋ ይዘት ወይም የዚህ ጥምቀት ይዘት ምን እንደሆነ ገና ስላልተብራራ። በተለይ የእኛ ትውልድ ስለዚህ ጉዳይ ልብ ልንል ይገባል። መንፈሳዊነት “አስማታዊ” ባሕርይ የለውም። እንደ አስማት በሚደገም ቃል (ቅርጽ ብቻ)፣ መንፈሳዊ ልዕልና አይመረትም። ይህ የመተቱ፣ የሟርቱ ዓለም ፍልስፍና ነው። የሆነ አንድ ቁልፍ ሐረግ በመናገር የሚከፍት መንፈሳዊ በር የለም። “ቅርጹን” አምኖ ይዘቱን የካደ፣ ሐይሉንም የካደ ነው። በጥልቀት የምናስተውለውና በሙሉ ልብ የምናምነው እውነት፣ በሕይወታችን ከምንለማመደው መለኮታዊ ሕልውና ጋር አይነጣጠልም። ትምህርታችንና የእግዚአብሔር መገኘት በጎራ አይመደቡም። ሁለቱን መነጣጠል የጀመርን ዕለት፣ ለትውልዳችን ሞትን ማገልገል የጀመርንበት ዕለት መሆኑን መገነዘብ ነበረብን። ሽማግሌው ዮሐንስ እንዲህ ዓይነቱን ችግር በተመለከት ጊዜ፣ “ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ቢኖር፣ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ(1 ዮሐ 2:24)። ለሰማነው ወንጌል ይዘት መጠንቀቅ፣ ለእግዚአብሔር ክብር መጠንቀቅ ነው። ለአስተምህሮ መጠንቀቅ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ መጠንቀቅ ነው። አንዱን ያለ ሌላው ባለ ዐደራዎች አይቀበሉም፣ ለሌሎችም አያቀብሉም። ወንጌል ሕይወት ነው። ወንጌል ግን ማንነት አለው። ቅርጽ አለው። ይዘትም አለው።

ይዘት ያለ ቅርጽ

ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርነው፤ “የወንጌል ቅርጽ” ስንል በአንድ መልኩ የሚያነሳው የሥልጣንን ጥያቄ ነው። ወንጌል ምንድር ነው? ምንስ አይደለም? ወይም ወንጌል ስለማን ነው? ወዘተ… ለሚሉት ጥያቄዎች አያሌ አስተያየቶች መሰንዘር ይቻላል። ግን ትክክለኛውን መልስ መስጠት የሚችለው ማን ነው? እንደገና ይህ የቅርጽ ጥያቄ ነው። በገላትያ የነበረው ሁለት ምርጫ፣ ጳውሎስ የሰበከው ከኦሪት-ነጻ የሆነው ወንጌል? ወይስ አዋኪዎች የሰበኩት ኦሪት-ተኮሩ (የመገረዝ) ወንጌል? ማነው እውነተኛ? ይሄስ እንዴት ይዳኛል?

ጳውሎስ የተለያየ ማስረጃዎችን እያቀረበ፣ ከተሰበከላቸው ወንጌል የተለየ ይዘት ያለውን ኦሪት-ተኮሩን ወንጌል ቢቀበሉ “ክርስቶስ ፈጽሞ ለእናንተ እንደማይበጃችሁ እኔ ጳውሎስ እነግራችኋለሁ” ይላል (ገላ 5:2)። ይህ የይዘት ጥያቄ ነው። ስለዚህም በገላ 3:16 ላይ በተሰቀለ-ክርስቶስ ባመኑ ጊዜ እንዴት መንፈስን እንደተቀበሉ እያሳሰበ፣ የግል ልምምዳቸው እንደ ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ ይሞግታቸዋል። በገላ 3:79 ላይ ደግሞ ከአብርሃም እምነት አንጻር ይሞግታል። ከኦሪትና ከነቢያትም እየጠቀሰ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሙግት ያቀርባል (3:1014)። እንዲሁም የተለያዩ ምስስሎችን እያቀረበ፣ ነጻነǘ#4725;ን የሚሰጠው ወንጌል እርሱ የሰበከላቸው ወንጌል ብቻ እንደሆነ ሊያሳምናቸው ይጥራል (31518; 3:2329; 4:17)። ወደ ሌላው ወንጌል መመለስ ወደ ባርነት መመመለስ ነው። በአጭር ቃል፣ ወንጌል በይዘቱ ላይ ምንም ነገር ሊከለበስበት አይገባም።

ሆኖም ግን ጳውሎስ የደብዳቤውን ሙግት የጀመረው በይዘት ጥያቄ ሳይሆን በወንጌል “ቅርጽ” ጥያቄ ነው (ገላ 1:11-2:10)። የሰበከው ወንጌል መለኮታዊ-መነሾ (divine origin) ያለው እንጂ “ሰው ሠራሽ አለመሆኑን እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ ከማንም ሰው አልተቀበልሁትም፤ ከማንም አልተማርሁትም፤ ይልቁንስ በመገለጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀበልሁት ይላል (ገላ 1:1112)። አንዱ ወንጌል “እንዲህ ነው” ሲል፣ ሌላው ደግሞ “በጭራሽ ይህንንም ይጠቀልላል” ብሎ ይሞግታል። ለዚህ ዓይነት ሙግት ታዲያ ዳኛው ማነው? ይህ ሙግት የቅርጽ ሙግት ነው። ሐዋሪያዊው ወንጌል (በሐዋሪያት የተሰበከው ወንጌል) ጳውሎስና ሌሎቹ ሐዋሪያት ከክርስቶስ በቀጥታ የተቀበሉት መልዕክት ነው። ቅርጹ የተወሰነው በክርስቶስ ስልጣንና በሐዋሪያት መልዕክት ነው። “እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው ይህንኑ ነው…ያመናችሁት ይህንኑ ነው” (1 ቆሮ. 15:11)። ይኽም፣ በሐዋሪያቱ ሁሉ የተሰበከው ወንጌል በቅርጽም ሆነ በይዘት መሠረታዊ አንድነት ነበረው ማለት ነው። በገላ 2:6 ላይ እንደተናገረው፣ “ለመልእክቴ የጨመሩልኝ ነገር የለም” ይላል። የሰብኩት ወንጌል መሠረታዊ አንድነት ነበረው ማለቱ ነው። ስለዚህ ወንጌል በቅርጽም ይሁን በይዘት ምን ማለት እንደሆነ በሐዋሪያቱ ተጠይቆ የተመለሰና መልሶ የማይጠየቅ ነው፡ “ለዚህ ወንጌል የምሥራች ነጋሪና ሐዋርያ፣ አስተማሪም ሆኜ ተሾምሁ…ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ የእኔም ወንጌል ይኸው ነው” (2 ጢሞ. 1:11; 2:8)

ስንደመድም፤ ከዚህ በኋላ ጥያቄው የዐደራ ጥያቄ እንጂ የቅርጽና የይዘት ጥያቄ አይነሳም። ወንጌል በቅርጽም በይዘትም በዐደራ ተሰጥቶናል። ወንጌል ይዘቱ ከመደፈሩ በፊት፣ የሚደፈረው ቅርጹ ነው። ቅርጹ፣ የክርስቶስ ሥልጣን ነው። ይኽም ሥልጣን የተማከለው እንደራሴዎቹ አድርጎ በሾማቸው በሐዋሪያቱ ሥልጣን አማካኝነት ነው። እነርሱም የወንጌልን ትርጓሜ ቀርጸውልናል። ይዘቱም በዐደራ ተላልፎልናል። ማንም አገልጋይ ይሁን አማኝ፣ ሆን ብሎ ራሱን በወንጌል ቅርጽና ይዘት ሥር የማኖር ግዴታ አለበት። ሁለተኛ፣ ዐደራው ግርድፍ መረጃን ማቀበል አይደለም። ወይም “እውቀትን” ማስተላለፍ ብቻም አይደለም (እርሱንም ቢጨምር)። የወንጌል ዐደራ ተቀባይ ለመሆን የሚሻ ሁሉ ሁለንተናዊ ለውጥንም ወደ ሕይወቱ ለመጋበዝ ፈቃደኛ መሆንና ራስንም በእግዚአብሔር ፊት ማቅረብን ይጠይቃል (2 ጢሞ 2:15)። ወንጌልን በቅርጽም በይዘትም እንድናውቅም ይሁን በዐደራ እንድንጠብቅ፣ ከእኛ የሚጠበቅብን ምን እንደሆነ 2ኛ ጢሞቴዎስ በሰፊው የሚያትትልን በሚቀጥሉት ተከታታይ ክፍሎች የምንዳሥሠው ይሆናል።

 

መዝጊያ፡ አጠቃላይ የጢሞቴዎስ ጭብጦች

  1. 2ኛ ጢሞቴዎስ «የክርስቶስ ተከታይ» መሆን ማለት፣ የወንጌል ዐደራ-ማኅበረተኛም አባል የመሆን ግዴታ እንዳለበት የሚያሳስብ ግብዣ ነው
  2. 2ኛ ጢሞቴዎስ የዐደራ-ማኅበርተኞች በጋራ የሚጠብቁት “መልካም-ዐደራ” እንዳለ ያስተምረናል፡- ይህም ዐደራ፣ የእውነትን ቃል የመጠበቅና በታማኝነት የማስተላለፍ ዐደራ ነው።
  3. 2ኛ ጢሞቴዎስ የዐደራ-ማኅበርተኞች የሚካፈሉት “መልካም-ተጋድሎ” እንዳለ ያሳስበናል ‑ ባለ ዐደራዎች ጉዞቸው ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው የተገነዘቡ እና መከራን ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ናቸው።
  4. 2ኛ ጢሞቴዎስ በታማኝ ባለዐደራዎች እና ከእውነት ርቀው በሚባዝኑት ሰዎች መካከል፣ ደማቅ መስመር አስምረን እንድንለይ ያዘናል።በእኛና በእነርሱ መካከል ያለው ደብዛ አይጥፋ።
  5. 2ኛ ጢሞቴዎስ የዐደራ-ማኅበረተኞች ሊጨብጡት የሚገባ ነገረ-ፍጽመታዊ እይታ እንዳለ ያስገነዝበናል! ይኽም ዐደራችንን ስንወጣ የእርሱን መገለጥ በመናፈቅ ነው። ብድራታችን ትኩር ብለን እንመልከት።

One Comment

Leave a Reply to Tesfaye Taye Cancel reply

Your email address will not be published.