
የተሰቀለ-ክርስቶስ፡ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ በመልዕክታችን ይኑር
የአንደኛ ቆሮንቶስ 1:10 – 2:5 ሐቲት
ኢየሱስን እንደ “ክርስቶስ” መቀበል እና እንደ “ተሰቀለ-ክርስቶስ” መቀበል ይለያያሉ። እኛ የምንሰብከው “የክርስቶስ መስቀል” ከሌሎች መስቀሎች እንዲለይ ያደረገው፤ “መሰቀል” የሚባለው እውነታ አይደለም (በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁድ ወጣቶች ተሰቅለው ነበር – በተለይ በ4 ዓ.ዓ. አካባቢ ላይ)፤ ክርስቶስም የሚለው ቃል አይደለም (ብዙ መሲህ-ነኝ ባዮች ከኢየሱስ በፊት እንደ ስምዖን ወልደ-ጊዮራ ያሉ፣ በኋላም እንደ ስምዖን ወልደ-ኮኸባ ተነስተው ነበር) ይልቁንም በመስቀሉ ላይ የተሰቀለው እርሱ «ማን መሆኑና» እንደተሰቀለ ሆኖ መሰበኩ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ «የተሰቀለ-ክርስቶስ» የመልዕክታችን እንዲሁም የሕይወታችን ማዕከል ሆኖ እንዲኖር ደግሞ ለማሳሰብ ነው። ይህ የምንናገርለት መስቀል “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል” ነው። በሰው አስተሳሰብ ሁለቱ ቃሎች፡ “ክርስቶስ” እና “መስቀል” አብረው የማይቀመጡ ቃሎች ናቸው። ኢየሱስ አስቀድሞ መከራን እንደሚቀበል እና እንደሚገደል ሲናገር ጴጥሮስ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ” (ማቴ. 16:22) ይለናል። ኢየሱስም “የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።” ምክኒያቱም “አንተ ክርስቶስ ነህ” የሚለው ቃል እና “መከራ..መገደል” በሰው-ጥበብ አብረው አይቀመጡም። የሰው ጥበብ በውርደት ከፍታን አያስብም። የሰው ጥበብ በመከራ ክብርን አያይም። የሰው ጥበብ “እንዴት አድርጌ በሌሎች ላይ ተረማምጄ እነግሳለሁ” እንጂ “ለሌሎች ራሴን እንዴት ልስጥ” አይልም። ስለዚህ በሰው ጥበብ ውስጥ “ክርስቶስ” እና “መስቀል” አብረው አይሔዱም። ክርስቶስ ይነግሳል፡ ወንጀለኛ ይሰቀላል። ንጉስ የበረታ በእንጨት ላይ የተሰቀለ ደግሞ የተረገመ፣ ደካማ ይባላል። ሆኖም ግን፤ የእግዚአብሔር ጥበብ በዚህ በሰው ዓይን ሞኝነት በሚመስል መንገድ ተገለጠች። ይህን እውነት ሐዋሪያው “የመስቀሉ ቃል” ወይም “የስብከት ሞኝነት” ይለዋል።
በሮማውያን ንጽረተ-ዓለም፣ ልክ እንደ ተቀረው የሜድትራኒያኑ ዓለም፣ “ክብረትና ውርደት (Honor/Shame)” ሞትና ሕይወት ነበር። ከዚህ የተነሳ «ውርደት>> ከሞት የበለጠ ሞት እንደሆን ይነገርለት ነበር (Seneca, De Beneficiis 4.16.2)። ከውርደት ሞት አንዱ ደግሞ ስቅለት ነበር። በሮማውያኑ ዘንድ ስቅለት እጅግ የውርደት ሞት ከመሆኑ የተነሳ በሮም ቄሳር ትዕዛዝ ካልሆነ በስተቀር አንድ ሮማዊ በስቀለት አይቀጣም ነበር። ከዚህ የተነሳ የመጀመሪያዪቱ ቤ/ያን የተሰቀለ-ክርስቶስን መስበኳ ትልቅ ነቀፌታ አትርፎባት ነበር። ለምሳሌ የሮም ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ ክርስቲያኖችን “በመተት የሚያምኑ” (Tacitus, The Annals 15.44) ሲል፣ ትንሹ ፕሊኒይ ደግሞ “የሚጋባ መተት ይዘው የሚዞሩ “contagious superstition“ ይላቸዋል (Pliny, Letters to Trajan, X, 96)። ሆኖም ግን እንደ ችቦ እያተጋዩም ቢሆን “የተሰቀለ-ክርስቶስ” መስበክ የማያፍሩበት መልዕክት ነበር።
የተሰቀለ-ክርስቶስና የቆሮንቶስ ሰዎች
ቆሮንቶሳውያን በቃልና በዕውቀት እንዲሁም በመንፈሳዊ ጸጋ(1፡5-6)ቢጥለቀለቁም መንፈሳዊ ብስለትን ግን ገና አልተላበሱም (3:1)። የመስቀሉንም ሎጂክ አልጨበጡም። መንፈሳዊ ስጦታዎች “ኢየሱስ ጌታ እንደሆን” የሚመሰክሩበት ፤ የስሉሱን አምላክ አንድነትና ብዝኀት በመካከላቸው በክብር የሚንጸባርቅበት መንገድ መሆኑ ቀርቶ ሁከት ሰፍኗል (14:33)። የእርስ በርስ ግንኙነታቸውም እንዲሁ በመካሰስ (6:1)፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ራስ-ጠቀም መሆናቸው (6:8)፤ እስኪመለስ ሞቱን የሚያውጁበት የጌታንም ራት ማቃለላቸው (11፡18-34)፣ የወንጌል ትርጉም (የተሰቀለ-ክርስቶስ) ስላልገባቸው ነው። ለዚህ ነው ደብዳቢውን ሲጀምር (1:18 – 3፡25) በተሰቀለ-ክርስቶስ ጀምሮ፤ ተመልሶ በሞት፤ በመስቀልና በትንሳኤ የሚዘጋው (15:1-58)።
የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን! (1:10-17)
በመጀመሪያ በ1:10 ላይ፣ ሐዋሪያው የደብዳቤውን ይዘት የሚጀምረው የቆሮንቶስ አማኞችን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም (ሥልጣን) ስለ ሦስት ጉዳያት በመማጸን ነው። እነዚህም (1) “ሁላቸውም አንድን ነገር እንዲያጸኑ” «ቶ አውቶ ለጌተ/τὸ αὐτὸ λέγητε» ወይም “አንድ ዓይነት ነገርን እንዲናገሩ” ሲሆን፣ ከዚህ የተነሳ፡- (2) በመካከላቸው መለያየት እንዳይኖር እና (3) በአንድ ልብና ሐሳብ እንዲተባበሩ ነው። እነዚህ ሦስቱም እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ናቸው። «አንድነታቸው» እና «በአንድ ልብ መተባበራቸው» “አንድን ነገር” አጥብቀው ከመያዛቸው ይጀምራል። ይህ የይዘት ጥያቄ ነው። በቁ. 10 ላይ ሦስት ጊዜ “አንድ..አንድ…አንድ…» ብሎ በመደጋገም ደመቅ አድርጎ ያሰምርልናል። ይህ አንድ ንግግር፣ አንድ-ነትን እና አንድ ልብን የመፍጠር ኃይል አለው። ይህ ሁላቸውም የሚያጸኑት “አንድ ነገር” ምንድር ነው? ወረድ ብሎ በ1:18-2:5 ግልጽ የሚሆንልንና የደብዳቤው ዋነኛ መልክት የሆነው “የመስቀሉ-ቃል” ነው። በዚህ ረገድ የሆነ አንድነት ሐዋሪያው አሉታዊና አዎንታዊ የሆኑ ክትለቶች እንደሚያመጣ ይነግረናል። አሉታዊው ክትለት “መለያየት በመካከላቸው እንዳይሆን” ሲያደርግ፤ አዎንታዊው ደግሞ “በአንድ ልብና ሐሳብ» መተባበራችው ነው። ምንም እንኳ በአካሉ ውስጥ የጸጋና የመንፈሳዊ ሥጦታ ብዝኀት ቢኖርም (12፡4-11; ተጓ. ኤፌ. 4፡7-16) የወንጌል ዋነኛ መልዕክቱ ግን (የተሰቀለ–ክርስቶስ) አንድ ነው። ለእኛም የሚቀርብልን ጥያቄ «ይህ ዘመን መጠቅ፤ ዘርና ጎሳ ዘለል የሆነው ዋና-ዋነኛ የወንጌል መልዕክት ምንድር ነው?» የሚል ነው። አማኞች ወደ አንድነት የምንመጣውና አንድ ሐሳብና አንድ ልብ የሚኖረን በመጀመሪያ ሕይወታችንና እምነታችን በመስቀሉ-ቃል የተቃኘ እንደሆን ነው። አንድነት ስምምነት ከመሆኑ በፊት ታማኝነት ነው። እርስ በእርሳችን “እንሥማማ” ከማለታችን በፊት «በአንድ ነገር ላይ በእውነት ተስማምተናል ወይ?» ብለን መጠየቅ እንዳለብን ሐዋሪያው ያስገነዝበናል። እናስተውል “ሁላችሁም ስለ ሁሉም ተስማሙ” አልተባልንም። “ሁላችሁም አንድን ነገር ተናገሩ/አጽኑ” እንጂ። ስለዚህ መጀመሪያ “ምን ያህል የመስቀሉ ቃል ይዘት ገብቶናል? ጨብጠነዋል? እየሰበክነው ነው? በታማኝነትስ ለመጪው ትውልድ እያስተላለፍነው ወይ?» የሚሉት ጥያቄዎች ተቀዳሚ ናቸው።
ሁለተኛ፣ በ1:11-16 ላይ ጳውሎስ ቆርንቶሳውያን “ሁላቸውም አንድ ነገር” እንዳይናገሩ ወዳደረጋቸው ጉዳይ ያመራል። ከላይ ሐዋሪያው “በጌታ በክርስቶስ ስም” መማጸኑ እዚህ ወረድ ብሎ ለሚያቀርበው “በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?” ለሚለው ግሳጼ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ስም ስልጣንን ይወክላል። ይህ “እኔ የእከሌ ነኝ…እኔስ የእከሌ ነኝ” በሚል ከንቱ ብሂል የተቃኘው የቆሮንቶስ መንፈሳዊነት ችግሩ፣ ቆሮንቶሳውያን “መስቀል-ቃል” ተኮር ሳይሆኑ «አገልጋይ-ተኮር» መሆናቸው ነው። እያንዳንዱ ቡድን የእያንዳንዱን መሪ “መልክት” ማዕከል አድርጎ ተከፋፍሏል። ለዚህ ነው በም3፡7 ላይ “የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም” ያለን። ይህንን “ሰው ተኮር” መንፈሳዊነት ለማፍረስ ጳውሎስ ሦስት ጥያቄዎች ይጠይቃል። ሐዋሪያው እነዚህን ጥያዌዎች ሲያዋቅር፣ እያንዳንዱ ዓረፍተ-ነገር በአማርኛችን «ን» በሚል ድህረ-ቅጽል ማለቁ (μὴ)፣ አንባቢው ለሦስቱም ጥያቄዎች “በፍጹም” የሚል ምላሽ ለሐዋሪያው እንዲሰጥ አቅዶ ነው። “ክርስቶስ ተከፍሏልን?” አረ በፍጹም! “ጳውሎስስ ስለ እናነት ተሰቀለን?” እንዴት ሆኖ! “በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?” ከቶ በጭራሽ!። ለዚህ ነው፣ በቁ. 14-16 ላይ ጳውሎስ ያጠመቃቸውን ሰዎች ስም ይጠቅስና ደግሞ ያመነታል። “ተመስገን!” ከመካከላችሁ “ከቀርስጶስና ከጋይዮስ” በስተቀር ማንንም ባለማጥመቄ ይልና ደግሞ እነ እከሌንም ማጥመቄም ትዝ ይለኛል ይላል። የዚህ ማመንታት አላማው ግልጽ ነው። እኔ ጳውሎስ ያጠመቁትን ስም ዝርዝር ይዤ አልዞርም። ዋናው ጉዳይ “መጠመቅህ” እንጂ በማን አገልጋይ እጅ “ተጠምቅሽ” አይደለም። “ማንም በሰው አይመካ ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና” (3:21)። ይህ ለአንባቢው ግልጽ ካልሆነ ደግሞ በመጨመር “ክርስቶስ የላከኝ ለማጥመቅ ሳይሆን ወንጌልን ለመስበክ እንጂ” በማለት ጳውሎስ ፍትልክ ብሎ ወደ ዋናው ነጥብ ይዞን ይገባል። አንድ ሰው “በማን እጅ ተጠመቀ” ድነታዊ ክትለት የለውም። ሆኖም ግን የምንሰብከው የወንጌል ይዘት ግን አለው። ዋናው ነገር ይለናል “ስብከቴ በጥበብ ቃል” አልነበረም ምክኒያቱም “የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን!” ጳውሎስ ሁለት ነገሮችን በተቃርኖ ያስቀምጥልናል፡- “የጥበብ-ቃል” አሊያም “የመስቀሉ-ቃል፣” “ወንጌልን ማብሰር” አሊያም “ጥበብን ማቀንቀን”። በመካከል ገደል ብቻ ነው ያለው። የወንጌል ሰባኪ ግዴታው ወንጌልን “በጥበብ” መቃኘት ሳይሆን “ወንጌልን እንደተቀበለው መስበክና ማስተላለፍ ነው (15:1-3፤ 4:1-2)። ጳውሎስ ይህንን ጥረት፣ በሰዎች ፊት ወንጌል ቅቡል እንዲሆን የሚደረገውን መዳከር፣ “ከመስቀሉ-ቃል” ጋር የሚቃረን “የጥበብ-ቃል” ይለዋል። ወንጌል በአድማጩ ጆሮ መዓዛ እንዲኖረው፤ ለታዳሚው ቅምሻ እንዲጣፍጥ የምንጨምርበት ቅመም ይሁን ለንጽረተ-ዓለሙ “እንዲመች” የምናስተካክለው ማንኛውም ነገር አደጋው፣ የክርስቶስን መስቀል “ከንቱ” ማድረጉ ነው። መስቀሉ መካን ይሆናል። በወንጌል ላይ መጨመር፤ ወንጌልን መቀነስ ነው። የተቀነሰ ወንጌል ደግሞ “ከንቱ” ነው። ይህ ማለት ወንጌልን ስንሰብክ ለይዘቱ ካልተጠነቀቅን፤ መስቀሉን እያወጅን፤ ጉልበቱ ግን አይገለጥም። ከዚህ የተነሳ ውሎ አድሮ “ስብከት ብቻ ምን ያደርጋል?” ወደሚል ከንቱ ብሂል ማምራታችን አይቀሬ ነው። “ወንጌልን” እንደተቀበልን፤ ከነ እንቅፋቱ፤ ከነ ሞኝነቱ እንድንሰብከው ሐዋሪያው ያስጠነቅቀናል። የክርስቶስም መንፈስ ግድ ይለናል። አሊያ ስብከታችን “በቃልና በጥበብ ብልጫ….በሚያባብል የጥበብ ቃል” የተመሠረተ ይሆንብናል (2:1-5)። ስለዚህ የመስቀሉ-ቃል ለአድማጮች ጆሮ እንዲመች ተደርጎ አይስተካከልም። (ይህ በፊል. 1፡15-18 ላይ ካለው የተለየ ነው። በዚያ ስፍራ ችግሩ ሰባኪው ጋር/ the Motive/ እንጂ ስብከቱ ጋር አልነበርም)። አንደኛ፤ ሐዋሪያው ከ1:18 – 2:5 ባለው ክፍል “የምንሰብከው ቃል ሞኝነት/የስብከት ሞኝነት” ምን እንደሆነ ከይዘቱ አንጻር ሲገልጽልን፤ ሁለተኛ በ1፡26-31 ባለው ክፍል ደግሞ የመስቀሉን ሎጂክ “ከቆሮንቶሳውያን አጠራር” አንጻር አሳይቶን፤ በሦስተኛ ደረጃ፤ የመስቀሉ-ቃል እንዴት እንደሚቀርብና ይዘቱ “ክርስቶስ እርሱም እንደተሰቀለ” ሆኖ በምን አይነት ጥንቃቄ መሰበክ እንዳለበት በሰፊው ይዳስሣል።
የስብከት ሞኝነት፡ እኛ ግን የተሰቀለውን-ክርስቶስን እንሰብካለን (1:18-25)
ጥንታዌው ሰው ልክ እንደ ዘመናዊው፣ ሕብረተሰብን በቀለም፤ በዘር፤ በጎሳ፤ በሐብት፤ በእውቀት፤ በጾታ፤ በእድሜ…ወዘተ በመከፋፈል፣ ሰውን ያከብራል ወይ ይንቃል። ለጳውሎስ ግን ከክርስቶስ መስቀል የተነሳ ዓለም ከነጥበቧ እያለች አልፋለች። ሐዋሪያው የሰውን ዘር በሁለት ጎራ ይመድባል። እንደ አይሁድ «የተገረዘና ያልተገረዘ» ወይም እንደ ግሪክ-ሮማውያን አስተሳሰብ «ሮማዊና ባርቤሪያን» ደግሞም «ነጻና ባሪያ» «ወንድና ሴት» እያለ ሳይሆን «ከሚድኑ ወገን አሊያም ከሚጠፉ ወገን» እያለ ነው (1:18)። እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካኝነት በመስቀል ላይ ከሠራው ሥራ የተነሳ መንግሥቱ ተመርቃለች። የወዲያኛው ዘመን፣ የትንሳዔው ሃይል (the age to come) አሁን በምንሰብከው የመስቀል-ቃል እና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተነሳ (2:1-5)፣ በዚህ በአሁኑ ክፉ ዘመን ውስጥ ድነት ተመረቀ (inaugurated eschatology)። ይህ ዕውነታ ሁሉን ነገር ለሁለት ከፍሏል። ደ/መዝሙራዊ ሕይወትም በዚህ ሰማያዊ እውነታ የተቃኘ ሆኗል። ከመስቀሉ ባሻገር ያሉ አማኞች መምጣቱን የምንጠባበቅ (1:7)፤ “የዘመናት መጨረሻ የደረሰብን” ሰዎች ነን (10:11)። የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና” (7:31; ተ.ጓ. 1 ቆሮ. 4:5; 2 ቆሮ. 6:2; ሮሜ. 8:18; 13:11; ተሰ. 5:1)። አሁን ሰውን ሁሉ የምናውቀው በክርስቶስ ነው (2 ቆሮ. 5፡16-17)። ጳውሎስ ለዓለም፤ ዓለምም ለጳውሎስ ተሰቃቅለዋል። የሰው ኗሪ ቅርሱ ለመስቀሉ-ቃል የሚሰጠው ምላሽ ብቻ ነው (1:18)። ስለዚህ ከመንግሥቱ አንጻር የሰው ዘር የሚመደበው፡- «ከሚድኑ አሊያም ከሚጠፉ ወገን» ነው።
በመጀመሪያ፤ ምንም እንኳ የመስቀሉ-ቃሉ ለሚጠፉት ሞኝነት ቢሆንም በዘመነ-ፍጻሜ ድነትን እየተቀበሉ ላሉ አማኞች ግን “የእግዚአብሔር ኃይል” ነው (1:18)። መልክቱ አንድ ነው። በአንዳንዶች ላይ በሐይል ትገለጣለች፣ በሌሎች ደግሞ ትናቃለች (ማቴ. 13፡18-23)። “ይሁን አለ…ሆነም” እንደሚለው የፈጣሪ-ቃል (creation)፤ የመስቀሉም ቃል ብርሃንን በሰሚው ልብ ውስጥ (2 ቆሮ. 4:4) መፍጠር የሚችል አዳኝ-ኃይል ነው (New Creation)። ሁለተኛ፣ ለሐዋሪያው የመስቀሉ-ቃል ጥበብም ጭምር ነው። በኢሳ. 29:14 ላይ ያህዌህ በከንፈሩ ብቻ ለሚያከብረው እና በሰው ሥርዓትና ትምህርት (29:13) ለሚያመልከው ዕውር ሕዝቡ (ኢሳ. 29:18; 42:18-19) የሰጠው የድነት ተስፋ “ድንቅ ነገር እንደገና አደርጋለሁ” የሚል ነበር (29:14)። ይህ ድንቅ ነገር በኢሳያስ ምን እንደሆን ባይገለጥም፣ ምን እንደሚያስከትል ግን ተነግሮናል። በዚህ ድንቅ “የጥበበኞች ጥበብ ትጠፋለች፣ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች (29:14)።” ጳውሎስ ያ ኢሳያስ አስቀድሞ የተነበየው ድንቅ ሥራ “የክርስቶስ መስቀል ነው” ይለናል (1:19)። በዚህ ድንቅ ሥራ አማካኝነት እግዚአብሔር የሰውን ጥበብ ሞኝነት አድርጎታል። እንደ ሮሜ 1:18-32፣ የሰው ብልሃት የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት፤ መልኩንም በእንስሣት መስሎ ይለውጣል። ከቆሮንቶሳውያኑ ዘመን እስከ ዘመናችን ድረስ፤ የሰው ብልሃት አሁንም መስቀሉን ለማስጌጥ፣ የመስቀልን እንቅፋት ለማስወገድ ይጥራል። ቅቡል እንዲሆን ይጠበባል። ግን በመስቀሉ ፊት ጠቢቡ፣ ተመራማሪውና የሕጉ-ሊቅ ሞኝ ሲሆኑ፣ በመስቀል-ሞኝነት ያመነው ደግሞ ጠቢብ ሆኗል (1:20-21)። እዚህ ጋር ሞኝነት የተባለው “ስብከት” ሳይሆን የስብከታችን ይዘት የሆነው የተሰቀለ-ክርስቶስ ነው። አይሁድ ምልክትን የግሪክም ሰው ጥበብን ይሻል፤ ቸሩ አምላክ ዓይኖቻቸውን ላበራላቸው ለተጠሩት ግን (1:24) ክርስቶስ ሞኝነት ሳይሆን፤ “የእግዚአብሔር ሃይል፤ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው” (1:24)። ዓለም በጥበቧ እግዚአብሔርን ማወቅ አልቻለችም። ምክኒያቱም ሕያው እግዚአብሔር ራሱን ሊገልጥ የወደደው በመስቀሉ በኩል ነውና፣ ያለ መስቀል አስተርዮተ-እግዚአብሔር የለም። መስቀሉን ያላማከለ የሰው ሃይማኖት ፈራሽ፤ አምልኮው ከንቱ ነው። “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን!”(1:23) ብርቱ የሆነው እርሱ፣ ደክሞ ድካማችንን በመስቀል ላይ በመሸከም ክብሩን የገለጠልን ጌታ የተባረከ ይሁን!
የስብከት ሞኝነት፡ የዓለምን ምንምንቴ መረጠ (1:26-31)
ሐዋሪያው ከላይ በ1:18-25 ላይ፣ የመስቀሉ-ቃልና የሰው ጥበብ አብረው መሔድ እንደማይችሉ ያቀረበው ማስረጃ፣ የመልዕክታችን ይዘት “የተሰቀለ-ክርስቶስ” በመሆኑ ነው። ይህም በሰው አይን ሞኝነት ነው፤ የእግዚአብሔር ሞኝነት። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በ1:26-31 ላይ የመስቀሉን ሎጂክ ከቆሮንቶሳውያን የገዛ-ልምምድ አንጻር እንዲመለከቱ ይጋብዛቸዋል፦ «እስኪ የራሳችሁንም መጠራት ተመልክቱ፤ ‘ሞኝ’ እንጂ እናንተን ማን ይመርጣል?» ይላል። እዚህ ጋር የሚያስገነዝባቸው፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም (1:26)። የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ (1:28)። “ሞኝነቱ” ግን ጥበብ ነው። «አለሁ አለሁ» የሚለውን ከንቱ ሊያደርግ፣ ይለናል ሐዋሪያው፣ እግዚአብሔር በሰው ዓይን «ምንም ምንምንቴ» የተባለውን መረጠ (1:28)። ጥበበኞችን “አለሁ ባዮችን” እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ (ምንሞችን)፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ። ልክ ነው ወንጌል የአንዳንድ ባላባቶችንም በር አንኳክቷል። ግን የሐዋሪያው ዓላማ የወንጌል መንገድ የውርደት መንገድ መሆኑን ቆሮንቶሳውያን “ሲጠሩ” ማን እንደነበሩ ልልምምዳቸው እንኳ የመስቀሉን መንገድ ሊያስረዳቸው እንደሚገባ ለማሳየት ነው። ብርቱ የሆነው እርሱ ደክሞ እንደ እኛ ያሉ ደካሞችን ስለመረጠ የተባረከ ይሁን!
የስብከት ሞኝነት፡ የተሰቀለ-ክርስቶስና አሰባበኩ (2:1-5)
ሌላው የሰው ጥበብ ቃል ከመስቀሉ ቃል ጋር የሚቃረነው፤ ስብከት ሰባኪውን የሚክብ፤ ሰባኪውን የሚያስኮፍስ፤ የሆነ እንደሆን ነው። በውርደት ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ የማያሳይ የስብከት አቀራረብ፤ መስቀሉን ከንቱ ያደርገዋል። ስለዚህ የመስቀሉ-ቃል ይዘት መሰረታዊ እንደሆነ ሁሉ፤ ቃሉንም ስናቀርብ መስቀሉን አንጸባራቂ መሆን አለበት። ስለዚህ ነው “ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም (2:1)” ያለን። “በቃልና በጥበብ ብልጫ” የተሞረደ ስብከት አለ ማለት ነው። ሰባኪውን የሚክብ፤ ሐይልን ከድካም ነጥሎ የሚያውጅ ስብከት። በአጭሩ ይህ “ከመስቀሉ ላይ ደሙን ያጠበ” ወይም መከራውን ያጸዳ ስብከት ነው። የክርስቶስን ሐይል ያውጃል፣ ግን ያለ መስቀሉ ድካም። ሆኖም እግዚአብሔር ያሰበልን ሙላት በሙሉ፤ በዚህ የሚቃረን በሚመስል እውነታ፣ የተሰቀለ-ክርስቶስ በሚል ውጥረት ውስጥ ተካቷል። ብርቱ የሆነው እርሱ ደክሞ ድካማችንን በመስቀል እንደተሸከመ፤ እኛም የወገኖቻችንን ድካም እየተሸከምን፤ ከደከሙት ጋር ደካማ ሆነን የመስቀሉን ድካም በቃልና በኑሮ እናንጸባርቅላቸው እንጂ “ድካሙን” በእኛ ሐይል እንዳንፎርሸው ጌታ ያግዘን። በእኛ በደካሞቹ ስብከት ውስጥ ድካሙንም ደግሞም ታላቅ የማዳን ሃይሉን የሚገልጠው የተባረከ ይሁን!
ማጠቃለያ፡ “ክርስቶስ እርሱም እንደተሰቀለ በቀር…”
“በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና…”(2፡2)በመጨረሻም፤ የመስቀሉ-ቃል ይዘት አጽንዖት ያረፈው “ክርስቶስ–እርሱም–እንደተሰቀለ” መሆኑ ላይ ነው። “እርሱም” የምትለው ቃል ‘አስማሪ ቃል’ ናት (Topical-Framing/ Emphatic)። በመካከላቸው ሳለ ጳውሎስ በስብከቱ ቅርጽ፣ ይዘት እና አቀራረብ አስረግጦ የነገራቸውና ያሳያቸው የተሰቀለ–ክርስቶስን ነው። ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች (የአሕዛብ መንገድ ለመከተል ለተፈተኑ) ይሁን “መገረዝን እና የሕግን ሥራ” ለመቀበል ለተፈተኑ (ይሁዲነት ለቃጣቸው የገላትያ ሰዎች ) መልሱ አንድ ነው – «የተሰቀለ-ክርስቶስ!» “በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር (ገላ. 3:1)”። ከላይ በተሰቀለ-ክርስቶስ ማመን ለግሪኮች ሞኝነትና የሚቃረን እውነታ እንደሆን አይተናል። ምክንያቱም ስለ ተሰቀለ-ክርስቶስ ሲሰሙ ልክ “ጥልቀት-አልባ-ውቂያኖስ” ወይም “የማያቃጥል-እሳት” እንደማለት ነው! ስሜት አይሰጥም። “ክርስቶስ” ንጉሥ ሊሆን የተቀባ ማለት ከሆነ ታድያ ንጉሥ መስቀል ላይ ምን ያደርጋል? መስቀል ለወንበዴዎችና ለደካሞች የተለየ የውርደት ቅጣት ነወና። ይሁንና የእግዚአብሔር ሞኝነት የሆነው “የተሰቀለ-ክርስቶስ” ከጠቢባን ጥበብ ይጠበባል። እንዲሁም የተሰቀለን-ክርስቶስ ማዕከል ያደረገ ወንጌል ደግሞ ለአይሁድ እጅግ መሰናክል ነው! ለምድር ሁሉ የምስራችን የሚሰብከው ቅዱሱ መሲህ፤ የእሥራኤል ታዳጊ፤ አይሁድ ለዘመናት የጠበቁት የዳዊት ልጅ እርሱ «ጴንጤናዊው ጲላጦስ የሰቀለው ኢየሱስ እርሱ የአይሁድ መሲህ ነው» ብሎ እንደማወጅ አስደንጋጭና የሚያስቆጣ ድርጊት ምን ነበር? ለምን? ምክንያቱም ኦሪት “በእንጨት ላይ የተሰቀለ የተረገመ” ስለሚል ( ዘዳግም 21፡23)። በአይሁድ አስተሳሰብ ኢየሱስ፤ «ለይስሙላ ክርስቶስ የተባለ» መሆኑ ማረጋገጫው በመስቀል ላይ መሞቱ ነበር። ሐዋሪያትና ወንጌላውያኑ ክርስቶስ በእንጨት ላይ መሞቱን ይልቁን አጎሉ እንጂ አላድበሰበሱትም ነበር። ለምሳሌ፤ ሮማውያን መስቀልን “እንጨት/ዛፍ [ξυλον]” ብለው አይጠሩትም ነበር። ነገር ግን በተደጋጋሚ በሐዋሪያት ሥራ ላይ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሳይሆን “በእንጨት/ዛፍ” ላይ፤ ሰቀላችሁት ሳይሆን “አንጠለጠላችሁት [κρεμαννυμι]” (Acts 5:30; 10:39; 13:29; ገላ 3:13; 1 ጴጥ. 2:24) በማለት የክርስቶስን ስቅለትና መሰቀል ከዘዳግም 21:23 ጋራ በቀጥታ ያገናኙልናል። ይህንን እንቅፋት አይሁድ እንዳይሰናከሉ ብለው ከስብከታቸው አልከረከሙትም። ይልቁንም አጎሉት። ለምን? ይህ የመስቀል እንቅፋት መሰረታዊ ስለ ነበር። ክርስቶስ በመልክታችን እንደተሰቀለ ሆኖ ሊኖር የግድ ነው። ሰንሰለት በጣሽ የሆነው ሃይሉ ያለው እዚያ ብቻ ነውና። «ክርስቲያኑን ጳውሎስ» «ከፈሪሳዊው ጳውሎስ» የለየው ይኸው በተሰቀለው-ክርስቶስ ማመኑ ነበር። ስለ አባቶች ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀና ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ሲገሰግስ የነበረውን ጳውሎስ (ገላ 1:14)፤ የከበረው ጌታ እስኪያገኘው ጊዜ ድረስ፤ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስም ሆነ ስለ ክርስቲያን ሊያስብ የሚችለው ነገር “ክርስቶስ ርጉም እንደሆነ በእርሱ የሚያምኑትም እርጉማን” መሆናቸውን ነበር። ከደማስቆ መንገድ ባሻገር የምናየው ክርስቲያኑ-ጳውሎስ ግን የወንጌሉ እውነት በራለት! “ለካ የተረገመው” አለ ጳውሎስ “ስለ እኔ፤ በእኔም ምትክ ነበር!” ጳውሎስ በራሱ ቃል እንዲህ ይላል፦ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን…” (ገላ 3:13)። ወይም ኢየሱስ በገዛ ወንጀሉ የተገደለ ሳይሆን በፈቃዱ ራሱን ለጳውሎስ በነፍስ-ወከፍ እንደሰጠው ሲናገር “..በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ” ይላል ( ገላ. 2 :20 )።
ስለዚህ ወንጌል የሃጥያት ርግማናችንን በመስቀል ላይ የተሸከመውን የናዝሬቱ ኢየሱስን ጌታና ክርስቶስ አድርጎ ይሰብክልናል። እግዚአብሔር ያሰበልን ሙላት ሁሉ በዚህ የሚቃረን በሚመስል እውነታ ውስጥ ተካቷል ( ቆላ. 2 ፡2-4)።” ለዚህ ነው የጳውሎስ መልዕክት የተሰቀለውን ንጉሥ ማዕከል ያደረገው። ለእኛም እንዲሁ ነው። ሕይወታችን በሞት፤ ክብራችን በመከራ፤ ድላችን ለሌሎች ሕይወታችንን በመስጠት ውስጥ ነው። እውነተኛው ወንጌል ውርደትና ክብርን፣ መስቀልንና ዙፋንን፤ ጥበብንና በሰው ዓይን ሞኝነትን በአንድ ላይ ወጥሮ ያዋሃደ ነው። ይህንን ውጥረት ነው ጳውሎስ “የስብከት ሞኝነት” የሚለው። ይህንን መልክት ስዘጋ ሁለት ልመና አለኝ። አንደኛ፤ የተሰቀለ-ክርስቶስ በመልክታችን፤ በቃልና በሥራችን በእኛ ዘንድ እንዲኖር ሲሆን፣ሁለተኛ ደግሞ ትውልድ ተኮር የሆነ ጭንቀት አለኝ፦
“ቤተ ክርስቲያን ከጤናማ አስተምህሮ ወደ ክህደት እንድታፈገፍግ ሶስት ትውልድን ይጠይቃል። የመጀመሪያው ትውልድ በታማኝነትና በተጋድሎ ይጠብቀዋል። ሁለተኛው ትውልድ ግን በመጀመሪያው ትውልድ መንፈሳዊ ጎን ላይ ተደግፎ፤ ጤናማውን ትምህርት እያመነ ነገር ግን አጽንዖት አድርጎ አያውጀውም። ይልቁንስ የዚህ ሁለተኛ ትውልድ አጽንዖቱና ትኩረቱ የመጀመሪያው ትውልድ “ተሳስቷል ወይም ዘንግትቶታል” ባለው በሁለተኛ እና ከዋነኛው ጋር ሲወዳደር «ትርፍ በሚባል» ነገሮች ላይ ይሆናል። ይህ ሆኖ እያለ፤ ሶስተኛ ትውልድ ይነሳል። ይህ ሦስተኛ ትውልድ የመጀመሪያ ትውልድ በተጋድሎ የያዘውን አያምንም። ምክኒያቱም ሁለተኛው ትውልድ ግርዶሽ ሆኖበት አላስተላለፈለትም። ስለዚህ የሦስተኛው ትውልድ ዋና ትኩረት፤ ሁለተኛው ትውልድ «አጽንዖት» ባደረገበት ነገር ላይ ይሆንና፤ ያ የመጀምሪያው ትውልድ አስተምሮት ያለፈውን ጤናማውን እውነት ይክዳል…” (በ2010 ላይ በD. A. Carson ከተሰጠ መርሃ ግብር ከተሳተፍሁት የተወሰደ)
አሁን ይህ ሦስተኛው ትውልድ እየተነሳ ይመስለኛል። ለዚህ ቀውስ ተጠያቂ ማነው? እንደ ዲ. ኤ. ካርሰን አነጋገር ሁለተኛው ትውልድ ነው። ትኩረቱ ያነጣጠረው በዋናው ነገር ላይ ስላልሆነ። ያ ሁለተኛ ትውልድ ይድናል። ምክኒያቱም ከጅምሩ ዋነናውን አምኗል። አጽኖት አላደረገበትም አንጂ። ነገር ግን ለሦስተኛው ትውልድ ሞትን እያገለገለ ነው። ለዚህ ነው ብዙዎቻችን ከእንቅልፍ የመንቃት ያሕል “እንዴት እዚህ ደረስን?” ብለን እየጠየቅን ያለነው። መፍትሄው ወደ ዋነኛውና ወደ መካከለኛው መመለስ ነው። ወደ ተሰቀለው–ክርስቶስ ትውልዳችንን እንመልስ ዘንድ ልባዊ ጸሎቴ ነው።
(ይህ ጽሑፍ ለሚድዌስት አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት 50ኛ ዓመት አስመልክቶ ያቀረብኩት ነበር)


2 Comments
Eleni
Praise the lord,I am very happy to find True biblical teaching in Amharic. May God bless you more and more!
Samson Tilahun
Hi Eleni, amen to that. Thank you so much for visiting the site.