Articles,  Blog,  GOSPEL,  ወንጌል

-1- የወንጌል ማዕከላዊነት

መግቢያ

(If you would like to read the whole article in English, click here AcrobatPDF The Story of the Gospel)

‘ወንጌል’ የሚለው ቃል እጅግ ከመለመዱ የተነሳ፤ ‘ወንጌል የብዙ ነገሮች ገላጭ ቃል ሆኖ ሲውል ይደመጣል። ሁልጊዜም እንደሚባለው፤ አንድ ቃል ብዙ ነገሮችን እንዲወክል በተጠቀምነው ቁጥር የቃሉ ይዘትና ክብደት ይቀንሳል። ለምሳሌ ያሕል፤ ጸጋ የሚለውን ቃል በንግግራችን CentralityOftheGospelእንዴት እንደምንጠቀመው እንመለከት። ዝናሽና አስቴር ወደ ዋናው አዳርሽ እየገቡ ሳሉ፤ ዝናሽ ዘወር ብላ ለአስቴር “ዛሬ ደግሞ በጣም አምሮብሻል!?” ትላታለች። ዝናሽ ደግሞ ትከሻዋን ነቅንቃ “ጸጋው ነዋ!” ትላታለች። ይህ እየሆነ ሳለ ሁለት አብሮ አደግ ጓደኛሞች ከተለያዩ ከብዙ ዓመት በኋላ በጌታ ሲገናኙ፤ እርስ በርሳቸው ተያይተው “የድሮው ሕይወታችን ትተን ትዳር ይዘን እንኖራለን!” ብለው ሲጥያየቁ፤ የሰጡትን መልስ አውቃችሁታል “ጸጋው ነው”። አበራ ደግሞ ከአምልኮ ፕሮግራም በኋላ ለዮሴፍ “ዛሬ ፕሮግራም ስትመራ ድምጽህ በጣም ቆንጆ ነበር” ሲለው የዮሴም መልስ ከዝናሽ የተለየ አይደለም። አሁንም መልሱን አውቃችሁታል። እነዚህ ሰዎች “ጸጋ” የሚለውን ቃል በተለያየ መልኩ አውለውታል። ለሁሉም በርቀት ሊሉ የፈለጉት ነገር፤ “ይህ የሆነልን ነገር ከእኛ ውጪ በሆነ አሰራር ነው” ለማለት ይመስላል። ዝናሽ ከደም ግባት ጋር፤ ዮሴፍ ከታለንት/ክሕሎት ጋር እንደዚሁም ደግሞ አብሮ አደግ ጓደኛሞቹ ከሥነ-ምግባር ለውጥ ጋር አያይዘውታል። ከዚህ የተነሳ “ጸጋ” የሚባለው ቃል የትርጉም ቅርጹ መደብዘዝ ብቻ ሳይሆን ሰሚውን “እንዴ!? ይህ ጸጋ የሚባለው ነገር ምን ማለት ይሆን?” ብሎ እንዲጠየቅ ይገፋፉታል። ጸጋ ሁሉም ነገር ከሆነ ጸጋ ትርጉሙን ያጣል። ምክኒያቱም ትርጉሙ ድብስብስ ብሎ (domesticated ሆኖ) ቅርጹን እንዳያጣ ። ወንጌል የሚለውም ቃል እንዲሁ እጅግ ከመለመዱ የተነሳ በአዲስ ኪዳን ገጾች ላይ ወንጌል ምን ማለት እንደሆነ እንደገና መልሰን መቃኘት የግድ ይሆንብናል።

ወንጌልን መተርጎም ያስፈልግ ይሆን?

“ወንጌል” የሚለውን ቃል ብዙ ነገሮችን እንዲወክል በተጠቀምነው ቁጥር፣ የቃሉ ይዘትና ቅርጽ ይደበዝዝብናል። አውዳዊ አገባቡንም በአግባቡ ሳናስተውል በፈለግነውም መንገድ ቃሉን በሙያ ላይ ስናውል፣  በመረጥነው መንገድ ስንረዳው እና ትርጉሙ ስንለጥጠው ወንጌል ውሎ አድሮ “ተራ-ብሂል” ይሆናል።

አውዳዊ አገባብ

በመጀምሪያ ልንጀምር የሚገባን “ቃሉን እንዴት መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቀመዋል?” በሚለው አውዳዊ ጥያቄ ነው። ለምሳሌ መጽሀፍ ቅዱስ ወንጌልን “የእግዚአብሔር የጸጋው ወንጌል” ይለዋል። ይህ “የእግዚአብሔር የጸጋው” የሚለው ተቀጽላ ቃል ስለ ወንጌል ይዘትና ትርጉም አስተዋጾ እያበረከተልን ነው። ይህም ማለት ወንጌል ስለ እግዚአብሔር የነጻ ስጦታ የሚያውጅ የምስራች ቃል ነው። ከላይ እንዳየነው ጸጋ እግዚአብሔር ስለክብሩ ሲል ለዚህ ለጠፊው ዓለም የሰጠው የነጻ-ሥጦታ የሆነው አንድያ ልጁ ነው።

  • የእግዚአብሔር ወንጌል (ሮሜ 1:1; 15:16; 2 ቆሮ 11:7; 1ተሰ 2:8; 1ተሰ 2:9; 1 ጴጥ 4:17)
  • የእግዚአብሔር መንግስት ወንጌል (ማቴ 24:14)
  • የክርስቶስ ወንጌል (ሮሜ 15:19 ; 9:12; 2 ቆሮ 2:12; 9:13; 10:14; ገላ 1:7; ፊል 1:27; 1 ተስ3:2)
  •  የሰላም ወንጌል (ኤፌ6:15)
  •  የድነት ወንጌል (ኤፌ 1:13)
  • የጌታችን ወንጌል  (2 ተስ 1:8)
  • የእግዚአብሔር ልጅ ወንጌል (ሮሜ 1:9)
  • ብሩክ የሆነው የእግዚአብሔር ክብር ወንጌል (1 ጢሞ 1:11)
  • የክርስቶስ ክብር ብርሃን ወንጌል (2 ቆሮ 4:4)
  • የጸጋ ወንጌል (ቆላ. 1:6)

ስለዚህ ከወንጌል ጋር አብረው አውዳዊ አገባብ ያላቸውን ቃላቶች ማገናዘብ አለብን።

ወንጌል ሲደመር…

በሁለተኛ ደረጃ፣ “ወንጌልን እና ወንጌል ከእኛ የሚጠይቀውን” በአንድ እጅ ወይም “ወንጌልን እና ወንጌል በሕይወታችን ከሚያፈራው ፍሬ” በሌላ እጅ (ሳንለያያቸው) ለየት ማድረግ ግን አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል ሰባኪው ለታዳሚው “ራስን ስለ መካድና መስቀልን ተሸክሞ ስለ መከተል” ቢሰብክ ይህ የቅድስና-ሕይወት-ግዴታ ላዳነን ጌታ የምንመልሰው አማራጭ-የለሽ አጸፋ ነው እንጂ ይህ የወንጌል ይዘት አይደለም። ይህ ወንጌል በእኛ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚያፈራው ፍሬ ነው። ስለዚህም “ወንጌል” ተቀዳሚ” ሲሆን ለወንጌል የሚሰጥ “ምላሽ” ደግሞ ተከታይነት አለው ማለት ነው። ልክ እንዲሁ “እመኑ” የሚለው ቃል በወንጌል ጥሪ ውስጥ ቢካተትም እምነት ግን የወንጌል ይዘት አይደለም፡- “ጊዜው ደርሶአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ” እያለ ይሰብክ ነበር” (ማር. 1:15)። “ንስሓ ግቡ እና እመኑ” የሚሉት ቃሎች ለወንጌል የሚሰጡ ምላሽ-ጥሪዎች ናቸው “[የምሥራቹ-ቃል እነሆ ስለዚህ] ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ”። አሊያ ወንጌልና ለወንጌል የሚሰጠው ምላሽ ከተደባለቀ “እምነት ወንጌል” ሊሆንብን ነው። ያም ከሆነ “እምነትን” አምነን ነው የዳነው ማለት ነው። “ንሥሃ” ወንጌል ከሆነ የምስራቹ ቃል “ንሥሃ” እንደ ማለት ይሆንብናል። ይህን ስል በእምነትም ላይ ይሁን በቅድስና ላይ ላላ ማለቴ አይደለም። በተቃራኒ! የወንጌልን ቃል ይዘት መጠበቃችን ወንጌሉ በብዙ ሐይል በመካከላችን እንዲሰራ መንገድ ይከፍትለታል። “በወንጌል አላፍርምና…ለሚያምኑ ሁሉ ለማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።” ስለሚል። አያችሁ፤ የወንጌሉ ቃል፤ ባዶ ቃል አይደለም ለመቀደስ፤ ለመለውጥ የሚችል “ሐይል” ነው። በሊአላ አነጋገር “የወንጌል ይዘቱ ነው፤ የወንጌል ጉልበቱ!” ይህ ሐይል እንዲሰራ የወንጌል ይዘቱ በንጽህና መጠበቅ አለበት። የገላትያ ቤተ/ ክርስቲያን ትልቁ ችግር የወንጌሉን ይዘት መቀነሷ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ መጨመሯ ነበር። ከዚህ የተነሳ የተጨመረበት ወንጌሏ ልዩ አስብሎታል፡ “በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ ….ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? ….ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል። …ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ።ስለዚህ ወንጌልና ወንጌል ከእኛ የሚፈልገውን ወይም ወንጌልንና ወንጌል በሕይወታችን ከሚያፈራው ፍሬ/ውጤት መለየት አለመቻል ሲስተዋል “ወንጌል ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ግድ ይሆንብናል።

ወንጌል ሲቀናነስ…

በሦስተኛ ደረጃ፤ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ “ወንጌል” የሚለው ቃል የክርስቲያን መሰረታዊና የመጀመሪያ ዶክትሪን/አስተምህሮቶች (ስለ እምነት፤ መዳን፤ የክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ፤ የኃጢአት ስርየት፤ ጥምቀት፤ ወዘተ…) በመወከል የጥቅል መጠሪያ ስም ሆኖ ጥቅም ላይ ሲውል ይደመጣል። በርግጥ የወንጌል መንቀሳቀሻ መኪናው “ስብከት” ነው። ይህ ስብከት ደግሞ ለዳኑም እንዲሁ ላልዳኑ እኩል አስፈላጊ የሆነ መሳሪያ ነው። የዚህ “ስብከት” ለሕይወት ሁሉ ያለው እንደምታ ግን የሚቀርበው “አስተምህሮ” በሚባል መኪና ነው። ይህን መሠረታዊ ልዩነት ካልተረዳን “ወንጌል” ላልዳኑ ሰዎች፤ ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ወይ ገና ላልበሰሉ ሕጻናት የሚሰጥ የመጀመሪያ ወተት (የደሕንነት/የጥምቀት ትምህርት) ይሆንብንና “አጥንት የሆነው” አስተምህሮ  ግን ከዚህ መሰረታዊ ትምህርት ቤት (ወንጌል) የተመረቀ ነገሮች ላይ ያርፍብናል። ለምሳሌ “የእ/ርን ክብር ለማየት፤” “የሃይልን ሕይወት ለመለማመድ” ወዘተ የሚሉት ርዕሶች አብዛኛውንም ጊዜ “ጥልቅና በሳል” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ስንሰማ “ወንጌል” የእግዚአብሔር ክብር መሆኑን የዘነጋን ይመስላል። የጠለቀ ትምህርት ወንጌል እየፈለቀቀ የሚተለትል እንጂ ከወንጌል የሚሸጋገር አይደለም። ስለዚህ ቅዱሳን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል ማለት ነው።

የወንጌል ማዕከላዊነት

ለክርስቲያን ወንጌል  ህልውናው ነው። ሁለንተናውን የሚያካትት፣ ብሎም ለዕለት-ዕለት ሕይወቱ በቂ የሆነና ሁሉን አቀፍ እውነታው ነው። የክርስቶስ ወንጌል የሕይወትን ሁለንተናዊ ይዘትና ቅርጽ የምናይበት ሁሉን አቀፍ «ንጽረት-ዓለም» ነው። ወንጌል የሰውን አስተሳሰብ የሚቃኝ (ቆላ 3:1-2፤ ሮሜ 12:1-4)፤ የሕይወትን አቅጣጫ የሚቀይስ (ኤፌ 2፡ 11-19፤ 1ጴጥ 2፡9-10 )፤ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ (ማቴ 28:18-20)፤ የቤተሰብ መዋቅር ንድፍ (ኤፌ 5፡21-6:9)…ወዘተ… ነው። ወንጌል ጠቅላላ ኑሮአችንን የሚቃኝ መሪ ነው።ወንጌል ሁሉን ይቃኛል፤ ነገር ግን ራሱ በምንም አይቃኝም። ወንጌል የእግዚአብሔር ጥልቅ ሚስጥር አሰራር ነው። አስተውላችሁ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ “የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገሮች” የምንላቸው ትኩረታቸው በወንጌል ላይ ያረፉ አይደሉም። ብዙ ጊዜ ወንጌል  ለብዙዎቻችን የክርስትና መጀመርያ ሲሆን፣ አማኞችም ወዲያው በአፋጣኝ ሁኔታ “ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች” ወደሚባሉ እንዲሻገሩ ይበረታታሉ። ከላይ እንዳየነው እነዚህ “ጥልቅ ነገሮች” ከወንጌል ውጭ ያተኮሩ ርእሰ-ጉዳያት ናቸዉ። ቀረብ ብለን አዲስ ኪዳንን ስናማክር ግን ወንጌል የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን ክርስቶስን ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን ( 2 ቆሮ. 4፥ 4)” ነው። መንፈሳዊ-ሕይወት የሚለውካው በዚህ ብርሃም ነው። እንዲሁም የአንድ አማኝ እድገት የሚታወቀው ምን ያህል ስለ ወንጌል ጥልቅ ምስጢር ምን ያህል እንደጨበጠ በመመዘን ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሐዋርያው ጳዉሎስ ሲጸልይ ግን፤

“ የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ ፣ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኃይልን እንድታገኙ ነው” ( ኤፌ. 3፥14-19) ብሎአል ።

በተጨማሪም ሐዋርያው እንዲህ ብሏል፤

“…ከዘመናትና ከትውልዶች ተሰውሮ ምስጢር ሆኖ ቆይቶ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጧል”( ሮሜ. 16፥25-26፤ ቆላ.1፥26)

ይህን መገለጥ እንዲያስተምር ለጳውሎስ በኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን ይህም፤

“ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው ” ( 1 ቆሮ. 1፥26)።

ያም…

“ እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው። ….ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካኝነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች፣ እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው” ( ቆላ. 1፥27፣ ኤፌ.3፥6)።

ይህ ሁሉ የተሰራው…

“ሞትን ደምስሶ በወንጌል አማካይነት ሕይወትንና ኢመዋቲነትን ወደብርሃን ባመጣው በጌታችን በኢየሱስ መምጣት “ ነው (2ጢሞ. 1፥10)።

ሐዋርያው ጳውሎስ ሲደመድም…

“ በወንጌል አላፍርም፣ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኃይል ነው” (ሮሜ. 1፥16) ብሏል።

– ወንጌል እንደ ንጽረተ-ዓለም –

እነዚህ እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ወንጌል ከሚመስክራቸው ለናሙና ያህል የተወሰዱ ናቸው። እውነቱ ግን ወንጌል የእግዚአብሔር ተስፋ ሲሁም፤ ይህ ተስፋ ለብዙ ዘመናት ተሰውሮ የቆየ ቢሆንም አሁን ግን በክርስቶስ መምጣት ይፋ ሆኖ የሚታወጅ የምሥራች ቃል ነው። ይህም ሚስጢር በክርስቶስ ማንነትና ሥራ በክብር ተገልጧል።  የእግዚአብሔር ቃል ስለ ወንጌል-ተቀዳሚነትና ዋነኛነት ብዙ ምስክርና ማስረጃ ቢያቀርብም እኛ ግን አዲስ ኪዳን ልዩ ትኩረት በመስጠት በግንባር ቀደምትነት የሚያስቀምጠውን ወንጌል በሞላ ጎደል ያነሰ ትኩረት ስንሰጠው፤ በአንጻሩ ደግሞ አዲስ ኪዳን መለስተኛ ትኩረት የሚሰጣቸውን ነገሮች ግምባር ቀደም አድርገናቸው አብይ ትኩረት ስንሰጣቸው እንታያለን። በምድር ላይ የተሳካና በድል የተሞላ ኑሮ ለመምራት የሚያስችለንን “ቁልፍ” ነገር ያለማሰለስ እንፈልጋለን። እስከ አሁን ብዙ “ቁልፎች” ተገኝተዋል፤ እነርሱም በሌላ አዲስ “ቁልፎች” ተተክተዋል። ለሕይወት ሥምረት ብዙ ዘዴዎችና ብልሃቶች እንደብርቅ ተስተምረዋል። ይህ ሲሆን ግን ገና ከጅምሩ ወደ ኋሊት ወደ ሕግ-አጥባቂነት/አትንካና አትቅመስ (legalism) እያመራን መሆናችንን አላስተዋልንም። ልባችን ከጨበጥነው ያለፈ የተለየ አዳዲስ ተግዳሮቶችን ይመኛል (to-do-list) ይፈልጋል። ይህን ስናደርግ ግን የጥንቱን አሮጌው ነገር በዑደት (recycling) ውስጥ እያለፈ እንደሆነ አንገነዘብም። አትንካና አትቅመስ በጓሮ በር ገብቶ በፊት ለፊት ፀጉሩን ለውጦ ሲወጣ እንደ አዲስ አስተርእዮ ስንቀበለው ከረዥም ጊዜ በፊት ጀምሮ ራስን ለመርዳትና በራስ ለመጽደቅ ጥቅም ላይ የዋለ መሆኑን አናስተውልም። ይሁን አንጂ፤ እነዚህ ዘዴዎችና ብልሃቶች የለወጧት ሕይወት የለችም። አዲስ ኪዳን ያበረከትልንን ታላቅ ጸጋ፤ በእነዚህ በተጭበረበሩ መንገዶች ላይ አይገኝም። አንድ መንገድ አለ። “እኔ እውነት፤ መንገድ ሕይወት ነኝ” ብሎ የመረቀው መንገድ።  ዘዴ ሕይወትን አይቀይርም። ኢየሱስ ግን ሕይወትን ይለውጣል። ኢየሱስ የቅዱሳት መጻሕፍት ማዕከለኛ ነው “መጻሕፍት…ስለ እኔ ይመሰክራሉ” ብሏል ዮሐ 5፡ 39

“እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና።  ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም…እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ።  በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።”

ወንጌል ግን የመለወጥ ሐይል ያለው የጉልበት ቃል ነው። በጨለማ ብርሃን ይሁን ብሎ በቃሉ የፈጠረው እግዚአብሔር አሁን በወንጌል ቃል ብርሃን ይሁን ይላልና ነው። “ታዲያ ከእነዚህ ዘዴዎች ባሻገር ወንጌል ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ የሚችል በቂ ኃይል አለው ወይስ የለውም? ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል አይደለምን? ዘዴዎች ሳይለጠፉበት ብቻውን የመስቀሉ ቃል የውስጥ ማንነታችንን የመለወጥ ኃይል አለው አይደለምን?” መልሱ አንድ ነው። ያልተበረዘ ወንጌል ይህንን ያደርጋል። አዎ! በእርግጥም የሚያስፈልገን ወንጌልና ወንጌል ብቻ ነው፤ ህም ማጋነን አይደለም። ጳዉሎስ እንደሚያስገነዝበን ወንጌል ለክርስትያን ሁሉን-አቀፍ እውነታ ነው። ሁሉንም ነገር የሚይዝና የሚሸፍን ድንኳን ነው። ወንጌልን ተምረን ልንጨውርሰው አንችልም። የወንጌልን ምስጢርና ጥልቀት ሙሉ በሙሉ ማወቅ አንችልም። ምንጩ ዘላለማዊ የሆነው የሱሉስ አምላክ አሠራር እንደመሆኑ (የእግዚአብሔር ወንጌል…ወንጌሉም ስለ ልጁ ነው…በቅድስና መንፈስ ከሙታን የተነሳ [ሮሜ 1:1-5]) ወንጌል የሚደረስበት ዳርቻ የለውም። መታሰቢያውም ለዘላለም ይኖራል።

“…. መጽሐፉን ልትወስድ ፣
     ምሕተሞቹን ልትፈታ ይገባሃል፣
ምክንያቱም ታርደሃል፣
      በደምህ ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣
    ከወገን ሁሉ፣ ከህዝብ ሁሉ
  ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።
ለአምላካችንም መንግስትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤
እነርሱም በምድር ላይ ይገዛሉ።” (ራዕ. 5፥ 9፣ 10)

አንድ ጸሃፊ አንዴት ቤተ ክርስቲያን ከእምነት ወደ ስህተት እንደምታመራ ሲጽፍ እንደዚህ አለ:

“ቤተ ክርስቲያን ከጤናማ ትምህርት ወደ ክህደት እንድታፈገፍግ ሶስት ትውልድ ይጠይቃል። የመጀመሪያው ትውልድ በታማኝነትና በሕይወት ይጠብቀዋል፡ ሁለተኛው ትውልድ ግን የመጀመሪያውን ትውልድ መንፈሳዊ ጎን ተደግፎ፤ ጤናማውን ትምህርት ያምናል ነገር ግን በአጽንዖት አያውጀውም፤ አጽንዖቱና ትኩረቱ ግን በትርፍ ነገሮች ላይ ይሆናል። ሶስተኛው ትውልድ ግን ዋናውን ትምህርት፤ ሁለተኛው ትውልድ አጽንዖት ያደረገበት ትርፍ ነገር ላይ ይሆንና፤ ጤናማውን ግን ይክዳል።”

ለዚህ ቀውስ ተጠያቂ ማነው? ሁለተኛው ትውልድ ነው። ትኩረቱ ያነጣጠረው በዋናው ነገር ላይ ስላልሆነ ነው። ለዚህ ነው ብዙዎቻችን ከእንቅልፍ የመንቃት ያሕል “እንዴት እዚህ ደረስን?” ብለን እየጠየቅን ነው። በርግጥ በሦስተኛው ትውልድ ላይ ቆመናል። እንዴት ነው በሺዎች የሚቆጠሩ የሚታደሙበት ጉባኤ ላይ ከሳምንት እስከሳምንት ክርስቶስ ሳይሆን “አይዞህ በርታ…ትችላለህ…ትወርሳለህ…ትፈወሳለህ…ሀብታም ትሆናለህ…’ነው ያልሀው ይሆናል’…’ቃልህ ይፈጥራል’…’እንደ እግዚአብሔር ያለ እምነት ያዝ’…!” የሚል መስቀል አልቦ መልክት እየተሰበከ «ወንጌል» አደራ ተወጥተናል የምንለው? ለዚህ ሁሉ መፍትሔው፣ ሐዋርያው በኤፌሶን የሦስት ዓመታት የአገልግሎት ቆይታው በኋላ የተናገረውን እንደ አርዓያነት ብንወስድ ይረዳናል፡-

“የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም።  በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።  አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።(ሐዋ 20:27–32)

..በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና…እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።

…እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው።…

ስለዚህ ከሁሉ አስቀድመን አንድ ማድረግ የሚገባን ነገር አለ። ይህም የብሩክ እግዚአብሔርን የክብር ወንጌል (1 ጢሞ. 1፥ 11) ምን እንደሆነ መማር አለብን። ወንጌል የማንነታችንና የህልውናችን ማዕከል ነው። በዚህ ዓለም ሳለን ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰለል የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ፤ የመለኮቱ ሐይል የሚሰጠን፤ በዚህ መሰረት ላይ የቆምን እንደሆነ ነው። ወንጌል ለምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ አውዳዊ አስኳል፤ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት አቅም ብቸኛ ምንጭ መሆኑን ማወቅ አለብን። ይህንንም ስጽፍ፣ የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቅዱሳን፣ እነዚህ ነገሮች ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም። ነገር ግን በሐዋርያው ጴጥሮስ ቃል ላበረታታችሁ እውዳለሁ

“ወዳጆች ሆይ፤ ይህ አሁን የምጽፍላችሁ….ቅን ልቦናችሁን እንድታነቃቁ ለማሳሰብ ነው፤ ደግሞም ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያታችሁ አማካይነት በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትዕዛዝ እንድታስቡ ነው” ( 2ጴጥ.3 ፥ 1-2)

(ከዚህ ቀጥሎ ወንጌል በብሉይ ኪዳን እንዴት እንደተሰበከ በክፍል ሁለት እንመለከታለን)

(እነዚህን መጣጥፎች በማረም ላገለገለኝ ለወንድማችን ለካሳሁን መኩሪያ ጌታ ይባርክህ እላለሁ። እነዚህ ተከታታይ ትምሕርቶች አስቀድሜ በእንግሊዝኛ አዘጋጅቼ ያቀረብኋቸው ነበሩ።)

2 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published.