Blog,  የዮሐንስ-ወንጌል

የክብር ጎዳና፡ (መስቀልና ዙፋን – ክፍል 2)

ክርስቶስና የመስቀሉ ተልዕኮ መውረድ እና መውጣት በዮሐንስ ወንጌል

❝ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ «ሰዓቱ ደርሶአል»፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው…እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ❞

❝ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ የሚከብርበት «ሰዓቱ ደርሶአል»፤ እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች… “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚች ሰዓት ታድነኝ? የለም፤ ይሁን የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና። አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው❞

የዚህ ጽሑፍ አጠቃላይ ሐሳብ

በዮሐንስ ነገረ-መለኮታዊ አስተምህሮ ውስጥ ለይትና ጎላ ብሎ የሚታይ ዕሳቤ ቢኖር ይህ “የመውረድና የመውጣት” ድግግሞሽ ነው። እስኪ በሀሳባችን ከላይ ወደታች የሚወርድ አንድ ቀስት እንሳል። ደግሞ ሌላ ቀስት እንዲሁ የመጀመሪያው ቀስት ካበቃበት ወደ ጀመረበት የሚመለስ ሌላ ቀስት እንሳል። እነዚህ ሁለቱ የሚጋጠሙበት “ነጥብ” የዮሐንስ ወንጌል እምብርት፤ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እና “መስቀልንና ዙፋንን” ያማጠነ ክርስቲያናዊ ኑሮ ምን እንደሚመስል ይገልትልናል። ይህች ነጥብ ክርስቶስ እንደወረደ የወጣበት፤ እንደተዋረደ የከበረበት ነጥብ ናት፡፡ ከአብ ዘንድ ተልኮ የመጣበትን ዓላማ የፈጸመባት ሥፍራ፤ በመፈጸሙም አብን የያከበረበት፤ በዚያው ክብርም ራሱ ወልድ ወደ ከበሬታው የተመለሰባት ሥፍራ ናት።

ስለዚህ መስቀሉ የውርደት ሥፍራ ብቻ ሳይሆን፤ የክብርም ጎዳና ነው። እንዲሁም መስቀሉ በሐጥያት ላይ፤ በሞትናበዲያብሎስ ላይ ድልን የተጎናጸፈበት ሥፍራ ናት። እንግዲህ የዮሐንስ ወንጌል አስተምህሮ ሚዛን የተመጣጠነው በዚህ “መውረድና መውጣት” እውነታ ላይ ነው። እስኪ ይህንን እይታ በሠፊው እናብራራ።

አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል

በዚህ ዮሐንስ ወንጌል ውስጥ “ሰዓት” የሚለው ቃል ከሌሎቹ ወንጌላውያን ለየት ያለ ትኩረትና በዮሐንስ-ነገረ-መለኮታዊ ትረካ ውስጥ ደግሞ እያደገ የመጣ ሐሳብ ነው። ለምሳሌ ያህል፤ ለማርቆስ የሰዓቱ መድረስ/የዘመኑ መፈጸም/ (ማር 1:15) ከነብያት ድምጽ ጋር በማገናኘት (ማር 1፡2-3)፤ ክርስቶስ በማንነቱና በአገልግሎቱ የእሥራኤልን ተሥፋ በሰውነቱ ተላብሶ መገለጡን ይገልጽልናል (አገልግሎት የሚለውን ቃል ለክርስቶስ ስጠቀም በቃልና በሥራ የተሰጠውን የክርስቶስን መለኮታዊ አስተርዕዮ ማመልከቴ ነው።[1] ስለዚህ በማርቆስ ወንጌል “ዘመኑ ተፈጸመ” ሲል በክርስቶስ አገልግሎት (በማንነቱ፤ በቃሉና እና በሥራው) አማካይነት የእግዚአብሔር መንግሥት መጥባቷን ያውጃል (ማር. 1:11; መዝ 2፡7/ 2ሳሙ 7:14) ። እግዚአብሔር የሰጣቸው የማዳን ተስፋዎች ሁሉ አሁን በገሊላ አውራጃ እየተፈጸሙ ናቸው። የእግዚአብሔር መንግሥት ጠብታለች። ይህም የእ/ር ልጅ ወንጌል መጀመሪያ ነው።

ወንጌላዊው ዮሐንስ ግን ‘ሰዓት’ የሚለውን ቃል ሲጠቀመው ከወልድ ተልዕኮ ጋር በተያያዘ መልኩ ጥልቅ መለኮታዊ እውነትን እንዲያንጸባርቅ አድርጎ ነው። ክርስቶስ ማን እንደሆን ሲተርክልን ቃል-ሥጋ ከመሆኑ/ከትሥጉቱ (1:14) በማለፍ ሥነ-ፍጥረት ወደ መሆን ከመምጣቱ አንድ እርምጃ ዕምር ብሎ ይጀምራል (1:1)። እንደዚሁም ስለ ክርስቶስ አገልግሎትም ሲጽፍልን ከምኩራብ አገልግሎቱ ፈቀቅ በማለት በቃና ዘገሊላ ከተማ ከአንድ የሰርግ በዓል ይጀምራል (2፡1-11)። ዮሐንስ ሲነግረን “ይህን የታምራዊ ምልክቶቹ መጀመሪያ…አደረገ…ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ (2:11)።

ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ “ክብር”፤ “ምልክት”፤ “የአብ ፈቃድ መፈጸም”፤ “የወልድ ተልዕኮ”፤ “መውጣትና መውረድ”፤ “የመስቀሉ ውርደትና የትንሳኤው ክብር”፤ “የዘላለም ሕይወትና ፍርድ” ከዚህች አንድ ቃል “ሰዓት” ጋር የተያያዙ ናቸው። ሆኖም ግን ይህች ሰዓት ልክ ከእጀታው ወደ ጫፉ እየጋለ እንደሚመጣ ብረት፤ በዮሐንስ የነገረ-መለኮት ትረካ ውስጥ ከሰው ልጅ አገልግሎት መጀመሪያ ጋር ሳይሆን የሰው ልጅ ታልፎ ከሚሰጥባት “ቀን” ጋር የተያያዘች ነች።

ጊዜዬ ገና አልደረሰም

የመጀመሪያውን ምልክት በቃና ሲያደርግና ደቀ መዛሙርቱ ክብሩን ሲያዩም ሆነ በእርሱ ሲያምኑ፤ ይህች ሰዓት ገና አልደረሰችም፡-

❝የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፤ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም፤ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት❞[2] (ዮሐ 2:3-4)

ጊዜ ይመጣል…አሁንም መጥቶአል

ይህቺን “ሰዓት” ዮሐንስ በሁለት መንገድ ይገልጣታል። በአንድ ወገን ክርስቶስ “በቃሉና በሥራው” አገልግሎቱን ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ በከፊልም ቢሆን “ሰዓቱ” ደርሷል (ልክ የጸሃይ ትኩሳት ከጠዋት ወደ ቀትር እንደሚሄድ) ስለዚህ፦

❝በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት «ጊዜ ይመጣል»፤ አሁንም መጥቶአል (4:22-23)❞

❝እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት «ጊዜ ይመጣል»፤ አሁንም መጥቶአል (5:25)❞ ይህ አነጋገር በሌሎቹ ወንጌላት ላይ ከእግዚአብሔር መንግሥት አገላለጥ ጋር ስምረት አለው።

ጊዜው ገና አልደረሰም ነበርና

ሆኖም ደግሞ በመደጋገም በሌላ እጅ “ጊዜው ገና አልደረሰም” ይለናል።

❝ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን…❞ (John 7:30–31)

❝ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም። ኢየሱስም ደግሞ። እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው❞ (John 8:20–21)

ከላይ የተመለከትነው ዮሐንስ በጠንቃቃ አጻጻፉ፤ ሰዓቲቱ ገና አለምድረሷን ሲሆን፤ በሌላ እጅ ደግሞ የእ/ር ልጅ በቃልና በሥራው “የወዲያኛው ዘመን ሃይል” በአገልግሎቱ መገለጥ በመጀመሩ “ይመጣል…አሁንም መጥቷል” ይላል። ግን በዋነኝነት ደረጃ በመደጋገም “ሰዓቱ አልደረሰም” ብሎናል።

በዮሐ. 12:20-21 ላይ ግን ይህች ሰዓት መድረሷን አብ ለሚወደው ልጁ “ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን” ብለው በመጡት በግሪክ ሰዎች አመለከተው። ይህ የሆነው ኢየሱስ “ሆሳዕና…የእሥራኤል ንጉስ የተባረከ ነው” ተብሎ እየተዘመረለት ወደ ኢየስሩሳሌም ከገባ በኋላ ነው። መቼም ይህ ጽሑፍ እንዳይረዝም እንጂ፤ የህዝቡ በዝሙር በጣም ትልቅ ብሉ ኪዳናዊ እንደምታ አለው። ለዚህ ነው በዚህ ክፍል ላይ ዮሀንስ (12:16) “ደ/መዛ. ይህንን በመጀመሪያ አላስተዋሉም ነበር…ስለ እርሱ የተጻፈውን ልብ ያሉት ኢየሱስ ከከበረ በኋላ ነበር” ያለን። ሕዝቡ የዘመረው መዝሙር 118 ነው (118፡25-26)። ይህ መዝሙር “ግንበኞች የናቁት እንዴት የማዕዘን ራስ እንደሚሆን፤ በጌታም ስም የሚመጣ የተባረከ እንደሆነ የሚያወሳበትም ክፍል ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ 118:24 ላይ “እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ በእርሷ ሐሤት እናድርግ፤ ደስም ይበለን” ይላል። ይህንን ጥቅስ ስንጠቅስ ከአውዱ ስለምንለየው የጥቅሱን መልክት ስተነዋል። መዝሙረኛው የሚናገረው ስለወደፊት “መሲሃዊ ቀን” ነው። ይህቺ ቀን “ያህዌህ ህዝቡን” የሚያድነበት ቀን ናት። በጌታ ስም የዳዊት ልጅ መሲሁ የሚገለጥበት “እ/ር የሠራት ቀን” ናት። ዮሐንስ ጌታ ወደ ኢየስሩሳሌም ሊሰቀል የገባባትን ቀን ያች መዝሙረኛው “ያህዌህ የሠራት ቀን” ያላት ነች። ይህም አሕዛብ ወደ ኪዳኑ በረከት መጠጋታቸው ለአብርሃም የተሰጠውን የተሥፋ ቃል አሁን በወልድ የመስቀል ተልዕኮ የሚፈጽምበት ሰዓት መድረሱ ሲያመላክት ነው።

 

► የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል

ስለዚህ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ (ስለ ክርስቶስና ስለዚች ሰዓት ሲናገር «ገና አልደረሰም ነበርና» ሲል የነበረውን) እንዲህ ይላል፦

❝ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ «ሰዓቱ ደርሶአል»። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።… አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ? ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም። አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ…አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ። በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ❞ (ዮሐ. 12:27–33)

ከዮሐ. 12 በኋላ ስለዚህች ሰዓት ዮሐንስ በሚናገርበት ሥፍራ ሁሉ “ሰዓቱ ደረሰ” ይለናል።

❝ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው❞ (13:1)

❝አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው❞ (17:1)

ከዚህ ወደ ጥልቅ ጅረት ከሚወስደን ዋና እንውጣና ወደ ጀመርንበት መሪ-ክፍል እምር እንበል። ወልድ ወደ መስቀል ከመውጣቱ በፊት ሲጸልይ መጀመሪያ ከአፉ የወጣው ቃል “አባት ሆይ ሰዓቱ ደርሶአል” ነበር (17:3)። የዚህች ሰዓት ትልቅነት የተመሰረተው በዚህች ሰዓት ውስጥ የሚከናወነው ሥራ ነው። ጠቅለል ለማድረግ ይህ ሰዓት ወልድ ወደ መጣበት ተመልሶ የሚሔድበት፤ ተልዕኮውን የሚፈጽምበት “ሰዓት” ነው። ይህች ሰዓት ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በክበበ ስላሴ የታቀደች፤ ቃል-ሥጋ ሆኖ ወደ አገግሎቱን ከጀመረ በኋላ ይጠብቃት የነበረች ሰዓት ናት። ሐጥያትን ንቆ፤ በታላቅ ተጋድሎ የጸናው ለዚህች ሰዓት ነበር፤ “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚች ሰዓት ታድነኝ? የለም፤ ይሁን የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና። አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው” (Jn 12:27–28)። አሜን! የሕዝብህ ጀግና ኢየሱሰ።

መውረድና መውጣት

ከዚህች ሰዓት ጋር ተያይዞ በዮሐንስ ወንጌል ላይ የምናገኘው ሌላው ሐሳብ “መውረድና መውጣት” የሚለውን ነው። ይህ ብዙ እውነታዎችን ያቀፈ ነው፦ ለምሳሌ የወልድ ከሰማይ ተልኮ መምጣቱ (3:11-13፤ 3:31-33)፤ ወደ ነበረበት ክብር መመለሱ፤ ፈቃዱን መፈጸሙ፤ አብ መክበሩ…ወዘተ…ይህ ሐረግ በአጭሩ ሦስት ነገሮችን ያቅፋል፤

  • መምጣቱ/ መውረዱ፦ ስለ ብርሃን፤ ስለ አብ፤ ስለ እውነት፤ ሊመስከር ወደ ዓለም መጥቷል (1:5, 9, 11; 3:19; 9:39; 12:46-47; 16:28; 18:)
  • ከአብ ዘንድ መምጣቱ/ መላኩ፦ 5:43; 7:28
  • “መውረዱ እና መውጣቱ”/ “መምጣቱና መመለሱ” እንደ ወረደ ተመልሶ መውጣቱ፦ 7:35; 8:14; 8:21-22; 13:33; 14:2-5, 12, 18, 28; 16:5, 7, 10, 17, 28; 17:11, 13)

ይህ መውጣትና መውረድ በአንድ ወገን ወልድ ከአባቱ ጋር የነበረውን ግንኙነት እና ምጡቅ ማንነቱን (ሰው ከመሆኑም በፊት መለኮትነቱና ከአባቱ ጋር ያለውን ምጡቅ ግኙነት) ሲያረጋግጥልን በሁለተኛ ደግሞ ይህ “መውጣትና መውረድ” የብሉይን ተስፋ መፈጸሙን ያሳያል። ይህን ጽሑፍ ለማሳጠር ያህል፤

  • ኢየሱስ በዳንኤል 7 ላይ «ሲወጣና ሲወርድ» የምናየው ‘የሰው ልጅ” እንደሆነ፤
  • በምድረበዳ ሕዝቡ በሕይወት እንዲኖር “ከሰማይ ከወረደው መና” ጋር መመሰሉ እና
  • በተለይ ደግሞ በም.12 ላይ “ከፍ ከፍ/ὑψόω” የሚለውን ቃል ሲጠቀም በኢሳያስ ትንቢት ላይ በ52:13 ላይ የተዋረደው የጌታ ባርያ “ባሪያዬ ከፍ ከፍ ይላል” ተብሎ ከሥቃዩ በኋላ ወደ ከበሬታ ከሚወጣው ጋር መመሰሉ ነው። ኢሳያስ ስለዚህ ባሪያ በም.53 ላይ በስቃይ እንደሚያልፍ ከመተንበዩ በፊት “እነሆ ባሪያዬ…ገናና ይሆናል፤ ከፍ ከፍ ይላል (MT: נשׂא, LXX: ὑψωθήσεται)፤ እጅግ ይከብራልም…” ማለቱ እና በዮሐንስ ነገር መለኮታዊ ትረካ ደግሞ ክርስቶስ ገና ወደ መስቀል ስቃይና ውርደት ሲቀርብ “ስለ መክበሩ” መናገሩ የምንናገረውን ይህንን ንፅፅር ይበልጥ ያረጋግጥልናል።

የክርስቶስ መስቀል የክብር ጎዳና ነው

እስከ አሁን ዮሐንስ ሲያሰናዳን የቆየው ወልድ ይጠብቃት የነበረችው ሰዓት “ወደ መስቀል የሚወጣባት ሰዓት” መሆኗን ሊያሳየን ነው። በዚህች ሰዓት ላይ የሰው ልጅ በእንጨት ላይ “ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” አለ። ይህም ዮሐንስ በተለምዶ ድርብ አነጋገሩ በአንድ እጅ በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ማመልከቱ ሲሆን «በእንጨ ተቸንክሮ ወደ አየር መንጠልጠሉ»፤ ጠለቅ ብሎ ግን የሚነግረን “ይህ የመስቀል መንገድ «እንደ ወረደ የሚመለስበት» ሥፍራ መሆኑን ነው። ከምድር ወደ አየር ሲንጠለጠል፤ ከምድር ወደ ሰማያዊ ክብሩ መመለሱ ነው። ስለዚህ መስቀሉ የውርደትና የከበሬታ ሥፍራ ነው። መስቀሉ፤ የሥቃይና የሐሴት መጋጠሚያ ነው። ሞትና ትንሳኤ፤ ፍትህና ምሕረት፤ ጨለማና ብርሃን፤ የተገጣጠሙበት ስፍራ ነው። ያለ መስቀል ዙፋን አይገባበትም፤ ፍርድ ብቻ ነውና። ያለ ዙፋን መስቀል ደግሞ ትርጉም የለሽ ነው። ምክኒያቱም ከኢየሱስ ጋር ሌሎች ወንጀለኞች እንዲሁም ብዙ አይሁዳዊ ወጣቶች ሞተዋል። ይህንን መስቀል ከመስቀል መካከል የለየው በመስቀሉ ላይ የተሰቀለው «ከሰማይ ይወረደው እርሱ ከሁሉ በላይ» ስለሆነ ነው።

መስቀሉ እነዚህን ሁለት እውነታዎች ወጥሮ ይይዛል። ከአባቱ ጋር የመለኮት ክብር ገንዘቡ ሆኖ ሲኖር ከነበረበት ልዕልና ክብሩን ወደ ማታውቅ ወደዚህች ዓለም በመምጣት ራሱን አዋረደ (17:19, ፊል. 2:9-11)። የመጣው የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ነበር። ሆኖም ግን በዚህ በተዋረደ የመስቀል ሞት በኩል የአባቱን ፈቃድ በመፈጸሙ አብን አከበረ። አብ ደግሞ ወልድን ያለ ልክ አከበረው፤ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ሥልጣንን ሰጠው፤ ከብሮ እኛንም አከበረን። በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ደግሞ ክብር ገንዘባቸው ሆነ! (“የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ” 17:22)

የመስቀሉ ጥሪ

ምናልባት አንድ ሰው “እሺ እስማማለሁ፤ ግን ይህ ለኢየሱስ እንጂ እኛማ ከእርሱ የተነሳ ይህንን አልፈናል” ለሚል ሰው ኢየሱስ ደ/መዛ. እንዲህ ይላቸዋል፡-

❝እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ሕይወቱን የሚወድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል❞ (12:24-26)

ይህ ማለት የኢየሱስ የመስቀል ሥራ በአንድ እጅ ወልድን ብቻ የሚመለከት “የቤዝዎት ሥራ” ቢሆንም፤ በሌላ መልኩ ደግሞ “ፈለጉን እንከተል ዘንድ” ምሳሌያችንም ጭምር ነው (1 ጴጥ. 2:21)። ልክ ክርስቶስ በመከራው ጥምቀት ክብርን እንደተጎናጸፈ፤ እኛም የእርሱን ፈለግ ተከትለን “በዚህ ዓለም” መከራውን ከመሰልን፤ እኛም እርሱ አሁን እኛን ወክሎ በአብ ዘንድ “ወደ ሚታይልን” እጅ ወዳልሰራው መቅደስ (እኔም ባለሁበት) እንገባለን። ይህ የሚሆነው በክርስቶስ ውድ ለሆናችሁ ሁሉ ቅዱሳን፤ “መስቀልንና ዙፋንን” ያጣጣመ እምነትና ሕይወት የያዝን እንደሆን ነው።

ዛሬ ከነገረ ዮሐንስ፤ “መስቀልና ዙፋን” የሚለውን ሐሳብ ተመልክተናል። በሚቀጥለው ደግሞ ከሌሎቹ ወንጌላትና ከጳውሎስ ነገረ መለኮታዊ አስተምህሮ ይህንኑ ሐሳብ እንቃኛለን። ከዚያ ቀጠል አድርገን በመጨረሻ “መስቀልን እና ዙፋንን ያማጠነች ቤተክርስቲያን ምን ትመስላለች?’ ብለን ወደ ጀመርነው ጥያቄ ተመልሰን ተግባራዊና ምጋቢያዊ የሆኑ ጉዳዮችን እንዳሥሣለን።

[1] what some call the ‘Christ-event’, see Scobie, Wright, Hays

[2]“οὔπω ἥκει ἡ ὥρα μου” ‘ሆራ-ሙ’ ለሚለው የግሪኩ ቃል ‘ሰዓቴ ገና አልደረሰም” ብንል ምናልባት ሐሳቡ ይበልጥ ግልጥ ብሎ ይታያል

Leave a Reply

Your email address will not be published.