Blog,  የአዲስ ኪዳን ነገረ-መለኮት

የተሰቀለ-ክርስቶስ

ዛሬ እንደ ግሪጎሪያን አቆጣጠር የክርስቶስ የስቅለት ቀን ነው። በዚህ ቀን አንድ ጸሎት አለኝ “የዚህ ቀን እውነታ ሳያቋርጥ በዘመናችን እና በትውልዳችን እንዲቀጥል…ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ በመልዕክታችን እንዲኖር! (ገላ 3:1 |፡1 ቆሮ. 2:2-3)”

ኢየሱስን እንደ ክርስቶስ መቀበል እና እንደ ተሰቀለ-ክርስቶስ መቀበል ይለያያሉ። እኛ የምንሰብከው “የክርስቶስ መስቀል” ከሌሎች መስቀሎች ልዩ ያደረገው፤ “መሰቀል” የሚባለው እውነታ ሳይሆን (በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁድ ወጣቶች ተሰቅለው ነበር – በተለይ በ4BC አካባቢ ላይ)፤ በመስቀሉ ላይ የተሰቀለው እርሱ «ማን መሆኑ ነው»። ይህ የምንናገርለት መስቀል “የክርስቶስ መስቀል” ነው። በሰው አስተሳሰብ ሁለቱ ቃሎች፡ “ክርስቶስ” እና “መስቀል” አብረው የማይቀመጡ ቃሎች ናቸው። ኢየሱስ አስቀድሞ መከራን እንደሚቀበልና እንደሚገደል ሲናገር ጴጥሮስ አይሁንብህ እያለ “ይገስጸው ጀምር” ይለናል። ኢየሱስም “የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው” ምክኒያቱም “አንተ ክርስቶስ ነህ” የሚለው ቃል እና “መከራ..ሞት” በሰው ሐሳብ አብረው አይሔዱም። የሰው ጥበብ በውርደት ከፍታን አያስብም። የሰው ጥበብ በመከራ ክብር አያይም። የሰው ጥበብ “እንዴት አድርጌ በሌሎች ላይ ተረማምጄ እነግሳለሁ” እንጂ “ለሌሎች ራሴን አሳልፌ እንዴ እሰጣለሁ” አይልም። ስለዚህ በሰው ጥበብ “ክርስቶስ እና መስቀል” አብረው አይሔዱም። ክርስቶስ ይነግሳል፤ ወንጀለኛ ይሰቀላል። ንጉስ ይበረታል፤ በእንጨት ላይ የተሰቀለ ደግሞ ርጉም ይሆናል። ሆኖም ግን፤ የእግዚአብሔር ጥበብ፤ በዚህ በሰው ዓይን ሞኝነት በሚመስል መንገድ ተገጠ። ይህን እውነት ሐዋሪያው “የመስቀሉ ቃል” ወይም “የስብከት ሞኝነት” ይለዋል። እዚህ ጋር ሞኝነት የተባለው “ስብከት” ሳይሆን የስብከቱ ይዘት ነው። የተሰቀለ-ክርስቶስን ገንዘቡ ያደረገ ስብከት፤ በሰው አይን ሞኝነት ነው። ስለዚህ ነው “ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም” ያለን። “በቃልና በጥበብ ብልጫ” የተሞረደ ስብከት አለ ማለት ነው። ሰባኪውን የሚክብ፤ ሐይልን ከድካም ነጥሎ የሚያውጅ ስብከት። በአጭሩ ይህ “ከመስቀሉ ላይ ደሙን ያጠበ” ስብከት ወይም መከራውን ያጸዳ ስብከት ነው። የክርስቶስን ሐይል ያውጃል፣ ግን ያለ መስቀሉ ድካም። ሆኖም እግዚአብሔር ያሰበልን ሙላት በሙሉ፤ በዚህ የሚቃረን በሚመስል እውነታ ውስጥ ተካቷል። የተሰቀለ-ክርስቶስ በሚል ውጥረት። ደ\መዝ በሆነው ህይወታችን እንዲሁ በእያንዳንዱ ተግዳሮታችን ውስጥ (ስብከታችን፤ መዝሙራችን፤ አገግሎታችን፤ ግንኙነታችን ወዘተ..) በዚህ እውነታ ራሳችንን መቃኘት እና ይህንን እውነታ ማንጸባረቅ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው።

የተሰቀለ-ክርስቶስና የገላትያ ሰዎች

“በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (ገላ. 3:1)

ጳውሎስ እንዴት ቃሎቹን እንደሰካካ ማጤን ይኖርብናል። ክርስቶስ ኢየሱስ በገላትያ ሰዎች ፊት «ማዕከል» መሆኑ አይደልም አነጋጋሪው ጉዳይ። አነጋጋሪው ጉዳይ “ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ” በፊታቸው መሳሉ ነበር። ይህም የተሰቀለ-ክርስቶስን ያላማከለ እምነትና ሕይወት “ከሰበክንላችሁ ወንጌል” (ገላ 1፡8) ከተባለው የተለየው ወንጌል መሆኑ ነው። ሐዋርያው ራሱን ምጥ-እንደያዛት ሴት የሚመስልበት ጉዳይ ይሀው “የተሰቀለ-ክርስቶስ” በፊታቸው ባለመሆኑ ነበር። የልቡም ጭንቀት “ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል” ነበር። ሥዕላዊ ዕይታው ሽምቅቅ ያደርጋል። ልክ አንድ ጊዜ የወለደችውን ልጇን መልሳ ለመውለድ በምጥ የምትዳርክ እናት አድርጎ ራሱን በዘይቤ ይመስላል። “ዳግመኛ ምጥ ይዞኛል” ይላልና። በአንድ ወቅት የገላትያ ሰዎች የመስቀሉን-ቃል ሰምተው ዳግም ልደት አግኝተው ነበር። አሁን ግን ልውጥ-ወንጌል በመካከላቸው መጥቶ “የተሰቀለ-ክርስቶስን” ከፊታቸው ዘውር አድርጎ ሌላ ክርስቶስ ስለተተካ እንደገና “በምጥ” ላይ ነው። የሚገርመው ይህ ሁሉ ሲሆን የገላትያ ሰዎች እየሆነባቸው ያለውን ጉድ አልተረዱም “አታስተውሉም” …”አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (አፍዝ አደንግዝ??)” የተሰቀለ-ክርስቶስን ማዕከል ያላደረገ እምነት የማይረባ እምነትና ልዩ-ወንጌል ነው። ሕይወትን የሚለውጥ የክርስቶስ ወንጌል ማዕከሉ የተሰቀለ-ክርስቶስ ነው።

የተሰቀለ-ክርስቶስና የቆሮንቶስ ሰዎች

ተመሳሳይ አነጋገርም ለቆሮንቶስም ሰዎች ይጽፋል (እነዚህ ደግሞ እንደ ገላትያ ሰዎች «የሕግ-ሥራን» ለመቀበል የሚዳክሩ ሳይሆኑ፤ «የዚህችን ዓለም ጥበብ» ሙጭጭ አድግረው ከመያዝ መላቀቅ ላቃታቸው ሰዎች የተጻፈ መልክት ነበር። በሰማያዊ በረከቶችንና መፈሳዊ ጸጋ ቢጥለቀለቁም መንፈሳዊ ብስለትን አልተላበሱም። የመስቀሉንም ሎጂክ አልጨበጡም። መንፈሳዊውን ሕይወት ሊያወልቁ በተቸገሩበት አረማዊ ጓንታቸው እያረከሱት ነው። ለእነርሱ መንፈሳዊ መሪነት መታወቂያና የቡድን መሪነት ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎች የስሉሱን አምላክ ማንነት በሕይወታቸው መንጸባረቅ ቀርቶ (ትርጉምና ሥርዓት ያለው) በአረማዊ አስተሳሰባቸው በመበረዙ ምክኒያት መንፈሳዊ ሥጦታ የሁከትና በፍሬው “ኢየሱስ ጌታ እንደሆን” የማይመስከር ሆኗል። የእርስ በርስ ግንኙነታቸውም እንዲሁ በመካሰስ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ራስ-ጠቀም መሆናቸው የወንጌሉ ትርጉም (የተሰቀለ-ክርስቶስ) ስላልገባቸው ነው፡፤ ለዚህ ነው ደብዳቢውን ሲጀምር (1:18 – 2፡15) በተሰቀለ-ክርስቶስ ጀምሮ፤ ተመልሶ በመስቀልና ትንሳኤ የሚዘጋው (15:1-58)። ስለዚህ እንዲህ ይላቸዋል።

“በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና…እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም”

ልክ በገላትያ ላይ እንዳየነው አሁንም አጽኖቱ ያረፈው “ክርስቶስ-እርሱም-እንደተሰቀለ” መሆኑ ላይ ነው። “እርሱም” የምትለው ቃል ‘አስማሪ ቃል’ (emphatic or Topical-Framing discourse function) ሆና ታገለግላለች። በመካከላቸው ሳለ አስረግጦ የነገራቸው ስለ “ተሰቀለ-ክርስቶስ” ነው። የቆሮንቶስ ሰዎች የቡድንና የወገንተኛ አስተሳሰባቸው (1 ቆሮ. 1:11-13) መንስኤ የመስቀሉን አርዓያነት ገንዘቡ ያላደረገ ዓለማዊ መንገድና ጥበብ መከተሉ ነው። የሚማጸናቸውም “ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን” ነው (1:10)። አውዱ እንደሚያስረዳን፤ በመካከላቸው ያለው ልዩነትና ክፍፍል፤ የመስቀሉን መልክት እንደምታ በሙላት ባለመረዳታቸው ነው። ጳውሎስ ሁለት ዓይነት ሰዎችን ብቻ እንደሚያውቅ ነካ እያደረገ (ስለ መከፋፈላቸው) ያሳውቃቸዋል፡ “የሚጠፉ ሰዎች” እና “የሚድኑ ሰዎች” (1:18)። ጥንታዊው ሰው ልክ እንደ ዘመናዊው፤ ሕብረተሰብን በቀለም፤ በዘር፤ በጎሳ፤ በሐብት፤ በእውቀት፤ በጾታ፤ በእድሜ…ወዘተ በመከፋፈል፣ ሰውን ያከብራል ወይ ይንቃል። ለጳውሎስ ግን ዓለምም ጥበቧም ከክርስቶስ መስቀል የተነሳ አልፏል። እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም (1:26)፡፡ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ (1:26)፡፡ «አለሁ» የሚለውን ከንቱ ሊያደርግ«ምንም» የተባለውን መረጠ፡ (1:28)፡፡ ስለዚህ ሰውን ሁሉ አሁን የምናውቀው በክርስቶስ ነው (2 ቆሮ. 5፡16-17)። “የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና” (7:31)። ጳውሎስ ለዓለም፤ ዓለምም ለጳውሎስ ተሰቃቅለዋል። የሰው የማንነቱ ርባና ለመስቀሉ-ቃል የሚሰጠው ምላሽ ብቻ ነው (1:18)። ምክኒያቱም ክርስቶስ ሰዎችን ሁሉ ከነገድ ከቋንቋ፤ ከዘርና ከጎሳ ዋጅቷልና። ሆኖም ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች (የአሕዛብ መንገድ ለመከተል ለተፈተኑ) ይሁን “መገረዝን እና የሕግን ሥራ” ለመቀበል (ይሁዲነት) ለተፈተኑ የገላትያ ሰዎች መልሱ አንድ መሆኑን ነው! «የተሰቀለው-ክርስቶስ» የመስቀሉም ቃል “የተሰቀለ-ክርስቶስን” ማዕከል ያደረገ ነው።

በተሰቀለ-ክርስቶስ ማመን ለአሕዛበ ሞኝነት ነው። ምክንያቱም የተሰቀለ-ክርስቶስ በጆሮዎቻቸው ሲሰሙ ልክ “ጥልቀት አልባ ጉድጓድ” ወይም “የማያቃጥል እሳት” እንደማለት ነው! ስሜት አይሰጥም። “ክርስቶስ” ንጉሥ ሊሆን የተቀባ ማለት ከሆነ ታድያ ንጉሥ መስቀል ላይ ምን ያደርጋል? መስቀል የተመደበው የሮም ዜጋ ላልሆኑ ወንጀለኞችና መንግሥት-ግልበጣ ሙከራ ላደረጉ ወንበዴዎች ነውና። ይሁንና የእግዚአብሔር ሞኝነት ከጠቢባን እውቀት ይጠበባል። የተሰቀለን-ክርስቶስ ማዕከል ያደረገ ወንጌል ደግሞ ለአይሁድ እንደ ግሪኮች ትርጉም የማይሰጥና የሚቃረን ብቻ ሳይሆን የሚያስቆጣም ነው። መሰናክል ነው! ለምድር ሁሉ የምስራችን የሚያመጣው ቅዱሱ መሲህ፤ እሥራኤልን የሚታደግ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚመሰርተው የዳዊት ልጅ፤ እና አይሁድ ለዘመናት ሲጠባበቁት የነበሩትን ይህን መሲህ «ያ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ታልፎ የተሰቀለው» በእነርሱ አስተሳሰብ «አስመሳይ-መሲህ» የሆነውን ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ ማወጅ አስደንጋጭና የሚያስቆጣ ድርጊት ነው። ለምን? ምክንያቱም ኦሪት “በእንጨት ላይ የተሰቀለ የተረገመ” ስለሚል ( ዘዳግም 21፡23)። በአይሁድ አስተሳሰብ ይህ ኢየሱስ፤ «ለይስሙላ ክርስቶስ የተባለ» መሆኑን ማረጋገጫው በመስቀል ላይ መሞቱ ነው። ይህ የእስራኤል መሲህ አለመሆኑን ያረጋግጣል። በእንጨት ላይ የተሰቀለ ወንጀለኛ እና እርጉም ነውና። ሆኖም ግን «ክርስቲያኑን ጳውሎስ» «ከፈሪሳዊው ጳውሎስ» የለየው ይኸው በተሰቀለው ክርስቶስ ማመኑ ነበር። ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀና ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ሲገሰግስ የነበረው ጳውሎስ (ገላ 1:14)፤ ይህ የከበረው ኃያሉ ጌታ በደማስቆ መንገድ ላይ እስኪያገኘው ጊዜ ድረስ፤ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስም ሆነ ስለ ክርስቲያን ሊያስብ የሚችለው ነገር “ክርስቶስ ርጉም እንደሆነ እንዲሁም ክርስቲያኖች በእርሱ በማመናቸው እርጉማን” መሆናቸውን ነው። ይህ እምነቱ ነፍስ እስከ ማስገደል ድረስ እንዲቀና እንዳደረገው መገመት አያዳግትም። ከደማስቆ መንገድ ባሻገር የምናየው ክርስቲያኑ-ጳውሎስ ግን የወንጌሉ እውነት የበራለትን ሰው ነው! “ለካ የተረገመው” አለ ጳውሎስ “ስለ እኔ፤ በእኔም ምትክ ነበር!” ጳውሎስ በራሱ ቃል እንዲህ ይላል፦

“በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና *ክርስቶስ ስለ እኛ* እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን…”(ገላ 3:13)

ወይም ክርስቶስ ወንጀለኛ ሆኖ የተገደለ ሳይሆን በፈቃዱ ራሱን ለጳውሎስ በነፍስ-ወከፍ እንደሰጠው ሲናገር

“..በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ“ ብሏል ( ገላ. 2 :20 )።

ወይም በጴጥሮስ አነጋገር

“….ለኃጢያት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢያታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ “ ( 1 ጴጥ. 2:24 )።

ስለዚህ ወንጌል የሃጥያት ርግማናችንን የተሸከመውን የናዝሬቱ ኢየሱስን ጌታና ክርስቶስ አድርጎ ይሰብክልናል። እግዚአብሔር ያሰበልን ሙላት ሁሉ በዚህ የሚቃረን በሚመስል እውነታ ውስጥ ተካቷል።

“….ፍፁም የሆነውን የመረዳት ብልጥግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ እተጋለሁ ፤ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በእርሱ ዘንድ ነውና። 4 ማንም ንግግር በማሳመር እንዳያታልላችሁ ይህን እነግራችኋለሁ ( ቆላ. 2 ፡2-4)።”

ለዚህ ነው የጳውሎስ መልዕክት የተሰቀለውን ንጉሥ ማዕከል ያደረገው። “እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደተቀበላችሁት እንዲሁ በእርሱ ኑሩ ፤7በእርሱ ተተክላችሁና ታንፃችሁ፣ እንደተማራችሁት በእምነት ፀንታችሁ ፤ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ” (ቆላ. 2:6-7)።

ለእኛም ሕይወታችን በሞት ውስጥ፤ ክብራችን በመከራ፤ ድላችን ለሌሎች ሕወይታችንን በመስጠት ውስጥ ነው። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ እስከመስቀል ሞት ድረስ ከታዘዘ እኛም የለምንም ወገንተኛነትና ራስ ወዳድነት እንድንኖር እንጋበዛለን (ፊል 2:1-11)።

የሐዋርያው ወንጌል (የሚሰብከው መልዕክት) ውርደትና ክብርን፣ መስቀልንና ዙፋንን፤ ጥበብንና በሰው ዓይን ሞኝነትን በአንድ ላይ የምይጣጣሙና የሚቃረኑ የሚመስሉ ሃሳቦችን ያዋሃደ ነው።

“ጠቢብ የት አለ ? ሊቅስ የት አለ ? የዘመኑስ ፈላስፋ የት አለ ? እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ ሞኝ አላደረገምን ? ከእግዚአብሔር ብጥበብ የተነሳ ዓለም በገዛ ጥበብዋ እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ ተሳናት ፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአል። መቸም አይሁድ ታምራዊ ምልክትን ይፈልጋሉ ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ ፤ እኛ ግን የተሰቀለው ክርስቶስን እንሰብካለን ፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል ፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው። እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን ፣ አይሁድም ሆኑ ግሪኮች ፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይል ፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። ምክንያቱም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል ፣ ከሰውም ብርታት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል ( 1 ቆሮ. 1 : 20-25)። “

ጸሎት

ይህንን መልክት ስዘጋ ሁለት ልመና አለኝ። በመጀመሪያ በክርስቶስ በማመን በመስቀል ላይ ልተገለጠው የእግዚአብሔር ፍቅር ምላሽ ያልሰጣችሁ፤ የሓጥያት እዳችሁ በክርስቶስ እንዲሰረይ፤ ይህም ከእግዚአብሔር ቁጣ እንድታመልጡ፤ በክርስቶስ ፍቅር ሕይወታችሁን ለክርስቶስ እንድትሰጡ እጠይቃችኋለሁ፤ ወደ ተሰቀለው ክርስቶስም በመመልከት በንስሃ የሃይጥያትን ይቅርታ እንድትቀበሉ እጸልያለሁ። ክርስቶስን እንድትከትሉ አጠይቃለሁ።

ሁለተኛ ደግሞ ለትውልዳችን ይህ ጥያቄ አለኝ፦

“ቤተ ክርስቲያን ከጤናማ ትምህርት ወደ ክህደት እንድታፈገፍግ ሶስት ትውልድን ይጠይቃል። የመጀመሪያው ትውልድ በታማኝነትና በተጋድሎ ይጠብቀዋል። ሁለተኛው ትውልድ ግን በመጀመሪያው ትውልድ መንፈሳዊ ጎን ላይ ተደግፎ፤ ጤናማውን ትምህርት እያመነ ነገር ግን አጽንዖት አድርጎ አያውጀውም። ይልቁንስ ይህ ሁለተኛ ትውልድ አጽንዖቱና ትኩረቱ የመጀመሪያው ትውልድ “ተሳስቷል” ባሉት በሁለተኛ እና ከዋነኛው ጋር ሲወዳደር «ትርፍ በሚባል» ነገሮች ላይ ይሆናል። ይህ ሆኖ እያለ፤ ሶስተኛ ትውልድ ይነሳል። ይህ ሦስተኛ ትውልድ የመጀመሪያ ትውልድ በተጋድሎ የያዘውን አያምንም፡፤ ምክኒያቱም ሁለተኘው ትውልድ ግርዶሽ ሆኖበት አላስተላለፈለትም። ስለዚህ የሦስተኛው ትውልድ ዋና ትኩረት ሁለተኛው ትውልድ «አጽንዖት» ባደረገበት ነገር ላይ ይሆንና፤ ያ የመጀምሪያው ትውልድ አስተምሮት ያለፈውን ጤናማውን እውነት ግን ይክዳል…” (በ2010 ላይ በD. A. Carson በተሰጠ መርሃ ግብር ከተሳተፍሁት የተወሰደ)

አሁን በሦስተኛው ትውልድ ላይ እንዳለን ምንም ጥያቄ የለውም። ለዚህ ቀውስ ተጠያቂ ማነው? እንደ ካርሰን አነጋገር ሁለተኛው ትውልድ ነው። ትኩረቱ ያነጣጠረው በዋናው ነገር ላይ ስላልሆነ ነው። ሁለተኛ ትውልድ ይድናል። ምክኒያቱም ከጅምሩ ዋነናውን አምኗል። አጽኖት አላደረገም አንጂ። ነገር ግን ለሦስተኛው ትውልድ ሞትን አገልግሎ አልፏል። ለዚህ ነው ብዙዎቻችን ከእንቅልፍ የመንቃት ያሕል “እንዴት እዚህ ደረስን?” ብለን እየጠየቅን ያለነው። በዚህ በጌታ ስቅለት ቀን፤ ወደ ዋነኛውና ወደ መካከለኛው ይህንን ትውልዳችንን ለመመለስ ውሳኔ እንዲሰጠን ለትውልዳችን ጸሎቴ ነው።

2 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published.