Blog,  ማቴዎስ ወንጌል,  የአዲስ ኪዳን ነገረ-መለኮት

ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ

❝የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ❞ (ማቴ. 7:15–20)

❝Προσέχετε ἀπὸ τῶν ψευδοπροφητῶν, οἵτινες ἔρχονται πρὸς ὑμᾶς ἐν ἐνδύμασιν προβάτων, ἔσωθεν δέ εἰσιν λύκοι ἅρπαγες. ἀπὸ τῶν καρπῶν αὐτῶν ἐπιγνώσεσθε αὐτούς.❞

የምንባቡ መዋቅራዊ ዓውድ (Structural Context of the Passage)

የማቴዎስ ወንጌል “በትረካ-ንግግር” የተዋቀረ መጽሐፍ ነው።[1] ለምሳሌ ያህል፦

  • (ትርካ) – ከማቴ. 1 – 4: የክርስቶስ ትውልድ፤ ልደትና አገልግሎት
  • (ንግግር) – ከማቴ. 5 – 7: የክርስቶስ ቃሎች/የተራራው ስብከት
  • (ትረካ) – ማቴ. 8 – 9: የክርስቶስ ሥራዎች/የፈውስ አገልግሎት
  • (ንግግር) – ማቴ. 10:1 – 11:1: የደ/መዛ. ተልዕኮ (ወዘተ..)

በመጽሐፉ ውስጥ አምስት ንግግሮች አሉ። አምስቱም ወደ “ትርካ” ከመመለሳቸው በፊት “ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ…” የሚል ሐረግ እና የማስጠንቀቂያ ቃል ይታከልባቸው። ስለዚህ ምንባባችን የሚገኘው በክርቶስ “በመጀምሪያው ንግግር/First Discourse Unit”፤ ይኸውም “የተራራው ስብከት (ማቴ. 5 – 7)” ተብሎ በሚጠራው ክፍል ውስጥ ነው።[2] የተራራው ስብከት ያተኮረው በብጹዓን ላይ ሲሆን፤ እነዚህ ብጹዓን ደግሞ መለዮአቸው ከጻፎችና ከፈሪሳውያን “የሚልቅ-ጽድቅ” ስላላቸው ነው። የተራራውም ስብከት ማዕከላዊ መልክት “የሚልቀው-ጽድቅ” ምን እንደሚመስል ለማተት (5:21-5:48) እና ደ/መዛሙርት ይህንን ጽድቅ ጽድቃቸው ያደርጉ ዘንድ ለሚያስጠንቀቅ ነው (7:13-27)።

የተራራው ስብከት አወቃቀር (5:3-7:27)

በአጠቃላይ፤ የስብከቱ ይዘት በማቴ. 5:3 ላይ ይጀምርና በማቴ. 7:27 ላይ ያበቃል። ሆኖም ግን ማቴ. 4:23-5:2 እና 7:28-8:1 ያሉት የስብከቱ ክፈፎች ናቸው፡ መንደርደሪያ እና መቋጪያ። መንደርደሪያውም መቋጫውም አንድ ዓይነት የሐሳብ ቅኝት አሏቸው። ሁለቱም ክፍሎች ስለ ኢየሱስ፦

➳ (1) ብዙ ሕዝብ እንደተከተለው፤

➳ (2) ወደ ተራራ

➳ (3) እንደወጣ/እንደወረደ፤

➳ (4) ስለ ትምህርቱ (4:23-5:2) ይናገራሉ።

ምንም እንኳ የማቴ. 4:23 – 5:2 እና 7:28 – 8:1 ዓላማ ሰባኪውና ተሰባኪው ማን እንደሆነ ለመጦቆም እንደዚሁም ከስብከቱ በኋላ የሕዝቡ ምላሽ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ቢሆንም፤ ከዚያ ያለፈ ትልቅ ግልጋሎት ግን አላቸው። ወንጌላዊው ማቴዎስ በ5:1-2 ላይ ስለ ኢየሱስ “ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ (ἀνέβη εἰς τὸ ὄρος)” ብሎ ሲጽፍ በማያወላውል መልኩ ዘጸ. 19:3ን ሊያስታውሰን ብሎ ነው (በተለይ ከሰብዓ-ሊቃናት ትርጉም)። በዚያ ሥፍራ ላይ “ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ [ተራራ] ወጣ/ Μωσῆς ἀνέβη εἰς τὸ ὄρος” የሚል እናነባለን። ይህንን ሲል ማቴዎስ የኢየሱስን ስብከት/አገልግሎት ከሙሴ ጋር እንድናመሳስል እየጋበዘን መሆኑን ማስተዋል አለብን። ሙሴ ወደ ተራራው እንደወጣ፤ ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣ።

እንዲያ ከሆነ፤ እነዚህ ሦስቱ ምዕራፎች የሚያትቱት ከዳዊት የሚልቀው ንጉሥ እና ከሙሴ የሚልቀው ታላቁ ነቢይ ኢየሱስ (ዘዳ. 18:15,18) ለደ/መዛሙርቱ ስለ ሰጠው ደንብ ነው (but not a new law)። ሙሴ ሲወለድ ህጻናት እንዳለቁ ኢየሱስም ሲወለድ እንዲሁ (ማቴ. 2:20)፤ በሙሴ አማካኝነት ጸዓት ለእ/ር ሕዝብ እንደሆነ ኢየሱስም “ስሙን ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱም ህዝቡን ከሃጥያት ያድናቸዋል” ይላል። በሙሴ መሪነት ህዝቡም በደረቅ ምድር እንደተሻገረ፤ በምድረበዳ ለ40 ዓመታት እንደተፈተኑ፤ ደግሞም በኢያሱ መሪነት ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደገቡ፤ ኢየሱስም እንዲሁ በውሃ በዮርዳኖስ ማዶ ተጠመቀ፤ ከዚያም ወደ ምድረበዳ ተነድቶ ለ40 ቀንና ለሊት ተፈተነ፤ በመስቀል ሞቱም አዲስ-ጸዓት ተካሔደ..ወዘተ..እነዚህ ሁሉ ንፅፅሮች የሚያሳዩን የአዲስ ኪዳን ታላቁ ነቢይ ኢየሱስ መሆኑን ነው! ሙሴ የኪዳኑን ሕግ ተቀብሎ ለእስራኤል ሰጠ። በኢየሱስም አዲስ ኪዳን ተመረቀ። እንደ ሙሴ ኢየሱስም ወደ “ተራራው” ወጣ (ውሱን ምስተአምሩን ልብ ይበሉ) “አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ (5:2)”። ስለዚህ ኢየሱስ ከሙሴ የሚልቅ ነብይ ነው፤ ደግሞም አስተማሪ ነው። ይህ የመጀመሪያው ወንጌል በኢየሱስ አስተማሪነት (በቃሎቹ) ላይ አጽንኦት አድርጓል (8:19; 9:11; 10:24-25; 2:38; 17:24; 19:16; 22:16, 24, 36; 23:8; 26:18)።

ከላይ ያየነው የስብከቱን መንደርደሪያ እና መዝጊያ (5:1-2/7:28-8:1) ሲሆን፤ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ የስብከቱ ይዘት ነው (ማቴ. 5:3 – 7:27)። የተራራውን ስብከት ይዘት በትልቁ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባል፦

➳ (1) የስብከቱ ራስ: ብፁዓንና የቀረበላቸው ጥሪ (5:3–16)
➳ (2) የስብከቱ ሰውነት: የደ/መዛሙርቱ የላቀ-ጽድቅ (5:17–7:12).[3]
➳ (3) የስብከቱ መዝጊያ: ከዘመን-ፍጻሜ ፍርድ ለማስመለጥ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (7:13–27)

የተራራው ስብከት ዋና መልክት (5:17–7:12)

በአጭሩ የክርስቶስ ተከታዮች መታወቂያቸው፤ የጽድቅ-ኑሯቸው ነው፤ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (Mt 5:16)። የተራራው ስብከት የታይታ የሆነ ውጪያዊ ጽድቅን ይኮንናል (ማቴ. 6:1-15)፤ አትኩሮቱ በውስጣዊ ጽድቅ ላይ ነው። የውስጥ ጽድቅ ማለት፤ ከተለወጠ ልብ የመነጨ፤ እያደገና እየሰፋ የሚመጣ፤ ትኩረቱን “የሰማይ አባት እንደሚያይና ዋጋ እንደሚከፍል” የተገነዘበ ነው። “ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም።” ስለዚህ የአማኝ ጽድቅ በአንድ እጅ “ወግ-አጥባቂነት ወይም አትንካ/አትቅመስ አለመሆኑን (Nomisim) በሌላ እጅ ደግሞ በጸጋ-ብቻ እንጂ ሥራ-ምን ፋይዳ አለው ብሎ መረን እንደማይወጣ (Anti-Nomisim) ያስገነዝበናል። የአማኞች ጽድቅ “የላቀ-ጽድቅ” ነው። በመጨረሻ ማጤን ያለብን፤ በተራራው ስብከት ላይ “ጽድቅ” የደቀመዝሙሩ የሕይወት-ፍሬ እንጂ በሐዋርያው ጳውሎስ ነገረ-መለኮታዊ አስተምህሮ ጎልቶ የምናገኘውን “የተቆጠረልን-ጽድቅ/ reckoned or imputed righteousness” አለመሆኑን ደግሞ ከዚያም ጋር አለመጋጨቱን ነው። የማቴዎስ አጠቃቀም ጳውሎስ “የመንፈስ ፍሬ” ብሎ ከሚናገረው ጋር ሥምረት አለው (ለምሳሌ ማቴ. 5:20ን ከኤፌ 5፡5-13 ጋር ያወዳድሩ/ ገላ 5:5)። (ይህን ጹሑፍ አጠር ለማድረግ የጽሑፉን መዋቅር እዚህ ጋር እናበቃለን)።

የምንባቡ ሐቲት (ፍታቴ) – 7:15 – 21
(በዚህ ክፍል የምንመለክተው ማቴ. 7:15 ብቻ ይሆናል)

❝የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ❞

ተጠንቀቁ

በመጀመሪያ ደረጃ ምንባባችን የሚጀምረው “ተጠንቀቁ” በሚል የማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ ነው። ጌታ ምክር-ቢጤ ወይም “ብታደርጉት ትጠቀማላችሁ” የሚል አስተያየት ማከሉ አይደለም። ይህ ማስጠንቀቂያ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። ለምን? ይህንን ከሁለት አንጻር መመልከት ይኖርብናል። አንደኛ፤ ምንባባችን የሚገኘው በማቴ. 7:13-8:1 ባለው ክፍል እንደመሆኑ፤ ይህ ክፍል ደግሞ የተራራው ስብከት ተብለው ለሚታወቁት ሦስት ምዕራፎች (ማቴ. 5 – 7) መደምደሚያና የመልክቱ ማጠቃለያ ስለሆነ ነው። ስለዚህ ማስጠንቀቂያው ከ5:17 ጀምሮ እስከ 7:12 ድረስ ለዘለቀው ደቀ-መዝሙራዊ አስተምህሮ መቋጫ ነው{1}። በተጨማሪ፤ ይህ መዝጊያ ክፍል (7:13-8:1) ሦስት ክሎች አሉት። ሁሉም ተምሳሌታዊ አነጋግሮች ሲሆኑ የተራራውን ስብከት መልዕክት ጠቅለል አድርገው የሚያቀርቡ እና ጥበብ-ነክ ቅርጽ/ይዘት ያላቸው ናቸው፡-

➳ ማቴ. 7:13-14 (ሁለት ዓይነት መንገዶችና ደጆች)፤
➳ ማቴ. 7:15-23 (ሁለት ዓይነት ዛፎችና ፍሬዎች እንዲሁም የሐሰት-ነቢያት የመጨረሻ ዕጣ-ፈንታቸው።
➳ ማቴ. 7:24-27 (ሁለት ዓይነት ሰሚዎችና ቤት-ሠራተኞች)

ስለዚህ ከላይ እንዳየነው “ከሐተኞች ነብያቶች ተጠንቀቁ” የሚለው ትዕዛዝ የሞትና የሕይወት ጉዳይ የሆነበት የመጀምሪያው ነጥብ 7:13-27 ያለው የተራራው ስብከቱ መቋጫ ከመሆኑ የተነሳ ነው። የስብከቱን ሙሉ ክብደት የተሸከሙት እነዚህ መደምደሚያ ክፍሎች በመሆናቸው። ሁለተኛውን ምክኒያት ከቃሉ ስዋስው ማግኘት እንችላለን። የቃሉ ንብረት “ትዕዛዛዊ” ነው/Imperative Mood” ወዮታን ያዘለ ትዕዛዝ ነው። በማቴዎስ ወንጌል ላይ “ተጠንቀቁ/Προσέχετε” ስድስት ጊዜ ተደጋግሟል (6:1፤ 7:15፤ 10:17፤ 16:6፤ 16:11፤16:12) (ምንም እንኳ የ6ኛው ንብረት ትዕዛዛዊ ባይሆንም አውዳዊ አጠቃቀሙ ግን “ተጠንቀቁ” የሚለውን ስሜት ያንጸባርቃል)። ለምሳሌ፤ 6:1 ላይ ከታይታ-ጽድቅ “ተጠበቁ”…”ከ[ክፉ] ሰዎች ተጠበቁ”…”ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠብቁ።” ሁሉም አበክረው የሚናገሩት ማስጠንቀቂያውን አለማድመጥ ከባድ የሆነ መዘዝ እንዳለው ነው። ተጠበቁ የሚለውን ቃል BDAG የተሰኘው የግሪክ-መዝገበ ቃላት ሲተነትነው “በንቅሀት ውስጥ መሆን፤ የጉዳዩን አሳሳቢና አንገብጋቢነት ማየት ፤ ጠንቃቃ ሆኖ መገኘት፣ እንክብካቤን ማሳየት ነው ይለዋል…(to be in a state of alert, be concerned about, care for, take care)።

ከማቴዎስ ውጪ ይህ ቃል በሐዋ. 20፡28 ላይ (ከማቴዎስ ጋር እጅብ በተቀራረበ መልኩ) ተገልጾ እናገኘዋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ የቤተክርስቲያን መሪዎችን አስጠርቶ የመጨረሻ የኑዛዜ ቃሉን ሲሰጣቸው እንዲህ ይላል፤

❝ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ…እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ነጣቂ ተኵላዎች (λύκοι βαρεῖς) መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ” ዐውቃለሁም…❞

ይህ የጳውሎስ ንግግር የኢየሱስን ቃሎች እንዲያሳስቡ ተደርገው የተቀናበሩ ናቸው (Verbal Allusions)። ልክ እንደ ኢየሱስ ጳውሎስም “ለገዛ ራሳችሁ” እና “ለመንጋው ሁሉ ተጠንቀቁ” (προσέχετε ἑαυτοῖς καὶ παντὶ τῷ ποιμνίῳ) ሲል “መጠንቀቅ…መንጋ/በግ (ምዕመናንን የሚወክል ዘይቤያዊ አነጋገር)” እንዲሁም ቀጥሎ “ነጣቂ ተኵላዎች” ብሎ ሲል ጳውሎስ የጌታን ማስጠንቀቂያ እያሰበ መሆኑን ያሳየናል (ምንም እንኳ ማቴዎስ ገና ባለመጻፉ በ7:15 ላይ ላይ የተመሰረተ ነው ባንልም)። ይህም የጌታ ማስጠንቀቂያ (የሐሰተኞች ነቢያት ጉዳይ) ገና ቤተክርስቲያን ከመቆርቆሯ አንገብጋቢ ደረጃ መድረሱን ያመልክተናል። ይህ ማለት ጌታ እስኪመለስ ድረስ፤ ቤተክርስቲያን ባለችበት ቦታ ሁሉ፤ ይህ ጉዳይ የማያባራ ማስጠንቀቂያ ነው። ቤተ-ከርስቲያን አርፋ አታውቅም፤ ማረፍም የለባትም።

በተጨማሪም፤ በጥንታዌቷ ቤተክርስቲያን በሥራ ላይ ይውል የነበረ “አስተምህሮ/ዲዳኼ” የተሰኘው መጽሐፍ ላይ፤ ማቴዎስን በቀጥታ እየጠቀሰ እንዲህ ብሎ ያስጠነቅቃል፦

❝not everyone who speaks in the spirit is a prophet, but only if he exhibits the Lord’s ways. By his conduct, therefore, will the false prophet and the prophet be recognized….If the one who comes is merely passing through, assist him as much as you can. But he must not stay with you for more than two or, if necessary, three days…But if he is not a craftsman, decide according to your own judgment how he shall live among you as a Christian, yet without being idle. But if he does not wish to cooperate in this way, then he is trading on Christ. Beware of such people.❞[4]

ከላይ የጳውሎስን ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ከቤተክርስቲያን ታሪክ ወስደን “የጌታ ተጠንቀቁ ጥሪ በመጀመሪያቱ ቤተክርስቲያን ላይ ይስተጋባ እንደነበር አይተናል። የጌታ ጥሪ ግልጽ ነው። በሐሰት ነብያት ጉዳይ አማኞች (በተለይ መሪዎች) ለአፍታ መተኛት አይችሉም። ብልሃታቸውንና መልካቸውን ቢለዋውጡም፤ እንደ ጉበኛ አይኖቻቸው ነቅተው ሊጠብቁ ይገባል። መቼም ቢሆን። ኢየሱስ እስኪመጣ።

ሐሰተኞች

ሁለተኛ፤ ማስጠንቀቂያው ያነጣጠረው፤ “በሐሰተኞች ነቢያት” ላይ ነው። አማርኛው ትርጉም ላይ “ሐሰተኞች” የሚለው ቃል ለአንዳንዶቻችን ምን አልባት “ድርጊት ገላጭ” ሊመስለን ይችል ይሆናል። ይህም እነዚህን ሰዎች “ሐሰተኞች” ያስባላቸው “ሐሰተኛ ትንቢት” መናገራቸው ነው የሚል ይመስል። ነገር ግን ቃሉ ድርብ-ቃል ነው “ሐሰተኞችነብያት/ψευδοπροφητῶν።” ምናልባት “የሐሰት-ነብያት” ወይም “የውሸት-ነብያት” ብንል ሐሳቡ ፍንትው የሚል ይመስለኛል። “ኛ” የሚለው ተቀጽላ ድርጊትንም ስለሚገልጽ፦ ለምሳሌ አንድ ሰው “የውሸት-መኪና” ቢል፤ መልክቱ ግልጽ የሚሆን ይመስለኛል (‘ኛ’የሚለው ወጥቶ ማለቴ ነው)። ይህ ማለት፤ ገና ከጥንሥሡ ወይም ከነአካቴው “ይህ እቃ” መኪና እንዳልነበር ይነግረናል። ስለዚህ “ሐሰተኞች ነብያት” አስመሳይ-ነብያት እንጂ፤ ነብያት ሆነው ሐሰት ነገር የተናገሩ አይደሉም። ነብያት ሆነውም አያቁም። ይህ ወደ ሚቀጥለው ሐሳብ ያመራናል።

ሐሰተኞች ነቢያት

ሦስተኛ፤ እነዚህን ሰዎች ጌታ በሁለት መልክ (አረፍተ-ነገሮች) ይገልጣቸዋል። ምንም እንኳ ከአማርኛው የቋንቋ ሥርዓት የተነሳ እነዚህ ሁለቱ አረፍተ-ነገሮች “ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ” ከሚለው ዓረፍተ-ነገር ቀደም ብለው ቢመጡም፤ በዋናው ቋንቋ ላይ ግን እንደሚከተለው ቀርቧል፦

—> ጠንቀቁ

   —>ከሐሰተኞች ነቢያት (7:15 ሀ)

  • —>(7:15 ለ) የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ
  • —>(7:15 ሐ) በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ

ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።

ከላይ “15ለ” እና “15ሐ” ብለን የሰየምናቸው አረፍተ-ነገሮች፤ የሐሰት-ነቢያት “ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጡናል። ጌታ በሁለት መልክ ይገልጻቸዋል፡- «በውጪ ምን እንደሚመስሉ እና በውስጥ ማን እንደሆኑ»። በውጪ አንድ፤ በውስጥ ግን ሌላ ማንነት አላቸው። ማቴዎስ ሲጽፍ “በውሥጣቸው/ἔσωθεν” የሚለውን ቃል ወደ ፊት ያስቀደመው «ደመቅና ሠመር» አድርጎ ለመናገር ነው። የእነዚህ ሰዎች ትልቁ ችግር “በውስጣቸው” ያለው ነገር ነው። ይህ “የውስጥ-ውጪ” ጉዳይ በነገረ-ማቴዎስ ውስጥ (Matthean Theology) ያደገ ቁልፍ ሐሳብ ነው። ይህ ሐሳብ ከምንባባችን ጋር እንዴት እንደተያያዘ በሚቀጥለው ክፍል እናያለን። ለምሳሌ “ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ…” ሲል የፈሪሳውያን ጽድቅ ከውስጥ-ወደ ውጪ የወጣ ሳይሆን፤ ውጪያዊ ብቻ በመሆኑ ነው (“በውስጣቸው ግን ቅሚያና ስስት ሞልቶባቸዋል”/ የተለሠነ መቃብር ናቸውና (ማቴ 23ን ይመልከቱ)። እንዲሁም ማቴ. 5:48 ላይ የሰማይ አባታችሁ ሙሉ (ፍጹም) እንደሆነ እናንተም ሙሉ (ፍጹም) ሁኑ (be telios as your heavenly Father is telios)። ይህ የፍጹምነት ጉዳይ ሐጥያት-አልባነትን አያመለክትም (sinless perfection)። ፍጹምነት ማለት ‘ያልተገመሠ’፤ ‘ያልተከፋፈለ’ የሚለውን ሀሳብ ያንጸባርቃል።ለምሳሌ ያህል በም 19:21 ላይ “ኢየሱስም፣ “ፍጹም (telios) ለመሆን ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ…ተከተለኝ!” ጎልማሳው ውስጡን ያጣበበ የብልጽግና ሐሳብ ስለነበር ጥሪውን መቀበል አልቻለም። ይህ ሰው “ፍጹም” አይደለም። በእብራይስጡም “ታሚም” የሚለው የዚህ ቃል አቻ ነው። እነ አብርሃም እና እነ ዳዊት “ታሚም” ነበሩ «ልባቸው ፍጹም ነበር»። ስለዚህ የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች በውስጥም፤ በውጪም አንድ አይነቶች ናቸው። አምልኮታቸውና የልባቸው መሰጠት “ነጠላ’ ሰዎች ናቸው። መንትያ የላቸውም። ሙሉ ናቸው። ውጪያዊ አይደሉም። ሐሰተኛ ነብያት ግን “ውስጣቸው” እና “ውጪያቸው” አይመሳሰልም። ይህ መጀመሪያ ራሳችንን እንድንጠይቅ ካላደረገን የማቴዎስ መልክት አልገባንም ባይ ነኝ። እኔ ነኝ? በፍጹም ልቤ ለአምላኬ ተሰጥቼአለሁ? በርግጥ?

[7፡15ለ] የሐሰት-ነቢያት “ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

የመጀመሪያው ዘይቤያዊ አነጋገር፤ “የበግ ለምድ ለብሰው” የሚለው፤ የሚያሳየን የሐሰት-ነቢያት በውጪ በሚገልጹት ማንነታቸው ከበግ እንደማይለዩ ነው። በርግጥ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ሐሰተኛ ነቢይ/ አስተማሪ/ወንድም የሚለዩት በሚያምኑት (በሚያሳዩት) ነገር ሳይሆን በሚክዱት (በማያሳዩት) ነገር ነው። “ኢየሱስ በሥጋ እንደመጣ የሚክዱ” (1ዮሐ 4፡1-3) ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ እኮ ያምናሉ። በተለይ ብዙዎች በጎችን ቅንነታቸውን በመጠቀም የሚያታልሉበት መሳሪያቸው ይህ ነው። መምሰላቸው። እንዲያውም ጠበቃ እንቁምላቸው ያስብላሉ። ስለሚመስሉ። በማቴዎስ ላይ “በግ” የሚለው ዘይቤ የክርስቶስን ደ/መዛሙርት ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል (Matt 10:16; 26:31)። ስለዚህ ከክርስቶስ እውነተኛ “በጎች” ጋር ቀልቀል ያሉ በመሆናቸው፤ በዓይን ለመለየት አዳጋቾች ናቸው።

በውስጣቸው “ነጣቂ”

ሁለተኛ እነዚህ ሰዎች በውስጣቸው “ነጣቂ” ናቸው። ነፍሰ-ገዳዮች ናቸው። ጌታ ሲገልጻቸው “ነጣቂዎች ተኩላዎች/ λύκοι ἅρπαγες” ይላቸዋል። ይህን ቃል BDAG “’በቃኝ የማያውቅ አዳኝ አውሬ’ ወይም ‘አረመኔ፣ ተናካሽ (ravenous or rapacious)” በማለት ይገልጸዋል። ነጣቂ የሚለው ቃል በዘፍ. 49:27 ላይ ለቢኒያም ነገድ ውሏል “ብንያም ነጣቂ ተኵላ ነው፤ የበዘበዘውን በጥዋት ይበላል፥ የማረከውንም በማታ ይካፈላል።” በቅዱሳት መጻህፍት ላይ የቢንያም ሰዎች አንዳንዴ የቀስት ሰዎች አንዳንዴም ደግሞ ጨካኞች/አረመኔዎች እንደሆኑ እናያለን። በመሳ. 20:21-25 ላይ ለምሳሌ ያህል በአንድ ቀን 18,000 የገዛ የእሥራኤል ወገኖቻቸው ገድለው ሲያበቁ በሚቀጥለው ቀን ደሞ በተጨማሪ 22,000 ጨመረው ገደሉ (በጥቅሉ 40 ሺህ ሕዝብ)። የመሳፍንት ጸሐፊ ሲናገር “የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፥ አለቀሱም። በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ።”

ስለዚህ እነዚህን ሰዎች “ነጣቂ ብሎ” ጌታ ሲሰይማቸው ሐሰተኞች ነብያት ርህራሄ የማያውቁና በእጃቸው የወደቀውን የማያስተርፉ መሆናቸውን ማመልከቱ ነው። ምንም አይነት እግዚአብሔራዊ ምህረት አይታይባቸውም። በተቃራኒው ግን የክርስቶስ ደ/መዛ. “የሚምሩ ብጹዓን” ናቸው (ማቴ 5:8)። ሲጸልዩም “የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” ይላሉ (ማቴ 6፡12)። ምን ያህል ይቅር እንደተባሉ ስለሚያውቁ “ሰባ ጊዜ ሰባት” በቀን ይቅር ይላሉ (ማቴ. 18:22)። የጌታም ጥሪ ግን “ከመስዋዕት ይልቅ ምህረትን እወዳለሁ (ኸሰድ)” (ማቴ. 12፡7) ነበር። የሐሰት-ነብያት ግን “ነጣቂ ተኩላዎች” ናቸው። ለማንም አይራሩም። ምህረትን አያውቋትም።

በተጨማሪም ከነብያት መጻህፍት ብጨምር በሕዝቄል 22:27 ላይ በዘመኑ የነበሩትን የእስራኤልን “አለቆች”፤ “ካህናት”፤ “ነብያት” እና “ሕዝብ” ነብዩ ሲከስ እንዲህ ብሎ ይገልጻቸዋል፤

“በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው። እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል።”

በሕዝቄል 22 ላይ ሰው ሁሉ በያህዌህ ፊት በተጠያቂነት ተይዟል። ሁላችንንም ይመለከታል። መቼም “ሐሰተኛ” የሚባለውን ቃል ስንሰማ ራሳችንን ከዚያ ጎራ አውጥተን በሰዎች ላይ ጣት መጠቆም ምቹ ነው። ሆኖም ግን ሁላችንም ራሳችንን ካልመረመርን በሐሰተኞች ነብያት ስህተት ልንወድቅ እንችላለን። ይህ ማስጠንቂያ እኔን አይመለከተኝም ማለት የሚችል አማኝ የለም። ጌታ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው እኮ ለሐሰተኞች ነብያት ሳይሆን «ደ/መዝሙሩ ነኝ» ለሚል መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ኢየሱስ የሐሰት-ነብያትን “ነጣቂ” ብሎ ሲሰይም ሥራቸውን በሕዝቄል ዘመን “ደም አፍሳሽ፤ ነፍስ አጥፊ ነጣቂ ተኩላዎች” ከነበሩት የእሥሪኤል አለቆች ጋር ማመሳሰሉ ነው ብንል አልተሳሳትንም (at the very least it is a legitimate verbal allusion)። የሐሰት-ነብያት አይነተኛ መሣሪያቸው ከገዛ ልባቸው የወለዱትን ቃል “ቃል-አለኝ-ከእ/ር” ማለታቸው ነው። ስለዚህ ከሕግ፤ ከታሪክና ከነብያት መጻሕፍት “ነጣቂ የሚለው ቃል እንዴት ሙያ ላይ እንደዋለ አይተናል።

ግን የትኛው ተግዳሮታቸው ነው ነጣቂ ያደረጋቸው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ቀደም ብሎ የመጣውን ጹሑፋዊ ውቅርና ዓውድ መመልከት ይኖርብናል። ምንባባችን የሚገኘው “በሁለት ዓይነት መንገዶችና ደጆች (7፡13-14)” እና “በስምህ አጋንንት አውጥተናል” (7:22-23) በሚሉት መካከል ነው። ይህም የሚያሳየን እነዚህ ሰዎችን “ወደ ጥፋት ወደ ሚወስደው ሰፊ ደጅ” እና “ትልቅ መንገድ” ቀያሾች መሆናቸው ነው። ይህ ነው የሐሰት-ነብያት ጉዳይ የሕይወት ጉዳይ የሆነበት ምክኒያት። በሌላ አባባል፤ ወደ ሕይወት ወደ ሚወስደው ጠባቡ ደጅና ቀጭኑ መንገድ ለመድረስ ጆሮቻችንን እና ሕይወታችንን ከሐሰት-ነብያት መጠበቅ አለብን። ወደ ጥፋት መንገድ የሚወስዱን “በውሃ ውስጥ ስትቀቀል እንደማታውቀው እንቁራሪት” ቀስበቀስ እያታለሉን ነው። በዘመናችን ሰዎች የሚሰጡት ማመካኛ፤ እነዚህ ሰዎች እኮ “መልካምም ነገር እኮ አሏቸው! ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸው…እናስተካክላቸው” በማለት የሐሰት-ነብያትን ጉዳይ የትምህርት ጽንፈተኛነት ወይም ከመፈሳዊ ብስለት እጥረት አንጻር እንደ መጣ ማሰብ ነው። መቼም ይህ የተለመደ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን ጌታ አስተካኳቸው አላለንም። ድሮውንም በመንገዱ ላይ አልቆሙም። በግ መስለዋል እንጂ ከጥንሥሡ በጎች አልነበሩም። በጎች ለመሆን ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ በተማሪነት መንፈስ እና በተለውጠ ልብ የቀረቡ ዕለት፤ የዛን ጊዜ የንስሃ ፍሬ፤ የማስተካከሉ ተግዳሮት ይጀምራል። ያ እስካልሆነ ድረስ ጌታ “ተጠንቀቁ” ይለናል። ጥንቃቄውም በመጀመሪያ ደረጃ ከራሳችን ይጀምራል። ልባችንን በመመርመር። የገዛ ራሳችንን። ከዚያም ዙሪያችንን። ስለዚህ ሐሰተኛ ነብያት ርህራሄ የሌላቸው፤ ለመንጋው የማይራሩ፤ በየዋህነት የቀርቡዋቸውን (የበግ ለምድ በመልበሳቸው) በጎች የሚነጥቁ ተኩላዎች ናቸው። ተጠንቀቁ!

ሦስተኛ፤ ምንም እንኳ “የበግ ለምድ” የለበሱ ቢሆኑም ጌታ ግን “መፈተኛ” ሰጥቶናል። ከላይ 7:15ለ እና 17ሐ፤ የሐሰት-ነብያት ምን እይነት ሰዎች እንደሆኑ እንደገለጹልን፤ ቁ16 ደግሞ እንዴት እንደምንለያቸው ይነግረናል። አሁን ደግሞ ቁ.16ን ጠጋ ብለን እንመልከት።

(የመጨረሻው ክፍል 2 ይቀጥላል)

[1] Narrative-Discourse units. For more see: Dale Allison; B. W. Bacon

[2]As far as record goes, it was Augustine who first coined the expression “Sermon on the Mount” for the discourse material that we find in chapters 5 through 7

[3]ይህ ክፍል ሲጀምር (በ5:17) እና ሲጨርስም (በ7:12) “ሕግን እና ነብያት” በሚል ሐረግ ተከፍቶ ይዘጋል። ሐረግን በመድገም ሀሳብን ጀምሮ መዝጋት (Inclusio) የጥንት ጸሃፊዎች ይጠቀሙበት የነበረ ስነ-ጹሑፋዊ ዘዴ ነበር።

[4]Michael William Holmes, The Apostolic Fathers: Greek Texts and English Translations, Updated ed. (Grand Rapids, MI: Baker Books, 1999), 265–267

Leave a Reply

Your email address will not be published.