Blog,  ትምህርተ አስተርእዮ,  ትምህርተ ድነት

አስተርዕዮተ-እግዚአብሔር እና ነገረ-ድነት

(ከማኅደር፡ አስቀድሞ በጥቅምት 2014 ተጻፈ)

የዘላለም ሕይወት እግዚአብሔርን ማወቅ ነው

_የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ሐሳብ፡-
መዳን እግዚአብሔርን ማወቅ ነው፤ ይህም በወንጌል አማካኝነት የተሰጠን ጥሪ ነው።

_የዚህ ጽሑፍ ምጋቤያዊ ምልከታ፦
ድነት ሁሉን የሚዳሥ ሰፊ ፕሮጀችት ነው። ስለዚህ መዳን ሁለንተናችንን ይመለከታል። ለመዳን የሚያስችል እምነት አንድ፤ ለጉዳዮቻችንና ለሕይወታችን ደግሞ ሌላ ዓይነት እምነት የሚባል ነገር አይደለም። ለመዳን በክርስቶስ እንዳመንን፤ በዚያው እምነት በሕይወት እንኖራለን። ስለ እምነት እንደዚህ አይነቱ አመለካከት፤ አማክሎተ-ክርስቶስን ከአይናችን ዘወር ያደርጋል። በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት የሁለንተናችን ማዕከል ነው፤ ከዚህ አናድግም፤ አንሻሻልም፤ ሥር እየሰደድን እናድጋለን እንጂ። ስለዚህ የእምነት ዓይነት የለም።እምነት 7 ደረጃዎች የሉትም! እምነት ክርስቶስን ማዕከል እንዳደረገ ውሎ፤ አድሮ ይሰነብታል፤ እስከ ሽበት! አንድ እምነት! ለዚያ ነው “ከእምነት ወደ እምነት” የተባልነው፤ አንዳንዶች እንዳሉት “ከአንድ ዓይነት እምነት ወደ ሌላ አይነት እምነት” ጳውሎስ አልወጣውም። ጳውሎስ ያለው በወንጌል የተገለጠው እና ያዳነን የእግዚአብሔር ጽድቅ “ጅምሩም እምነት፤ ፍጻሜውም እምነት” ማለቱ እንጂ። ያ በመጀመሪያ ያዳነን በክርስቶስ ላይ የነበረን እምነት፤ ዛሬም በሕይወት የሚያኖረን፤ በጉዳዮቻችንን ላይ እ/ርን ፡በክርስቶስ” የምንታመንበትም ጭምር ነው። ስለዚህ ድነት ሁሉን ይዳሣል ካልን፤ የእለት ኑሯችንም ላይ ድነታችን እየሰራ ነው ማለት ነው።


[su_quote]እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። ከአንተ ለተቀበላቸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና (ዮሐንስ 17:2-3)[/su_quote]

ጠቢብ የሆነው አንዱ እግዚአብሔር፤ በመለኮታዊ ኪነ-ጥበቡ መዳናችን በክበበ ሥላሴ፤ በአካላት ምክር፤ ከዘመን ዘመናት በፊት ሲቀምም፤ “ነገረ-ድነት” እና “ነገር-አስተርዕዮ” የማይለያዩ አንድ እውነታዎች አድርጓቸዋል። ይህ የታላቁ መሐንዲስ ንድፍ፤ የድነታችን መሥራችና ሐዋሪያ ዕቅድ ነው። በአጭሩ፤ የሰው ልጆች “መዳን” እና “እግዚአብሔርን ማወቅ” አይለያዩም። የዳኑት እነርሱ እግዚአብሔርን የቀመሱት ናቸው። መዳን እግዚአብሔርን ማወቅ ነው!

የብሉይ ኪዳን ራዕየ-መለኮትና የሁለቱ አካላት ተልዕኮ በአዲስ ኪዳን
እዚህ ጋር ስለ ትምህርተ-ድነት ነካ አድርገን ልናልፍ የሚገባን መሠረታዊ ነገር ቢኖር፤ ወልድ ወደ ምድር የመጣው ለሌላ አላማ ሳይሆን ሰዎችን ለመቤዠት ነበር (ገላ 4:4)። ሆኖም ግን በዚያው አንድ የቤዝዎት ተልዕኮ ውስጥ፤ ስሉስ የሆነው እግዚአብሔር ራሱንም የሚገልጥበት መንገድ ነው። ይህም የወልድ ተልዕኮ የሥሉሱ አምላክ አስተርዕዮ ነው። በክርስቶስ የዳኑ ሁሉ ገና ከጥንሥሡ፤ ገና የወንጌልን መሠረታዊ እውነት በቃላት ማስቀመጥ ከመማራቸው እና መንፈሳዊ ሆሄያትን መቁጠር ከመልመዳቸው በፊት፤ ጥልቅ የሆነ “ዕውቀተ-እግዚአብሔርን” በሕይወታቸው ተለማምደዋል። ምንም እንኳ ገና አሁን ቃላትን አሰካክተውና አደረጃጅተው ለመናገር መማር ቢጠበቅባቸውም፤ ግን የጀመሩት እግዚአብሔርን በማወቅ ነው (እዚህ ጋር ግን ማብቃት ትልቅ አደጋ እንዳለው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊያት ደጋግመው ነግረውናል “እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ” ቆላ. 1፡10)። ስሉሱን አምላክ ቀምሰውታል። የአብን አባትነት በወልድ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተለማምደውታል። ለምን? ምክኒያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ መዳን እግዚአብሔርን ማወቅ ስለሆነ ነው። በዋነኛነት መዳን “የሆነ ነገር” ማግኘት (ሠላምና ደስታ) አሊያም “የሆነ ሥፍራ” መሔድ (መንግስተ ሰማይ) አይደለም። በፍጹም። በመጀመሪያ ደረጃ መዳን እግዚአብሔር ማወቅ ነው። እግዚአብሔርን ያወቁት እነርሱ ሠላምና ደስታ አላቸው። እነርሱ እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላቸው፤ እምባና እሮሮ ወደ ሌለበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይገባሉ።

እግዚአብሔር ሲያድነን በብዙ መንገድ ሊያድነን ይችል ነበር፤ ሁሉን ቻይ ስለሆነ። ሰዎችን የፈጠረበት ምክኒያት ግን ስለነበረው፤ ሊያድነን የወደደው በአንድ በተወሰነ ዓይነት መንገድ ነው። ይህ መንገድ “ወንጌል” ነው። በወንጌል እርስ-በርሳቸው የሚዋደዱና እርስ በርሳቸው የሚኗኗሩ አካላቶች የቀመሩት የመዳን መንገድ ነው። ቃል ከምጡቅ መጋረጃው ብቅ ብሎ ሥጋ በመሆን፤ ከአባቱ ጋር ያለውን ሰማያዊና ምጡቅ ግንኙነቱን “ሰው ሆኖ” ተረከልን። አለም ሳይፈጠር ከአባቱ ጋር ፍቅርን ይለዋወጥ የነበረው ያው አንዱ “አካል ወልድ”፤ ፍጹም ሰው ሆነ። ስለዚህ ሰው እንደመሆኑ በሰው ቃልና በሰው ዘዬ ከአባቱ ጋር ሲገናኝ አየን ይለናል ዮሀንስ በመልእክቱ። ይህ መለኮት በሰውነት ተገልጦ ለሰው ልጆች ክብሩን መግለጥ በዘመን ይጀምር እንጂ በዘመን አያበቃም። አምነን ወደ ክርስቶስ ስንጨመር እርሱ ስለመዳናቸን የሆነልንን ነገር ሁሉ፤ (እግዚአብሔር እንዲያው የሰጠንን) መለማመድ ጀመርን። ክርስቶስ “አማክሎት” ሆነልን ማለት ነው። በክርስቶስ ውስጥ ከወልድ ጋር የሚገናኙት መለኮታዊ አካላት ጋር እኛም መገናኘትና ማንነታቸው መቅመስ ጀመርን፡

❝የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከእርሱም ጋር እንኖራለን። የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።❞ (ዮሐንስ 14:21, 23)

ልክ እነዲሁ በነገረ-ጳውሎስም ላይ፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆናችን፤ እርሱም መዳናችን፤ እርሱም በክርስቶስ ውስጥ ወዳለው የመለኮት ሙላት መጋበዛችን ነው።

❝የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ይኖራልና (ὅτι ἐν αὐτῷ κατοικεῖ πᾶν τὸ πλήρωμα τῆς θεότητος σωματικῶς) እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል። በእርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከእርሱ ጋር ደግሞ ተነሣችሁ❞

በቆላስያስ 2:9 ላይ “ና” የሚለው ድኅረግንድ (suffix) የሚያሳየን (በግሪኩ ሃቲ/ὅτι) ከቁ. 9-15 ያለው ክፍል፤ ከላይ አስቀድሞ በቁ. 8 ላይ ለሰፈረው ሐሳብ ማብራሪያ እንደሆነ ነው (ይህንን “ና-አንቀጽ/ὅτι-clause” እንበለው)። “ምክኒያቱም” የሚለውን ቃል በመጀምሪያ ብናስገባ ሀሳቡ ግልጽ ይሆናል፡

❝ምክኒያቱም የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ስለሚኖር…❞

ይህ የሚያሳየን ቁ. 9 ያለ ቁ. 8 ትርጉም እንደማይሰጥ ነው። በቁ. 8 ላይ ጳውሎስ የመለኮት ሙላት የሌለበትን ነገር (ባዶ መንፈሳዊነት) እየነገረን “ተጠንቀቁ” ይለናል።

❝በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ❞ (ቈላስይስ 2:8)

የመለኮት ሙላት የሌለበት ሥፍራ “የሰዎች ልማድና የዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ የተመሠረተ ፍልስፍና” ነው። ስለዚህ ማንም በከንቱ ማግባቢያ ማርኮ እንዳይወስዳችሁ እያለ ያስጠነቅቀናል። እግዚአብሔር ያቀደልን ሙላት “በክርስቶስ” ብቻ ነው የሚገኘው። ይህንንም አስቀድሞ በቈላስይስ 1:19 ላይ “እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይሆን ዘንድ ወዶአልና (ὅτι ἐν αὐτῷ εὐδόκησεν πᾶν τὸ πλήρωμα κατοικῆσαι)” ብሎናል። በዚህም ሥፍራ ላይ የ”ና-አንቀጽ” ለቁ. 1፡18 ምክኒያታዊ ሆኖ እናያለን፡

“ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው። እርሱ…የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው…እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው…”

ምክኒያቱም

“እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይኖር ዘንድ ስለወደደ ነው”።

ያለ ክርስቶስ መዳን የለም እንደምንል ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወትም በክርስቶስ ጀምሮ ወደ ሌላ “ወደ በሰለ ልምምድና ሚስጢር” የሚደረግ ሽግግር አይደለም። ይህ ለዘመናችን ታላቅ ማስጠንቀቂያ ነው “የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በእርሱ ዘንድ ነውና” (ቈላስይስ 2:3)። መዳን ቢመነዘር የማያልቅ ታላቅ ሐብት ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር የማዳን ፕሮጀክት እና ራሱን የመግለጥ ፕሮጄክት የማይነጣጠሉ አንድ ተግዳሮቶች ናቸው።

እሥራኤልና የጸዓቱ ትድግና በብሉይ

ይህ እውነታ በአዲስም ይሁን በብሉይ እውነት ነው። እግዚአብሔር በብሉይም በአዲስም የማዳን ሥራው ወጥነት ያለው፤ እያደገና እየሰፋ የሚመጣ በመሆኑ። ለምሳሌ ያህል ያህዌህ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር የነበሩትን እሥራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ሲዋጃቸው እንዲህ ይላል፦“ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” (ዘጸ 6:7)። ይህ የሚያስገነዝበን፤ በአንዱ የጸዓት ትድግና ሥራ ውስጥ (እዚህ ጋር የሙሴን ተልዕኮና የወልድን ተልዕኮ ማነጻጸር ተገቢ ነው) እሥራኤላውያን ከባርነት ነጻ የሚወጡበት፤ ደግሞም አምላካቸውን “እንደ ያህዌህ” የሚያውቁበትም መንገድ ጭምር እንደሆነ ነው። አንድ ድርብ እውነታ ነበር ማለት ነው። ከዚህ ቀደም ያህዌህ ለአባቶች ራሱን ሲገልጥ፤ ሁሉን እንደሚችል እንደ ኤልሻዳይ እንጂ (እዚህ ጋር ዘፀ 3:14-15 እና ዘፀ 6:2 አወዳድሩ) በቃል ኪዳን ሥሙ አልተገለጠም። ይህ ማለት ያህዌህ ሕዝብን ገንዘቡ አድርጎና የሕዝብ አምላክ ሆኖ መገለጡ፤ የጸዓቱ ትድግና የቃል ኪዳን ሥሙን ፍንትው አድርጎ መግለጡን ያሳያል (የሕዝቡ የቃል ኪዳን ጌታ መሆኑ) ይህም ድነትና አስተርዮ አንድ ወገን ናቸው ማለት ነው።[1]

ከዚህ የተነሳ ያህዌህ ለአባቶች (ለአብርሃም፤ ይሥሐቅና ያዕቆብ) ሲገለጥ (ሲናገርና ሲሰራ) በመገለጡ ውስጥ ስለሚያመልኩት አምላክ የሚተላለፍም እውነት አለ። ያህዌህ ለአባቶች ተገለጠ (ዘፍ 17፡1-2፤ 35፡9-13) በሚሉት ሥፍራዎች ላይ እንደ ኤልሻዳይ እንደተገለጠ ጸሐፊው ይነግረናል (ወደ ፊት ሰፋ አድርጌ እገልጸዋለሁ) ። የዘጸዓቱ ትድግና ግን ለቅዱሱ ስም ያህዌህ መገለጥ የሚመጥን ሥራ መሆኑን እናያለን። ስለዚህ የእስራኤል ቤዝዎት ግቡ እስራኤል እግዚአብሔርን ማወቋ ነበር። ትድግናው አስተርእዮን አዝሏል ማለት ነው። አሁንም ጌታችን ሊፈጽመው ባለው ዳግም-ጸዓት (ሁለተኛ ትድግና) ተልዕኮ ውስጥ የስሉሱ አምላክ መገለጥ ያዘለ ትድግና ነው። ልክ በመጀመሪያው ኪዳን “ያህዌህ” በሚል ስሙ እንደተገለጠ፤ በሁለተኛው እና በመጨረሻው ኪዳን ውስጥ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃሽኋቸው…” በማለት የአዲስ አማኞች ድነታችን ስሉሱን አምላክ ወደ ማወቅ መጠራታችን ነው።

ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ በአዲሱ ኪዳን

የዚህ ቀደሙ ኪዳን ድክመት የተመሰረተው በኪዳኑ መካከል ከቆሙት መልዕክተኞች የተነሳ ነው። በኪዳኑ መካከል የእግዚአብሔር መልአክ እና የቃል ኪዳን መልዕክተኞች ሁሉ ቁንጮ የሆነው ሙሴ ነበሩና ነው። በዚህ ኪዳን መልዕክቱም እንዲሁ አስተርዕዮውም መለኮታዊ ነበሩ። ሆኖም ግን የመገለጡ ተረካቢዎቹና ገላጮቹ ግን መለኮታዊ አይደሉም። ከዚህ የተነሳ በልጁ የተመረቀውን ኪዳን የላቀ ኪዳን እንደሆን የዕብራውያን ጸሐፊ ሲናገር “ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል። በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን?” (Hebrews 2:1–2፟) ይለናል። አዲሱ ኪዳን ይልቃል ምክኒያቱም የኪዳኑ መካከለኛ ‘የክብሩ መንጸባረቅ እና የባህሪው ትክክለኛ ምሳሌ’ በሆነው በልጁ ስለተመረቀ። ሙሴ በቤቱ ላይ የታመነ ባሪያ ነበር፣ ኤሱስ ግን ልጅ ነው፡፡ ኢየሱስ ይልቃል፡፡

ለዚህ ነው መጥምቁ ዮሐንስ ጣቱን ጦቁሞ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል። ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም (John 3:30–32)” ቃሎቹ የእግዚአብሔር ቃሎች ናቸው። ሥራዎቹ የእግዚአብሔር ሥራዎች ናቸው። እግዚአብሔር ከሰማይ የላከው ይህ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ መንፈሱንም ሲሰጠው አይሰፍርምና! የፊደሉ ሕግ አሁን በመንፈስ ሕግ ተተክቷል። (ይህ ማለት ጨርሶ ትእዛዛት ሥፍራ የላቸውም ማለት ወይም የሕጉን መጽሐፍ አናነብም ማለት አይደለም። ሆኖም ግን ሕግ እንደ ኪዳን (law covenant) ሊፈጽም ያልቻለውን ልጁንና መንፈሱን ልኮ የሕግን አላማ በእኛ በመንፈስ ለምንመራና በክርስቶስ ለምናምን እውን ይሆናል።[2] ያህዌህ በህዝቄል ስለ አዲሱ ኪዳን “መንፈሴን በውስጣቸው አንኖራለሁ በማለት፣ በቀደመው ኪዳን የጎደለውን ተስፋ አድርጎ ሰጠ፡፡ ልጁና መንፈሱ የኪዳኑ መካከለኛ ስለሆኑ መዳናችን ፍጹም ነው፨

እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ መልአክ አለመላኩ

ከላይ እንደተመለከትነው በዚህም አንድ ተልዕኮ ውስጥ አብ ሁለት መልዕክተኞችን ልኳል።

“በዘመኑ ፍጻሜ ግን ከሴት የተወለደውን ከሕግ በታች የሆነውን ልጁን ላከ….አባ አባት ብሎ የሚጮሀውን የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ! ገላ 4:4”

እነዚህ ሁለት አካላት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ወይም እንደ ሙሴ ከውጪ ሰምተው እግዚአብሔርን የሚገልጡ ሳይሆኑ፤ መግለጣቸውም መገለጡም ሙሉ በሙሉ መለኮታዊ ነው። ምክኒያቱም ሁለቱም አካላት ከአብ ጋር አንዱ ሕላዌ ገንዘባቸው ስለሆነ ነው። ከዚህ የተነሳ የወልድ ቃል ከብሉይ ሕግና ከነብያት ቃል እጅጉን ይልቃል

“ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?” (John 5:46–47)።

ከ11ኛው ክፍለዘመን ቤተክርስቲያን አበው መካከል እንደ ምሶሶ ተደርገው ከሚቆጠሩት መካከል አንዱ ከካንትቤሪ የሆነው አንሰልም “ለምን አምላክ ሰው ሆነ?- ‘Cur Deus Homo” በተሰኘው መጽሀፉ ከብዕር ጓደኛው ጋር ሲወያይ እንዲህ ብሎ ጻፈ፡

❝የሰው ልጆች ቤዝዎት ከራሱ ከእግዚአብሔር በስተቀር በሌላ ሰው አሊያም መልአክ አማካይነት ሊከናወን አይችልም። ከእግዚአብሔር ሌላ የሆነ አካል ሆኖ ቢሆን ከዘላለም ሞት ያዳነን፤ የዳኑት ለዚህ ላዳናቸው አካል (ሰው ወይም መልአክ) አዳኜ ብለው ባርያ በሆኑለት ነበር። ታድያማ ይህ እንዴት መዳን ይባላል! ምክኒያቱም የዳኑት ከእግዚአብሔር ሌላ ለሆነው ባርያ ናቸውና። ይህ አሁን እንደሆነው ማለት ነው…በአየሩ ላይ ላለው አለቃ ሰዎች ይገዛሉና❞

ይህ የቤተ-ክርስቲያን አባት አስምሮ የተናገርው ነገር ምንድር ነው፤ የሰው ልጆች ሐጥያት እምብርት አመጽ ስለሆነ፤ ይህም ለእግዚአብሔር አለመገዛት፤ ከእግዚአብሔር ሥልጣንና አገዛዝ ማፈንገጥ፤ የእግዚአብሔርን ክብር በሌላ በተፈጠሩ ነገሮች እንደዚሁም የእግዚአብሔርን መለኮታዊ እውነት በሐሰት መለወጥ እስከሆነ ድረስ፤ እውነተኛ ቤዝዎት እነዚህ ነገሮች ያስተካከለ እንደሆን ብቻ ነው። ሰው ወደ እግዚአብሔር ሥልጣን ሲመለስ፤ ተንበርክኮ ይህንን አምላክ አዳኜ ያለ እንደሆን ብቻ ነው። አንሰልም ጥሩ አይቷል። በነብዩ ኢሳያስም ያህዌህ እንዲህ ይላል፡

❝ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም። እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ❞ (Isaiah 45:20–25)

ስለዚህ እውነተኛ መዳን ሁለት ነገሮችን ያቅፋል። እነዚህ ሁለት እውነታዎችን በብዙ መንገድ አዲስ ኪዳን ያሰቀምጣቸዋል። ለግልጽነት እንዲመች ግን ሁለት መደቦችን ልጠቀም። በአንድ እጅ እነዚህን ቃሎች እንያዝ፦ መጽደቅ፤ ቤዝዎት፤ እርቅ፤ ሰላም፤ መግባት፤ ሥርየት። በሌላ እጅ ደግሞ መክበር፤ ልጅነት፤ ተስፋ፤ ርስት። እነዚህ ሁለት እውነታዎች የሚያንጸባርቁት በአንድ ወገን ከየት እንደመጣን ሲሆን በሌላ እጅ ደግሞ ወዴት እንደምንሔድ ነው። በአንድ ወገን ድነናል በሌላ ወገን ደግሞ ገና በሙላት እንድናለን። መጽሀፍ ቅዱሳዊ ደህንነት ‘ከ’ እና ‘ወደ’ የሚሉትን መስተዋድዶች ገንዘቡ ማድረግ አለበት።

❝እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና። እንዲሁ ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና❞ (2 Peter 1:9–11)

ክርስቶስ ራሱን መስዋዕት አድርጎ በማቅረብ ለሐጥያታችን ሥርየት ሲል “ሐጥያታችንን በእንጨት በሰውነቱ ተሸክሞ ከእግዚአብሔር አብ ቁጣ፤ ከሞትና ከሐጥያት አድኖኗል። እዚህ ጋር ግን አያበቃም። ይህ ግማሽ እውነት ነውና። ስለዚህ እውነተኛ ደህንነት ግን “የልጁን መልክ” በመምሰል መክበርን ገንዘቡ ማድረግ አለበት። የመጨረሻ ግባችን ልጆች መሆን ነው (1 ዮሐ 3:1-5) መዳናችንን ከሌሎች ፍጥረታት ቤዝዎት የሚለየው መዳናችን የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስን መምሰላችን ነው። የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በመሆን ከመለኮት ባሕርይው እንድንካፈል ተዋጅተናል (2 Pet 1:2; John 1:2-3)።

የአካላት ሚና በወንጌል

ይህ ከፍ ብዬ ወደ ጀመርኩት ነጥብ ያመራኛል። ይህም የመንፈስ ቅዱስ በበዓለ ሃምሳ ተልኮ መምጣቱና በልባችን ማደሪያ መሥራቱ አላማው በግል የልጁን መልክ እንድንመስል እንዲሁም እንደ አካል ደግሞ እግዚአብሔር የሚኖርበት ሕያው ቤተ-መቅደስ ሆነን እንድንሰራ ነው (there is an eschatological progression of sonship as well as temple imagery) መንፈሱንም ‘የክርስቶስ መንፈስ’ በማለት የመንፈስ ቅዱስን ተልዕኮና ሥራ ይገልጽልናል። ይህ መንፈስ በስሉሱ አምላክ የውስጥ ሕይወት ውስጥ የሚሰርጽ እንደመሆኑ መጠን ለአካሉ የሚመጥነውን ሥራ ደግሞ በእኛም ሕይወት ይሰራል። ከዚህ የተነሳ መዳናችንን ስሉስ በሆነ መልክ በኤፌሶን ተገልጧል። ይህም የምንቀርብበት መንገዱም ሆነ ፍጻሜያችን በስሉሱ አምላክ የተቀመረ ነው። ስለ አቀራረባችን ሲያሳየን “በእርሱ [በክርስቶስ] ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና (Ephesians 2:18)” የምንቀርበው በአብ ፊት ሲሆን መንገዱ ደግሞ በወልድ ሥራ አማካይነት በአንዱ በመንፈስ ቅዱስ በኩል ነው (depicted highly in Trinitarian terms but reverse order. The father revealed himself to us, through Christ, by the holy Spirit. We experience this revelation by the Spirit, through Christ.)
ከዚህ የተነሳ የመንፈስ ቅዱስን ፕሮጄክት ሐዋርያው ሲነገርን “

“እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን። (2 Corinthians 3:18)

በውስጣችን ያለው የልጅነታችን መንፈስ ሊመጣ ላለው ርስት መያዣ መሆኑንም መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል (በዚህ ምክኒያት ሐዋርያው መንፈስ ቅዱስን የርስታችን መያዣ/አራቦን የሚል ሥያሜ ይሰጠዋል ‘ἀρραβὼν ኤፌ. 1:14’)

ስለዚህ መጽሀፍ ቅዱስ በልጁ በኩል የተገለጠውን ደህንነት ‘የማስመለጥ’ ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን (ምንም እንኳ ይህ ትልቁን ሥፍራ የሚይዝ እውነት ቢሆንም) ‘የመለወጥ’ ተልዕኮን ይጨምራል። ይህንን ተልዕኮ ወልድ ይዞ ተገልጧል። ከዚህ የተነሳ መዳን እግዚአብሔርን ማወቅ ነው። እግዚአብሔር ሲያድነን ከጠላትነትና ከሃጥያተኛነት ወደ ክብርና ወደ ልጅነት አምጥቶናል። ከአባቱ ጋር የመለኮት ክብር ገንዘቡ ሆኖ ሲኖር ከነበረበት ልዕልና ክብሩን ወደ ማታውቅ ወደዚህች ዓለም በመምጣት ራሱን አዋረደ (John 17:19, Phil 2:9-11)። የመጣው የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ነበር። ሆኖም ግን በዚህ በተዋረደ የመስቀል ሞት በኩል የአባቱን ፈቃድ በመፈጸሙ አብን አከበረ። አብ ደግሞ ወልድን ያለ ልክ አከበረው፤ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ሥልጣንን ሰጠው፤ ከብሮ እኛንም አከበረን። በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ደግሞ ክብር ገንዘባቸው ሆነ!

እኛም በባህሪያችን ሞት የተገባን፤ በሐጥያት የተለወስን ጸያፍ ሰዎች፤ ከልጁ ሕይወት/ደም ክቡርነት የተነሳ ከዚህ ስሉስ ሕይወት እንድንካፈል በር ተከፈተልን (በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ)። መዳን የዘላለም ሕይወት ነው። ሕይወትንም ማግኘት መዳን ነው። መዳን እግዚአብሔርን ማወቅ ነው፡፡ ይህም የዘላለም ሕይወት ነው። ለምን ይሆን ወደ መንግሥቱ ገብተን፤ ከእልፍኙ ውስጥ አብረን ታድመን ከስሉሱ ንጉስ ገበታ የምንጋራው? የማይጠገበውን የልጁን ክብር እናይ ዘንድ ነው። ይህም ክብር ወልድ በአብ መወደዱ ነው። ይህ መወደድ ለወልድ ክብሩ ነው (አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ)። ከዚህ ገበታ የሚፈረፈርውን የፍቅር ፍርፋሪ ብንለቅም አቤት እንዴት ታላቅ ክብር ይሆን!? ነገር ግን አብ ያፈሰሰልንን ፍቅር ተመልከቱ (1ዮሐ 3:1-5)! ልጆች አደረገን። ይህም ልጁ በሚወደድበት ፍቅር ተወደድን! ይህንን ፍቅር ተመልካቾች ብቻ ሳንሆን ነገር ግን ከዚህም ፍቅር ተካፋዮች እንድንሆን አበቃን! (እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ)። ፍቅር እንደዚህ ነው! እኛ እንደወደድ ሳይሆን አብ እንደወደደንና ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከልን ነው። ለምን ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት ይናፍቀናል? አንዳንዶች እንደሚሉት ወርቅ ስላለ ነው? እረፍት ስላለ ነው? ወይስ ለመዘመር ነው? የመጠቀ ዕይታ አለን፤ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ብሎናል፡-

❝የሰጠኸኝ ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ❞

ማራናታ እንበል! ወደ መዳናችን ለመግባት እንዘጋጅ። ስንሔድ የልጁን ክብር እናያለንና! መዳን ማለት ስሉሱን አምላክ በማወቅ ወደ ሚገኝ ፍጹም አንድነት መድረስ ነው። ይህንን ዳርቻ በልጅነት ይገልጸዋል። ልጆች ሆነን እንከብራለን። ሆኖም ግን ያ ክብር አሁን በውስጣችን እንዲኖር ከሰጠን በመንፈሱና በሐዋርያቱ አማካይነት ትቶልን በሔደው ቃሎቹ መቅመስ ጀምረናል።

[1]in this Exodus narrative, you have here the beginning of sonship language applied to a nation present, unlike the Genesis narrative

[2]In a nutshell this is Pauline paradox when it comes to the relationship of the Christian with the Law. Paul sees ‘faith in Christ’ and ‘life in the Spirit’ superseded Torah observance, without abolishing the need for commandments in Christian obedience. It is neither nomisim or antinomisim. For me, this is the tension that we must hold.

Leave a Reply

Your email address will not be published.