Blog,  ትምህርተ ሰብዕ

አስተርዕዮተ-እግዚአብሔርና ሰው

እውነተኛ ክርስትያናዊ አስተምህሮ (በምንም አይነት ጉዳይ ላይ ያተኮረ) የእግዚአብሔርን መገለጥ ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት። ከዚህ የተነሳ ማንኛውም ትምህርት ይሁን ስብከት፤ መዝሙር ይሁን ስግደት፤ እንዲሁም አምላክ ተኮር የሆነ ማንኛውም ንግግር/ ጹሑፍ፤ እግዚአብሔርን ያጎላል ወይም ያማክላል፤ አሊያ ያንኳስሰዋል ወይም ያደበዝዘዋል። ይህ የማይመለከተው አማኝ የለም። ያህዌህ ኢዮብን “ዕውቀት በጐደለው ቃል፣ ዕቅዴን የሚያጨልም ይህ ማን ነው?”(ኢዮ. 38:2) ብሎ እንደገሰጸው አንዳንድ ጊዜ ንግግራችን ከእግዚአብሔር ማንነት ጋር የሚጋጭ፤ ክብሩን የሚያደበዝዝና የመገለጡን ብርሃን የሚያጨላልም ይሆንብናል። ማስተዋልን ገንዘቡ ያላደረገ ንግግር በመሆኑም በሰሚው ልቡና ውስጥ አብርሆት ሰጪ አይሆንም።

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ትምህርተ-ሰብዕ (ሰው) እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ ትምህርት ነው

ስለ አስተርዕዮተ-እግዚአብሔር (ስለ እግዚአብሔር መገለጥ) ስንነጋገር ልናገናዝብ የሚገቡ ሁለት መሠረታዊ ገጽታዎች አሉት። ወይም መገለጡን ከሁለት ገጽታዎች አንጻር መመልከት ይገባናል። በአንደኛ ደረጃ መግለጠ-መለኮትን እ/ር እርስ-በርሱ ካለው ምጡቅ-ግንኙነት አንጻር ማየት እንችላለን (Essential Trinity)። ይህ ለፍጥረት መሠረት ለሕላዌው ደግሞ ወሳኝ ነው። አብ ከልጁና ከመንፈሱ ጋር ያለው የውስጥ ግንኙነት (relationship in the Essential Trinity or Ad-Intra)፤ ለገሓድ ሥራውና ከፍጥረቱ ጋር ላለው ግንኙነት (the Economic Trinity, Ad-Extra) ምክኒያትና መሠረት ነው። የአካላትም መሠረታዊ ልዩነት የተመሰረተውም በውስጥና በዘላለም ባለ ግንንኙነት ላይ ነው። ለምሳሌ፤ የአብ ለወልድ አባትነቱና ወልድ ከአብ ዘንድ ልጅነቱ፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ (ወይም እንደ ምሥራቅ አበው አነጋገር ‘ከአብ-በወልድ’) መሥረጹ እንደ አይነተኛ መውሰድ እንችላለን። በተጨማሪ፤

  • እ/ር እኛን መውደዱ የተመሰረተው አብ ለወልድ ባለው ፍቅር ላይ ነው፤ “ዓለም አንተ እንደላከኝ፤ በወደድከኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል” (ዮሐ. 17:23)፤
  • “እኛ አንድ እንደሆንን እነርሱም አንድ ይሆኑ ዘንድ” ሲልም የአማኞች አንድነት የተመሰረተው እ/ር ከራሱ ጋር ባለው የውስጥ ግንኙነት እንደተመሰረተ ማሳየቱ ነው።
  • ደግሞም “[አብ] ወደ ዓለም እንደላከኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላኳቸው” በማለትም የአማኞች ተልኮ አብ ወልድን በላከው ተልዕኮ ላይ መመስረቱን ያሳየናል።

ይህ እንደ ምሳሌ አድርገን ያየናቸው ክፍሎች የሚነግሩን፤ በእግዚአብሔር አብ በልጁንና በመንፈሱ መካከል ያለው ግንኙነት የአስተርዕዮ (የመገለጥ) መሠረት ነው። ወልድ በታሪክ ውስጥ ተልኮ የሠራው ሥራ (in the Economy; or as Augustine puts it፣ Ad-Extra)፤ በክበበ ሥላሴ በዘላለም ውስጥ ከነበረው ግንኙነቱ ጋር የሰመረ እንዲሁም ለገዛ አካሉ የሚመጥን ሥራ ነው። ወልድ አብን ወደ ምድር ቢልከው ኖሮ ይህ ይጣረስ ነበር። እኛም የሓትያትን ይቅርታ አግኝተን በልጁ አማካኝነት የልጅነትን መብት ስናገኝ፤ ከልጁ ጋር አብረን ወራሾች መሆናችን የተመሰረተው በዚህ ጥልቅ ሰማያዊ እውነት ላይ ነው። የአብ ላኪነት በዘላለም ውስጥ ካለው የአብ አባትነት ጋር ይዛመዳል፡፤ የወልድም መላክ እንዲሁ። መንፈስ ቅዱስም ከልጁ ሥራ ተከትሎ በበዓለ ሃምሳ መውረዱ፤ መንፈስ ቅዱስ ለአካሉ እንዲሁም ከሁለቱ አካላት ጋር ላለው የዘላለም ግንኑነት የሚመጥን ተልኮ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ በክርስቶስ የተሰጠን መገለጥ የማይታየውን ዘላለማዊ አምላክ የሚያንጸባርቅ መገለጥ ነው። ከዚህ የተነሳ በድፍረት እግዚአብሔርን በርግጥ እናውቀዋለን እንላለን (ገላ. 4:8-10)። ምንም እንኳ “ሙሉ በሙሉ አንጠፍፈን እናውቀዋለን ብለን መናገር ባንችልም።

በአንድ እጅ፤ ወደ ምጡቅ መጋረጃው ውስጥ ዘልቆ የገባና ያየ ማንም ፍጡር ባለመኖሩ (ደግሞም ሊኖር ባለመቻሉ፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ውስጥ ስለሚኖር) እግዚአብሔርን ፍጹም በፍጹም አብጠርጥሬ አውቀዋለሁ የሚል ማንም ፍጡር አይኖርም። ሆኖም ግን እንዲያ ብለው የሚናገሩ ሁለት አካላት አሉ። በኢየሱስ አማካኝነት ስለተመረቀው አዲስ ኪዳንና መገለጥ ዮሐንስ ሲነግረን:

“ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነው የምድር ነው፤ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን ምስክርነቱን ማንም አይቀበልም” (ዮሐ. 3:31–32)።

መጥምቁ ዮሀንስ እግዚአብሔር ከምድር ከላካቸው እና አስተርዮተ እግዚአብሔርን ካካፈሉ ነብያት የመጨረሻው ነበር። እርሱም ወደ ኢየሱስ እየጦቀመ “እኔ ላንስ እርሱ ሊልቅ ይገባል” አለን። ግን ለምን? ምክኒያቱም “ከሰማይ የመጣ ስለሆነ” የሚናገረውም በአባቱ ዘንድ ከምጡቅ መጋረጃ ጀርባ ያየውንና የሰማውን ስለ ነበር ነው። ለዚህ ነው “እርሱ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና…መንፈሱን ሲሰጥው አይሰፍርምና” ያለን። መጥምቁ ዮሐንስ እና እርሱን መሰል ነብያቶች (ሙሴንም ጨምሮ) “ከሰው ጎራ ነበሩ።” ከሰው መካከል በጸጋ ተመርጠው የተላኩ መልክተኞች ነበሩ። እነርሱም እንደ ሰው ሁሉ ሃጥያት ስላለባቸው፤ እግዚአብሔርን በሙላት መግለጥ አልቻሉም። ለዚህ ሙሴ አይነተኛ ምስላኤ ነው፡፤ የተስፋይቱንም ምድር መውረስ አልቻለም። ነገር ግን ያህዌህ “ከወንድሞችህ መካከል” የሚነሳ ነብይ እንደሚኖር አስቀድሞ ተስፋ ሰጠ። በተጨማሪ ፍጡራን በመሆናቸው እነርሱን ያየ እግዚአብሔርን ያየ ማለት አይቻልም። እነዚህ ሁሉ መልክተኞች፤ በዘመን መጨረሻ ስለሚመጣው እውነተኛ መልክተኛ (ከዮናስ የሚበልጥ የንስሃ ሰባኪ) የሚጦቁሙ “ጥላዎች” ነበሩ (ዕብ. 1:1-3)። ይህ መልክተኛ መልእክቱ መለኮታዊ (በልጁ ተናገረን)፤ ራሱም መለኮታዊ ነው (የክብሩ መንጸባረቅ የባህርዩም ምሳሌ ነው)። ስለዚህ ኢየሱስ ይልቃል፤

“እንግዲህ የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፤ የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ። ሙሴ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ ታማኝ እንደ ነበር፣ እርሱም ለሾመው ታማኝ ነበር። ቤትን የሚሠራ ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው፣ ኢየሱስም ከሙሴ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተገኝቶአል፤ እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው። ሙሴ ወደ ፊት ስለሚነገረው ነገር እየመሰከረ፣ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ እንደ አንድ ታማኝ አገልጋይ ነበር፤ ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን” Heb 3:1–6

እግዚአብሔር ራሱ ስለራሱ ባይነግረን ኖሮ አናውቀውም ነበር

በተጨማሪም እ/ር ራሱን በአንድ ጊዜ ፍንትው አድርጎ አልገለጠልንም። ራሱን በቃልና በሥራ አማካኝነት ሲገልጥ፤ እየጨመረና እያደገ በሚመጣ መልኩ፤ በሺዎች በሚቆጠሩ ዓመታት መካከል ነበር (በመገለጥ-ሒደት/ እድገተ-አስተርእዮ/ progressive revelation)። የዚህ አስተርእዮ ቁንጮና ፍጻሜ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ….እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ” (Ga 4:4–7)። ይህ ክፍል የሚያስረዳን ሁለት መሰረታዊ ነገሮች ቢኖር እ/ር፡ ልጁንና መንፈሱን መላኩ ነው። ሆኖም ግን፤ ምንም እንኳ የሁለቱም የተልዕኮ ዓላማ አንድ (የማዳን ግብር) ቢሆንም፤ በዚህ በአንዱ የማዳን ሥራ ውስጥ ግን ሁለቱ አካላት ሚና/ድርሻ አላቸው። ይህ ሚና፤ ለአካላቸው የመጠነና ከአብ ጋር በውስጥ በዘላለም ካላቸው ግንኙነት ጋር የሠመረ ነው። ለምሳሌ ስለ ልጁ ሲናገር፤ መንፈሱ እንደተላከ ልጁም ተልኳል። ሆኖም በዚህ አንድ የማዳን “ተልዕኮ/ ግብር” ውስጥ ልጁና መንፈሱ የተለያዩ ሚናዎች አሏቸው። አንድ ሥራ ነገር ግን ሦስት ሚናዎች። አብ ላኪ፤ ወልድ ደግሞ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት (በመስቀል ሥራው) በታሪክ ውስጥ ተላኪ። መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በአንድ እጅ ከአብ ዘንድ ወደ ልባችን የተላከ ሲሆን በሌላ እጅ ከወልድ አንጻር ደግሞ “የልጁ መንፈስ”፤ ከእኛ አንጻር ደግሞ “አባ አባ ብሎ የሚጮህ የልጅነታችን መንፈስ” ተብሏል። ስለዚህ በዚህ የመዋጀት አንድ-ሥራ ውስጥ የአካላት (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) ግንኙነትና ማንነትም ተገልጧል። ከዚህ የተነሳ የማዳን ሥራው ራሱ፤ የአስተርእዮም (መግለጥም) ሥራ ነው (Redemption is Revelation)። ልጁን በመላክ የሠራው የማዳን ሥራ መገለጥን ያረገዘ ሥራ ነው ብንል አልተሳሳትንም። ይህ የድነት ሥራ ስሉስን አምላክ የምናውቅበትም የመግለጥ ሥራ ነው።

“ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም።“እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ” Mt 11:27-28.

በፈጣሪና በፍጡር መካከል ልዩነት መኖሩ

እስኪ በምናባችን ሁለት ክበባትን እንሳል። የመጀመሪያው ክብ ውስጥ ሦስትና ሦስት ብቻ አካላት (አብ-ወልድ-መንፈስ ቅዱስ) ያሉበት ክበብ ነው እንበል። በሁለተኛው ክብ ውስጥ ደግሞ ፍጡር የሆነውን ነገር ሁሉ እንክተትበት (መላዕክት፤ ሰው፤ እንሣት፤ እጽዋት፤ ግዑዝ ወዘተ)። እነዚህ ሁለት ክበባት እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ልዩ መሆኑን አበክረው ያሰምራሉ። እግዚአብሔር ብቻውን አምላክ ነው። የመጠቀ ሉዓላዊ ንጉስ ነው። በፍጥረቱና በእርሱ መካከል አማካኝ የሆነ ሌላ “አካል” ፈጽሞ የለም። በመለኮት ዳራና ጎራ የሚመደብ፤ በክበበ መለኮት የሚኖር ማንም ፍጡር የለም። ሊኖርም አይችልም (Creator-Creature Distinction) ለዚህ ነው ሐዋርያው “አንድ እግዚአብሔር አለና፤ ደግሞም በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አንድ አስታራቂ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሰዎች ሁሉ ቤዛ አድርጎ ሰጠ፤ ይህም በትክክለኛው ጊዜ ተመስክሮለታል (1 ጢሞ. 2:4–6) ያለው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ፍጹም አስተርዮ ነው የምንለው ምክኒያቱ፤ እርሱ ብቻ በመጀመሪያው ክበብ ውስጥ አለምም ሳይፈጠር በፊት ይኖር የነበረ ደግሞም የሚኖር፤ እንዲሁም መለኮት ገንዘቡ የሆነ አካል በመሆኑ፤ እርሱን ማየት እግዚአብሔርን ማየት ነው። በተጨማሪ፤ በወልድ ውስጥ አብና መንፈስ ቅዱስ ያለተከፍሎ ስለሚኖሩ (ዮሐ. 14:10፤ 10:38)፤ ወልድን ማወቅ አብን እና መንፈሱ ከማወቅ ሊነጠል አይችልም። የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ በሆነ በዚያ አማኝ ውስጥ አብና ወልድም ይኖራሉ። መንፈሱን ላከልን ማለት የስሉሱ አምላክ፤ የአንዱ እግዚአብሔር መኖሪያ ሆንን ማለት ነው።

እግዚአብሔር ምጡቅና አኻዜ-ኹሉ መሆኑ

ግን እነዚህ ሁለት ክበባት መጽሀፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ሙሉ እውነት እንዲያንጸባርቁ መጨመር ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ደግመን እስኪ አሁን በእነዚህ ሁለት ክበባት መካከል አምሥት መስመሮች በማስመር እናገናኛቸው። እነዚህ መስመሮች የእግዚአብሔር ሥራዎች ናቸው፡- የማቀድ ሥራ፤ የመፍጠር ሥራ፤ የመመገብ ሥራ፤ የማዳን ሥራ፤ እና የመፍረድ ሥራ። እግዚአብሔር ፍጥረቱን ፈጥሮ ያልተወ ነገር ግን እለት እለት የሚንከባከብ፤ ከእኛ ያልራቀ አምላክ ነው (ሐዋ. 17:23–31፤ መዝ. 50፡12)። የሳልናቸው ክበባት በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት (Creator-Creature Distinction) እንደሚያሳዩ፤ እነዚህ መሥመሮች ደግሞ እግዚአብሔር ምጡቅና አኻዜ-ኹሉ (God’s Immanence and Transcendence) መሆኑን ይገልጹልናል። አለምን የወደደ፤ ራሱም ወርዶ ያድናት ዘንድ ያቀደ፤ ደግሞም ሁሉን በዘመን ማብቂያ ላይ ወደ ፍርድ የሚያመጣ የምድር ሁሉ ዳኛ ነው። እነዚህን ሥራዎች በአንድ ቃል ብናጠቃልላቸው፤ ይህም ለምን አቀደ? ለምን ፈጠረ? ለምን ይመግባል? ያድናል? ደግሞም ይፈርዳል? ምክኒያቱም ፍጥረት ሁሉ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆን ያውቅ ዘንድ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሥራዎች ሁሉ በአንድነት አላማቸው፤ “ክብሩን ለመግለጥ ነው”። አስተርዕዮተ-እግዚአብሔር የሥራዎቹ ሁሉ ዓላማ ነው ማለት እንችላለን። ያዳነን ለስሙ ክብር እንሆን ዘንድ ነው።

ስለዚህ ፍጡር የሆነ አካል ሁሉ መደቡ በሁለተኛው ክበብ ውስጥ ነው። መለኮት ፍጡር አይደለም፤ ፍጡርም መለኮት ሊሆን መቼም አይችልም (Creator-Creature Distinction) እግዚአብሔርም በሕይወታችን በሥራ ላይ ነው። በፍጥረቱ ላይ ገዢ ነው። ለምሳሌ ያህል በዘመናችን ያሉት የሩቅ-ምሥራቅ ሃይማኖቶች (Buddhism) እና የኒው-ኤጅ እንቅስቃሴ (or its variations such as ‘I am part of god’ mantra) የጥንቱን የግሪክ-ሮም እምነትን (እንዲሁም የጥንታዌ ቅርብ-ምሥራቅ እምነትን ጨምሮ) ያንጸባርቃሉ። በጥንታዌው ዓለም አማልክት የሚታሰቡት እነደሚከተሉት ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር፦

  1. በሰማይ ሃይላት፤ በእንሥሳት፤ በእጽዋዕት (Animism) አይመሰልም [ዘፍ. 1:16/ ዘጸ 20:2-5]
  2. ከአማልክት መካከል እንደ አንዱ (Henotheism) አይመለክም [መዝ 100:1-3]
  3. ከአማልክት ጋር ድርብ አምላክ አይደለም (ብዙ አማልክት፤ ብዙ ጌቶች) (Polytheism/ Paganism) [ኢያ. 24:14-15፤ መሳ. 6:10]
  4. ፍጥረት በጥቅሉ (Pantheism) ወይም በከፊል (Panentheism) መለኮትን አይጋራም
  5. አምላክ ባይተዋር አይደለም (Desim)
  6. መለኮትነት በመንትያ ጎራ አይመደብም (Dualism)። የሚታይና የማይታይ፤ መንፈሳዊና ቁሳዊ የሰማያዊና የፍጥረታዊ ልዩነት አይደለም።[1]

የመጨረሻውን ነጥብ ብናነሳ፤ የእግዚአብሔር ገዢነትና አምላክነት በመንፈሳዊና በቁሳዊ፤ በሰማያዊና በምድራዊ አይከፋፈልም። እግዚአብሔር መንፈሳችንን ይገዛል ነገር ግን ሥጋችንን አይቆጣጠርም፤ መንፈሳችን ድኗል ሥጋችን ግን አልዳነም የሚል ይህ መንትያ አለም መጽሀፍ ቅዱሳዊ አይደለም (ይህ ብዙዎች አቤቱታ ያቀረቡበት የእምነት-ቃል እንቅስቃሴ (Word-Faith) ኑፋቄ ነው)። ይህ አስተምህሮ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ተፋልማ የተዋጋችው አስተምህሮ ነበር። ብዙዎች እንደሰሩት ስኅተት እ/ር መንፈስ ስለሆነ ፍጥረታዊውን ነገር የሚያማክልለት ድልድይ ይፈልጋል የሚለው አስተምህሮ ከመጽሀፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ትምህርት ነው። ለእ/ር በፍጥረታዊና በመንፈሳዊ መካከል ልዩነት የለም። እ/ር ሁለቱንም በአንድነት ይገዛል። የኖስቶሳውያን/ዶሲቲዝም አመለካከት መንፈስ የሆነ ከመንፈሳዊና መለክታዊ የሆነ ሲሆን ቁሳዊ/ፍጥረታዊው ደግሞ ሐጥያትና ክፉ ነው ባይ ነበር። ኖስቶሳዊ አመለካከቶች በተለያዩ መዓዛዎች ቀርበዋል (1) መንፈሳዊ የሆነ ነገር መለኮታዊ ባህርይ አለው (Gnosticism)። ይህም በቀጽላነት የሰው ነብስ/መንፈስ ከመለኮት የወጣ እንጂ የተፈጠረ አይደለም ይላል። ስለዚህ በሥጋ የምናደርገው ነገር ችግር የለውም ባይ ነው። እውነተኛ የሰው ማንነቱ መንፈሱ/ነብሱ ነው ብሎ ስለሚያምን (ለምሳሌ ፕሉቶኒክ ንጽረተ-ዓለም)። ስለዚህ እንደ እነርሱ አባባል፤ እውነተኛ እውቀት መንፈሳዊ፤ መዳን ደግሞ የእውቀት ብልጭልጭታን ማግኘት ነው። እንዲህ ብለው በማመናቸው (ደግሞ በዘመናችን ነፍሳችን እንጂ መንፈሳችን ያልተፈጠረ በመሆኑ እንደ እግዚአብሔር ከመለኮታዊ ባህርይ ይጋራል ‘የሰው መንፈስ’ ሁሉን ያውቃል የሚሉትም የዚህ ኑፋቄ ሰለባዎች ናቸው)። ከዚህ የተነሳ ማንበብ፤ ማጥናትና መማር፤ እነዚህ እውነተኛ እውቀቶች ሳይሆኑ አዕምሮአዊ ብቻ ናቸው እንባላለን። ስለዚህ እንደኖስቶሳዊ ርዝራዥ አመለካከት መዳን ማለት ወደ ሰማያዊ እና ሚስጢራዊ አብርሆት መድረስ ነው። (2) ሌላው የኖስቶሳዊ አስተምህሮ መዓዛ ደግሞ በቁሳዊ ነገር ላይ ማተኮር ሐጥያት ነው ባይ ነው። ስለዚህ መንፈሳዊ ሕይወትና የዕለት ዕለት ህይወት የተለያዩ መንትያ ጎራዎች ናቸው። ጋብቻ ስጋዊ ነው። ዕለት ዕለት የሕይወት ጉዳዮሽ ስጋዊ ናቨው። ለምሳሌ ይህ አስተምህሮት ክርስቶስ በሥጋ እንደተገለጠ ይክዳል፤ ምክኒያቱም ክርስቶስ ከዚህ ክፉ ቁሳዊ ነገር ጋር ሊካፈል ስለማይችል ብለው ስላሰቡ። መንፈሳዊነት ከእለት ዕለት ሕይወት መለየት ነው። ከዚህ የተነሳ በየምድረ በዳው ከሰው ተለይቶ መመነን እንደ መንፈሳዊነት ታይቷል።

ይህንን ጠቅለል ለማድረግ፤ “ሰው ማነው?” የሚለው ጥያቄ “እ/ር ማነው?” በሚለው ጥያቄ ውስጥ የታቀፈ ነው። ይህም አስተርዮተ-እግዚአብሔርና ትምህርተ-ሰብዕ (ሰው ማነው?) በጣም የተቀራረቡ ጉዳዮች ናቸው። ምክኒያቱም የመገለጡ ተረካቢዎች በዋነኛነት ደረጃ እነዚህ በአምሳሉ የፈጠራቸው ሰዎች በመሆኑ ነው። ስለዚህ፤ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለው ጥብቅ ግንኙነት ያንጸባርቃል። እንዲሁም እግዚአብሔር ራሱን በመግለጥ ሒደት ውስጥ ሰው ትልቅ ሥፍራን ይይዛል። (በተለይ ከድህረ-ሥጋዌ፤ ቃል-ሥጋ ከሆነ በኋላ በግልጽ ማየት እንችላለን)።

ከላይ ያየነው የእ/ር የውስጥ ሕይወትና ግንኙነት በአምሳሉ ለፈጠረው ሰው መሰረት መሆኑን ነው። እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው። ሰው ደግሞ በሃጥያት ከወደቀ በኋላ ያድነው ዘንድ በኪዳናቱ አማካኝነት ተስፋን ቃል ሰጠ። ይህም ተስፋ አፈጻጸሙ በዘመናት መካከል የተዘረጋ ሲሆን፤ ለአዳም በኤደን ገነት የሰጠው ተስፋ፤ በኖህና ብልጆቹ፤ በአብርሃምና በዘሩ፤ በእሥስራኤልና በዳዊት ብሎ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰ የትድግና ትረካ ነው። የዚህ ድነት አላማ የእ/ርን ክብር መመለስ ሲሆን፤ ክብሩም በዋጀው ሕዝብ መታወቁ ነው። ሆኖም ይህ ድነት ዳግም ክርስቶስ ሲገለጥ የሚፈጸም በመሆኑ ድነታችን ተስፋም ጭምር ነው። ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት እ/ር ማን እንደሆን፤ (ፈጣሪ፤ ሏላዊ ገዢና አዳኝ፤ ሕላዌ) ያውጃል። የዚህ ጹሁፍ አላማ ግን ይህ ልዩ አምላክ ራሱን ሲገልጥ፤ የአስተርእዮው ዋና ተቀባይ በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ነው። ስለዚህ “ሰው ማነ ነው?” የሚለውም ጥያቄ እንዲሁ ዋነኛ ጥያቄ ነው። ስለዚህ ሰው ማን ነው?

ይቀጥላል….

[1]Samson Tilahun, Person of Yahweh Our God, 85-7

Leave a Reply

Your email address will not be published.