
ነገረ-ክርስቶስ በዕብራውያን መልዕክት: መቅድም
(The Christology of Hebrews: An Introduction)
የእብራውያን መጽሐፍ የሹመት መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉን ሙሉ ነገረ–መለኮታዊ ክብደት የሚሸከመው «በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ» የሚለው እውነታ ነው (ዕብ 1:3; 1:13; 8:1; 10:12-13; 12:2)። ኢየሱስ ከሁሉ እንደሚልቅ ሰባኪያችን ሲሞግት (ጸሐፊውን የምጠራው ሰባኪው በማለት ነው) የሚያቀርባቸው መሠረታዊ ማስረጃዎች በሙሉ በዚህ ልዕልና እና እውነታ ላይ የተመረኮዙ እንዲሁም የተቃኙ ናቸው። እውነታው «ተቀመጠ» (ኧካቲሰን | ἐκάθισεν)” (1:3) የሚለው ሲሆን፤ ልዕልናው ደግሞ የተቀመጠበት ምጡቅ ሥፍራው ነው “በሰማያት በግርማው ቀኝ”። ስለዚህ የሰባኪው ማዕከላዊ መልዕክት <ኢየሱስ ይልቃል! ምክኒያቱም ኢየሱስ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጧልና> የሚል ነው። ይህንን ልዕልና ከእብራውያን የነገረ–መለኮታዊ አቀራረብ ስልት አንጻር በሁለት ንጽጽራት መድበን መመልከት እንችላለን። አንደኛው ምድራዊ–ሰማያዊ የሚል ‘የቁም ንጽጽር’ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ይኸኛውና ወዲያኛው ዓለም የሚል ‘ሰያፍ ንጽጽር’ ነው። በሰማያት የተቀመጠበትን ልዕልና በምድር ካሉት ካህናት፤ መስዋዕት፤ ድንኳን ወዘተ…እንደሚልቅ ያነጻጽራል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ልዕልናው ገና ሊመጣ ባለው ዓለም ውስጥ መጥቆ አሁን የተመረቀ በመሆኑ ይልቃል። ገና ወደፊት የሚገለጠውን ክብር አሁን “የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ” እናየዋለንና (2፡9)። በሁለቱም ንጽጽሮች ውስጥ የምናየው ልጁ በግርማው ቀኝ መቀመጡን ነው። ወደዚያ ልዕልና ያረገና የተቀመጠ ማንም አልነበረም፤ ከእርሱም ሌላ ሊኖር አይችልም።
መልከጸዴቃዊ–ካህንና ንጉስ
በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት የከለከላቸው የቀደሙት ካህናት ብዙዎች ነበሩ (7:23)። እነርሱም ዕለት ዕለት “ቆመው” (ኧስቴከን | ἕστηκεν) ያገለግላሉ። ይኸኛው ካህን ግን ለዘላለም ፍቱህ የሆነውን አንዱን መሥዋዕት <ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ> አቅርቦ፣ በሰማያት በግርማው ቀኝ <ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ> “ተቀምጧል (ኧካቲሰን\ἐκάθισεν)” (10:11-12)። እነርሱ “ቆመዋል” (10:11)! ኢየሱስ ግን ተቀምጧል (10:12)! የቆመ ጉድ–ጉድ ይላል። የተቀመጠ ግን አርፏል። የተቀመጠ አጠናቋል። የተቀመጠ በእንቅስቃሴ ላይ ስላይደለ ‘ፍጻሜ\ግቡ’ ላይ ደርሷል ማለት ነው። ከሙታን መካከል “ወጥቶ” (13፡10) በሰማያት አልፎ (4፡14) መቀመጡ ክህነቱ የዘላለም እንደሆነ አረጋግጦልናል (7፡24)። እነርሱ ሟች በመሆናቸው (7፡23) ክህነታቸው በትውልድ ሐረግ ላይ የተመሠረተ ነበር። እርሱ ግን በማይጠፋ የሕይወት ሃይል ለዘላለም ስለሚኖር፣ ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ነው (7፡17)። ይህንን ያወቅነው ስለ “ተቀመጠ” ነው። “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ…ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (4:14፣ 16)። ኢየሱስ ጸጋ ሰጪ በሆነ ዙፋን ላይ፤ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጧል። ኢየሱስ ይልቃል! ሃሌ ሉያ!
ስለዚህ በእብራውያን መልዕክት ውስጥ ሁሉም ነገር የጸናው በዚህ መሠረት ላይ ነው! “ፍጹም”፣ “ፍጻሜ”፣ “ፈጻሚ”፣ የሚሉትም ቃላት በመልክቱ ውስጥ የተራቡት ከዚህ እውነታ የተነሳ ነው። የሌዊ ክህነት “ፍጹምነትን” (ተሌይኦሲስ\τελείωσις) አላስገኘም ወይም ግቡን መምታት አልቻለም (7:11)። የክህነቱም ሕግ “ማንንም ፍጹም ሊያደርግ” አልቻለም (7፡18–19)። የእንሥሣት ደም ይቀርብባት የነበረችው “ፊተኛይቱ ድንኳን” ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገዷ ዝግ በመሆኑ ፍጹም አልነበረችም። የሚደረጉትም የምግብ፤ የመጠጥና የመንጻት ሥርዐቶች አዲሱ ሥርዐት እስኪመጣ ድረስ የሚደረጉ “ሥርዐቶች” ብቻ እንጂ አምላኪውን በህሊና “ፍጹም” ሊያደርጉት አልቻሉም (9፡9–10)። ይህ “የተቀመጠው” ካህን ግን በሥጋው መጋረጃ ‘መንገዷ-ክፍት’ ወደ ሆነችው ወደ ታላቅ እና “ፍጹም (ተሌይዖስ\τέλειος)” ድንኳን ገባ። ሕጉ ማንንም እግዚአብሔር ወደ አቀደው ፍጻሜ (ኧተሌይኦሰን\ἐτελείωσεν) ማድረስ አልቻለም (7:19)። ማለትም ማንንም ወደ እግዚአብሔር ፍጹም አድርጎ ማቅረብ አልቻለም። ስለዚህ የማይጠቅም ስለሆነ “በሚሻል ተስፋ” ተሽሯል (7፡18)። ይህ “የሚሻል ተስፋ” ምንድር ነው? ኢየሱስ <በመሃላ> ሊቀ-ካህናት የሆነበት ክህነት ነው። “እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም…አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” (7:20-21; 5፡6; 6፡20; 7፡21; መዝ። 110፡4)። የኢየሱስ ክህነት የተማለበት እንጂ እንደ ሌዊ ክህነት በነቀፌታና በጸጸት የተሞላ አልነበረም “በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል” (ሚል 2:8)። ስለ ልጁ ግን ሲናገር “ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ብሎ ማለ አይጸጸትም።” አሮን ሊቀ–ካህናት እንዲሆን እንደ “ተሾመ” (5፡1፤ 5)፤ ኢየሱስም በእግዚአብሔር ተሹሟል። ነገር ግን የሌዊ ኪዳን ፍጹም የሆነው እስኪመጣ ሻጥ የተደረገ ጊዜያዊ ሹመት እንጂ እንደ ልጁ “ከመሐላ ጋር” የመጣ አልነበረም (7:20–21)። ከዚህ የተነሳ <መልከጼዴቃዊ ካህን–ንጉሥ> የሆነው የልጁ ክህነት ይልቃል። እርሱ መዳናችንን ፈጽሟል\τελειῶσαι (2:10)። ከሥራው አርፏል። የአዲሱ ኪዳን ተስፋ “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስብም” (8፡12) የሚለው በክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ አነጻው (9:14)። የተጠሩት የተሰጠውን ተስፋ አሁን በእርግጥ መውረስ ይችላሉ። ምክኒያቱም ከሕጉ በኋላ የመጣው መሃላ “የአዲስ ኪዳን መካከለኛ” የሆነውን “ፍጹም ልጅ” ሾሟልና ነው (7፡28) ። ይህ ፍጹም ልጅ ፍጹምናን የሚያስገኝ ፍጹም መስዋዕት አቅርቧል፤ “ከኀጢያታቸው ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቶአል” (9፡15)። ሰባኪው እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ <በመሃላ> ያጸናቸው 2 ተስፋዎች እንደነበሩ ያያል፦ ለአብርሃም ማለ እንዲሁም ለዳዊት ልጅ በመዝ 110፡4 ላይ ማለ። እኛም የምንመካበትን ተስፋ (3፡6) እስከመጨረሻ ድረስ አጥብቀን ብንይዝ (3፡14)፣ ተስፋው እስኪሞላ ድረስ (6፡11)፣ የተስፋችንን ምሥክርነት (10፡23) ጸንተንም ሃይማኖታችንን ብንጠብቅ (4፡14) በፊታችን ያለው ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ ይሆንልናል (6፡17–18)። ርስታችንን እንወርሳለን። እንዴት እርግጠኛ እንሆናለን? ምክኒያቱም “ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ” የተማለለት ካህን ስላለን ነው። እርሱም “ወደ መጋረጃውም ውስጥ” ገብቶ በግርማው ቀኝ ስለተቀመጠ ነው። በዚያ “ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ” ገብቷል (6፡20) ዘወትር ይማልድልናል (7፡25)፤ በእግዚአብሔር ፊት ይታይልናል (9፡24)። ይህ ሁሉን በአፉ ቃል የሚያንቀሳቅሰው ልጅ (ፌሮን | φέρων)፤ እርሱ በምድር ላይ ተንቀሳቅሶ (ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ)፤ በሰማያት አልፎ ተቀምጧል። ስለዚህ እስካሁን በእብራውያን መጽሐፍ ነገረ–መለኮታዊ አቀራረብ ውስጥ፣ “ተቀመጠ” የሚለው ቃል የኢየሱስን ልቀት ለማጉላት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ነው። እንደ እርሱ የተቀመጠ ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ አሁንም የለም። ኢየሱስ ይልቃል።
በመጪው ዓለም ላይ የሚገዛ ንጉስ
እንዲሁም፣ ሥራውን ፈጽሞ የተቀመጠው “በሚመጣው ዓለም | τὴν οἰκουμένην τὴν μέλλουσαν” ላይ ነውና ኢየሱስ ይልቃል (2:5)። ማናችንም ገና ያልገባንበት ፍጹምነት አሁን ገንዘቡ ነው። ከሞት ትንሳኤው በኋላ በሰማያት አርጎ፤ በግርማው ቀኝ ሲቀመጥ፣ “በኵርን ወደ [መጪው]ዓለም ሲያገባ” በመንገድ “መላእክት ይሰግዱለት” ይላል (1:6)። ሲቀጥልም፤ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የነበረውን ኣላማ (2:6-8; ተጓ. መዝ. 8:6; ዘፍ. 1:26-28) ነገር ግን በአዳም ሐጥያት ምክኒያት ፉርሽ የሆነውን ግብ፤ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ በመገኘት ፈጽሞታል። ከመላክት ለጥቂት ጊዜ በጥቂት አንሶ የነበረውን፤ አሁን “የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን” (2፡9)። በጌታ የድነት–ትረካ ውስጥ የነበረው ይህ ሰያፍ እንቅስቃሴ [መለኮታዊ ሐሳቡ] አሁን በሰው–ልጅ ‘መቀመጥ’ ፍጻሜ አግኝቷል። ተዋርዶ የተዋረደውን አክብሯል። በሐጥያት ምክኒያት የፎረሸውን ሰው ሊያድን፤ እርሱ የፉርሾችን ሞት ቀምሶ ፉርሽ ያደረጋቸውን ዲያብሎስን እንዲፎርሽ (2፡14–15) ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው (2፡17)። በሥጋና በደም ተካፍሎ ፍጹም ሰው ሆነ። [በግሪኩ፦ “በሞቱ ‘ያ የሞት ሃይል ያለውን’ ይሽር ዘንድ፣ እርሱም ዲያብሎስ ነው” የሚለው እና “ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ እንዲያወጣ” የሚሉት አላማ–ገላጭ አንቀጻት “በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ” ለሚለው ዋና አረፍተ–ነገር ጥገኛ ናቸው]። ስለዚህ ሰባኪው ሲሞግት፤ ኢየሱስ እንደ «እግዚአብሔር ልጅ» በመሾሙ ከመላክት ይልቃል (1፡13)፤ «የሰው ልጅ» በመሆኑም እንዲሁ በመልከጸዲቅ ሥርዓትም «ሊቀ-ካህናት» ሆኖ በመሾሙም ከሌዊ ክህነት ይልቃል። ግን እንዴት? ለሁለቱም የሰጠን ማስረጃ በ1:13 ላይ “ከመላእክት፤ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ያለው ለማን ነው?” ሲሆን በ8:1 ላይ እንዲሁ “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን” በማለት ነው። ስለተቀመጠ ይልቃል።
መልከጸዴቃዊ–ካህንና ንጉስ
ይህ ብቻ አይደለም። እነዚህ ሁለቱም የተለያዩ አሊያም በተለያዩ ዘመናት የተደረጉ ሹመቶች ሳይሆኑ ኢየሱስ ወደ አባቱ አርጎ በመቀመጡ የተቀዳጀው ጣምራ ሹመቶች ናቸው “መልከጸዴቃዊ ካህንና ንጉስ” ። ኢየሱስ እንደ “እግዚአብሔር ልጅ (1:1-14)” ወይም እንደ “ሰው-ልጅ (2:5-18)” ወይም እንደ “ታላቅ ሊቀ-ካህናት” (5:1-10; 7:1-8:6) ላቂ (የላቀ) ያደረገው “ልጅና ካህን” ሆኖ በሰማያት በግርማው ቀኝ መሾሙ ነው። ይህ ሹመት ማንም ያልደረሰበት የሹመት ጫፍ ነው። ሆኖም ግን ኢየሱስ ልጅ እንደተባለ፤ ያህዌህ ለዳዊትና ለልጆቹም ኪዳን ሲገባ “አንተ ልጄ ነህ (1:5; መዝ 2:7)” ብሎ ጠርቷቸው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ “ልጅ” ተብሎ መሾሙ በራሱ ልዩ አልነበረም። በተጨማሪም ዳዊት “የበኩር ልጅ” ተብሎ እንደነበር (መዝ. 89)፤ እርሱም ሁሉን ወራሽ በኩር ነው (1:3, 6)። ኢየሱስ ሊቀ-ካህናት ተብሎ እንደተሾመም፤ አሮንም እንዲሁ በእግዚአብሔር ተሹሞ ነበር። ሆኖም ግን በመዝ. 110:1 ላይ ዳዊት የልጅ ልጁን “ጌታዬ” ብሎ በመጥራት (ማቴ 22:43-44) ተራ-ልጁ እንዳልሆነ ያልቀዋል፤ እንዲሁም ያህዌህ “በቀኜ ተቀመጥ” በማለቱ ወደ መለኮት መደብ ይመድበዋል። ደግሞም ወረድ ብሎ፣ በመዝ 110፡4-5 ላይ፣ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም “አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” በማለት በነገድ የተለያዩትን ሹመቶች፤ ከይሁዳ ቤት የሆነውን መሲህ፤ ከሊዊም ነገድ ያልሆነውን በተለየ ሥርዓት “ካህን” ነህ ይለዋል። ስለዚህ ጴጥሮስ በበዓለ ሐምሳ ቀን ሲሰብክ “ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም መቃብሩ እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው….” በማለት በድፍረት ይናገራል። ዳዊት ሞቷል፤ በስብሷል፤ አጥንቱም ደርቋል። ሲቀጥል “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም” ይህ በመዝ 110:1 ላይ ያለው ከፍታ ዳዊት አንቃሮ የተመለከተው ከፍታ ነበር። ጴጥሮስም “ነገር ግን እርሱ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው…እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ (ሐዋ. 2:34-35)” ጴጥሮስ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከመዝ110:1 ላይ በማገናኘት የክርስቶስ መክበር (ዕርገቱና መቀመጡ) ለተስፋው መንፈስ ቅዱስ መሰጠት ምክኒያት ሆኗል “በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው (2:33)”። የእብራውያን ሰባኪ ግን ከሌሎቹ ጸሐፊያት ለየት የሚያደርገው ክርስቶስ በግርማው ቀኝ እንደ “ልጅ-ካህን” ሆኖ መቀመጡን ማጉላቱ ነው። ስለዚህ ዳዊት ያንቃረረውን ሹመት የዳዊት ልጅ “ሁሉን ወራሽ ሆኖ ተሹሞ” እናየዋለን። ስለዚህ ኢየሱስ “መልከጸዲቃዊ ካህን-ወ-ንጉስ” ነው። “ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል” ይላል (7:28)። ተመለከታችሁ? የቀደመው ሕግ (በም.8 ላይ ተተክቷል የሚለን ሥርዓት – “አዲሱ ኪዳን በእብራውያን መጽሐፍ ላይ” በሚለው ስለዚህ ጉዳይ በሰፊው እንዳስሣለን) ደካሞ «ሰዎችን» ካህናት ያደርጋል። ይህ አዲስ ሥርዓት ግን “ፍጹም የሆነውን ልጅ ካህን” አድርጎ ሾሟል። በደማቅ ቀለም የሚያሰምረው “ልጅ-ካህን” የሚለውን ነው።
ለማጠቃለል ያህል፤ ሰባኪያችን ተስፈንጥሮ ወደፊት “ጠላቶቹ ሁሉ የእግሩ መቀመጫ” ወደሚሆንበት ቀን [ወደ ዳግም ምጻቱ] ሲያሳየን (1:13; 10:13; 9:28)፤ የኋሊትም ተመልሶ በሥጋው ወራት ስለ ተቀበለው መከራ ሲነግረን (5:7-8) እንዲሁም የቅድመ-ትሥጉት ማንነቱን ሲገልጽልን (1:3) ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተመላለሰ ስለ ክርስቶስ ማንነት እና ሥራ ሲመሰክርልን፣ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ክርስቶስ ጌታና ካህን ሆኖ ከተሾመበት ልእልና እና ዕውነታ ላይ ተመርኩዞ ነው። በመልክቱ ሁሉ፣ ይህንን ስፍራ አይለቅም። ስለዚህም ለእብራውያን መልክት ሰባኪ፣ ክርስቶስ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ “ወደ ግርማው ቀኝ ለመቀመጥ” በእግረ-መንገድ ላይ ያደረገው ነው ብንል ሀሳቡን ሰብሰብ ያደርግልናል {በተለይ ይህ “የመንገድ ላይ” ጉዳይ ለማርቆስ ልዩ ትረካዊ ገጽታ ይሰጠዋል። ኢየሱስ ያደረገው ታምራት፤ ስብከት፤ ወደ መስቀል ‘መንገድ ላይ ሆኖ ነው። ሲጀምርም ‘የጌታና መንገድ ጥረጉ’ ብሎ ወንጌሉን ከፍቶታልና}። በመጀምሪያ፤ ወደ ክብር ሲሄድ በመንገድ ላይ ሃጥያታችንን አነጻ “ሃጥያታችንን ካነጻ በኋላ በግርማው ቀኝ «ተቀመጠ» (1:3) [ውጤቱም] ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላ ዕክት እንደሚበልጥ እርሱም ከመላክት ይበልጣል (1:4)። ሲቀጥልም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ራሱን እንደ መስዋዕት አቅርቦ «ተቀመጠ» (10:12)፤ ስለዚህ የሚቀደሱት ለዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል (10:14)። ሲጨርስም በፊቱ ያለውን ክብር [መቀመጡን] እያሰበ ነውርን ንቆ “በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ” ተቀመጠ (12:2) ስለዚህ በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ (12:3)። “በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ” ተዋርዶ ነበር። አሁን ግን “ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን (2:9) ስለዚህ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር አመጣ (2:10)፤ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞቱ ሻረ (2:14-15)፤ በሥጋና በደም የተካፈለ ፍጹም ሰው ስለሆነ፤ ሰው ሆኖም መከራን ስለተቀበለ፤ ሰው ሆኖም መከራን ተቀብሎ ግን ሃጥያትን ስላላደረገ “የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥” የተገባው ሆኗል።
ስለዚህ ብዙ ካህናት ነበሩ ሞት የከለከላቸው። ሐጥያት ያደከማቸው። እንዲሁም፣ ብዙ የዳዊት ልጆች ነበሩ፤ ኢላማቸውን የሳቱ። ከዚህ የተነሳ በ586 ቅ.ዓ. ላይ ያህዌህ የዳዊትን ቤት አሳልፎ ሰጠ (ሕዝ. 1:3 ዮአኪን በተማረከ በ5ኛ ዓመት)፤ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባውን ኪዳን ያፈረሰ እስክሊመስል፤ ዙፋኑን ከሰው አጸዳ። ከዚያ ቀን ጀምሮ፤ የባሕርይው ምሳሌ-የክብሩ መንጸባረቅ፤ የሆነውን፤ ዓለማትን በእርሱ የፈጠረበትና ሁሉን የሚመግብበት ልጁን ወራሽ አድርጎ በዳዊት ቤት ላይ እስኪሾም ድረስ፤ የዳዊት ዙፋን ወና ሆነ።ስለዚህ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ” ያለው ማንም አልነበረም። ይህን ሲል ግን አሁንም ሰባኪው አይኑ ያተኮረው በግርማው ቀኝ አርጎ የተቀመጠባት ቀን ላይ ነው፥ “ዛሬ ወለድሁህ” የምትለው የተፈጸመችው፣ የዛሬ 2000 ዓመት ልጁ በግርማው ቀኝ ሲቀመጥ ነው። በጴጥሮስ አነጋገር “እናንት የሰቀላችሁትን ኢየሱስን ጌታና ክርስቶስ አደረገው ይላል። ለእብራውያን መልክት ሰባኪ ደግሞ “መልከጸዲቃዊ ካህን ወ ንጉስ” ሆኖ ተሹሟል! እሰይ!!
ስለዚህ የእብራውያንን ነገረ ክርስቶስ ለመጨበጥ፣ ይህንን እውነታ አስቀድመን መገንዘብ የግድ ነው። ክብር ሁሉ ለተሾመው ይሁን!
(ይኽ ጽሑፍ ለሕንጸት መጽሔት የተጻፈ ነው)
https://hintset.org/articles/exposition/exposition-on-hebrew?fbclid=IwAR0TV-JN6JPuDTzuYLjDfd0YKToSMr0o2fw594gXZbECcic8U5j5CbHymDM

