
ነገረ-ክርስቶስ በማርቆስ ወንጌል
[su_quote]ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብና የዮሴፍ፤ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት (ማር. 6:3)[/su_quote]
ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት፡ የማይለያዩት ‘ማንነቱና ሥራው’ በማርቆስ ወንጌል
በመንግሥቱ ወንጌል መሰበክ አማካኝነት፤ በንሥሃ መንፈስ የተለወጠ ልብ ለሌለው ሰው የክርስቶስ ማንነት “ስውር” እንደሆን በማርቆስ ወንጌል ላይ እናያለን። ከሌሎቹ ወንጌላውያን ለየት ያለው ይህንን የማርቆስ አጽንኦት፣ የአዲስ ኪዳን ሊቃውንት “የእግዚአብሔር-ልጅ-ነገረ-ክርስቶስ”; “Son-of-God Christology (Lewis S. Hay)” ይሉታል።
የወንጌሉ ምንባባዊ አወቃቀር
የማርቆስን ወንጌል በሦስት አበይት ክፍሎች መመልከት እንችላለን፡
(1) የእግዚአብሔር ልጅ እና መሲሃዊ መንግሥቱ (1:1-15) – መግቢያ በዮርዳኖስ ወንዝ
(2) የእግዚአብሔር ልጅ እና በእርሱ መሲሃዊ ዘመን በሃይል መፈንጠቁ (1:16-8:26) – በገሊላ
(3) የእግዚአብሔር ልጅ እና መሲሃዊ መከራው (8:27-16:8) – በኢየሩሳሌም
የመጀመሪያው ክፍል ላይ “የእ/ር መንግሥት”፤ “ወንጌል” እና “የክርስቶስ ማንነት” በአንድ ላይ የተገመዱ እውነታዎች እንደሆኑ ያሳየናል። የመጥምቁ ስብከት ከክርስቶስ በይዘት ልዩነት አልነበረውም፡፡ ሁለቱም የእግዚአብሄር መንግስት መቅረቧን አውጀዋል፥ ሆኖም ግን መጥምቁ እጁን ከእርሱ በኋላ ወደሚመጣው እየጠቆመ ሲሰብክ፣ ክርስቶስ ግን እጁን ወደ ራሱ እየጠቆመ “ጊዜው ደርሶአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ” ይል ነበር። መልካሙ የምስራች የመንግሥቱ መገለጥ ነው። ይህም በክርስቶስ ማንነት፤ ሥራ እና ተልእኮ ላይ ያነጣጥራል።
ነገረ-ክርስቶስና የእግዚአብሔር ልጅ ስያሜ
በትክክል ኢየሱስን ማወቅ የሚችሉ ሰዎች ክርስቶስን እና የመስቀሉን ሥራ ለማየት ብርሃን የበራላቸው ናቸው። ከዚህ የተነሳ፤ በዚህ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ «የእግዚአብሔር ልጅ» እንደሆነ የመሰከሩት
- ወንጌላዊው ማርቆስ (1:1)
- እግዚአብሔር አብ (1: 11; 9: 7)
- አጋንንቶች (1: 25; 3: 11– 12; 5: 7)
- ክርስቶስ ራሱ (12: 6; 14: 61)
- ሮማዊው የመቶ አለቃ (15:39) “እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ ‘ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር’ አለ”
ይህ የሚያስረዳን ከሰዎች መካከል ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ልጅ” መሆኑን ያወቀ “የመቶ አለቃው” ብቻ እንደነበር ነው። ይህ በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ፣ ይህ ሮማዊ “አህዛብን” ይወክላል። ይህ ሰው ከመስቀሉ ሥር ሆኖ የተፈጸመውን የመስቀል ሥራ በቅርበት የተመለከተ ሰው ነበር። በኋላ እንደምናየው፤ የማርቆስ ትረካ እየገሰገሰ ወደ መስቀሉ በቀረበ ጊዜ፤ የክርስቶስም ማንነት እንዲሁ መገለጥ ይጀምራል (በአዲስ ኪዳን ጥናት ታዋቂ የሆነው Martin Kähler famously quoted that Mark’s Gospel is “a passion narrative with an extended introduction” )። እስከዚህ ድረስ ከሰዎች መካከል የኢየሱስን ማንነት በትክክል የተረዱ ባይኖሩም፤ አሁን ግን እ/ር የመስቀሉን ጉልበትና ለአህዛብ ያለውን አላማ በዚህ አህዛብ (ሮማዊ) ያሳይ ዘንድ፤ ኢየሱስ ሲሞት ባየ ጊዜ አይኖቹ በሩለት። በሁለተኛ ደግሞ፣ የወንጌሉ ተደራስያን በሮም ያሉ ሰዎች እንደ መሆናቸው፤ [የማርቆስ ወንጌል ሊቃውንት ሲናገሩ]፤ በወንጌሉ ውስጥ የተንጸባረቀው ይህ የእ/ር ልጅ ስያሜ፤ “ኢየሱስ እንጂ ቄሳር (የሮም ንጉስ) የእ/ር ልጅ አይደለም” ለማለት ነው። አሁን ምድር አዲስ ‘ጌታ’ አላት፤ እርሱም ቄሳር ሳይሆን “ክርስቶስ ነው።
የኢየሱስ ልጅነትና የደቀ-መዛሙርቱ የልብ ድንዳኔ
ይህ የክርስቶስ የእግዚአብሔር-ልጅነት [ነገረ-ክርስቶስ] ጉዳይ በአይነተኛነት የምናየው በማር. 8፡29 ላይ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ነው።
በማቴዎስ ወንጌል 16:16 ላይ «ስምዖን ጴጥሮስም ‘አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ’ በማለት መለሰ» ሲለን
ማርቆስ ግን «ጴጥሮስም ‘አንተ ክርስቶስ ነህ’ አለው ይላል» (ማር. 8፡29]
በማርቆስ ወንጌል መጀመሪያ ላይ ሁለቱም ስያሜዎች ጥቅም ላይ ውለዋል፦ “የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ” (1:1) በማለት ክርስቶስና የእግዚአብሔር ልጅ እርስ በርሳቸው የሚብራሩ ቃሎች እንደሆኑ እናያለን። ልክ እንደ ማቴዎስ “ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ” ግን አይልም። ለምን? ማርቆስ “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለውን ስያሜ ለልዩ አላማው ይፈልገዋል። እኔ እና እናንተ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ልጅ” እንደሆን ስንመሰክር የቃሉን ሙሉ ትርጉም እና እንደምታ ይዘን ነው። የኢየሱስን ልጅነት ስናስብ፡-
- (#1) ዘላለማዊ/መለኮታዊ ልጅነቱን፤
- (#2) የዳዊት ልጅ መሆኑን -መሲሃዊነቱን
- (#3) በግርማ ቀኝ ልጅ ሆኖ መሾሙን (በእርገቱ ጌታና ክርስቶስ ሆኖ መገለጡ)።
እነዚህ ሦስት ገጽታዎች ወደ ልባችን ይመጣሉ። እነዚህ ሦስቱንም በአንድ ጊዜ ካልያዝን የእኛ ነገረ-ክርስቶስ በሽተኛ ነው። እርሱ በሥጋ የዳዊት ልጅ ከመሆኑም በፊት “የአብ አንድያ ልጅ” ነበር። ስለዚህ ሮሜ 1:2-4 ላይ “ወንጌሉም ስለ ልጁ…ነው” ይለናል ( #1 ከላይ)፤ ይህ ልጅ በአንድ ወገን “በሥጋ” የዳዊት ልጅ ሲሆን (#2 ከላይ) በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሳቱ የእ/ር ልጅ መሆኑ በሓይል የተገለጠ/የተሾመ ልጅ ነው (#3 ከላይ)። በተመሳሳይ መልኩ (ዕብ.1:1-4)
[su_pullquote]As Doug Moo aptly summarizes it “It is the Son who is “appointed” as Son…the transition from v.3 to v.4, then, is not a transition from human messiah to divine son of God (adoptionism), but from the Son as messiah to the Son as both messiah and powerful, reigning Lord.] (Douglas Moo, Romans – NICNT, 48-49[/su_pullquote]
ጴጥሮስ ምንም እንኳ ኢየሱስ “ክርስቶስ” ወይም “የሕያው እግዚአብሔር ልጅ” እንደሆን ቢመሠክርም፤ ነገር ግን ማርቆስ እንደሚያሳየን ጴጥሮስ የተናገረው በርግጥ ገብቶታል? ለእርሱና በዘመኑ ለነበሩ ብዙ አይሁድ ክርስቶስ ሊነገሥ እንጂ ሊሞት አይመጣም። ይህም ኢየሱስ “የዳዊት ልጅ\ መሲህ\ ክርስቶስ መሆኑን ነው፤ (የእ/ር ልጅ የሚለው ሥያሜ የዳዊትንም ኪዳን ያመለክታል 2ሳሙ. 7:14 ወይም መዝ. 2:7 ይመ.)። በተጨማሪ፤ ጴጥሮስ የኢየሱስ ተልዕኮ ምን እደሆነ ሙሉ በሙሉ ገና አለመረዳቱን ግልጽ አድርጎ ሲያሳየን ወረድ ብሎ ኢየሱስም “አንተ ሰይጣን” ብሎ ጴጥሮስን ሲገስጸው እናያለን። ኢየሱስ “ማን ነው? ተልዕኮውስ ምንድር ነው?” የሚሉት ጥያቄዎች ሙሉ ክብደታቸው ደ/መዛሙርቱን ገና አልተጫናቸውም። ገና ሊረዱ እንደሚገባ አልተረዱትም ነበር። ለዚህ ነው ማርቆስ “የሰው ልጅ ማን ይሉታል?” (8፡27-33) የሚለውን አንቀጽ ከመስጠቱ በፊት፤ ከፍ ብሎ በ8፡14-21 እና 8:22-26 ላይ ሁለት አንቀጽ “literary units” ሰጥቶ አሰናድቶናል።
[ሀ] ማር 8:17-21፡ እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?
“ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብስ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኖአል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን?…እርሱም፣ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?” አላቸው።”
በጣም የሚያስደንቀው ይህ አይነት ዕውርነት በማርቆስ ወንጌል ላይ “በውጭ ላሉት (4:11)” የክርስቶስን እውነተኛ ማንነት ለማያውቁ፤ አይኖቻቸው ለታወሩ ሁሉ ይወክል ዘንድ የገባ ገላጭ ቃል ነው። ከነዚህም መካከል ለምሳሌ ማርቆስ ለናሙና ያህል፦
- ቅፍርናሆም ለነበሩ ጸሐፍት ኢየሱስ ተሳዳቢ ነው (2:7)
- ለገዛ ዘመዶቹም ኢየሱስ “አእምሮውን ስቶአል” (3:21)
- ከኢየሩሳሌም ለመጡ ጸሐፍት ኢየሱስ “ብዔልዜቡል አድሮበታል” (3:22)
- ያደገበት ሰፈር ኗሪዎችም “ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብና የዮሴፍ፤ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት” (6፡3)
ለምን አላመኑበትም? ምክኒያቱም እውራን ስለነበሩ! “እርሱም፣ “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ነገር ሁሉ በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ ይኸውም፣‘ማየቱን እንዲያዩ እንዳያስተውሉትም፣ መስማቱን እንዲሰሙ ልብ እንዳይሉትም፣ እንዳይመለሱና ኀጢአታቸው እንዳይሰረይላቸው ነው’ አላቸው።”
አስደናቂው ነገር በ8:17-21 ላይ ኢየሱስ የገዛ ደቀ-መዛሙርቱን ልክ “በውጪ እንዳሉት”፤ “ልባችሁ ደንድኖአል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን?” ማለቱ ስለ ኢየሱስ ማንነት ገና ደ/መዛ በቂ ግንዛቤ እንዳልጨበጡ ያስገነዝበናል። ወይም ማርቆስ በትረካው መካከል ጠለቅ ብሎ በማር. 6:52 ላይ “ልባቸውም ደንድኖ ነበር” ብሎ ያስደንቀናል። ደ/መዛሙርቱ ኢየሱስ በባሕር ላይ የመራመዱ እንደምታ ምን እንደሆን ለመረዳት ያልቻሉት፤ ከዚያ ቀደም “የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና” ነው። ይህም የሰው የልብ መታወር እጅግ ጥልቅ እንደሆነና መፍትሔውም እንዲሁ ስር ነቀል መሆን አለበት። ከላይ ከላይ የሆነ እምነት፤ ከላይ ከላይ ይሆነ ነገረ-ክርስቶስ አለ። ስር ያልሰደደ መረዳት። ከዚህ መራቅ እንዳለብን የደ/መዛ. ሕይወት ያስተምረናል።
ለምን ይህ ብዥታ በደ/መዛ. ሆነ? ብንል ሁለት ዋና ዋና መልሶችን መስጠት እንችላለን።
(1) ከድነት-ታሪክ አገላለጥ የተነሳ ወይም ከእድገታዊ-አስተርዮ የተነሳ አንዳንድ ነገሮች ከመስቀሉ ሞትና ትንሳኤ በፊት እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ከመሰጠቱ በፊት ላሉ ሰዎች ግልጽ ባለ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ መጥ. ዮሐ. በማቴ 11 ላይ ያቀረበውን ጥያቄ መመልከት እንችላለን
(2) ከደ/መዛ. ልብ-ድንዳኔ/ አለማመን የተነሳ። ማወቅ ያለብን ጉዳይ ወንጌላት ከትንሳኤ ባሻገር የተጻፉ በመሆናቸው፤ የኋሊት ምልከትና ነገረ-መለኮታዊ አቀራረብ አሏቸው። ጌታ በተደጋጋሚ ደቀ.መዛ. ሊረዱ ይገባ እንደነበር ነቅፏቸዋል (ለምሳ. ሉቃ 24)። “ሚስጢር ማወቅ ተሰጥቷቿል..ግን አታውቁም…” ምንም እንኳ አንዳንድ ጉዳዮች ከመስቀሉ በፊት ላሉ ግልጽ ባይሆኑም የብዥታው ሰበብ ግን ሲመረምሩ፤ ማርቆስም እንዲሁም ዮሐንስ፤ በደ/መዛ. ሕይወት ውስጥ ጉልህ ሆኖ የሚታይ ‘ፉክክር’ እና ‘እኔ-እልቅ’ ነበረ። ይህ አሳውሯቸዋል። ማስተዋል ያለብን ክርስቶስን-አለማወቅ የመረጃ ጉድለትን ያልፋል። በዮሐንስ ላይ “ማንም የእ/ር ፈቃድ ማድረግ ቢወድ…ትምህርቴ ከአብ አንደሆነ ያውቃል” ይለናል። ይህ የሚያሳየን አለማመን ወይም አለማወቅ ‘ግብረገባዊ ችግር/ moral issue’ መሆኑንም ነው። ቅድስና “የአይን ጥራት” ያመጣል። ተቃራኒውም እንዲሁ።
መቼም ይህ ከመስቀሉ ሞት በፊት እንዲሁም ከበዓለ ሃምሳ በፊት ላሉት እንኳ አሳዛኝ ቢሆንም፣ ወይም ከድነት-ታሪክ አንጻር ኢየሱስ ይህንን ከፊል እውርነት ቢታገስም፣ ግን ግን ግን፣ ከመስቀሉ ባሻገር ላለን፤ የኢየሱስ ማንነት በሙላት በሚሰበክበትና መንፈስ ቅዱስ በተሰጠበት ዘመን ላለን አማኞች ምንም ማመካኛ የለንም። የክርስቶስ ማንነት ጉዳይ “ድንግርግር” ሲል ይህ እውርነት በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ደርሷል ማለት ነው። ከዚህ ወዲያ መስቀል የለም። የፍርድ ዙፋን ብቻ እንጂ! ስለዚህ ነገረ-ክርስቶስ ዋነኛ ጥያቄ ነው።
ጠቅለል ለማድረግ፤ በ8:17-21 ላይ ኢየሱስ የእ/ር ልጅ መሆኑን የገዛ ደ/መዛ. እንኳ እንዳልተረዱ ወይም ስለ ክርስቶስ ያላቸው መረዳት በቂ እንዳልነበር “በእነርሱም መታወር/ የልብ ድንዳኔ” ካስረዳን በኋላ፤ በ8:22-26 ላይ ደግሞ በቤተ ሳይዳ የተፈወሰውን የዐይነ ስውር ታሪክ ተጠቅሞ የደ.መዛ. መንፈሳዊ አይን በማስረጃ ያሳየናል። ይህንን ሰው ኢየሱስ በሁለት ደረጃ ይፈውሰዋል፤
[ለ] 8:22-26 – ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ
“እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። ኢየሱስም እንደ ገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ።
ይህ የፈውስ ታሪክ በሁለት ደረጃ መቅረቡ (8:22-26) በቀጥታ ከደ/መዛሙርቱ ጋር (8:17-21 ) ማርቆስ ያገናኝልናል። አሁን ክርስቶስን ያያሉ ደግሞም አብረውት ይመላለሳሉ። ነገር ግን ዕይታቸው ጥርት ያለ አልነበረም፡፤ እይታቸው “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ” እንደማየት ነው። አቤቱ ጌታ ኢየሱስ ሆይ እኛም ብርሃንህ በበራበት በዚህ ዘመን “አይናችን የሚንቀሳቀስ ዛፍ ካዩ” አጥርተን እናይህ ዘንድ አይኖቻችንን አብራልን! ለማየት እንድንችል አይኖቻችንን ኳለን (ራዕ. 3፡18)።
ነገረ-ክርስቶስና የክርስቶስ ስልጣን
[su_quote]”ኢየሱስም፤ “አንተ ልጅ፣ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል!” አለው። በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ስለዚህ ነገር በልባቸው እያሰላሰሉ፣ “ይህ ሰው እንዴት እንዲህ ይላል? በአምላክ ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ እኮ ነው! ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማን ኀጢአትን ሊያሰተሰርይ ይችላል?” ብለው አሰቡ (ማር. 2:5-7)[/su_quote]
በዚህ ክፍል ላይ (እንዲሁም በጥቅሉ በማርቆስ ወንጌል ውስጥ) የክርስቶስ ሥልጣን ጎልቶ ቀርቦልናል። የኢየሱስን ቃሎች ጉልበት በመጀመሪያ የምናየው ስም ዖንና ወንድሙን እንድርያስን ሲጠራቸው “ተከተሉኝ” አላቸው እነርሱም ወዲያው “ተከተሉት” (1:16)። የክርስቶስ ቃል ለመጥራት ጉልበት ያለው ቃል ነው። አጋንንትም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” በማለት ለስልጣኑ እውቅና ሲሰጡ እናያለን (1፡23-25)። ምንም እንኳ ጌታ የአጋንንት ምስክርነት ባይቀበልም፤ ኢየሱስን በተለይ ማርቆስ እንደ ‘ጦረኛ ንጉስ’/ ‘Warrior King’ አድርጎ ይስልልናል (ልክ ፈረሱንና ፈረሰኛውን ድል እንዳደረገው እንደ ጦረኛው-ያህዌህ)። በማር. 5 ላይ በጌርሴኖን በመቃብር ሥፍራ ብቻውን የሚኖረውን አሳዛኝ ሰው፤ ኢየሱስ ባህር ተሻግሮ ‘ተዋግቶ’ ነጻ አወጣው፤ አጋንንቱም ሲመልስ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ” ይላል በሽንፈት። ነገር ግን ዝናው እየተናፈሰ ወደ አደገበት መንደር ሲሄድ፤ በማር. 6 ላይ የጠበቀው ታላቅ አለማመን ነበር “..ኢየሱስም ባለማመናቸውም ተደነቀ (6:6)”። ይህንን ነው ከላይ ‘ስውር’ ያልኩት። በፊታቸው የእግዚአብሔር ልጅ ቆሞ፤ እነዚያን የማንነቱን ማስረጃ እያዩ ለብዙዎች ተሰውሮባቸዋል። በከፊል የገዛ ደቀ/መዛ. ጨምሮ። ለምን? ባለማመናቸው።
እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጅ ሥልጣን በ1:27 ላይ “ጸጥ በል፤ ከእርሱም ውጣ!” ብሎ ሲገስጽ የሰማው ሕዝብም “ይህ ነገር ምንድን ነው? ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት መሆኑ ነው! ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል! (1:27)” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ።
በማር. 2፡1-12 ባለው ክፍል ላይ የክርስቶስ ሥልጣን በሁለት መንገድ ተነግሮናል አንድ “በልባቸው የሚያስቡትን በመንፈሱ ተረድቶ” በማለት ኢየሱስ በሰው ልብ ውስጥ ያለውን ስውር ሐሳብ የመረዳት አቅም እንዳለውና ሁለተኛ “የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት ሽባውን፣ “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” ሲለው እንመለከታለን።
ሆኖም ደግሞ በዚህ ክፍል ውስጥ ከሥር ሥር የሚፈስ አንድ ትልቅ እውነትም አለ። ይህም አንድ ሰው ሐጥያትን መናዘዝና የሐጥያትን ይቅርታ መቀበል ያለው በቤተ-መቅደስ ወደ ካህን በመቅረብ ነበር (ለምሳ. ዘሌ 4-5)። ሆኖም ግን ኢየሱስ በቆመበት ስፍራ ሁሉ እርሱ ራሱ በሰውነቱ “የመቅደስን ሚና” ይጫወታል። በመቅደስ ሊከናወኑ የሚገቡ ነገሮች በእጁ ይከናወናሉ። ያለምንም ሥርዓት ኢየሱስ ሐጥያትን ይቅር ይላል (በብሉይ የእንሣት ደም ስርዓት፤ አሊያም እንደ መጥምቁ ዮሐንስ የውሃ ጥምቀት…ወዘተ…)። እንዲሁም ለምጽን ይፈውሳል። እንዲሁም ቁ. 25 ላይ ክርስቶስ በሰንበት ላይ ያለውን ስልጣን ሲያሳየን
“ዳዊት በተራበና የምግብ ፍላጎት በጸናበት ጊዜ አብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋር ያደረገውን አላነበባችሁምን? በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፣ ካህናት ብቻ እንዲበሉት የተፈቀደውን የተቀደሰ ኅብስት ራሱ በልቶ አብረውት ለነበሩትም ሰዎች ሰጣቸው…ስለዚህ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው”
ኢየሱስ ያላቸው (በተመሳሳይ መልኩ በማቴ. 12 ላይ) በሕጉ ውስጥ አንዳንድ ሕጎች (ጉዳዮች) ከሌሎች ሕጎች ተቀዳሚነት አሏቸው። ለምሳሌ ያህል በማቴ. 12 ላይ፤ የመቅደስ ሕግ ለካህናት በሰንበት እንዲሰሩ መብት ይሰጣቸዋል። ምክኒያቱም የመቅደሱ ሕግ ከቀናት ሕግ ስለሚበልጥ። በሁለቱ በሚነራረቡ ሰዓት፤ የመቅደሱ ህግ የሰንበትን ሕግ ይሽረዋል። ልክ እንዲሁ “ከመቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ” [‘አለ’ የሚለው ቃል ‘ተባእታዊ’ ሳይሆን ‘ግዑዝ’ መሆኑ ብዙ አስተያየቶችን ጋብዟል። ሆኖም ግን አጥጋቢ ሆኖ ያገኘሁት ይህ የክርስቶስንና የመሲሃዊ ተልኮው ጋር በአንድላይ እንድናይ የሚጋብዘን መሆኑን ነው(Eschatological-Christological reality of Jesus’ mission] ክርስቶስ ከሰንበት ይበልጣል። ሥልጣኑና ማንነቱ አይለያዩም። ቃሉና ሥራው፤ ማንነቱና ሞቱ አይነጣጠሉም። ስለዚህ ነገረ-ክርስቶስ (ማንነቱ + ሥራው ) እና ነገረ-ድነት አይነጣጠሉም።
ማጠቃለያ
አራቱም ወንጌላውያን ክርስቶስንና ሥራውን ሳንለያይ በአንድ ላይ መያዝ እንዳለብን ያስተምሩናል። “ክርስቶስ ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ እና ጤናማ መልስ ካልሰጠን፤ “ክርስቶስ ምን አደረገልኝ?” የሚለው ሥርዬታዊ ሥራው ብቻውን አይረባንም። ሞርሞንም ስለ ክርስቶስ ሞት እንዲህ ይላሉ:
[su_pullquote]”…substitutionary atonement for our sins. That offering is made efficacious as we exercise faith and trust in Him; repent of our sins; are baptized by immersion as a symbol of our acceptance of His death, burial and rise to newness of life; and receive the gift of the Holy Ghost” (https://www.mormonnewsroom.org)።[/su_pullquote]
ግን የእኛ ኢየሱስ ማንነት እና የእነርሱ ኢየሱስ ማንነት የተለያዩ ኢየሱሶች ናቸው። ስለዚህ በየስፍራው “ኢየሱስ ያድናል!” የሚለው መፎክር፤ “ኢየሱስ ማን ነው?” በሚለው በረጋና በሰከነ ንግግር ካልተደገፈ በራሱ በቂ አይደለም።
እንዲሁም “ክርስቶስ ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ሰጥተን ነገር ግን “በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ” አምናለሁ በማለት ሥርዬታዊና ቅጣታዊ ሞቱን በእምነት እውቅና ካልሰጠን፤ አጋንንቶችም እኮ “አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” እያሉ ያምናሉ፤ “በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ”።
ስለዚህ ክርስቶስ “ማነው?” እና “ምን ሠራ? የሚሉትን ጥያቄዎች አብረን በመያዝ ለሁሉቱም ያለተነጥሎ በእምነት ምላሽ ልንሰጥ ይገባል። ስለዚህ ነገረ-ክርስቶስ በሁሉ ሥፍራ ይሰበክ ዘንድ ጸሎቴ ነው!

