
ተወለደ!
‹ለምን ተወለደ?› የሚለው ጥያቄ የሕይወት ጥያቄ ነው። ሆኖም ግን በአዲስ ኪዳን ላይ «ተወለደ» የሚለው ቃል ወልድ ፍጹም ሰው ስለ መሆኑ (ስለ ነገረ-ትሥጉት) ከሚነግሩን አገላለጾች አንዱና ዋነኛው ይሁን እንጂ “ብቸኛ” ግን አይደለም። በአዲስ ኪዳን የትሥጉት ነገረ-መለኮት በብዙ ቃላት ያሸበረቀ ነው። «ተወለደ» በሚለው እሳቤ ላይ በተጨማሪ፣ በአዲስ ኪዳን ላይ እኩል አጽንዖት ተሰጥቷቸው የምናገኛቸው ተጨማሪ ነገረ መለኮታዊና ሙያዊ የሆኑ ቃላት አሉ። በእነዚህ ቃላት ነገረ-ትሥጉታችን ካልዳበረ፣ ቀጫጫ ይሆንብናል። የዚህ አጭር ጽሑፍ አላማ፣ ስለ ልደቱ (ስለ ገና) በግል በአምልኮ ሰዓት ስናሰላስል ይሁን በሕብረት ስንዘምረው፤ በስብከታችን ስናውጅ እንዲሁም በአስተምህⶂ ስናብራራ፣ የፋፋና የዳበረ ነገረ-ትሥጉት እንዲኖረን ይረዳን ዘንድ ነው።
የአዲስ ኪዳን ነገረ-ትሥጉት በሚከተሉት ቃሎች ያሸበረቀ ነው፦
- «ተወለደ» (ሉቃ. 2:10)
- «ሥጋ ሆነ» (ዮሐ. 1:14)
- «በመካከላችን አደረ» (ዮሐ. 1:14)
- «ራሱን ባዶ አደረገ»
- «ተገለጠ» (1ዮሐ 3:8)
- «ከሰማይ ወረደ» (ዮሐ. 3:11-13)
- «ተላከ» (ገላ 4:4\ሮሜ 8፡3)
- «የባሪያን መልክ ያዘ» (ፊል. 2:5-7)
- «መጣ» (1 ጢሞ. 1:15)
- «በሥጋና በደም ተካፈለ» (ዕብ ፪፡፩፬-፩፭)
- «በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ» (ሮሜ 8፡3) ወዘተ…
ከእነዚህ ቃላት ጋር የተያያዘ የዳበረም ነገረ-ክርስቶስ አለ። እነዚህን ቃላት በሦስት መደብ እናስቀምጣቸው። የመጀመሪያው መደብ ተጸንሶ ከመወለዱ አንጻርና እና የሰውን ባሕርይ ሙሉ ገንዘቡ አድርጎ መውሰዱን የሚያስገነዝቡን ቃላት ናቸው [ተወለደ፣ ሥጋ ሆነ፣ የባሪያን መልክ ያዘ፤ በሰው አምሳል ሆነ፤ በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ…]።
ሁለተኛው መደብ ደግሞ ከሞላ ጎደል፣ ሰው ከመሆኑ በፊት ስለ ነበረው ቅድመ-ሕላዌ የሚያስገነዝቡን ቃላት ናቸው [ከሰማይ ወረደ፤ ራሱን ባዶ አደረገ፥ ተገለጠ፣ በመካከላችን አደረ…]።
ሦስተኛው መደብ ደግሞ የመወለዱን ዓላማ የሚያስገነዝቡን ቃላት ናቸው [ተላከ፣ መጣ…]። እነዚህ “ለምን ተወለደ?” የሚለውን ጥያቄ ይመልሳሉ። ይኽም ነገረ-ትሥጉትንና ነገረ-ድነትን የተያያዙ መሆናቸውን ያሳዩናል።
► ተወለደ [τίκτω , γεννάω)
___“መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና (Lk 2:10–11)”
በየገናው የለመድነው ዕይታ “በግርግም የተኛ” ሕፃን ነው። ይህ በርግጥ አስደናቂ እውነት ነው። ለዘመናት የሚጠበቀው የምሥራች ቃል አሁን ታወጀ። ደስ ይበልሽ ምድር፣ ምክኒያቱም የዓለም መድኃኒት የሆነ “ሕጻን“ እርሱም የዳዊት ልጅ ክርስቶስ ተወልዷልና። የንጋት ጎህ ቀደደ። ተስፋው ተገለጠ።
በመጀመሪያ ይህ “ተወለደ” የሚለው ቃል አስረግጦ የሚያሳየን፣ የሕጻኑ መወለድ በአንድ እጅ አስቀድሞ እግዚአብሔር ከሰጠው የድነት-ታሪክ ፍጻሜ ጋር መያያዙን ነው። ለዚህ ነው በሉቃስ ወንጌል ላይ ከክርስቶስ መወለድ ጋር ተያይዞ “ተስፋው-ተፈጸመ” የሚለው እሳቤ እንደ አዝማች የሚደረደረው።
- የማርያም መዝሙር [ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው (Lk 1:55)]
- የዘካርያስ ትንቢት [ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው..ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ Lk 1:72–73]
- የስምዖን ባርኮት [ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና]፤
- ነቢዪቱ ሐና ስብከት [የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች]፡፤
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ «ተወለደ» የሚለው ቃል ኢየሱስ ፍጹም ሕፃን ልጅ መሆኑን ያሳየናል “በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት” ማደግ ያስፈልገው ነበር። በሰው ስም “ኢየሱስ” ተብሎ ተሰይሟል። ትውልዱ በዳዊትም ቤት ተቆጥሯል። እንደማኛውም ሕጻን ጡት ጠብቷል፤ ፊደል ቆጥሯል፤ ተርቧል፤ አልቅሷል…። ሕጻኑ ለአደጋ ግሉጥ ከመሆኑ የተነሳል፤ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ይዞት ሊሰደድ የተገባ ነበር። የማይወሰነው አምላክ ተወሰነ። ይህ ሕጻን በአንድ እጅ እንደማንም ሕፃን ልጅ፣ ሕፃን እንደ ነበር፤ ደግሞም በሌላ እጅ ‘ልዩ-ሕጻን፣’ ይህም “መለኮታዊ” መሆኑን በውጥረት ማቴዎስ ሲያሳየን “የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነው…እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” ይላል። ይህ ሕጻን ሰው ብቻ ሳይሆን “አዳኝም” ጭምር ነው። ሉቃስ ደግሞ ይህንን ውጥረት “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” በማለት ሕጻኑን “የእግዚአብሔር ልጅ” ይለዋል [መሲሃዊ ስያሜን ባለፈ መልኩ]።እንዴት ሁለቱ በአንድጊዜ እውነት ሆኑ? “ሚስጢር! ሚስጢር!” ብለን ከመጮህ የዘለለ እውቀት የለንም።
► ሥጋ ሆነ [γίνομαι]
___“ቃልም ሥጋ ሆነ…”
የዮሐንስ ወንጌል፣ እንደ ማቴዎስ አሊያም እንደ ሉቃስ በውስጡ “የልደት” ትረካ አናገኝም። በዮሐንስ ሕፃን ሲወልድ አናይም። የምናገኘው “ቃል” ከተሰኘና ቅድመ-ሕላዌ ካለው አካል ጀምሮ ወደ ነገረ ትሥጉቱ የሚሄድ እንቅስቃሴ ነው። ይህ ከላይ-ወደታች የሚሄድ የአተራረክ ዘዬ፣ ዮሐንስን ከሌሎቹ ወንጌላውያን ይለየዋል። በቅድመ-ትሥጉት ማንነቱ፣ ቃል ‹ነበረ» ይለናል። የሚጠቀመው ‹ሆነ› የሚለውን የመሆን-ግሥ፣ ይኽም “በመጀመሪያ ቃል የሆነ፤ እግዚአብሔር የሆነ…”፣ ሳይሆን “ነበር” የሚለውን የመሆን-ግሥ ነው። ይኸውም “በመጀመሪያ ቃል ነበረ…ቃልም ከእግዚአብሔርም ጋር ነበረ…ቃልም እግዚአብሔርም ነበረ።” ነበር…ነበር…ነበር! ሆኖም ግን ቁጥር 14 ላይ ሲደርስ፣ ዮሐንስ የመሆን ግሡን ከነበረ-ወደ-ሆነ ይለውጣል። “ቃልም ሥጋ ነበረ» ከማለት ይልቅ “ቃልም ሥጋ ሆነ” ይላል። ሆነ…አደረ። ይህ አስረግጦ የሚያሳየን «ቃል» በሁለት መደብ በአንድ ጊዜ የሚመደብ መሆኑን ነው። ቃል በመለኮት መደብ ይኖራል። እርሱ አማክሎተ-ፍጥረት ነው [agent of creation]፤ አማክሎተ-ድነት ነው[agent of redemption]፤ ቃል አማክሎተ-አስተርዮ ነው[agent of revelation]። ቃል ደግሞ ከዚህ ቀደም “ያልነበረውን” ነገር ወሰደ “ሥጋ ሆነ”። እንቅስቃሴውን እንመልከት። በቁ.1 ላይ “እግዚአብሔር” የሚለውን ቃል ዮሐንስ በሁለት ዓይነት መንገድ ይጠቀመዋል። አንድ አብን የሚወክል የመለኮት-አካል ስም ሆኖ ጥቅም ላይ ውሏል፦ ‘ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበር’ እርሱም አብ ነው። ደግሞም “እግዚአብሔር” የሚለው ቃል የመለኮት ባሕርይን ገላጭ ሆኖም ጥቅም ላይ ውሏል፦ ‘ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።’ ስለዚህ ይህ መለኮታዊ ባሕርይ ገንዘቡ ሆኖ ይኖር የነበረው፣ እንዲሁም መለኮታዊ ከሆነው ከሌላኛው አካል ፊት-ለፊት ሕልው ሆኖ ይኖር የነበረው ቃል፣ መለኮታዊ ባሕርይውን ሳይለቅ፣ ከዚህ ቀደም ያልነበረውን “ሰብዓዊ ባሕርይ” ገንዘቡ አደረገ። እንቅስቃሴው ከላይ ክምጡቅ ሕልውናው ይጀምርና ወደ ምድር ሰብዓዊ ማንነቱ ይሄዳል። ቃል “ሥጋ” አልመሰለም [merely appear to be human]። ቃል ሥጋ ሆነ! [the Logos took a fully human nature (flesh) . Thus, John retells the story of incarnation, not with the idea of ‘begetting’ [birth], but with the idea of ‘becoming’. The Word became a human being] ይህ አቅጣጫ በዮሐንስ ትረካ ኋላ እየዳበረ ይመጣል። ይህ ሕይወትና ብርሃን የሆነው ቃል (ዮሐ. 1፡4-5)፣ ሥጋ ሆኖ ተገልጦ (1፡14)፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር በተለይ በመስቀል ሞቱ ተርኮልን (፫፡፩፮)፣ ወደ ነበረበት ክብር ይመለሳል። እግዚአብሔር ሕይወት፤ ብርሃን፤ ፍቅር ነው። የፍቅሩ፤ የሕይወቱና የብርሃኑ መገለጫ ሞገድ፣ የክብሩም መንጸባረቂያ ሥፍራ ‘ትሥጉቱ’ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው።
ዮሐንስ የክርስቶን ልደት «ተወለደ» በሚለው ቃል ሳይሆን «ሆነ» በሚለው ስለተረከልን፤ ነገረ-ትሥጉቱን ከሌላና ከምጡቅ ገጽታው አንጻር እንድናይ ረድቶናል።
ስለ ልደቱ (ስለ ገና) ስናስብ በግል በአምልኮ ሰዓት ይሁን በመዝሙራችን፤ በስብከታችን እንዲሁም በአስተምህⶂችን የፋፋና የዳበረ ነገረ-ትሥጉት እንዲኖረን ይረዳን ዘንድ ነው።

