
ባሮክ ምን ጠይቆ ይሁን (ኤር. 45:5)?
וְאַתָּ֛ה תְּבַקֶּשׁ־לְךָ֥ גְדֹל֖וֹת אַל־תְּבַקֵּ֑שׁ כִּ֡י הִנְנִי֩ מֵבִ֨יא רָעָ֤ה עַל־כָּל־בָּשָׂר֙ נְאֻם־יְהוָ֔ה וְנָתַתִּ֨י לְךָ֤ אֶֽת־נַפְשְׁךָ֙ לְשָׁלָ֔ל עַ֥ל כָּל־הַמְּקֹמ֖וֹת אֲשֶׁ֥ר תֵּֽלֶךְ־שָֽׁם׃
► ❝አንተ! ለገዛ ራስህ ታላላቅ ነገሮችን ትፈላልጋለህ? (ወይም ታላላቅ ነገሮች የምትመኝበት ጊዜ ነውን?) እነሆ እኔ ክፉ ጥፋት በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ እያመጣሁ ነውና እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን አትፈላልግ!” ይላል ኧዶናይ (ያህዌህ)። ይልቁንስ በእነዚያ በምትሔድባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ላይ የገዛ ሕይወትህን እንደ ምርኮ አድርጌ ለራስህ እሰጣለሁ።❞ [የራሴ ትርጉም]
► Paraphrase: ❝ጊዜው አስጨናቂ የፍርድ ሰዓት በሰው ሁሉ ላይ እያመጣሁ መሆኑን እወቅ። ሕይወትህን አተርፋታለሁ፤ ስለዚህ የምትፈልገው ትልቅ ነገር ይህ ይሁንልህ እንጂ ሌላ ትልልቅ ነገሮችን ለራስህ አትፈላልግ! ይላል እግዚአብሔር❞ [የራሴ ትርጉም]
የM.Div. ተማሪ ሳለሁ ስምንት የቋንቋና የፍታቴ በግሪክና በእብራይስጥ መውሰድ የግድ ነበረብኝ። ከእነዚያ ክፍሎች አቅብጦኝ የተመዘገብኩት የኤርሚያስን መጽሐፍ ለማጥናት ነበር። መቼም የኤርሚያስን እብራይስጥ ከመተርጎም ድንጋይ በ32 ጥርሶቼ ብግጥ የሚቀል ነበር የመሰለኝ (በተለይ የኤርሚያስ ፈሊጣዊ አነጋገሮች)። ሆኖም ግን ደግሞ የኤርሚያስን የትንቢት መጽሐፍ ወደ እንግሊዝኛ ስንተረጉም፤ እኔና አብረን የምናጠና ጓደኞቼ ያስተዋልነው ብዙ ነገሮች ነበሩ። ከእነዚህ አንዱ እና እስከ ዛሬ ድረስ ከልቤ አልጠፋ ያለኝ ኤርሚያስ 45ን ስተረጉም በላዬ ላይ የወረደው ድንጋጤ ነበር። ምንም እንኳ ጥቂት ዓመታት ቢያልፉም፤ እስከ አሁድ ድረስ ያ ስሜት ከልቤ አልጠፋም “ለገዛ ራስህ ታላላቅ ነገሮች ትፈላልጋለህ?” የሚለው የያህዌህ ጥያዌ!
ባሮክ ምን ጠይቆ ይሁን ያህዌህ እንደዚህ ዓይነት መልስ የሰጠው?
መልሱ ምናልባት በ45፡1 እና 45፡3 ላይ ሳይገኝ አይቀርም።
❝ኤርምያስ በቃል የነገረውን ባሮክ በብራና ላይ ከጻፈ በኋላ፣ ነቢዩ ኤርምያስ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ የተናገረው ይህ ነው… ‘እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ሐዘን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ፤ ከልቅሶዬ ብዛት የተነሣ ደክሜያለሁ፤ ዕረፍትም የለኝም’ ብለሃል❞ (አ.መ.ት.)
ዓመቱ 604 ዓ.ዓ. ነው። ባሩክ በኤርሚያስ ሥር ከማገልገሉ ከ100 ዓመታት በፊት የምናሴ (687-642 ዓ.ዓ.) እኩይ ተግዳሮት የይሁዳን ዕጣ ፈንታ አስቀድሞ ወሰነ (ኤር. 15:1-4)። ሆኖም ግን በፈንታው በ8 ዓመቱ የነገሠው ኢዮስያስ (640-609 ዓ.ዓ.) ለመጨረሻ ጊዜ እ/ር ለይሁዳ የሰጣት እድል ነበር፤ (ከእርሱ በኋላ የተነሱት ነገሥታት በሙሉ የምናሴን እኩይ ተግባር ወደ ፍጻሜ እንዲገሰግስ ያደረጉ ብቻ ነበሩ (2ነገ. 23/ 2ዜና 34)። የኢዮስያህ መንፈሳዊ ተሐድሶና የተሐድሶው ጥሪ አንደምታ እስከ ሰማርያ ድርስ እንኳ አንጎድጉዶ ነበር። ሆኖም ምንም እንኳ ኢዮስያስ ታላቅ መንፈሳዊ ተሃድሶ በይሁዳ ህዝብ መካከል ቢያደርግም፤ በሚቀጥሉት ግማሽ ምዕተ-ዓመታት ግን ከ40 ዓመታት በፊት የተፈጸመው የምናሴ ሐጥያት ሥር ከመስደዱ የተነሳ፤ ከላይ ከላይ የሆነ መንፈሳዊ ተሃድሶ እንጂ ሥር ነቀል መንፈሳዊ ለውጥ አላመጣም። በውስጥ ውስጡ የህዝቡ ልብ ኪዳን አፍራሽ የሆነ እኩይ ተግዳሮቱን እስከ ባሮክ ዘመን ድረስ ቀጥሎበት ነበር። ባሮክ የኤርሚያስን ትንቢት ከመጻፉ ከ1 ዓመት በፊት ደግሞ የግብጽ ፈርዖን ኒካዑ በካርከሚሽ የባቢሎንን ሠራዊት ሊገጥም ተነስቶ ነበር። የዚህ ጦር አዛዥ ስም ናቡከደነጾር ይባላል። አባቱ ናቦፖላሳር በጠና እንደታመመና ኋላም እንደ ሞተ ስለሰማ ከጦር ሜዳ ወደ ባቢሎን ተመልሶ “ታላቁ ንጉሥ ዳግማዊ ናቡከደነጾር” የሚል ስያሜ አግኝቶ ለሁለተኛ ጊዜ በ601 ዓ.ዓ. ደግሞ ይመለሳል። የዚህን ጊዜ ያህዌህ በነብዩ ኤርሚያስ እና በባሮክ ጸሐፊነት ሲያስጠነቅቃት አልሰማ ያለችው ይሁዳ የመጀመሪያ “የምርኮ ፍርድ” ትቀምሳለች (ዳንኤል እና ወጣት ጓደኞቹ ከጥቂት ሹማምንት ጋር ወደ ባቢሎን ይጓዛሉ)። ይህ ሲሆን ሳለ በዙፋን የተቀመጠው የይሁዳው ንጉስ “ኢዮአቂም” ነበር። በዚህን ጊዜ ባሮክ ለኢዮአቄም እንዲነበብለት በብራና ከኤርሚያስ አፍ እየተቀበለ እየጻፈ ነው (ኤር. 36:1-8)። የይሁዳው ንጉስ ኢዮአቂም የኤርሚያስን መጽሐፍ በሚያስገርም ድፍረት እየቀደደ ቁርጥራጩን ወደ እሳት ውስጥ ይጨምር ጀመር! ፍርዱን አፈጠነ። ከንጉሱ ልብ ድንዳኔ የተነሳ በ597 ዓ.ዓ. ላይ ንጉሱ በባቢሎን ላይ ያምጻል፤ የናቡከደነጾርም ሠራዊት በቁጣ ኢየሩሳሌምን ይመሽጋታል። በዚህን ጊዜ ውስጥ ኢዮአቄም ተገድሎ በፈንታው ለሦስት ወር ብቻ ዮአኪን ይነግሳል። ለሦስት ወር ኢየሩሳሌም ከተመሸገች በኋላ ንጉሡ ዮአኪን ይማረካል። አብሮ ወደ 10ሺ የሚጠጋ ሕዝብ 700 ማይልስ በእግር ወደ ኒፑር አቅራቢያ ወዳለው ኮቦር ወንዝ እንዲሰፍሩ ይደረጋል። ከእነዚህ መካከል የ25 ዓመት ወጣት የሆነው ሕዝቅኤል ይገኝበታል። (ይህ የመጀመሪያው ምርኮ ይባላል)። በዮአኪንም ፈንታ ናቡከደነጾር አሻንጉሊት ንጉስ አድርጎ ሰዴቅያስን ሾመው። ሆኖም ሰዴቅያስ አሁንም አመጸ። በስድሳዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ ያለውን የነብዩ ኤርሚያስን ማስጠንቀቂያ ሆነ ከወንዝ ማዶ ላለፉት 7 ዓመታት መተንበይ የጀመረውን የወጣቱን ሕዝቄል ወዮታ ማንም አላደመጠም። የያህዌህ ትዕግሥት አለቀ። የፍርድ ጽዋ ሞላ። ስለዚህ ናቡከደነጾር ሙሉ ሠራዊቱ ይዞ ኢየሩሳሌምን ከበቧት (2 ነገ. 25:1-3)። ከበባው ለ18 ወራት በመቀጠሉ (አንድ ዓመት ከግማሽ፤ ከጥር 15, 588 እስከ ሰኔ18, 586 ዓ.ዓ.) የተመሸጉት የኢየሩሳሌም ኗሪዎች በረሃብና በበሽታ ማቀቁ (ኤር.37:21; ሰቆ. 2:4)። በመጨረሻም በ586 ዓ.ዓ. የኢየስሩሳሌም ቅጥሮቿ ተናዱ፤ የሰለሞን ቤተ/መቅደስ ፈራረሰች። ያህዌህ ርስቱን አሳልፎ ሰጠ። በደም የረሰረሰችው ይሁዳ፤ በፍትህ መጓደል የድሆች ጩሀት ይሰማባት የነበረችው ኢየሩሳሌም፤ በባዕድ አምልኮ ኪዳንን ባፈረሱ ህዝቦቿና መስፍኖቿ የረከሰችው የያህዌህ ምድር “የሰንበት እረፍት አገኘች” (2 ዜና 36:21)። ሕዝቅኤል ሲናገር ከዚህ በኋላ ተስፋው ወደ ፊት ነው “ያህዌህ ሻማ፡ እግዚአብሔር በዚያ ነው”።
ስለዚህ ባሮክ በዚህን ዘመን ውስጥ ነው “ስለ ታላላቅ ነገር ፍላጎቱን” ለያህዌህ ያሳወቀው። ኤር. 45:1-3 እንደሚያሳየን፤ ፍላጎቱንም የገለጸው ለኢዮአቄም የሚላከውን ደብዳቤ ጽፎ ከጨረሰ በኋላ ነበር። ባሮክ “በቃኝ እስከመቼ!” በሚል ምሬት ውስጥ ያለ ይመስላል። አንዳንድ ዘመናት አሉ፤ ከጌታ ዘንድ ትልልቅ ራዕይ እና አገልግሎት ብንጠይቅ መልካም የሚሆንበት። ለምሳሌ ❝“ማንም ኤጲስቆጶስነትን ቢፈልግ፣ መልካም ሥራን ይመኛል❞ ይላል። አንዳንድ ዘመናት ደግሞ አሉ “አስጨናቂ” የሆኑ ዘመናት። በዚህ ዓይነት ዘመን ውስጥ “ስማችን ይቅር”፤ “ዝናችን አፈር ይግባ”፤ “ለክብርህ ታላቅ ሰው አድርገኝ” የሚለው ጸሎት ቀርቶ “እባክህ ስለ ስምህ ቅና” ብቻ ተገቢ የሆነበት። ለምሳሌ ያህል ብዙ ጊዜ በሐዘን ቤት ውስጥ ለማጽናናት የመጣው ታዳሚ ወሬውን እያጦፈ ሳቅና ጨዋታው ሲደራ የሚሰቀጥጠን ሐዘንተኛው ሳይስቅ መሳቅ ተገቢ ስላይደለ ነው።
ኤርሚያስ 45ም ይህ ያለንበትን ዘመን በብዙ መንገድ ይመስላል። በእንዲህ አይነቱ ዘመን፤ በስማችን ፊት የማዕረግ ዓይነት ማንጠልጠል ተገቢ የማይሆንበት፤ ምሁር እከሌና ሊቅ እከሌ መባልን የማንፈልግበት፤ “ትልልቅ ሹመት ለራሳችን” መፈለግ ነውር የሚሆንበት ዘመን ነው። ባሮክ ለራሱ እንደ ኤርሚያስ ያለ ታላቅ ነብይ መሆን የፈለገ ይመስላል።ምን አልባት ምሬቱ ያተኮረው፤ “እንደዚህ መከራ አብሬው እየተቀበልኩ እውቅና እንኳ የማይሰጠኝ እከመቼ ነው?” “ሁለተኛ መሆን እስከመቼ?” “ምክትል አከሌ መባል እስከመቼ?” ሊሆን ይችላል። እርግጠኛ ባንሆንም፤ ሆኖም ግን የባሮክ ምሬት በእነዚህ ዙሪያ እንደሆን ብዙ ሊቃውንት ይስማማሉ። ባሮክ ከመኳንንት ቤተሰብ የተወለደ ነው። ቅድም አያቱ ‘መሕሤያ’ በኢዮስያስ ዘመን በተሐድሶ ሥራ ላይ ትልቅ ሚና ነበረው (2 ዜና 34:8/ ኤር. 32:12)። ስለዚህ ባሩክ ትልቅ ነገር ለራሱ መፈለጉ አይገርምም። ሆኖም ግን ባሮክ የኖረበት ዘመን፤ ነገር የሚፈራርስበት አስጨናቂ ዘመን በመሆኑ በያህዌህ ፊት ሰው የሚዋረድበት እንጂ ሹመት የሚፈለግበት ዘመን አልነበረምና ነው። ምክኒያቱም ፈረስ ከሠረገላ በኋላ እንጂ ሠረገላ ከፈረሱ ሲቀድም ትርጉም የለውም። ልክ እንዲሁ ያህዌህ የተከለውን በሚነቅለበት በፍርድ ሰዓት ላይ ስለ ራስ ትልልቅ ነገር መጠየቅ ተገቢ አይደለም። በሁለተኛ ደረጃ ግን፤ ይህ ግሳጼ ለባሮክ የማጽናኛም ቃል ጭምር ነው። ያህዌህ “በታማንነት ያገለገልከኝ ትጋት አልረሳም! ከሚመጣው ሰይፍ አድንሃለሁ፡፤ በሔድክበት ሥፍራ ሁሉ ካንተ ጋር እሆናለሁ፤ አተርፍሃለሁ” ይለዋል። መቼም ታሪካዊውን ዳራ ከያዝን ይህ ትልቅ ተስፍ ነው። የባቢሎን ሰይፍ ያልሰየፈው የአይሁድ አንገት (በሽሽት ላይ ያለ) በሌለበት፤ አድንሃለሁ የሚል ተስፋ ታላቅ ነው። ኋላም ከኤርሚያስ ጋር ወደ ግብጽ ወርዶ፤ ደግሞም የአይሁድ ታሪክ እንደሚናገረው ባሮክ ከግብጽ ሆኖ የኤርሚያስን ሠነድ በማደራጀት ኋላም ወደ ባቢሎን ድረስ ተጉዞ ከወንድሙ ከሠራያ ጋር (አስቀድሞ ሠራያ ወደባቢሎን እየተጓዘ መልክት ያደርስ ነበር (ኤር. 51፡59-64))። የኤርሚያስ ትንቢቶችንም በአንድ ጥቅል እንዲጠረዝ ሚና ተጫውቷል። እንደ ኤርሚያስ ሠነድ ጠበብት አስተያየት ከዕዝራ በኋላ የተነሳው የይሁዲ ጸሐፍት ሥራ የብሉይ መጻሕፍትን የመጠረዝ ሥራ ማጠናቀቅ ነበር። ኋላም “ለመዞራ” ለተሰኙ አይሁድ አሁን ያለንን የኤርሚያስ መጽሐፍ እንድናገኝ ምክኒያት ሆኗል ማለት ነው።
ስለዚህ እንደ ባሮክ ለራሳችን ትልልቅ ነገሮችን መፈለግ ትተን፤ ይልቁንስ በአንድ ላይ ተረባርበን “ማዕክሎተ-ክርስቶስን ወደ ክርስትና” የምንመልስበት ይሁንልን። በርግጥ “ትልልቅ ሥፍራን” ለራሳችን የምንፈልግበት ዘመን አለመሆኑን ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሁላችን ማዕረጋችንን ለጥቂት ጊዜ ወደ ጎን እንድናደረግ እ/ር ይርዳን፤ ይልቁንስ በትህትና “ክርስቶስ ሥፍራውን አጥቶ ሹመቴ ይቅር፤ በፈንታው እንደ ወንድም አናግረኝ…ምንድር ነው ማስተካከል ያለብን” ማለት ይሁንልን። ሐይላችንና ጉልበታችን ቅዱስ ቃሉ ማዕከላዊ እስኪሆን ድረስ፤ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ቃሉ መሠረት ተሐድሶ እስኪመጣላት፤ ማዕክሎተ ክርስቶስ በሁለንተናችን እስኪመለስ ድረስ ከፍ ያለው ዝቅ ቢል፤ ዝቅ ያለው እዚያው አፈር ውስጥ ቢደፋና (ሰቆ. 3፡29) ተሐድሶን ከአብ ዘንድ በክርስቶስ አማካኝነት በመንፈሱ በኩል እንዲፈስልን ብንማጸን በጣም መልካም ነው። አውቃለሁ የተለያየ ቤተ እምነት ውስጥ ስላለን ቀላል ነው የማይባል የአስተምህሮት ልዩነት እንዳሉን አልዘነጋሁም። ደግሞም ማዕከላዊ የሆነ እና ሕይወት የሚገኝበት መሠረታዊ እውነትንም እንደምንጋራ ደግሞ አውቃለሁ (1 ጢም. 1:15)። ይህ ማዕከላዊ የሆነ፤ ነገር መለኮታዊ እና መሠረታዊ እውነት ነው ጦርነት የተከፈተበት። ስለዚህ ተያይዘን መልካሙን ተጋድሎ እንጋደል። ከዚያ ሁላችን ወደ የቤቶቻችን!
ሐዋርያት 20:24
“ይሁን እንጂ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት”
የባሮክ ዘመን ምን ይመስል ነበር? ታሪካዊ አውዱ
ከላይ የሰጠሁት በጣም አጭር ታሪካዊ ትንታኔ ለሕዝቅኤል መጽሐፍ ታሪካዊ ዳራ ካዘጋጀሁት የወሰድሁት ነው። ለባሮክ ያህዌህ ለምን እንደዚያ አይነት መልስ እንደመለሰለት ለማየት ይህ ታሪካዊ ዳራ ማወቅ ተገቢ ነው። ወደ ፊት የሕዝቅኤል መጽሐፍ ስናጠና በሰፊው እንዳሥሣለን

