
በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት ያለ ዐደራ
(1 ጢሞቴዎስ 6:12-16)
በጣም ብዙ እያሰብኩበት ያለ ጉዳይ፤ ደግሞ ለረጅም ጊዜ የምጸልይበት ርዕሰ-ጉዳይ፤ ቤተክርስቲያን እና አማኞች የአስተርዕዮ ተርካቢዎች (መገለጥ) እና ባለአደራዎች መሆናችንን እንድንረዳ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ አስተርዕዮ የቀረጸው ሕዝብ እንደሆነ ሁሉ ይህንንም መገለጥ ለመጪው ትውልድ አስተላላፊ አካል ነው። በመከራ፤ በሥደት፤ በጅራፍ የጎረባበጠው ሰውነቱ እና በወህኒ እስር እንዲሁም በብርድ ስቅይት ያለው ሽማግሌው ጳውሎስ፤ ለሊት እንቅልፍ የነሳው ጉዳይ የእግዚአብሔር ሕዝብ እና ተተኪ መሪዎች ይህን አደራ ተረድተውት ይሆን? የተቀበሉትንስ እንደተቀበሉትስ ያስተላልፉት ይሆን? የሚል ይመስላል።
[su_pullquote]”መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት፥ በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ፤ ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል (1 ጢሞ. 6:12–15)[/su_pullquote]
እጅግ አስገራሚው ጉዳይ ጳውሎስ አገልግሎትህን ስትወጣ፤ በውጥረት ውስጥ ሁን ይለዋል። በአንድ እጅ “በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት መልካሙን መታመን በመሰከረ” ሲለው ጢሞቴዎስ ወደ ኋላ ዞር ብሎ በግራ እጁ የተቀበለውን “ምስክርነት” እንዲይዝ ሲሆን በቀኝ እጁ ደግሞ ተዘርግቶ “እስኪገለጥ ድረስ” ይህንን ትዕዛዙን ጠብቅ ይለዋል። በርግጥ እውነተኛ አገልግሎት ምልክቱ እነዚህ ሁለት ውጥረቶች ያላረገበ እንደሆን ተረድቼያለሁ። ባየነው ‘ራእይ’ ብዙ የምንመካ ሰዎች የግራ እጃችንንውጥረት አርግበነዋል። ጥሪያችን ከአብ ዘንድ ተልኮ “ስለ እውነት” የመሠከረውን የወልድን ምስክርነት መመስከር እንደሆን ረስተናል። የራሳችን መስካሪዎች ስለሆንንም ምስክርነታችን ውሸት ነው። የቀኝ እጃቸውን የረሳን ደግሞ ነገራችን ሁሉ የኋሊት ብቻ ነው። የሚያስገርመው ነገር ጳውሎስ “ኢየሱስ ታማኝ ምስክር/μαρτυρήσαντος” እንደሆነ አንተም ታማኝ ‘መስካሪ’ ሁን ሲለው ሁሉን በሕይወት ሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት እና በጌታ ኢየሱስ ፊት ነው። ታማኝ የመሆን ግዴታችን የመነጨው አገልግሎታችን “በአብና በወልድ” ፊት ስለሆነ ነው። ይህ ጥሪ ኢየሱስ በግርማው ቀኝ ተቀምጦ፤ “እኔ ከአባቴ የተሰጠኝን ‘ምሥክርነት መስክሬ ወደ ክብር መጥቻለሁ…አንተስ እኔ የመስከርሁትን ያንኑ ምስክር መስክረሀው ወደ እኔ ትመጣለህ?” የሚል ጥሪ ይመስላል።
ይህ “መታመን/ὡμολόγησας” በአዲስ ኪዳን ላይ “የተቀበልነውን እውነት እውነት እንደሆን ማመን፤ በሕይወታችን መግለጥና መመስከርን ያሳያል። ለምሳሌ ያህል እስኪ 1 ጢሞ. 1:3-4 እንመልከት።በ1ኛ ጢሞቴዎስ ላይ
“ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥…ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና *በእምነት ግን ላለ መጋቢነት* አይጠቅሙም [οἰκονομίαν θεοῦ τὴν ἐν πίστει] (1 ጢሞ.1:4.)” ይለዋል።
እነዚህ “እምነትና መጋቢነት/πίστει – οἰκονομίαν ” የሚሉት ቃሎች በነገረ-ጳውሎስ ሰፊና ጥልቅ ምልከታ አሏቸው።
በእምነት ላለ (ἐν πίστει)
በሐዋርያው ጽሑፍ ላይ እምነት ሁለት አይነት ገጽታ አለው። በመጀመሪያ አማኙ እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካኝነት በፈጸመው ሥራ ላይ ያለውን መታመን ያመለክታል። ይህም ልባዊ-አጸፋ ወይም ምላሽ ነው (a subjective appropriation of the truth or outworking/ response)። ሆኖም ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ፤ አንደ የአውዱ፤ ‘እምነት’ የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ ‘የእምነትን መንገድ’ (እምነትን የሚወልደው አስተምህሮ/ an objective body of truth) ወይም በቀደመው ትርጉማችን ላይ “ሐይማኖት” ተብሎ ተተርጉሟል። “እምነት” የሚለው ቃል ሁለተኛውን ትርጉም እንዲያንጸባርቅለት ሲፈልግ ጳውሎስ የሚጠቀመው ስዋስዋዊ ቅርጽ፦ “ሶስተኛ ንብረት” ወይም “dative case” የተሰኘውን ነው። በተለይ ደግሞ ከውስን ምስተአምር ጋር አብሮ በሚቀርብ ጊዜ ( ἐν τῇ πίστει/ ‘in the faith’) ። ለምሳሌ እነዚህን እንድታነቧቸው አበረታታለሁ፦ 1 ቆሮ. 16፡13; 2 ቆሮ. 13:5; ፊል. 1:27; ቆላስያስ 1:23; ቆላስያስ 2:7; 1 ጢሞ.1:2; ጢሞ. 2:7; ቲቶ 1:13።
ስለዚህ ይህ “የእምነት” ነገር ‘ግላዊ /subjective’ ባሕርይ ብቻ ሳይሆን “ነባራዊ/ objective” ገጽታም አለው። ይህም በጥንቃቄ እንደተቀበልን ማስተላለፍን ይጠይቃል። እምነትና ሕይወት የሚገኝበት ስለሆነ። ለዚህ ነው ሐዋርያው እርሱና መሰል ሐዋርያቱ የሚያስተምሩትን እውነት “ወግ” ብሎ የሚጠራው (2 ተሰ. 2:15)። ይህ “እምነት/ሃይማኖት” ቤተክርስቲያን የምትሰብከው “የእምነት ቃል” እንዲሁም በሰሚዎቹ ልብ ውስጥ እምነት ወላጅ ነው። ይህ “እምነት/ሐይማኖት” የእግዚአብሔር ሕዝብን የሚቀርጽ፤ ከአብ ወደ ወልድ፤ ከወልድ ደግሞ ወደ መንፈስ ቅዱስና ወደ ሐዋርያቱ የተላለፈ ቃል/ትምህርት ስለሆነ አይፋለስም፤ አይበረዝም። ስለዚህ ይህንን እምነት (እውነት) የመጠበቅ ግዴታ አለብን። መቼም መታረም የሚገባውን አረም አስወግዶ ስንዴውን ማስቀረት ጥበብን ስለሚጠይቅ ይሁን አይሁን ባላውቅም (“ጅዋ ጅዌ” መጫወት ይቀላል አይደል)፤ ሐይማኖት የሚለውን ጠቃሚ ቃል ይሀው ድምጥማጡን አጠፋንና ተቸገርን። ሐይማኖተኛ የሚለው ቃል በዘመናችን አሉታዊ ትርጉም አለው። በርግጥ እስማማለሁ ከጌታ ጋር ያለን ሕይወት በዘልማድ ብቻ የምናደርገው ተራ ተግዳሮት እንዳልሆነ። ሆኖም ግን ለመታረድ እንደሚነዳ በግ፤ “ሐይማኖት” የሚለውን ቃል መሰዋታችን ግን ትልቅ ስህተት ነው። ይህንን ያሉት እነማን እንደሆኑ ና ለምን እንዲያ እንዳሉም ታሪካዊ የሆነ አውድ አለው። በአውድ ውስጥ ስንመለከተው ‘ቅናታቸው’ መልካም ሆኖ ሳለ፤ ነገር ግን መንፈሳዊነት “ግላዊና ቅጽበታዊ” ነው ብሎ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን እውነት ግን መሰዋት ይኸው አሁን ያለንበት ጣጣ ውስጥ የከተተን ይመስለኛል። ግን ብናስብበት እኮ፤ ይህ አሁን ያለንበት ዘመን፤ “ሁሉ በገዛ አይኑ እንደመሠለው መንፈሳዊነት እንዲህ ነው” ወደ ማለት ጣጣ ውስጥ የገባነው እኮ ይህንን የእምነትን ገጽታ ስላጠፋ ነው ይመስለኛል (everything is subjective)። ማን ይዳኘን? ማን የማንን መንፈሳዊነት ሊዳኝ ብቃት አለው? እንዴት በእኔ ልምምድ ሌላውን ልዳኝ? ወይም በራሴ መረዳት ሌላውን ልዳኝ እኔ ማን ነኝ? በቅዱሳት መጻህፍት ላይ የምናገኘው መንሳዊነት ግን “ከአብ-ወደ-ክርስቶስ-ወደሐዋርያቱ” በመወራረድ የተሰጠ ሕይወት ነው።
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ መንፈሳዊ ሕይወት “የተላለፈ ሕይወት ነው”። ይህ አሁን በሕይወታችን እውን እየሆነ ያለው ሕይወት፤ የዛሬ 2 ሺህ ዓመት በፊት “በእርሱ ዘንድ ሕይወት ነበረች፤ ሕይወትም ለሰው ልጆች ብርሃን ነበረች…” የተባለለት “እውነተኛውም ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር…ቃልም ሥጋ ሆነ እውነትንና ጸጋን ተሞልቶ በእኛ አደረ…እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ያለው የጌታ ሕይወት ነው። ይህም ሕይወት ያለው ወልድ ወደ ሐዋርያቱ ባስተላለፈልን “የሕይወት ቃል ነው” (1ዮሐ. 1:1)። ስለሕይወት ቃል በመጀመሪያ የነበረውን…ሐዋርያቱ ከኢየሱስ የሰሙትን፤ ያዩትንና እጆቻቸው የዳሰሱትን ክርስቶስንና መልክቱን “እናንተ ከእኛ ጋር ህብረት እንዲኖራችሁ እንጽፍላችኋለን” ይለናል (እኛ የሚለውን ቃል ያስተውሉ (the ‘we’ language in the New Testament letters point to the Apostolic testimony or authoritative message of the gospel))። ወልድ ከአብ “መልእክት” ይዞ መጣ (Jn 3:14, 34; 7:16; 8:26, 28, 38, 40, 43, 47; 12:49; 14:10, 24; 15:15; 17:8, 14; 18:37)። ወልድ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ላከልን፤ እርሱም “ስለ እውነት የሚመሰክር” አካል ነው። የሚመሰክረውም ከራሱ ሳይሆን “አብ-ለወልድ” የሰጠውን መልእክት እስከ አለም ዳርቻ ለማዳረስ ነው። ስለ ሐጥያት፤ ፍርድ፤ ስለ ጽድቅ ይመሰክራል። ወልድ ወደ አባቱ ሲመለስ፤ ወልድ በቃልና በሥራ የፈጸመውን መንፈስ ቅዱስ አሁን በወልድ ስም ወልድን ወክሎ ያንኑ እውነት የሚያብራራ፤ የሚገልጽ፤ የሚመሠክር መንፈስ ነው(1ዮሐ. 4:1-6)። ዮሐንስ ሲመክረን “የእግዚአብሔር መንፈስ እና የስህተት መንፈስ” የሚለዩት በዚህ ነው ይለናል። ይህንን ታሪካዊና መለኮታዊ “የወልድ ምስክርነትና ማንነት” አጽኖት የማያደርግ መንፈስ “ሌላ” መንፈስ ነው። እውነተኛው የክርስቶስ መንፈስ “ክርስቶስ ተኮር” ያደርገናል። ሥራውም የክርስቶስን ተልኮ ያጎላል እንጂ አያድበሰብስም። ኢየሱስ ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ሥር የሚሰሩ “ሐዋርያትን” መርጦ የእርሱ አፍ አድርጎ ላካቸው፤ “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ” (Jn 15:26–27)።
ስለዚህ ኢየሱስ ወደ አባቱ ካረገ በኋላ የወረደው የክርስቶስ ወኪል የበዓለ ሐምሳው መንፈስ እና ወኪላት ሐዋርያቱ፤ ሥራቸው የወልድን ተልኮ (ይህም የምድር ወገን ሁሉ በአንተ ይባረካሉ የሚለውን የአብርሃምን ኪዳን ሊፈጽም በተላከው እውነተኛ የአብርሃም ልጅ ኢየሱስ) በአራቱም አጥናፋት ማወጅ ነው። ከቤተክርስቲያን አበው አንዱ የሆነው አረናየስ ሲናገር እግዚአብሄር ወልድና እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስ የአብ ሁሉት እጆች ይመሰላሉ “በቀኝ እጁ በወልድ የፈጸመውን ሥራ በግራ በመንፈስ ቅዱስ እጁ ያከፋፍላል። አለ። መቼም ምሳሌ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ሊል የፈለገው ነገር ክርስቶስ በታሪክ የሰራው ሥራ፤ በእኛ እውን የሚሆነው መንፈስ ቅዱስ በግልና በውስጣችን ያንኑ ሥራ እውን ማድረጉ ነው።[1]
ስለዚህ ወንጌል ራሱ “ወግ” ነው። ወንጌል አይፈለሰፍም፤ ወንጌል ግላዊ አደራ አይደለም። በግል አንድ አማኝ በራእይ አይቀበለውም። በሮሜ1፡1-7 ላይ እንደምናየው፤ ወንጌል የአብ ነው፤ ወንጌል ስለ ልጁ ነው፤ ልጁም በሥጋ ከዳዊት ዘር የሆነ ደግሞም በቅድስና መንፈስ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለተሾመው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም ወንጌል በአለም ዙሪያ አሕዛብ አምነው በእምነት ወደ ሆነው መታዘዝ እንዲመጡ፤ ጸጋንና ሐዋርያትን ሰጣቸው። ከላይ የሰጠኋችሁን ቅደም ተከተል አዚሁ ጋር ታያላችሁ። አብ አስቀድሞ በነብያት በቅዱሳት እጻህፍት የሰጠው ተስፍ፤ እውን የሆነው ብልጁ ነው። ይህም ታላቅ ወንጌል የመስበክ አደራ የተረከቡት “ሐዋርያነት” የተሰጣቸው ናቸው። ከዚያ ወደ እኛ በአደራነት ተረክበናል። ጌታ ለሐዋርያቱ አደራ ሰጥቶ የሔደው “የወንጌልን አደራ ነው”። ሐዋርያቱም እንዲሁ አደራ አሳልፈው የሰጡን የወንጌልን አደራ፡ኘው። ይህም ወንጌል መልኩም ይሁን ይዘቱ የማይለወጥ “ወግ” ነው።
“ወንድሞች ሆይ የሰበኩላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁነብት በእርሱም የምትድኑበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወዳለሁ፤ በከንቱ ካላመናችሁ በስተቀር *በምን ቃል* እንደሰበኩላችሁ አሳስባችኋለሁ። እኔ ተተቀበልሁትን (ሐዋርያዊ ምሥክርነት) ከሁሉ በፊት አሳልፌ የሰጥኋችሁ መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጥያታችን ሞተ፤ ተቀበረም፤ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሳ…እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም (ሐዋርያት) እንዲሁ እንሰብካለን (ሐዋርያት) እንዲሁም አመናችሁ (እኛ)” (1 ቆሮ. 15:1-4, 11)
“ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም (ሐዋርያዊ ምሥክርነት) ለእኛ አጸኑት” ዕብ 2:3
ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ 13 በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል” 1 ቆሮ 3:11–13.
የአንድ አገልጋይ አገልግሎት የሚፈተሸው በቀኑ መጨረሻ ላይ ምን ያህል በክርስቶስ መሠረት ላይ (በዚህ አንድ ጊዜ በተመሰረተው) መሠረትን እንደመሠረተ እንጂ “ዝም ብሎ መሠረትን” መመስረቱ ላይ አይደለም። በርግጥ የስንቶቻችን አገልግሎት የእሳት እራት ይሆን? ይህ ሁሉ ድካማችን? ይህ ሁሉ መስዋዕት? ይህ ሁሉ መሰጠት? በምን ያህል ተጋድሎና ጽናት ያቀረብነው አገልግሎት፤ እሳት ቢበላው በርግጥ አያሳዝንም? በክርስቶስ ፊት ግን “አንተ ታማኝ ባሪያዬ” የሚያስብለን፤ ለዚህ መሠረት ያለን ጥንቃቄ ነው። ስለዚህ ለእያንዳንዳችን ይህ ሽማግሌ “በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ” ይለናል።c
ለእግዚአብሔር መጋቢነት (οἰκονομίαν θεοῦ)
በአጭሩ “ምጋቤ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የእግዚአብሔርን እድገተ አስተርዕዮ እና መለኮታዊ ሐሳቡ (ዕቅዱ) በዘመናት መካከል እንዴት እደዘረጋ ነው። ይህ ቃል የቤተሰብ አስተዳደር ዘይቤን ይጠቀማል። በዘመናችንም “ኢኮኖሚ” የሚለው ቃል የመነጨው ከዚሁ ቃል ነው። ስለዚህ ይህ ቃል የሚያመለክተን ‘እግዚአብሔር ለድነትና ፍርድ ያቀደውን ሐሳቡን እንዴት በዘመናት መካከል እንደዘረጋ ወይም እንዳሰራጨው ነው። ልክ አንድ ሰው ደሞዙን ለተለያዩ ፍጆታና ወጪ ወሩን እንዲሸፍን እንዲያማጥን፤ እግዚዚአብሔርም መለኮታዊ ፈቃዱን በዘመናት መካከል ሲያመጣጥን ኖሮ “በዘመን መጨረሻ ግን ልጁን እና መንፈሱን በመላክ ሐሳቡን ተርትሮልናል (ገላ 4:4)። ሐሳቡም “ሐሳቡም በዘመን ፍጻሜ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በልጁ ለመጠቅለል ነው (ኤፌ. 1:10)” ይህ ታላቅ የማዳንና የመፍረድ ፕሮጀችት ከጥንት ጀምሮ የተዘረጋና በክርስቶስ መምጣት ወደ ሙላት የመጣ ነው። ይህንን አሠራር በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገር መለኮት “ሚስጢር/መገለጥ” ይባላል። ይህም የእግዚአብሔር እቅድ ወደ መሆን ሲመጣ ‘ተስፋው-መፈጸም/promise-fulfillment እና ሚስጢሩ-መገለጥ /Mystery-revelation በውጥረት ይይዛል። ስለዚህ በወንጌል በክርስቶስ አማካንነት ተስፋው ተፈጸመ፤ ሚስጢሩ ተገለጠ።
ስለዚህ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ፤ ስለ ሕግ የሚከራከሩ ሰዎች ሕግ በዚህ በእ/ር “የሐሳቡ” ምጣኔ ውስጥ ለተወሰነ ዓላማ እና ለተወሰነ ዘመን ብቻ እንደሆን ስለማያስተውሉ “ስተው፥ የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ፥ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል….በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም” 1 ጢሞ. 1:6–7, 3-4″
በክርስቶስ የተወደዳችሁ ቅዱሳን ሁሉ፤ በተለይ ጌታ ለአገልግሎቱ የጠራን የመጀመሪያ ተግዳሮታችን በየለቱ ይህንን ዘላለማዊ ፈቃዱን ወደ እውነት የመጣበት መንገዱንና አሠራሩን፤ ጥንት የጀመረ ነገር ግን በመስቀሉና በትንሳኤው የተመረቀውን የማዳን ስሌት ምን እንደሚመስል እንድንረዳ ይርዳን። በመጀመሪያ ግን ይህን ሚስጢር መረዳት “ያስፈልገኛል” ካላልን ወደ መፍትሔ መምጣት አንችልምና እግዚአብሔር ስለዚህ ጉዳይ ሁላችንንም ይምከረን እላለሁ።
[1]The language of Gal. 4:4 also shows us this. The Spirit was sent in our hearts, pointing us to the subjective appropriating work of the Spirit in our hearts of the objective and propitiating act of the Son in space-time-history.

