
በልጅ አንደበት ተናገረን፡ ወንጌልና አስተርዕዮ በእብራውያን መልዕክት (ክፍል-2)
«ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ…በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን» (ዕብ 1፡1:1-2)
ባለፈው ክፍል፣ እግዚአብሔርን መግለጥ የሚችለው «ራሱ እግዚአብሔር ብቻ» እንደሆን ተመልክተናል። ስለዚህም ያለ አስተርዮ እግዚአብሔርን ማወቅ አንችልም። ስለ ነገረ-አስተርዕዮም (እግዚአብሔር ራሱን እንዴት እንደገለጠ) በቂ ግንዛቤ ካልያዝን ስለ እግዚአብሔር ያለን ግንዛቤ ሊዛባ ይችላል። ሁለቱ የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ በማርቲን ሉተር አስተሳሰብ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ነገር፦ እግዚአብሔር “ዴዩስ አብስኮንዲቱስ\deus absconditus\ የተሰውረ-አምላክ” እንዲሁም “ዴዩስ ረቨላቱስ\deus revelatus\የተገለጠ-አምላክ” መሆኑ ነበር (“the hidden God” and “the revealed God”)። ለሉተር ሰው ያለ አስተርእዮ የእግዚአብሔርን ማንነት ይሁን ዘላለማዊ ፈቃዱን ማወቅ አይችልም። በተጨማሪም፤ ለሉተር ይህ የተስተረዓየው የእግዚአብሔር ክብር በክርስቶስ መስቀል ውስጥ ተሰውሯል። ተገልጧል-ግን-ተሰውሯል። የተሰወረው በመስቀሉ በኩል ሊያገኙት ለማይፈልጉት ነው። ለዚህ ነው ሉተር “የመስቀል ነገረ-መለኮት እና የክብር- ነገረመለኮት [the theology of cross & the theology of glory]” ብሎ የሚናገረው (ይህ አመለካከቱ ገና ቄስ በነበረበትም ጊዜ ያሰላስለው የነበረው፣ በተለይ በ1518 ዓ.ም. ላይ በኸይድልበርግ በነበረው ስብሰባ በጉባኤ የሞገተው ርዕስ ነበር)። እግዚአብሔር ራሱን በክርስቶስ የገለጠው፣ በሰው አስተሳሰብ ተቃራኒ በሆነ መንገድ በመሆኑ፤ ይህም ክብሩን በውርደት በመግለጡ፤ ክብሩን የሚያዩት እግዚአብሔርን በመስቀሉ በኩል የሚገናኙት ብቻ ናቸው።
ስለዚህ ከእብራውያን መጽሐፍም ወስደን ያየነው የመጀመሪያው ነጥብ፣ ለተገለጠልን እግዚአብሔር የምንሰጠው ምላሽ “ዳተኛነት፡ አለማመንና አለመታዘዝ” መሆን እንደሌለበት ነው።
“ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል” (2:1) ይላልና።
በሁለተኛ ደረጃ፣ በዕብራውያን መጽሐፍ ላይ ከአስተርዮ ጋር የተያያዘው ደግሞ፤ “የአይነትና የመጠን” ጉዳይ ነው (ዕድገተ-አስተርእዮ\Progressive Revelation)። እኛ የተቀበልነው አስተርእዮ ከቀደሙት አባቶች ጋር ሲነጻጸር፤የእኛ ሙሉና ፍጹም ነው። ጌታም ሲቀጥል “ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም” ይላል። ክርስቶስ ጣቱንም ወደ ራሱ እየጦቆመ፤ “ፊታችሁ ቆሜ የምታዩኝ እኔ አስተርዮተ-ያህዌህ ነኝ” ይለናል። ራሱን ለአባቶች በብዙ ዓይነትና መንገድ፣ በቃልና በሥራ፣ ሲገልጥ የነበረው ያህዌህ አሁን የእስራኤልን ተስፋና ክብር በሰውነቱ በተሸከመው “በልጁ” ተገለጠልን። ስለዚህ እኛ የተቀበልነው አስተርእዮ፣ ከቀደመው ጋር ሲነጻጸር “ይልቃል”። የሚልቀው ግን፤ ለአባቶች የተናገረው አምላክ እና ለእኛ የተናገረን አምላክ ስለሚለያዩ አይደለም። ለአባቶችም ይሁን ለእኛ የተናግረን አንዱ “እግዚአብሔር\ὁ θεὸς (1:1)” ነው። የብሉይና የአዲስ አስተርዮ ልዩነት የተመሰረተው “ተገላጩ ማን መሆኑ” ላይ ሳይሆን ‹ገላጮቹ እና የመገለጫ መንገዶቹ› ማንነት ላይ ነው። ጸሃፊውም ሲናገር፦ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ….በዚህ ዘመን መጨረሻ በልጁ ለእኛ ተናገረን” ይላልና።
የመጨረሻው ከቀደመው ተቀጣይነቱ (Continuity)
«በነቢያት ተናግሮ….በልጁ ተናገረን» ሲል የሁለቱም ዓረፍተ-ነገሮች ባለቤት (subject) “እግዚአብሔር” ነው። “እግዚአብሔር…ተናግሮ….[እግዚአብሔር] ተናገረን [ὁ θεὸς λαλήσας…. ἐλάλησεν]። ስለዚህ እዚህ ጋር «በተግባር-ማርሲዮናዊ» እንዳንሆን ያስጠነቅቀናል (ማርሲዮን ቤተክርስቲያን የተቃወመችው ሰው ነበር። በትምህርቱም፤ የብሉይ አምላክ ያህዌህና የኢየሱስ አባት የተለያዩ አምላኮች ናቸው ባይ ነበር)። የብሉይ አስተርእዮና የአዲስ አስተርእዮ «ወጥ-አስተርዮ» እንጂ አንዱ ሌላውን የሚፎርሽ አልነበሩም። በሁለቱም እግዚአብሔር ተገልጧል። ልዩነቱ “የመጠንና የአይነት ልዩነት” እንጂ በየትኛውም ዘመን፣ ያለአስተርእዮ ሰው እግዚአብሔርን ሊያውቅ አይችልም። ሰው ቢዳክር፤ ቢፈላሰፍ፤ ቢመራመር፤ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሔር ሊያገኘው አይችልም። አንድ መካከለኛ አለና። አንድም ሐይማኖት [መንገድ] አለና። እርሱም ሰው በሆነው አምላክ የምንገባበት መንገድ ነው (1ጢሞ. 2:5)። ከዚህ ውጪ ሰው ሌላ መንገድ ቢፈልግ፣ መንፈሳዊ ምንዝርና ውስጥ ይገባል [እዚህ ጋር ሁለቱንም የአስተርዮ ቀጠናዎች በግምት ማስገባት ያስፈልገናል፦ ልዩ እና ጥቅል አስተርዮ\ General vs. Special Revelation. In both cases, it is God who is being revealed]። አስቀድሞ በብሉይ “ሰማይንና ምድር ያገናኘ መሰላል” ያዕቆብ እንዳየ፤ “እኔ እኔ ነኝ!” ብሎ ለሙሴ በቁጥቋጡ እሳት እንደገለጠ፤ በዚህ ዘመን መጨረሻም ራሱን ገለጠልን። ሰው እግዚአብሔርን ማግኘት የሚችለው በሙላት በተናገረበት በልጁ በኩል ነው። ከእርሱ በፊት የነበረው ሁሉ ሽርፍራፊ መገለጥ ነበር። ሙሉው በክርስቶስ ተገልጧል።
የቀደመው በመጨረሻው መተካቱ (Discontinuity)
ይህ ማለት የቀደመው ተሽሯል ማለት ግን አይደለም። የቀደመው በልጁ ወደ ፍጻሜ ደርሷል እንጂ። ይህንን በዓረፍተ-ነገሩ አወቃቀር መመልከት እንችላለን። እግዚአብሔር በሁለት ዓይነት ሞገዶች\መንገዶች ተናግሮናል።
አንደኛ፤ ሰባኪው ሁለቱንም «በ + […]» በሚል መስተዋድዳዊ-ሐረጎች ይገልጻቸዋል፦
- “በ + ነቢያት” [ኤን-ቶይስ-ፕሯፌታይስ] ተናግሮ
- “በ + ልጅ” [ኤን-ሁዮ] ተናገረን
እነዚህ ሁለት መስተዋድዳዊ ሐረጎች የሚያስረዱን የአስተርዕዮ መሣሪያዎችን ነው። የመጀመሪያዎቹ ወደፊት የሚጦቁሙ ቀስቶች እንጂ ራሳቸው “አስተርዮተ-እግዚአብሔር” አልነበሩም። እንጠንቀቅ፤ መልዕክታቸው “መለኮታዊ ነበር” ግን መልክቱን አቅራቢዎቹ መለኮታዊ አልነበሩም። ሁለተኛው መስተዋድዳዊ ሐረግ፣ “በልጁ” የሚለው፣ የሚያስረዳን ደግሞ በክርስቶስ የመጣው ይህ የመጨረሻ አስተርዮ፣ “የልጅ ዓይነት” መገለጥ መሆኑን ነው። የልጁ መልዕክት እንደ ነቢያት “መለኮታዊ” ነው፤ ነገር ግን እርሱ በማንነቱ “የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” ስለሆነ መለኮታዊ ነው። ስለዚህ የልጁ አስተርዮ “በዓይነት” ስለሚለይ ይልቃል። መልክቱም መለኮታዊ፤ እርሱም መለኮታዊ ነውና።
በሁለተኛ ደረጃ፤ የልጁን አስተርእዮ ከቀደመው እንደሚልቅ ሲያስረዳን፣ ጸሐፊው በነቢያቱ የመጣውን አስተርእዮ በቦዝ-አንቀጽ (a participle verb) ግሥ በመጠቀም “ተናግሮ…” ይላል። ይህ ቃል\ግሥ የቀደመው አስተርዮ “ዕድገታዊ” ባሕርይ እንደነበረው ያሳየናል። “እግዚአብሔር ተናግሮ…ተናግሮ…ተናግሮ…” የሚል እንደምታ አለው። እግዚአብሔር “በነቢያት ተናገረ” ደግሞም “በልጅ ተናገረ” አይልም። እንዲያ ቢሆን ኖሮ ሁለቱም አስተርዕዮዎች በአንድ መደብና ደረጃ ይሆኑ ነበር። ነገር ግን “ተናግሮ” በማለቱ፤ በሁለቱ “መናገሮች” መካከል እድገታዊ ልዩነት መኖሩን አሳየን፦ “ተናግሮ…በመጨረሻ ተናገረን”። በልጁ እስኪናገረን ድረስ አስተርዕዮው ቀጣይነትና እድገት ነበረው። ሆኖም ግን ይህ እድገት ፍጻሜ አግኝቷል “ተናግሮ በልጅ ተናገረ”። ይህ «ተናገረ» የሚለው ሁለተኛው ግሥ ግን ቦዝ-አንቀጽ (participle) ሳይሆን ውሱን-ግሥ ነው (Finite Verb) «ተናገረ»። ንግግሩ ፍጻሜ እና እረፍት አግኝንቷል። ፍጻሜ ላይ ደርሷል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው! ነቢያት ተልከው «ቃል» ወደ አባቶች አመጡ። ይህ የምንናገርለት የእግዚአብሔር ልጅ ግን፤ ይህ መልከጸዴቃዊ ካህን-ንጉስ ግን፣ ራሱ መግለጠ-አምላክ፤ አስተርዮተ-እግዚአብሔር ነው! ሃሌሉያ!! ከልጁ አስተርዮ በላይ፤ አስተርዮ ለሚፈልግ የሚጠብቀው አሰቃቂ ፍርድ ብቻ ነው። ከኢየሱስ በላይና ውጪ ሌላ አስተርዮ ለሚፈልግ፤ እግዚአብሔር ሌላ ለማንም ምንም የለውም። ስለዚህ ዓይነት ሰው ጳውሎስ ሲናገር “በእርሱ [በክርስቶስ] የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ማንም በከንቱም መታለል እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” ይላል። ወደ ኋላ ተሸራርፎ ወደተሰጠበት መመለስ፤ አሊያም ከእርሱ ወደ ሌላ መካከለኛ መመልከት “በከንቱ” መታለል ነው። የመለኮት ሙላት ያለው በክርስቶስ ነው። እግዚአብሔርን ማወቅ የምንፈልግ፤ እግዚአብሔርን «በልጁ ቃል» ውስጥ እንፈልገው። ሌላው ሁሉ አሰቃቂ “መንፈሳዊ ምንዝርና” ነው። ኢየሱስ ሙሴ-መሰል ከነበሩ ነቢያቶች (ከሳሙሴል እስከ መጥምቁ ዮሐንስ) ሁሉ አብዝቶ ይልቃል። ከኢየሱስ የሚልቅ ሌላ “ሙሴ” አይመጣም። ሰባኪው ሲቀጥል፤ “ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ፥ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው(3:5)” ሙሴና ኤሊያስ በገናናው ተራራ ላይ ሲገለጡ፣ አብ ከሰማይ “የምወደው ልጄን ስሙት” ብሎ ለደ/መዝ. ያስጠነቀቀው ለዚህ ነው። ወደ ዕብራውያን ሰባኪ ስንመለስ፦
“ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል። ምክንያቱም በመላእክት በኩል የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነና ማንኛውም መተላለፍና አለመታዘዝ ተገቢውን ቅጣት ከተቀበለ፣ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ቸል ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን?”
ስለዚህ ዕብራውያን 1:1-2 ለማጠቃለል። እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ “ተናግሮ” “የተናገረ” አምላክ ነው ሲለን አራት ነገሮች እያነጻጸረ ነው።
- አስተርዮው የተሰጡባቸው ዘመናት ተነጻጽረዋል፦ “ከጥንት ጀምሮ ተናግሮ” – “በዘመናት መጨረሻ ተናገረን”
- የአስተርዮው አሰጣጥ ተነጻጽሯል፦ “በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና…ተናግሮ” – “[በሙላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ]…ተናገረን”
- የአስተርዮው ተረካቢዎች ተነጻጽረዋል፦ “ለአባቶቻችን..ተናግሮ” – “ለእኛ…ተናገረን”
- የአስተርዮው አቀባዮች ተነጻጽረዋል፦ “በነቢያት ተናግሮ” – “ለእኛ ተናገረን”
በእነዚህ አራት ንፅሮች መካከል እድገትና የደረጃ ልዩነት አለ።
- ከጥንቱ ይልቅ የዘመን መጨረሻው ይልቃል (ዘመነ-ፍጽመታዊ እይታው)።
- የልጁ አስተርዕዮ በአስጣጡ ይልቃል – በሙላት ፍጹም ሆኖ የመጣው እየተንጠባጠበና እያደገ፤ እየሞላና እየላቀ ከመጣው ይልቃል።
- የልጁ አስተርዕዮ በዓይነቱ ይልቃል – “በልጅ” ዓይነት ፍጹምናን የተላበሰው “አካል” (መገለጡም መግለጡም ራሱ የሆነው)፤ የእርሱ አምሳል ከነበሩት “ከነቢያት” ይልቃል።
- በልጁ የተናገረን እኛ በነቢያት ከተናገራቸው “ከአባቶች” እንበልጣልን።
ይህንን የመጨረሻ ነጥብ አብራርቼ ልዝጋ። ሰባኪው እነዚህ አምነው ስላለፉ አስደናቂ የእምነት ሰዎች ሲነግረን፣ ታላቅ እምነት የነበራቸው ቢሆንም የተስፋ ቃሉን ግን አልወረሱም። ለምን? እዚህ ጋር አስደናቂ ነገር ጸሐፊያችን ይነግረናል። ብዙ ግዜ ይህንን መዝጊያ አናስተውልም። “ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና። (11:39-40)” እነዚህ የእምነት ሰዎች፤ በተስፋ አምነው፤ ግን ተስፋውን አልጨበጡም “ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት” (11:13)።እኛ ግን በዘመን መጨረሻ ያለን አማኞች ተስፋውን መውረስ ጀምረናል። ከመስቀሉ በኋላ ቆመናልና፡፡ በሰማያት በግርማው ቀኝ ከተቀመጠው በመንፈሱ በኩል ሰማያዊውን ሥጦታ አሁን እየቀመስን፤ የሚመጣውን ዓለም ሃይል እየተለማመድን ነውና (6:4)። ተስፋው አሁን ገንዘባችን ቢሆንም የተስፋችን ፍጻሜ ግን ገና ወደ ፊት በመሆኑ በውጥረት ውስጥ አለን “ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል” (9:28)። የቀደሙት አባቶች ይሁን ነቢያት፤ ተዘርግተው ሳይደርሱ አለፉ፡፡ እኛ ግን ልጁ የተናገረበትና ሥራውን ፈጽሞ ወደ ሰማይ የተመለሰበት የዘመናት መጨረሻ ውስጥ ስላለን፤ ከእርሱም ጋር ከበኩራት ማሕበር፣ በጽዮን ተራራ ስለተሰበሰብን፤ ተስፋችንን መቅመስ ስለጀመርን፤ ከቀደሙት እንበልጣለን። የምንበልጠው በሠራነው ሥራ ወይም እምነታችን ከእነርሱ በልጦ ሳይሆን፤ ከጨበጥነው ተስፋ የተነሳ እንጂ። ሆኖም ግን ከእኛ በላይ አልፎ የቀደመን ደግሞ ሌላ አለ። ኢየሱስ ይባላል። እርሱ “ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል” (12፡2)። ስለዚህ ኢየሱስን እያየን “በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ”።
ማጠቃለያ፡ የሚናገረው-ስሉስ አምላክ በእብራውያን
ስንደመድም፤ የእብራውያን ሰባኪ እግዚአብሔር «የሚናገር አምላክ» ስለ መሆኑ በማስረጃ አይሞግትም። መናገሩ በግምት ውስጥ የገባ ሐቅ ነው። እግዚአብሄር አብ የሚናገር አምላክ ነው። በመናገርም ራሱን ይገልጣል! በሁለተኛ ደረጃ፤ ወልድም እንዲሁ የሚናገር አምላክ ነው። ቃሉ ያድናል፤ ይፈርዳልም። ይህ ታላቅ ድነት “በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት (2:3)”። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ነቢያት የተናገሩት፤ ለጸሐፊው በአንደኛ መደብ ወልድ የተናገረው ነው። ዳዊት በመዝ 22 ላይ “[እኔ] ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ” ያለውን፤ አሁን ኢየሱስ እንዳለው ይነገርናል (2:13)። ኢሳያስ በኢሳ 8 ላይ የተናገረውም እንዲሁ። በሦስተኛ ደረጃ እንዲሁም፤ በእብራውያን መፅሀፍ ላይ፡ መንፈስ-ቅዱስ ሕያው በሆነው ቃሉ አማካኝነት ይናገራል። በመጽሐፉ ሁሉ፤ “መንፈስ ቅዱስ” እንደሚል ይላል (3:7)። ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በፊት ዳዊት የጻፈውን ቃል፣ ዛሬም ሕያው ሆኖ የሚናገር ድምጸተ-መለኮት በመሆኑ፣ በሃላፊ ግሥ “ብሏል\εἶπον” ሳይሆን ልክ አሁን ከእግዚአብሔር አፍ እንደሚወጣ “…ይላል [ለጌይ\λέγει]” እያለ ይናገራል (1:6, 8, 9, 12)። ከ1500 ዓመት ገደማ በፊት በዘዳ 32:43 ላይ በሙሴ በኩል የተነገረው ቃል “መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ (ዕብ 1:6)” «ብሏል\εἶπον» ሳይሆን፣ በአሁን ግሥ “ይላል\λέγει” ብሎ ይናገራል። እንዲሁም “መላክቱን…አገልጋዮች ይላል”፣ “ስለ ልጁ ግን። አምላክ ሆይ..ይላል፤” “ደግሞም [ስለ ልጁ] ዓመቶችህ አያልቁም ይላል” ይህም በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር ድምጽ፣ ሕያው ሆኖ አሁንም የሚናገር ድምጽ መሆኑን ያሰምርልናል። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ-ቃሉን ስናነብ፤ በክርስቶስ ሥራ ላይ ተመርኩዘን እንድፈታው ይረዳናል (9:8; 12:8)። ሰባኪው ቅዱስ ቃሉ ድርብ ጸሐፊያት እንዳሉት ይመሰክርልናል። የመዝሙር 95:7-11 ተናጋሪ “መንፈስ ቅዱስ እንደሚል” ይላል (3:7-11)። ደግሞም በ4:7 ላይ ይህንኑ ክፍል ጠቅሶ፣ “ዳዊት ሲናገር” ይላል። ኤርሚያስ የተነበየውን ትንቢት “መንፈስ ቅዱስ ይመሰክልናል” ይላል (10:15–16)። እንዲሁም ይህ የሚናገረን-መንፈስ ቅዱስ፤ ወልድ ሥራውን ሲሰራ አብሮት የሠራም እንደነበር ሲጠቁመን “በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ (9:14)” ይላል። በዚህም መንፈስ ቅዱስ፣ ወልድ የፈጸመውን ጸጋ እንካፍላለን (6:4; 10:29)።
ስለዚህ እግዚአብሔር በልጁ የተናገረንን መልዕክት፤ ይህም በቅዱስ ቃሉ የቀረልን የወንጌል መልዕክት (2:3) አጥብቀን እንያዝ። በዘመናት መጨረሻ የተናገረን “በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና በነቢያት አንደበት” ሳይሆን በልጁ አንደበት ነው። ይህ ቃል የሰው-ቃል ሳይሆን “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው…የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው”። ይህንን ቃል አጥብቀን እስከመጨረሻው ብንይዝ፤ ወደ ተቀጠረልን የሰንበት እረፍት እንገባለን።
“እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ” (3:11)።

