Blog,  HEBREWS,  ዕብራውያን,  ዕብራውያን,  የአዲስ ኪዳን ሐቲት,  የአዲስ ኪዳን ነገረ-መለኮት

በልጅ አንደበት ተናገረን፡ ወንጌልና አስተርዕዮ በእብራውያን መልዕክት (ክፍል-1)

«ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ…በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን» (ዕብ 1፡1:1-2)

“እግዚአብሔር ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ በቂ ያልሆነ ወይም የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረን ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱና ተቀዳሚው፤ ስለ ነገረ-አስተርዮ በቂ ያልሆነ ግንዛቤ መጨበጥ ነው። ለምን!? ምክኒያቱም እግዚአብሔርን ማወቅ የምንችለው «እግዚአብሔር ራሱን የገለጠልን እንደሆነ» ብቻ ስለሆነ ነው። እግዚአብሔርንም መግለጥ የሚችለው ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህም ያለ አስተርዮ እግዚአብሔርን ማወቅ አንችልም። በግሌ ሕይወት ይሁን በሌሎች የተመለከትሁት አንድ ነገር ቢኖር «ስለ እግዚአብሔር የተዛባ አመለካከት ምንጩ የተዛባ ነገረ-አስተርዕዮ» መሆኑን ነው። ስለዚህ አስተርዕዮ ምንድር ነው? አስተርዕዮ የእግዚአብሔር ማንነትና የዘላለም ፈቃዱ መገለጥ ነው። የነገረ-አስተርዮም ቁልፍ መልክት “እግዚአብሔር ሕያው ሕላዌ\ a Personal Being” መሆኑ ነው። ይህ አምላክ «“እኔ” እያለ ስለራሱ፣ ይግባባው ዘንድ በአምሳሉ ለፈጠረው ሰው “አንተ” ብሎ» የሚገልጠው ነው። እግዚአብሔር ሕያው ሕላዌ [Living God] ስለሆነም «የሚናገር አምላክ» ነው። ለሙሴ በእሳት ቁጥቋጥ ውስጥ በቅዱስ ስሙ «ያህዌህ›» ሲገለጥለት «ያለና የሚኖር አምላክ – እኔ-እኔ ነኝ» ሲለው፣ ስሙ በአንድ ጊዜ በፊታችን ፍንትው አድርጎ ይገልጠዋል፤ ደግሞም በመዳፋችን ቆልፈን ተቆጣጠርነው እንዳንል “ከደመናት በላይ” ይሰውረዋል። ይህ ሥም “በቃልና በሥራ” የሚሰለጥን – የሚናገርና የሚሰራ- ሕያው አምላክ እንደሆን ይገልጣል። ሐልወተ-እግዚአብሔር ሲባል፤ የሚያስደስተን፤ የሚያጠግበን፤ ተስፋን የሚሰጠን፤ ክብር የሚሞላብን እውነታ እንደሆነ ሁሉ በዚያው ልክ የሚያስደነግጠን፤ እንድንፈራው የሚገፋፋን፤ በፊቱ በትህትና በመዋረድ እንድንመላለስም የሚያደርገን ይኸው እውነታ ነው {በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና (12:28-29}። ያህዌህ ትላንትን ነበር፤ ዛሬም አለ፤ በሕዝቄል እንደተናግረው ገና ወደፊት በሚመጣው ሥፍራ «ያህዌህ ሻማ!» አለ።

እግዚአብሔር ባይናገር ኖሮ እግዚአብሔርን ማወቅ ባልቻልን ነበር። ይህ ከሆነ ባልተፈረደብንም ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር እናውቀው ዘንድ ተገልጦልናል። አለማወቅ ምርጫችን አይደለም! እግዚአብሔር «እነሆኝ!» ብሎ ራሱን ፍንትው አድርጎ ስለገለጠልን ምርጫችን አንድ እና አንድ ብቻ ነው። እርሱን ማወቅ! ይህ ግዴታ አለብን። ራሱን ስላስተረዓየልን (because he disclosed himself to us)። በዘመን መጨረሻ፣ ከምጡቅ መጋረጃው ጀርባ ከአብ ጋር በዘላለም ይኖሩ የነበሩ፤ በክብርና በመለኮት እኩል የሆኑ፤ ከእርሱ ዘንድ «ተልከው» ወደ ምድር በመምጣት፤ ከእነርሱ በፊት ከምድር ተመርጠው ወደ ምድር ከተላኩት “ነቢያት” (ዮሐ. 3:30-36) በመጠንና በዓይነት በሚልቅ መንገድ ገልጠውልናል፦ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር…ልጁን ላከ…አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ” (ገላ 4:4)። ወልድ ከአባቱ ዘንድ ሰምቶ ያስተማረውን፤ መንፈሱ ዛሬም ያስተምረዋል፡፤ የገለጠውን፤ ዛሬም በሐዋሪያቱ አማካኝነት በጻፈልን ቃል በሥልጣን ይገልጥልናል። ወልድ በመስቀል የዛሬ 2ሺህ አመት «የፈጸመውን» (what the Son accomplished)፤ መንፈስ ቅዱስ «እንድንካፈለው» ያደርጋል (the Spirit applies)። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ምድር ላከ፤ መንፈሱም ወደ ልባችን ላከ! መንፈሱን ወደ ልባችንም ሲልክ፤ እርስበርሳቸው ሊነጣጠሉ የማይችሉት አካላት፤ አብረው ወደ ልባችን አደሩ (ዮሐ. 14:20-27)። ስለዚህ ሕያው ስላሴ በልባችን ማደሪያ አድርጎ ይኖራል። በልጁ የተቀበልነው፤ በሐዋሪያቱ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጻፉልን ውጪያዊ አስተርዕዮ፤ በልባችን በሚኖረው ስሉስ-አምላክ ውስጣዊ «አብርሖት» ይረጋገጣል። አስተርዮው ውጫዊ መልዕክት፤ ውስጣዊ ብርሃንም ነው። ሃሌ ሉያ! (It’s both an objective, external Revelation as well as an internal-subjective experience. The objective shapes the subjective and the subjective concretized the objective. As such we reject both the modernist as well as the post-modernist approach to Revelation) ።

በእብራውያንም መጽሐፍ የምናገኘውም አስተርዮተ-እግዚአብሔር እንዲሁ ነው። ለእብራውያን ሰባኪ፣ ይህ ዘመን እግዚአብሔር በልጁ የተናገረበት “ራሱን-ያስተረዓየበት” ዘመን ነው። ይህ ዘመን እንደ ጥንቱ እግዚአብሔር በመላዕክት ወይም በሙሴ አማካኝነት የተናገረበት ዘመን አይደለም። ከሙሴ ጀምሮ እስከ ሚልክያስ የነበሩ ነቢያት የተናገሩበት የነቢያትም ዘመን ተፈጽሟል (1:1-2) “ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር [እንደሎሌ] ምስክር” ነበር (3:5)። ይህ «በኋላ ዘመን» እግዚአብሔር በታመነው “በልጁ” የተናገረበት ዘመን ነው። እንደ ጥንቱ “ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፤ ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ” ይላል (12:18)። እኛም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ሲያስጠነቅቀንም እንዲህ ይላል “ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላስረዳቸው እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፥ ከሰማይ ከመጣው ፈቀቅ የምንል እኛስ እንዴት እናመልጣለን?” ይላል (12:25)።፡ይህ «ከሰማይ የመጣው» የሚለን ነገር ምንድር ነው? በ1:1-2 እና በ2:1-4 ላይ በጥልቀት የሚዳስሰውን፣ ከልጁ የተቀበልነውን መልዕክት ነው “ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት” (2:3)። ትውልድ የሚዳኘው እ\ር በልጁ ለተናገረን-ቃል፣ ይህም «ከወልድ ወደ ሐዋሪያቱ እንደመጣ፣» የመልክቱን ንጽሕና በጥንቃቄ በመጠበቁ እና ይህንንም አደራ በታማኝነት በመወጣቱ እንጂ “በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።” ጌታ የሚሰጣቸው መልስ “ከቶ አላወቅኋችሁም” የሚል ነው።

ሰባኪውም ሲናገር “አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይንና ምድር አናውጣለሁ” ይላልና (12:26)። አንድ ቀን እግዚአብሔር ሁላችንንም የሚያራግፍበት ቀን አለ። በዚያ ቀን የሚያጸናን “የተቀበልነው ጸጋ” ብቻ ነው (12:28; 4:16)። ክርስቶስም ሲናገር “ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው” እንጂ ሰዎችን በተአምር ያስደነቀ ሁሉ “ታማኝ ባለአደራ ነው” ማለት አይደለም። ስለዚህም የእብራውያን ሰባኪ፤ ጣቱን በአይናችን ላይ እየጦቆመ፤ የሚጠይቀን “ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል” (2:1) በማለት ነው። “እንዳንወሰድ” የምትለው ቃል (ፓራረዖ\παραρρέω) ከባህር-ጉዞ የተወሰደ ዘይቤ ናት። ትርጉሙም “ውሃ ሲወስድ አሳስቆ ነው” የሚለው ሐገርኛ ምሳሌ በጥሩ ይገልጠዋል (ይህ ቃል በምሳ. 3:21 ላይ በተመሳሳይ መልኩ ተገልጧል)። ከሰማነው ቃል ስንወሰድ እያወቅን አይደለም። ምናልባት “ድንቁን እያየን እየዘመርንም” ሊሆን ይችላል። ምክኒያቱም “ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ?…ለአርባ አመታት” ሥራውን ያዩ ናቸው። ስለዚህ ትልቁ ጥያቄ “በልጁ ለመጣው መልክት” ግድ የለሽ ከሆንንና ጆሮቻችን ከፈዘዙ (5:11)፤ የተቀበልነውን ታላቅ እውነት “በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ” ሲሆንብን፤ አማኞች “ለመማር ዳተኛ (5:11)” ስንሆን እና በሳል እውነትን መቆርጠም አቅቶን መንፈሳዊ ጥርሳችን ሲጠዘጥዘን (5:12)፤ ከግዜው የተነሳ አስተማሪዎች መሆን ሲገባን ግን “ከጽድቅ ትምህርት ጋር ገና” መተዋወቅ ሲያቅተን (5:13)፤ መሰረታዊው እውነት ጀምረን፤ ደግሞ እየጣልን፤ ገንብተን ደግሞ እያፈረስን፤ ከዓመት ዓመት “እንደ ገና መሠረትን” ስንጥል (6:1)፤ ደግሞ እንደገና መልሰን መሰረት ስንመሰርት (6:1-2)፤ ከልጁ ወደ ሐዋሪያቱ ብሎ ወደኛ አልፎ የተቀበልነውን መልዕክት አጥብቀን ባለመያዛችን፤ እንደ ንፋስ የመጣው አዳዲስ ትምህርት ሁሉ ከክርስቶስ ወደ ሁላ ቢመልሰን፤ ይህ በሰማያት አልፎ በግርማው ቀኝ የተቀመጠውን “ለገዛ ጥፋታቸን የእግዚአብሔርን ልጅ [ንጉስ-ካህን] እንደ ገና” እንሰቅለዋለን፤ እናዋርደውማለን (6:6)። ስለዚህ ሰባኪው “በልዩ ልዩ ዐይነት እንግዳ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን የሚጸናው በጸጋ” (13:9) ይሁን ይለናል። ለምን? ምክኒያቱም “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው (13:8)” ስለሆነ!! ያ ከእርሱ ሰምተው “የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው!” የተባልነው፤ ኢየሱስ ስላልተለወጠ ነው! መልዕክቱ አልተለወጠም! ዛሬም እግዚአብሔር በልጁ የተናገረበት ዘመን ነው። ኢየሱስ ከነቢያት፤ ከመላክት፤ ከዳዊትና ከሙሴ….ይልቃል! ይህ ለዛሬ 2ሺህ አመታት ከሰነበተው የመጨረሻ ዘመን አስተርዮ አይኖቻችንን ብናነሳ ፍርዱ እጅግ ታላቅ ነው። ኢየሱስ ሲናገር፤

“የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል።የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም” (ማቴ. 13:15-17)

ኢየሱስ ከአስተርዮ ጋር የተያያዙ ሁለት ችግሮችን ተናግሯል፡ አንድ ውስጣዊ፤ ሁለት ውጪያዊ። በመጀመሪያ ያለ እግዚአብሔር እግዚአብሔርን የሚገልጥ እንደሌለ ሁሉ፤ ሲገለጥም፤ መገለጡን “አሜን” ብሎ ለመቀበል የለዘበ-ልብ፤ የሚሰማ ጆሮ (ኢሳያስ የተበሳ ጆሮ ይላል)፤ እና የሚያዩ አይኖች ያስፈልጋሉ። ይህ ችግር “ውስጣዊ” ችግር ነው፦ የማያምን ልብ ያለው እግዚአብሔርን ማየት አይችልም። ይህ ውስጣዊ ችግር ካልተቀረፈ፤ ምንም ያህል እግዚአብሔር ቢገለጥ፤ ሰው እግዚአብሔርን ማወቅ አይችልም። ባለማወቁም ማመካኘት አይችልም። ለዕብራውያንም ሰባኪ በመላዕክት እና በሙሴ በኩል የመጣው ኪዳን ትልቁ ነቀፌታ “ፍጹምናን” አለማስገኘቱ ነው፤ ውስጣዊ አለመሆኑ ነው፦
“ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን።” ይላል ። (3:15-19)
በምድረበዳ የረገፈው ሕዝብ እግዚአብሔር ራሱን ስላልገለጠላቸው ሳይሆን፤ “ያደረግሁትንም ሁሉ ለአርባ ዓመት አይተዋል” ግን አላመኑም። ስለዚህ ሰባኪው
“ከመካከላችሁ ማንም በኀጢአት ተታሎ ልቡ እንዳይደነድን፣ “ዛሬ” እየተባለ ሳለ በየቀኑ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።” ይላል። ለእነርሱ በሙሴ በኩል እግዚአብሔር እንደተገለጠ ዛሬም ለእኛ በልጁ በኩል ተገልጦልናል። እግዚአብሔር ራሱን ስለአስተረአየልን (ስለተገለጠልን) ለተገለጠልን አምላክ የምንሰጠው አጸፋዊ ምላሽ በእምነት-የሆነ-መታዘዝ ነው። ለእብራውያን ሰባኪ እምነት-በ-መታዘዝ ነው፤ መታዘዝም በእምነት ነው። ስለዚህ “ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረው” «ባለመታዘዛቸው» ምክኒያት ነው ካለ በኋላ ወዲያውኑ ደግሞ “ወደ ዕረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው «ካለማመናቸው» የተነሣ እንደሆነ እንረዳለን” ይላል። አለማመን የሚገለጠው ባለመታዘዝ ነው። የአለመታዘዝም ምንጩ አለማመን ነው። ስለዚህ ከአስተርዮ ጋር የተያያዘው የመጀመሪያ ችግር «ውስጣዊ የልብ» ችግር ነው።

ለማጠቃለል፤ አለም በጥበቧ እግዚአብሔር ልታውቅ አልቻለችም (1ቆሮ. 1:21; ገላ 4:8)። ያለአስተርዮ ማንም እግዚአብሔርን ማወቅ አይችልም። በዚህ ዘመን መጨረሻም እግዚአብሔር ልጁን ልኮ ተናግሮናል። ምን ያህል ለዚህ ቃል ሥፍራ አለን? የሰሙትን ቸል ከሚሉት ነን (2:1-3) ወይስ አጥብቀው እስከ መጨረሻ የሚይዙት (3:14) ሰምተው ከሚያስመርሩት ነን? (3:16) ወይስ የምሥራቹን ቃል ሰምተው በእምነት ከሚያዋህዱት (4:2)፤ ሰምተው ግን ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ከለመኑት ነን (12:19) ወይስ “ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ፤ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም” ወደደረሱት ነን? (12:22-24) የትኞቹ ነን? ምርጫ የለንም! እግዚአብሔርን እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ በልጁ የተሰጠንን አስተርዮተ-እግዚአብሔር አጥብቀን እንያዝ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.