
በሁለት እውነታዎች ተወጥሮ የተቃኘ መንፈሳዊ ሕይወት (መስቀልና ዙፋን – ክፍል 3)
ከዚህ ቀደም “ዘራፍ ዘራፍ” የምትለውን ቤተክርስቲያን እና “በሽሽት ላይ ያለቸውን” ቤተክርስቲያን <<መስቀልን እና ዙፋን>> ያላማጠኑ ጽንፈኞች እንደሆኑ አይተን ነበር። ከወንጌላዊው ዮሐንስ ነገረ-መለኮታዊ ትረካም ወስደን፤ ወልድ ተልዕኮውን የሚፈጽምበት ሰዓት አይተናል። ይህም የመስቀሉ ሥራ ነው። ይህ ተልዕኮ ታላቅን መዳንን ገልጧል። ይህ አንድ ተልዕኮ እውነተኛውን አምላክ አብን እና ልጁን ወልድን የሚያሳይ ሥራ በመሆኑ፤ የድነት ሥራው አሰተርዕዮ ነው፤ ይህንን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው። ይህንን ተመልክተናል። ሆኖም ግን ደግሞ ሦስቱ ወንጌላውያን (ማቴዎስ፤ ማርቆስና ሉቃስ) በእግዚአብሔር መንግሥት ዙሪያ በተቃኘ ዕይታቸው ይህንን ታላቅ መዳን ከሌላ ገጽታ አንጻር ይተርኩልናል። ኢየሱስ የነብያት ድምጽ እና የዳዊት ኪዳን ሊፈጽም መንግሥትን ይዞ በመገለጡ ላይ በማነጣጠር ፤ መዳን የእግዚአብሔር መንግሥት አሰራር እንደሆን ያሳዩናል (ማር 1:15)። ልክ በዮሐንስ ወንጌል “መስቀልና የዘላለም ሕይወት” የማይለያዩ ገጽታዎች እንደሆኑ እንዳየን፤ ሦስቱ ወንጌላውያን እንዲሁ “መስቀልና መንግሥት” እነደማይለያዩ ይነግሩናል።
ስለዚህ መዳን የእግዚአብሔርን መንግሥት ባሕርይ የተጎናጸፈ እንደሆን እንመለከታለን። ከዚህ የተነሳ የመዳናችን ሌላው ገጽታና ሊሰመርበት የሚገባ እውነታ፤ አሁን በእውነት ድነናል! መዳንን ተጎናጽፈናል፤ ዘላለማዊ ሕይወት አሁን ገንዘባችን ሆኗል፤ ቃል ኪዳን ውስጥ ታስረናል። ሆኖም ግን መዳናችን ክርስቶስ በግርማው ከመላዕክቱ ጋር መንግስቱን ይዞ ዳግም እስኪገለጥ ድረስ ቀና ብለን አንጋጠን የምንጠብቀውም እውነታ ነው! ስለዚህ ልክ የእግዚአብሔር መንግስት በመጀመሪያ መምጣቱና በዳግም ምጻአቱ መካከል በሁለት ዘመናት እነደተወጠረ ከዚህ ቀጥሎ እንደምናይ፤ መዳናችንም የመንግሥቱ አሰራር በረከት እንደመሆኑ ይህ ዓይነት ውጥረት ይታይበታል።
በአንድ እጅ “ሽሽት ላይ ያለችው ቤተክርስቲያን” ወደ ፊት በሚገለጠው ክብርና መዳን ላይ ጤነኛ ባልሆነ መልኩ አትኩራ አሁን የተመረቀልንን ታላቅ የማዳን ሃይሉን ላላ አድርጋ በመያዟ አሁን እየተነጋገርን ያለውን የአዲስ ኪዳንን ውጥረት አርግባለች። “ዘራፍ ዘራፍ” ባይ ቢተክርስቲያን ደግሞ ሊገለጥ ያለውን ሙላት አሁን እንደተቀበለች በማጋነን፤ እርሷም ውጥረቱን አርግባለች። ሆኖም በአዲስ ኪዳን ያለን አማኞች ተስፋችንን አሁን ይዘናል (ዕብ 6:18-20)፤ የነፍስ መልሕቅ አለን…ግን ገና ደግሞ ሙሉ በሙሉ እንይዛለን (ተስፋችን ዘልቆ ክርስቶስ ሊቀ-ካህናትና ንጉስ ሆኖ ወደ ተሾመበት ወደ እ/ር ዙፋን ይዘልቃል)። አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን (1 ዮሐ. 3፡1-3)…ነገር ግን ምን እንደምንሆን ገና አልታወቀም፤ ሆኖም እርሱን ስናየው “እርሱን እንደምንመስል ወይም ልጅነታችንንን በሙላት እንደምንቀበል” እናውቃለን። የርስታችንን መያዣ አሁን ተቀብለናል (ኤፌ. 1:13)…ደግሞ የእግዚአብሔር የሆኑት እስኪዋጁ ድረስ ርስታችንን ለመውረስ እንጠብቃለን። አሁን አንድ ቀን የምንሆነውን “ቀብድ” ተቀብለናል፤ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነትና በክርስቶስ ሹመት መቅመስ ጀምረናል …በሌላ እጅ ደግሞ አሁን ገንዘባችን የሆነውን ነገር ወደ ፊት ገና በሙላት እንወርሳለን። ይህ አይነት ውጥረት ለምን? ምክኒያቱም መንግሥቱ ይህ ዓይነት ባሕርይ ስለሚያንጸባርቅ ነው። የቤተክርስቲያን ሕይወት ንጉሷን ፈለግ ተከታይ ስለሆነች። ለምሳሌ፦ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ዘላለማዊ ርስታችንን እንደምንወርስ ማረጋገጫችን ነው።
❝የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ ያገኘን እኛ ራሳችን የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነታችንን በናፍቆት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ተስፋው የሚታይ ከሆነ ግን ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ገና ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፣ በትዕግሥት እንጠብቀዋለን❞ (ሮሜ 8:23-25)
ልክ እንዲሁ ሐዋርያው ጳውሎስ በሳል ክርስቲያናዊ አመለካከት በመስቀልና በትንሳኤ የተመጣጠነ ሕይወት እንደሆን ሲነግረን
❝ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ፣ በሥቃዩ ተካፋይ እንድሆንና በሞቱም እርሱን እንድመስል እመኛለሁ፤ ለሙታን ትንሣኤም እንድደርስ እናፍቃለሁ። ይህን ሁሉ አግኝቻለሁ ወይም ፍጹም ሆኛለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ። ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ። እንግዲህ እኛ ብስለት ያለን ሁላችን ነገሮችን በዚህ ሁኔታ ማየት ይኖርብናል❞(ፊልጵስዩስ 3:10-15)
ክርስቶስ እስኪመለስ ድረስ ሕይወታችን ተዘርግቷል። የኋላችንን እየረሳን ወደ ፊቱ እንዘረጋለን። እውነተኛና አዲስ ኪዳናዊ ሕይወት በዚህ ውጥረት የተቃኘ ነው። በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ጅብደኛነት (መስቀሉን ገፈፍ ማድረግ) አሊያም አፈግፋጊነት (የትንሳኤውን ሐይል አለመልበስ) ክርስቶሳዊ ህይወትን ያጣምማል። ይህ አይነት ውጥረት ለምን! ለምን? ምክኒያቱም የምንኖረው “በዘመን መጨረሻ” ስለሆነ ነው። ስለዚህ በመጀመሪያ የመጨረሻው ዘመን ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማለቱ እንደሆን እንመልከት።
► የመጨረሻው ዘመን
በዘለማድ የዘመን መጨረሻ ተብሎ የሚባለው ክርስቶስ ሊመለስ አካባቢ ያለው ዘመንና ሑናቴ ነው። ይህ አስተምሕሮት ከዲስፐንሴሽናል እንቅስቃሴ ዘርፍ አንዱ የሆነው “የመነጠቅ” አስተምህሮት ነው (‘Dispensational Premillennialism,’ which is different from ‘Historic premillennialism.’) ይህ ዓይነት መረዳት ግን አዲስ ኪዳን ስለ ዘመን መጨረሻ የሚናገረውን ነገር ያገናዘበ አይመስለኝም። በአዲስ ኪዳን ገጾች ላይ የምናየው የዘመን መጨረሻ የሁለት ዘመናት እውነታዎች “ንብብር” ወይም “overlapping of the ages” ውጤት ነው (በሰፊው ስለዚህ እንመለከታለን)። ይህ መነባበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ላይ “የመንግሥተ ሠማያት ሚስጢር” ብሎ ያስተማረን ነው። መንግሥተ ሰማያት ምን ትመስላለች? “ዘር ትመስላለች” (ማቴ. 13:1-9) በአንድ ሰው ታፈራለች፤ በሌላው ትጣላለች “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች” (ማቴ. 13:24-30)። ወይም መንግሥተ ሰማይ “የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች”። በእነዚህ ምሳሌዎች ሁሉ አንድ መሪ ሐሳብ ቢኖር የእግዚአብሔር መንግሥት በዚህ ክፉ ዘመን ውስጥ ሰርጻ በመግባት በአንድ እጅ ይህ አሮጌውና ክፉ ሥርዓት እየቀጠለ እንዳለ (የእንክርዳዱ ምሳሌ እና የመረቡ ምሳሌ)፤ አዲስና ሰማያዊ ሥርዓት ተደርቦ ውስጥ ውስጡን መስራቱ ነው (የዘር ምስሌ፤ ወይም የእርሾ ምሳሌና የሰናፍጭ ምሳሌ)። ሆኖም ግን ይህ መንግሥት በሰው ዓይን “ደም ግባት” የሌላት ወይም “የማትርባ፤ ኢሚንት፤ ዋጋ ቢስ” ትመስላለች (የተደበቀ ሀብትና የዕንቍ ነጋዴ ምሳሌ)። የመንግሥተ ሰማያትን ሚስጢር ለማወቅ ዓይኖቻቸው እንዲያዩ፤ ጆሮቻቸው እንዲሰሙና ልቡናቸው እንዲያስተውል ለተሰጣቸው ግን (ማቴ. 13:11-16) መንግሥቱ “በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት” ነች። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል
❝ዘመኑን በማስተዋል ይህን አድርጉ፤ ከእንቅልፋችሁ የምትነቁበት ጊዜ አሁን ነው፤ መዳናችን መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው❞
በዚህ ዘይቤያዊ አነጋገር አማኞች በሁለት “ሰዓታት” መነባበር ውስጥ ይኖራሉ፡ “ቀን” እና “ለሊት” በተባለ። ለሊት አልፎ ቀን ሲመጣ በደማቅ መስመር የተሰመረ አይደለም። ሁለቱም ስለሚንባበሩ፤ “ንጋት” እንለዋለን። ጨለማው ስፍራ እየለቀቀ፤ ብርሃኑ እየደመቀ ይሔዳል። ይህንን ሽግግር አዲስ ኪዳን “የመጨረሻው ዘመን ይለዋል። ከዚህ እውነታ የተነሳ በአንድ ወገን አማኞች ሰማያዊ ዜጎች ሲሆኑ በአንድ ወገን ደግሞ ገና ከሃጥያት ጋርና ከሞት ጋርም የሚታገሉ ሰዎች ናቸው፡፤ ሁለቱም በአንድ ጊዜ እውነት ናቸው; ከዚህ የተነሳ፤ ሁለቱንም በውጥረትና በሚዛን አለመያዝ መዘዙ ከባድ የሆነ ስህተት ውስጥ ቤተክርስቲያን ትገባለች። ለዚህ ደግሞ አሁን ያለንበት ግራ የተጋባና ውሉ የጠፋ የሚመስለው አስትምህሮቶቻችን ምስክር ነው፤ እኛ አንኳ ብንክድ። እውነተኛ አምልኮና የቤተክርስቲያን አገልግሎት እነዚህን ማገናዘብ አለባት። እስኪ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ላሉ “በመከራ፤ በታላላቅ ስቃይ፤ ግራ በመጋባት፤ በሐዘን፤ በቁጭት፤ በከባድ የአይምሮ ጭንቀት፤ በፈረሰ ትዳር..ወዘተ…” ላሉ አማኞች ቤ/ያንችን አገልግሎቷ ምንድር ነው? “ዘራፍ ዘራፍ” ከሚለው የወትሮ ፉከራ ውጪ ማለቴ ነው። ከእነርሱ ጋር ክርስቶስ ሃጢያታችንን እንደተሸከመ እና ውርደታችንን የራሱ አንዳደረገ፤ “እኛም ከእነርሱ ጋር አብረን በመስቀሉ እግር ሥር ተደፍተን አብረን ይዘናቸው እንነሳ ይሆን?
► ድነትና የዘመን መጨረሻ
የዘመን መጨረሻ በክርስቶስ መጀመሪያ መምጣቱና በዳግም መምጣቱ መካከል ያለው እየተለጠጠ እስከሚመለስ ድረስ የሚዘረጋው ዘመን ሲሆን በዚህ የመጨረሻ ዘመን “የአሁን ክፉ ዘመን እና የወዲያኛው ዘላለማዊ ዘመን” ንብብሮሽ ነው (የሚቀጥለውን ይመ.)። ይህ ለአዲስ ኪዳን መሠረታዊ ነው። ወደ ወንጌላት ከመሔዳችን በፊት ጥቂት ከጴጥሮስና ከእብራውያን ወስደን የኋለኞች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንዴት በዚህ ዕይታ ጽሑፋቸው እንደተቃኘ በትንሹ እንመልከት።
1 ጴጥሮስ 1:3–5 ❝በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ (ἀποκαλυφθῆναι ἐν καιρῷ ἐσχάτῳ | …ካይሮ ኧስካቶ) ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ❞
1 ጴጥሮስ 1:19-20 ❝ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። እርሱ አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን አሁን ግን በመጨረሻው ዘመን (φανερωθέντος δὲ ἐπʼ ἐσχάτου τῶν χρόνων | …ኧስካቱ ቶን ክሮኖን) ስለ እናንተ ተገለጠ❞
እነዚህ ሁለቱም ጥቅሶች በአንድ መጽሐፍ ውስጥ (1ኛ ጴጥሮስ)፤ በአንድ ምዕራፍ ላይ (ም.1)፤ እና ስለ አንድ ርእሰ ጉዳይ (ስለ ድነት) ይናገራሉ። ጴጥሮስ “የዘመን መጨረሻ” የሚለውን ቃል በሁለት ዓይነት መልኩ (ዘመናት) ይገልጠዋል። የመጀመሪያው አጠቃቀም፤ “የመጨረሻ ዘመን” መዳናችን (በተዘዋዋሪ መንገድ ክርስቶስ ዳግም) የሚገለጥበት የወደፊት ቀን ሲሆን፤ ሁለተኛው አጠቃቀም ደግሞ ክርስቶስ ስለሓጥያታችን መስዋዕት ሊሆን የተገለጠበት (ሃላፊ ግሥ) (መጀመሪያ የመጣበት) ቀን ነው። ስለዚህ በሐዋርያው ጴጥሮስ አስተሳሰብ የመጨረሻ ቀን ሲል “ክርስቶስ በመጀመሪያ ከመጣበት ቀን ጀምሮ ዳግም እስኪመለስ ያለውን” ርዝማኔ ያመለክታል እንጂ አንድ በዘምን መካከል ያለ ወቅት አይደለም። ስለዚህ ጴጥሮስ ‘መዳናችንን በአንድ ወገን አሁን እየተቀበልን ነው’ (1:9) ሲለን፤ ደግሞም ገና “ወደ ፊት ሊገለጥ የተዘጋጀ ነውም” ይለናል (1:3)። ይህ በሁለት ውጥረት (ድነናል-እንድናለን) የሚለው አነጋገር የተመሠረተው ከዚህ የመጨረሻው ዘመን እውነታ የተነሳ ነው ማለት ነው።
የእብራውያንም ጸሐፊ እንዲሁ፤ ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም የተገለጠበትን ቀን “የዘመናት መጨረሻ” ይለዋል። ወረድ ብሎም “ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ” እንደሚታይም ይነግረናል።
(ዕብ. 9:25–28) ❝ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም; እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር; አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ (በዘመናት መጨረሻ) (ἐπὶ συντελείᾳ τῶν αἰώνων | ኧፒ ሱንተሌያ ቶን አዮኖን) ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል❞
እስከአሁን የተመለከትነው፤ የልጁና የመንፈሱ ወደ ዚህ ክፉ ዘመን ተልከው ከአብ ዘንድ የመጡ እለት ይህ ክፉ ዘመን እንዲፈጸም አድርጎታል (ገላ 4:4)። ይህ የአሁኑ ዘመን ተፈርዶበታል። “ይህ የአሁኑ ዘመን” አልቋል። እያንዳንዱ ቀን በእግር ኳስ ጨዋታ አነጋገር “ባለቀ ሰዓት” ውስጥ ያለ ኑሮ ነው። ዘላለማዊው ሐይል (የልጁና የመንፈሱ ተልኮ) ከዚህ ክፉ ዘመን ጋር እንዲነባበር ተደርጓል። ይህ የዘመን መጨረሻ ባህርይ ነው። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ እሥራኤል በምድረበዳ ይደረሰባት ተግሳጽ “የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ” ይለናል (1 ቆሮ 10፡11)። ወይም በዕብራዊያን “መልካሙን የእግዚአብሔር ቃልና የሚመጣውን ዓለም [ዘመን] ኀይል የቀመሱትን (6፡5)” በማለት የሚመጣውን የወዲያኛውን ዘመን ኃይል በዚህ በአሁኑ ክፉው ዘመን ሰዎች መቅመስ እንደ ጀመሩ ያስረዳናል። ይህም የሚያመለክተው ሁለቱ መነባበራቸውን ነው! ለዚህ ነው በአለም ሳለን መከራ እንዳለብን ነገር ግን ዓለምን ደግሞ አሁን አሸንፈችኋል የተባልነው! ሁለቱንም በውጥረት መያዝ አለብን። ሁሉቱም እውነት ናቸው።
ይህ መነባበር ግን ነብያት ያላዩት ሚስጢር ሆኖ የቆየ እውነታ ነው (ምንም እንኳ በዳን 2 ላይ በከፊል ቢገለጥም)። ኢየሱስም “ሁለቱም እስከ መጨረሻ ይደጉ ተዋቸው!” ያለው ለዚህ ነው። የሚከተለውን ሰዕላዊ መግለጫ ይመልከቱ (For more, see the seminal and pivotal work of George Ladd’s “The Presence of the Future: The Eschatology of Biblical Realism.”)
► የአሁኑና የመጪው ዘመን
ይህ ልጁ የተገለጠበት “የመጨረሻ ዘመን” የእግዚአብሔርን ሰዓትና የሰው ልጆችን ታሪክ በሁለት ዘመናት ከፈለ። ነብያት ይመጣል ብለው የተነበዩት “የጌታ ቀን” ይህም ታላቅ የመዳንና የፍርድ ቀን ደረሰ (ማር. 1:15) ነገር ግን አፈጻጸሙ ማንም ባልጠበቀው መንገድ ነው (ማቴ. 13)። ይህም ሚስጢር የተመሰረተው ሰማያዊ መንግሥቱ በዚህ ሐጥያት ሞትና ሰይጣን በሚሰለጥኑበት “የአሁን ክፉ ዘመን” (ገላ 1፡4) ውስጥ መገለጡና ሁለቱም አብረው መቀጠላቸው ነው። ለምን? ምክኒያቱም ክርስቶስ በመጀመሪያ መገለጡ የብረት በትርን ይዞ ሳይሆን “ሥጋን አዘጋጀህልኝ እነሆ ፈቃድህን ላደርግ ወረድሁ” አለ። የሰው ልጅ የመጣው ለብዙዎች ቤዛ ለመሆን እንጂ ለፍርድ አልነበረምና ነው (ማር 10:31)። ለዚህ ነው ደ/መዛ. እሳት ከሰማይ እናውርድ ባሉት ጊዜ ጌታ የገሰጻቸው። የክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት ተልዕኮ ደህነቱን ገልጦ ፍርዱን ማዘግየት ሲሆን ሁሉን በፍርድ ሥራ መጠቅለሉ ደግሞ በዳግም ምጽዓቱ ይሆናል (ከበጉ ቁጣ ሰውሩን የሚሉበት ቀን)። አሁን የእግዚአብሔር መንግስት በልጁ ትንሳኤና እርገት ተመርቃለሽ። ትሰራለች። ነገር ግን ልክ አንድ ዘሪ ዘርን እንደሚዘራ ናት። በአንዳንዱ ሕይወት ታፈራለች በሌሎቹ ደግሞ ትናቃለች።
ስለዚህ እግዚአብሔር በነብያቱ በዘመናት ፍጻሜ ይሆናል ብሎ አስቀድሞ የተናገረው “ቀን” በሁለት ዘመናት ተከፈለ ማለት ነው። ይህም የልጁ ሁለቱ መገለጦች ናቸው።
የልጁ ሁለቱ ምጽዓቶች የብሉይን ተስፋ በሁለት ዘመናት ክፍሎታል! ይህን ክርስቶስ እንደሚከተለው አስተምሮናል
ማቴዎስ 12:31–32 “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል; በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም [ዘመን] ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።’
ማር. 10:29–30 “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም [ዘመን] የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።
ሉቃ 20:34–36 “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። የዚህ ዓለም [ዘመን] ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፥ ያን ዓለም [ዘመን] እና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።
ከላይ እንዳየነው ክርስቶስ “ዘመንን” በሁለት መንገድ ያያል፤ “ይህ” እና “የወዲያኛው” ዘመን። የወዲያኛው ዘመን ዘላለማዊ ሕይወት ሙሉ የሰፈነበት፤ ከሙታን ትንሳኤ ባሻገር ያለ ሕይወት፤ ሁሉ ነገር የሚታደስበትና የእ/ር ሐሳብ በሙሉ የሚከናወንበት ዘመን ነው። በአጭር ከዳግም ምጻአቱ ባሻገር ያለው ዘመን ነው። ሆንም ከላይ እንዳየነው እግዚአብሔር ልጁንና መንፈሱን ስለ ላከልን፤ በዚህ ዘመን መጨረሻ የወዲያኛው ዘመን ሕይወት ተለጥጦ አሁን መቅመስ ጀምረናል። በክርስቶስ አገልግሎት የእግዚአብሔር መንግስት ተመርቃለች። የዚህ እንደምታ በአንድ እጅ አሮጌው ስርዓት እንዳለ ሆኖ ከአዲሱ ጋር መቀጠሉ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ መንግሥቱ አሁን በሃይል “እውን” ትሁን እንጂ (በልጁ የመጀመሪያ መምጣት) ነገር ግን ደግሞ ገና በሙልዓት ወደ ፊት የምትገለጥበት ቀን አለ (የልጁ ዳግም ምጻአት)። እስከዚህ ቀን ድረስ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በሙሉ በዚህ ውጥረት ውስጥ ተቃኝቷል።
► የእግዚአብሔር መንግስትና የዘመን መጨረሻ
❝ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና። ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ❞ ማር. 1:14-15
ክርስቶስ አገልግሎቱን የጀመረባት ቀን ማርቆስ “የዘመኑ ፍጻሜ/Πεπλήρωται ὁ καιρὸς | ፐፕሌሮታይ ሃ ካይሮስ” የደረሰበት ቀን ነው ይለናል። ይህ ቀን የመንግስቱ ጎህ የቀደደበት ቀን ነው። ማርቆስ ከኋለኞቹ ነብያት ሁለቱን፤ ኢሳያስና ሚልክያስን እንደ ደብተር ሽፋን በመጠቀም የመጥምቁ ዮሐንስን አገልግሎት የመጨረሻው መንገድ ጠራጊ ነብይ መሆኑ ሲያሳይ፦
“እነሆ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ (ሚልክያስ)፤ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ድምፅ’ (ኢሳያስ)”
በኢሳያስም ይሁን በሚልኪያስ ከመንገድ ጠራጊዎቹ በኋላ እየገሰገሰ የሚመጣው “ጌታ” የሚባለው ነው። የዚህ እንደምታ መጥምቁ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊ ከሆነና ከኋላ የሚመጣው ኢየሱስ ከሆነ፤ ኢየሱስ “ያህዌህ” ነው። “የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል (ሚል. 3:1)፤ “…የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል” (ኢሳ. 40፡5)
አሁን በዚህ በጨለማው ዓለም ውስጥ መሲሃዊ ልጁን በመበላክ የእግዚአብሔር መንገስት ተመርቃለች፤ ሆኖም ግን መንግሥቱ ሁሉን ልትጠቀልል ገና ትገለጣለች። ይህንን ለምሳሌ ማር 2 ላይ እንዲህ ይላል፡-
❝የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም። የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም አላቸው። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም። ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ። በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ❞ (ማርቆስ 2:18–22)
ክርስቶስ በምድር ሳለ የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ በሐይል ተገልጣ ነበር። ስለዚህ ደ/መዛሙርቱ መጾም አያስፈልጋቸውም። ምክኒያቱም መሲሐዊ ዘመን ስለፈነጠቀ። ነብያት ይሆናል ያሉት መሲሃዊ ድግስ መፈጸም ጀመረ ሆኖም ግን ፍርድ ዘገየ (here you have fulfillment without consummation) የኢየሱስ ደ/መዛሙርት በአዲሱ መሲሃዊ ዘመን ውስጥ ናቸው። መንግሥቱ በዙሪያው ላሉ ሁሉ ሠፍኗል። እውሮች እያዩ፤ አንካሶች እየዘለሉ፤ ሙታን እየተነሱ፤ ወንጌል ለድሆች እየተሰበከ ነው፡፤ ምክኒያቱም መሲሃዊው አዲስ ኪዳን ዘመን ፈነጠቀ፤ ገና ከሙታን ሳይነሳ ሞት ከእግሩ ሥር መቀጥቀጥ ጀመረ። አሁን መሲሃዊ ድግስ ነው። መብላትና መጠጣት የመሲሃዊ ግብዣ ምሳሌ በመሆኑ ንጉሱ እያለ ጾም ተገቢ አይደለም (ኢዮ 2 ላይ ይህ ተስፋ ተሰጥቷል)። ሆኖም ግን አሮጌው የሙሴ ኪዳን አልፎ አዲስ ኪዳን ስለሚመረቅ፤ አሮጌው የሕግ ሥርዓት ስለሚሻርና አዲሱ የመንፈስ ሕግ ስለሚደነገግ፤ እንደ ድሮው ሥርዓት መመላለስ አይችሉም። አሁን ንጉሱ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር እያለ መጦም አያስፈልጋቸውም። ሆኖም ግን አንድ ቀን “ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ” ይህ ማለት ክርስቶስ፤ ሙሽራው ከመካከላቸው ሲወሰድ ከዚህ ቀደም ወዳልነበረ እውነታ ውስጥ ስለሚገቡ መጦም ይጀምራሉ። ይህ እውነታ ሙሽራው ክርስቶስ መጥቷል ደግሞም ለሁለተኛ ጊዜ ይመጣል የሚል ነው…ይህን እውነታ ነው በውጥረት መያዝ ያለብን ያልኩት። ይህ ጾም በዚህ ምድራዊ ድንኳን ከብዶብን ማራናታ የሚል ጾም ነው። አዳኛችን ተመለስ…መድኅናችን ተገለጥና መዳናችንን ፈጽም የሚል ጩሀት ነው። ይህንን ዘመን ነው የመጨረሻ ዘመን የሚለው። ይህ ልጁ የተገለጠበት ዘመን ነው። እግዚአብሔር በብዙ መንገድ በብዙ ጎዳና በነብያቱ የተናገረበት ዘመን ሳይሆን፤ ይህ አሁን በልጁ የተናገረበት የመጨረሻ ዘመን ነው። መንፈሱ የተላከበትና ከነገድ ከቋንቋ አሕዛብ እየተቀደሱ በእምነት ወደሆነ መታዛዝ የሚቀደሱበት ዘመን ነው። መዳናችን በተሰጠን መያዣ እናረጋግጣለን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ይሄው መንፈስ ለቤዛ ቀን የታተምነበትም መንፈስ በሆኑ ፍጻሜ ገንዘቡ የሆንን ሕዝቦች ነን። አዲስ ኪዳን ይህንን እውነታ በዚህ ውጥረት ያሳየናል! በመስቀሉና በትንሳኤው እ/ር ቤተ-ክርስትያንን ያማጥናት!

