
ቁጣው ተወግዶልሻልና ተነሺ! – ክፍል አንድ
ይህ ልጠፋዬ፣ በክፍል ሁለት ላይ ለምለጥፈው፣ በኢሳ 51:17-23 ላይ ላተኮረው ሐቲት፣ መግቢያና መንደርደሪያ እንዲሆን ነው። የምንባቡን ይዘት በጥልቀት ለመረዳት እንዲያስችል፣ ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው ‹አጠቃላይ ምንባባዊና ጽሑፋዊ አውድ› በመስጠት ላይ ነው።
ከእግዚአብሔር እጅ፣ የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ፣ ዝቃጩ እንኳ ሳይቀር፣ ሰዎችን የሚያንገደግደውን ዋንጫ የጨለጥሽ፣ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ ተነሺ! ከወለደቻቸው ልጆች ሁሉ የሚመራት የለም፥ ካሳደገቻቸውም ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም። እነዚህ ሁለት ነገሮች ሆነውብሻል፥ ማንስ ያስተዛዝንሻል? መፈታትና ጥፋት ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንዴትስ አድርጌ አጽናናሻለሁ? ልጆችሽ ዝለዋል፤ ወጥመድ እንደተያዘ ሚዳቋ በአደባባይ ሁሉ ራስ ላይ ተኝተዋል፤ በእግዚአብሔር ቍጣና በአምላክሽ ተግሣጽ ተሞልተዋል። ስለዚህም ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፥ ይህን ስሚ፤ ስለ ወገኑ የሚምዋገት አምላክሽ ጌታሽ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሚያንገደግድን ጽዋ የቍጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ ትጠጪውም። ነፍስሽንም። እንሻገር ዘንድ ዝቅ በዪ በሚሉአት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ ጀርባሽንም ለሚሻገሩት እንደ መሬትና እንደ መንገድ አደረግሽላቸው (ኢሳያስ 51:17-23)
► መግቢያ
በኢሳያስ 51:17 – 23 ላይ ለጽዮን የቀረበላት “የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ ንቂ ንቂ!” የሚለው ጥሪ፣ ከምዕራፍ 51-55 ድረስ በሚዘልቀው ምንባባዊ አውድ ውስጥ ንዑስ ክፍል ነው። ከ51፡1-55፡13 ያለው ክፍል ደግሞ እንዲሁ፣ ከ49፡1 – 55፡13 ድረስ ላለው ወጥ ምንባብ (Discourse Unit) ሁለተኛው ንዑስ ክፍል ነው። ይኽም፣ እነዚህ 7 ቁጥሮች የሚያስተላልፉትን መልዕክት በትክክል ለመረዳት፣ የተገኙበትን ምንባባዊ ክፍል እና የምንባቡን የሐሳብ አፈሳሰስ መረዳት እጅግ ወሳኝ ነው። ስለዚህ፣ ኢሳያስ ከ49:1-53:12 ባለው ክፍል ውስጥ የሚተነብየው፣ የያህዌህ ባሪያ ስለሚያስገኘው የኅጢአት ሥርየትና ሥርየቱን ተከትሎ ስለሚገኘው ትድግና ነው። በአንድ እጅ ቂሮስ የሚያስገኘው ‘መፈታት’ (44:24-48:22) ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እንደምታ ያለው ሲሆን፣ በተጓዳኝ መልኩ ደግሞ ይህ የጌታ ባሪያ የሚቀዳጀው ትድግና (49:1 – 53:12) ‘ዓለም-አቀፋዊ’ እና ‘በኅጢአት ይቅርታ’ ላይ ያተኮረ ነው። የሐሳቡን ፍሰት እንደሚከተለው ማቅረብ እንችላለን።
◘ ያህዌህ ትድግናውን የሚገልጥባቸው አገልጋዮቹ (44:24 – 53:12)
‣ ቂሮስ፡ መፈታትን (44:24 – 48:22)
‣ አገልጋዩ፡ ሥርየትን (49:1 – 53:12)
◘ የድነት ግብዣ ለሰው ዘር ሁሉ (54:1 – 55:13)
‣ ግብዣ ለጽዮን (54:1-17)
‣ ግብዣ ለምድር ሁሉ (55:1-13)
ይህ ቢጋር (Outline) እንደሚያሳየን፣ ቂሮስ በምርኮ ላለው ሕዝብ ‘መፈታትን’ የሚያመጣ መልዕክተኛ ሲሆን፣ የጌታ ባሪያ ተልዕኮ (49:1-53:12) ደግሞ ያነጣጠረው ለሕዝቡ የኅጢአት ይቅርታን የሚያስገኝ ሥርየት በማስገኘት ላይ ነው (52:13 – 53:12)፣ ይኽም፣ በያህዌህ ቁጣ ሥር በምርኮ ላለው ሕዝብና ለአሕዛብ ሁሉ ሥርየትን ማምጣት ነው። ያህዌህ በባሪያው በኩል የድነትን ምንጭ በማፍለቁ ደግሞ “የድነት ግብዣ” ለዓለም ሁሉ ይቀርባል (54:1 – 55:13)።
- ግብዣ፦ “አንቺ መካን እልል በዪ…ልጆችሽ ይበዛሉና” (54:1)
-
ግብዣ፦ “እናንት የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ ያለ ገንዘብ ግዙ” (55:1)
ስለዚህ 49-55 ያለውን አበይት ክፍሎች እንደሚከተለው በአጭሩ ማስቀመጥ እንችላለን ማለት ነው።
- የጌታ ባሪያ ድርብ ተልዕኮና ለተሰጠው ጥሪ ታዛዥ መሆኑ (49:1-50፡11)
- ድርብ ተልዕኮው (49:1-50:3) “የያዕቆብን ነገዶች እንድታስነሣ ከእስራኤልም የዳኑትን እንድትመስል ባሪያዬ ትሆን ዘንድ እጅግ ቀላል ነገር ነውና እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ ይላል (49:6)”
- የባሪያው ምላሽና ቁርጥ ውሳኔ (50፡4-11) “ጀርባዬን ለገራፊዎች ጕንጬንም ለጠጕር ነጪዎች ሰጠሁ፥ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም። ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛልና ስለዚህ አልታወክሁም፤ ስለዚህም ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌዋለሁ፥ እንዳላፍርም አውቃለሁ” (50:6–7)
- ለጽዮን ምላሽ እንድትሰጥ የቀረበ ጥሪ (51:1 – 52:12) ጽዮን ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ንቂ፥ ንቂ፥ ቁሚ (51:1፣ 51:4፣ 51:7፣ 51:17፣ 52:1፣ 52:11)”
- የጌታ ባሪያ ኅጢአት መሸከሙ፣ ማስተሰረዩ እና መከናወኑ (52:13 – 53:12)
- የድነት ግብዣ ለዓለም ሁሉ (54:1 – 55:13)
- ► ስለዚህ በዚህ አውድ ሥር፣ “ቁጣው ተወግዷልና ተነሺ!” የሚለው ጥሪ (51:1-52:12) እና “ኑ! በነጻ ግዙ!” የሚለው፣ ድነትን በነጻ የመቀበል ግብዣ (54፡1-55፡13)፣ ለአንባቢው ያልረገበ ውጥረት ይፈጥርበታል። እንዴት ‹የቁጣው ዋንጫ ተወገደ?› ‹ለምንስ ድነት ለሰው ሁሉ በነጻ ቀረበ?› ኢሳያስ በአስደናቂ የአጻጻፍ ስልቱ መልሱን በመሃል (52:13 – 53:12) ሻጥ ያደርገዋል። የሐሳቡን አወቃቀር እንደሚከተለው እንመልከት።◘ [1] ማዳኑ እንደቀረበና ቁጣው እንደተወገደ የሚያበስር ጥሪ (51:1 – 52:12)
◘ [2] የጌታ ባሪያ የሥርየት ሥራ (52:13 – 53:12)
◘ [3] የድነት ግብዣ በነጻ (54:1 – 55:13)
ጥያቄው፦
- ተስፋ-አዘል ጥሪ ለምን (51:1-16)?
- “የቁጣው መዓት ዋንጫ” መወገዱስ በምን ምክንያት (51:17-52:12)?
- ግብዣውስ ለምን (54:1 – 55:13)?
ኢሳያስ በጣቱ እየጠቆመ የሚሰጠን መልስ “እነሆ፥ ባሪያዬ” የሚል ነው፦
“እነሆ፥ ባሪያዬ በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል (52:13)” የሚል ነው!
ሃሌ ሉያ!! ይህ የጌታ ባሪያ ራሱን የኅጢአት ሥርየት አድርጎ በማቅረቡ፣ ቁጣው ተወገደ፣ ድነት በነጻ ለሰው ሁሉ ግብዣ ሆኖ ቀረበ። ምክኒያቱም ባሪያው ሥርየትን አስገኝቷልና ነው (52:13 – 53:12)። ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ፣ ኢሳያስ ይህንን መልስ የሚሰጠን፣ ጽሑፋዊ አወቃቀሩን የተመለከትን እንደሆነ ብቻ ነው። በሌላ አባባል፣ ኢሳያስ በዚህ መልኩ ጽሑፉን በማዋቀሩ መልዕክት እያስተላለፍለን ነው። ለዚህ ነው፣ ጽሑፋዊ መዋቅሩን ልብ ብለን ማጤን ያለብን።
ስለዚህ፣ ኢሳ 51:17-23 ያለው በትንሹ፦ ከ51:1-52:12 ድረስ በሚዘልቀው አውድ ክፍል ውስጥ ይገኛል። ይኽም ንዑስ ክፍል፣ የያህዌህ ማዳን እንደቀረበ በሚያበስረው ክፍል (51:1-16)፣ ቁጣው እንደተወገደላት (51:17-23)፣ ከመወገዱም የተነሳ፣ ሰንሰለቷ ከአንገቷ እንደምታወልቅ፣ በትቢያ ፈንታ የንግሥናና የቅድስና አልባሳትን እንደምትደርብ (52:1-6)፣ ሕዝቡን ከግብጽ ሲዋጅ እንደነበረው አሁንም ያህዌህ ዳግም-ጸአት እንደሚያመጣና በቀስታ እየመራ ሕዝቡን ከባርነት ቀንበር እንደሚያላቅቅ (52:11-12) ያውጃል። ይኽ እንዴት ይሆናል? ኢሳ 52:7-10 ያለው እና ኢሳ 52:12-53:12 ያለው ክፍል ያብራሩልናል።
► (1) በኢሳ 52:7-10 አውድ ውስጥ፣ ያህዌህ ከሰፈር ውጪ ራሱ ጠላቶቹን ይዋጋል፦ “የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፥ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ (52:10)” ይላል። ፈርጣማው የያህዌህ ጡንቻ ይገለጣል። ሸሚዙን ይሰበስባል። ይህ ብርቱ፣ ፈርጣማ ጡንቻውም ማዳንን ያመጣለታል! በዚህ አውድ ውስጥ “ክንዱን ያያሉ” የሚለው አዎንታዊ የሆነ የአነጋገር ዘዬ ነው። ያያሉ የሚለው፣ ክንዱን ይቀምሳሉ፣ ይለማመዳሉ ወይም “የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ” ማለቱ ነው። ይህ የበረታ ክንዱን የቀመሱ ይድናሉ። ስሙ ይባረክ። ኀይሉ ያድናል። ሐዋሪያውም ሲናገር “በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው (ሮሜ 1:16) እንዳለን ነው። ከኅጢአት በሽታና ከዓመጽ አጸፋ መዓት ይድናሉ። እነዚህ ብርቱ ጡንቻዎች፣ ሰማያትን የዘረጉ፣ ተጋጥመውም በእፍኝ ውኆችን የሰፈሩ እጆች፣ በቀራንዮ ላይ ተዘረጉ! እሰይ! እንኳንም ሊያደቀን አልተዘረጉ! ቢሆን ኖሮ ከትቢያ ጋር እንደተደባለቅን ለዘላለም በቀረን። አሁን ግን እነዚያ ብርቱ ክንዶች መድሃኒትን ስላመጡልን፣ ከሞት እንቅልፍ የሚያነቃ ሥራ ስላስገኙልን “ተነሺ! ተነሺ! (51:17)፣ ንቂ! ንቂ! (52:1)፣ ውጡ ውጡ (52:11)” የሚል ድምጽ ከሞት ሰመመን ውስጥ ሆነን አደመጥን። ምክኒያቱም እነዚያ ብርቱ ክንዶች በመስቀል ላይ ስለ ተዘረጉ። ምክኒያቱም “የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት” ስለ ገለጠ። ስለዚህ የመጀመሪያው ማብራሪያ (52:7-10) የሚያሳየን ክንዱ፣ ታዳጊ ንግሥናውን ወይም መዳን ያለበት መንግሥቱን (52፡7) እንደገለጠ ነው። ይህ ወደ ሁለተኛው ማብራሪያ ይወሰደናል።
► (2) በኢሳ 52:13-53:12 ያለው ክፍል እንዲሁ፣ በቁጣው መዓት ፈንታ (51:17-23)፣ ቅድስና (52:1-6) እና ነጻነት (52:11-12) “እንዴት ሆን?” ደግሞም ማዳኑ እንዴት በነጻ ለሰው ዘር ሁሉ “ግብዣሆነ? (54:1-55:13)” ለሚሉት ጥያቄዎች ሁለተኛውን ማብራሪያ ይሰጠናል። ይህ ክፍል ከመጀመሪያው ማብራሪያ ጋር “ክንድ” በሚለው ቃል ሐሳባቸው ተጣምረዋል። በኢሳ 53:1 ላይ “የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል?” በማለት፤ ያህዌህ ድነት የሚገኝበትን ድል የተቀዳጀበት ክንድ፣ የባሪያው ክንድ መሆኑን ያሳየናል። በባሪያው “ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” (53:5–6)።
ከዚህ ሥራ የተነሳ፣ ለአለም ሁሉ ጥሪ ይቀርባል። ጥሪው “ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ” ይላል፣ “ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም…ግዙ።” የሚለው “ያለ ገንዘብ…ግዙ” ነው። ያለ ገንዘብ በነጻውሰዱ አይልም። ይህ ኢሳያስ ደግሞ ደጋግሞ የሚጠቀመው የአነጋገር ስልት ነው። ምንም እንኳ ይህ ድነት ለእኔና ለእናንተ የምንቀበለው በነጻ ቢሆንም (ያለ ገንዘብ)፣ ነገር ግን “ዋጋ” የተከፈለበት በመሆኑ (የጌታ ባሪያ የምትክ-ስቃይ ሞት) “ያለ ገንዘብ…ግዙ” ይላል። ሒደቱ ግዢ ነው እንጂ “በጎ አድራጎት” አይደለም። ይህ ድነት ያህዌህን ዋጋ አስከፍሎታል። የኅጢአት ይቅርታው በነጻ ቢሰጠንም፣ ኅጢአታችን ግን ባሪያውን ነፍስ አስከፍሎታል።
ሰለዚህ “ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፥ ይህን ስሚ እነሆ፥ የሚያንገደግድን ጽዋ የቍጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። (51:21 22)
እንግዲህ ኢሳ 51:17-23 ያለው ንዑስ ክፍል የተገኘበትን ምንባባዊ አውድ (51:1-53:12) ከሞላ ጎደል አውዳዊ ምልከታው ይህንን ይመስላል። አሁን ጠለቅ ብለን፤ በጠባቡ ኢሳ 51:17-23ን ለመተንተንና ወደ ሕይወታችን ለማዛመድ የምንችልበት ሥፍራ ላይ ቆመናል። (ይህ ትንታኔ በክፍል ሁለት ይቀጥላል)

