Articles,  Blog,  የመጽሐፍ ቅዱስ አፈታት,  የአዲስ ኪዳን ሐቲት,  ፍታቴ/ Exegesis

ስለ አፈታት ጥቂት፡ ከምንባቡ ይዘት ጋር በቅርበት መተዋወቅ


ለአንዳንዶች ይጠቅም ስለሚችል፤ በአንድ ምንባብ ላይ ያተኮረ ትምህርት/ስብከት ሳዘጋጅ ወይም ጽሑፋዊ ሐቲት ስጽፍ፣ ጽሑፋዊ ዓውዱን ለማግኘት የምከተለው ቅደም ተከተል ከሞላጎደል በጥቂቱ እነሆኝ። መጠነኛ የቋንቋ ስልጠና ለወሰዱ ደግሞ አንዳንድ ይጠቅማሉ ብዬ ያሰብኳቸውን መርጃ መጻሕፍቶችንም እጠቁማለሁ ።ከዚህ ቀጥሎ የማሰፍረው በተከታታይ አለፍ አለፍ እያልኩ ስለ ምንባብ አተታተት የማቀርበው ይሆናል። የሚከተለው የመጀመሪያው መርህ ነው።


#አንደኛ፡ ከምንባቡ ይዘት ጋር በቅርበት መተዋወቅ

ወፍ በረር ትውውቅ (Big Picture Reading)

  1. የምንባቡን ወሰን ማወቅ። «ምንባባችን የት ጀምሮ የት ያበቃል?» የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል። አማርኛ አንባቢዎች የምንባባችንን አወቃቀር (outline) ወደ ሦስት የሚጠጉ ማጥኛ ጽሑፎችን (Study Bibles) ወይም ማብራሪያዎችን ማወዳደር ተገቢ ነው። መጠነኛ የቋንቋ ስልጠና ለወሰዱ ደግሞ ንባባዊ-ትንታኔ የሚያደርጉ (Discourse Analysis) ሥራዎችን ማመሳከር ይገባል። ለምሳሌ 1 ቆሮ. 1፡23 ስናጠና የምንባባችን ዋና ክፍል ወሰኑ ሊሆን የሚገባው 1:18-25 ነው። ሆኖም ሰፊው ምንባባዊ አውድ ግን ከ1:10 ጀምሮ እስከ 2፡5 ድረስ፣ ሰፋ ሲል ደግሞ እስከ [2:16] -› [3:23] -› [4:21] ድረስ የሚዘልቅ ነው። ይህን ማወቃችን የንባባችንን ወሰን እንዲሁም ተገቢውን አውድ እንድናገኝ ከመርዳቱ ባሻገር፣ በየሳምንቱ የስብከታችንም/ጥናታችን ርዕስ ምን እንደሆነ እየወሰንም ጭምር ነው።
  2. ደጋግሞ ማንበብ፦ ለምንባባችን አሁን ወሰን ካበጀን በኋላ፣ ይህንን ክፍል ደጋግሞ በማንበብ ከይዘቱ ጋር መተዋወቅ።
  3. ዙሪያዊ ዓውዱን መቃኘት፦ (የት ነኝ፤ ከየትመጣሁ ወዴትስ እየሔድሁ ነው?)፦ እያነበብን ሳለን ከምንባባችን አንቀጽ ቀድሞ የነበረውንና ቀጥሎ የሚመጣው አንቀጽ ዋና መሪ ሐሳባቸው ምን እንደሆነ ግምት ውስጥ ማስገባት። ዓላማችን ይህ ምንባብ ከቀደመውና ከሚመጣው ጋር በሐሳብ እንዴት እንደሚያያዝና ምንባባችን ምን አይነት አስተዋጾና የሐሳብ ጥምረት እንዳለው ለመመልከት እንዲረዳን ነው ። ይህንን ስናደርግ ግን የጥናታችን ትኩረት ወደ እነዚያ አንቀጾች እንዳይሔድ መጠንቀቅ አለበን። አላማችን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሰፈረውን የጸሐፊውን መልክት ለመጨበጥ ሲሆን የምንባቡ ፍሰቱ ከየት መጥቶ ወዴት እየሔደ እንደሆን ማወቅ የመጀመሪያው ጥረት ነው።

የቡና ሻይ ትውውቅ (Close reading)

ከምንባባችን ጋር በቂ ትውውቅ ካደረግን በኋላ፤ አሁን ቁጭ ብለን ጠለቅ ያለ ምልከታ ለማድረግ የመጀመሪያውን ርምጃ እንወስዳለን፡፡ ለዚህም፦

(1) አማርኛ አንባቢ፡-

በእጅ ክፍሉን መገልበጥ። ዓላማው ራሳችንን «ዝግ» ለማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግመን ያነበብን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን፤ አዕምሮአችን «ተርርርር» ብሎ ይሸመጥጣል። ብዙ ጊዜ ጠለቅ ላለ ምልከታ እንቅፋት የሚሆንብን ይህ “መላመድ” ነው። ለዚህ በእጅ መገልበጥ ዝግ እንድንልና እያንዳንዱን ፊደል ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ወደ ጥናት ደብተራችን ስናሰፍር «እያንዳንዱን ቃል፤ መስተዋድ፣ ዘይቤያዊ አነጋገር፣ የተደጋገሙ ቃሎች፣ ምጸታዊ አነጋገሮች ወዘተ…» ልብ እንድንል «ግድ» ይለናል። ይህን ስታደርግ/ጊ በፊትህ/ሽ ለማመሳከሪያ ሌላ ዓይነት ትርጉም ይኑር። ይህ ትርጉም እንዴት ከምትገለብጥበት ትርጉም ጋር እንደሚለይ አጢን። መሰረታዊ ልዩነት ስታዪ፣ ቆም በዪ። ልዩነቱ ጎላ ብሎ ከታየሽ፣ 2-3 የእንግሊዝኛ ትርጉሞችን ማመሳከር። ልዩነቱ አሁንም ጎላ ካለ በቀይ ቀለም አስምረሽ እለፊው። ኋላ ማብራሪያዎችን ወይም በዋናው ቋንቋ የተደረጉ ስራዎችን ታመሳክርበታለህ።

(2) መጠነኛ የቋንቋ ስልጠና ለወሰዱ፦

በቀጥታ ከግሪክ\እብራይስጥ ወደ አማርኛ መተርጎም። ይህንን የምናደርገው የራሳችንን ትርጉም ለመስራት ሳይሆን (ወይም “የግሪኩ ቃል እዚህ ጋር እንዲህ ይላል!” ለማለትም አይደለም! ወይም “እዚህ ጋር አማርኛው ተሳስቷልማ” እግዚአሔር አያድርገው! በፍጹም አይደለም) ከቃሉ ጋር ቀጥተኛ ትውውቅ ለማድረግ ነው (ይህ ምን እንደሚመስል ከሥር አብራርቼዋለሁ)። ይህ የራስ ትርጉም በስብከት ሰዓት ግልጋሎት ባይውል እጅግ ይመከራል፡፡ የዚህ አላማ ሰባኪውን እንዲረዳው እንጂ ስብከት እንዲሆን አይደለም፡፡

➦ ዋና ቁም ነገር

ይህንን የምናደርገው፤ እኔን እና እናንተን – የቃሉን አገልጋዮች – ጥርት ያለ በቂ ግንዛቤ እንድንጨብጥ እንዲረዳን እና በሐሳባችን ውስጥ ቃሉ ግልጽ እንዲሆን ነው። ይህ ሁሉ ምልከታ በስብከትና በትምህርት ውስጥ ፍሬው ይወጣል እንጂ አይታዩም፡፡
አንድ የተቀበልኩት ጥሩ ምክር “በሰባኪው ልብና አዕምሮ ውስጥ ንባቡ ግልጽ ካልሆነ፤ ስብከቱም እንዲሁ ግራ የሚያጋባና ግልጽነት የጎደለው ይሆናል” ለዚህ ነው እንዲህ መድከም ያለብን። [ግልጽ መረዳት = ግልጽ ስብከት]

ይህ መርህ በተግባር

ለምሳሌ በቅርቡ ላዘጋጀሁት ጽሑፍ፦

  • መጀመሪያ ደጋግሜ በሚመቸኝ ትርጉም 1 ቆሮንቶስ 1:10 – 2:5 አነበብሁት።
  • ሁለተኛ ምንባቡን በሐሳቡ ቅደም-ተከተሉ ከፋፈልሁት (1 ቆሮ. 1:10-17; 1:18-25; 1:26-31; 2:1-5)
  • እያንዳንዱን ክፍል ተራ በተራ፤ ከግሪክ ወደ አማርኛ ተረጎምኩት (1 ቆሮ. 1:10-17)። ይህን ማድረጌ መንፈስ ቅዱስ በሐዋሪያው በኩል ላስቀመጠልኝ ለእያንዳንዱ ቃል ዝግ ብዬ እንዳስተውል ግድ ስለሚለኝ ነው። ሌላው በጣም እየረዳኝ ያለው፣ ቀዳሚው ትርጉም ላይ ለምሳሌ፣ ከዚህ ቀደም አማርኛ ቋንቋዬ ሆኖ ያላስተዋልኩትን አንዳንድ ነገሮች እንዳስተውል አድርጎኛል። ከዚህ የተነሳ አስፈላጊ ሳይሆን “የግሪኩ ቃል” እንዳልል ይረዳኛል። ምክኒያቱም ይህ “በግሪኩ” ላይ የማየው ቃል፤ ጸጉሩን ለውጦ በሐገርኛው ተተርጉማለች። ይቺ የአማርኛዋ ቃል (ወይም ቅንጣት) ምን እያደረገች እንደሆን ለአድማጪዬ ከለገለጽኩለት በቂ ነው፡፡ አድማጪዬ መጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ የሌለውን ነገር «እይ» እያልኩ ስገልጥለት ከመዋል ያድነኛል። ስለዚህ ከዋናው ቋንቋ ወደ አማርኛ ስተርጉም፤ በግሪኩ ወደ ፊት በማስቀመጥ “ጎላ” የተደረገው ቃል፣ አንዳንዴ ከአማርኛችን ቋንቋዊ የስዋስው ስርዓት የተነሳ ወደ ሁላ ተሰልፏል። ያንን በስብከቴ “ድምጼን ጎላ”፤ ወይም በጽሁፍ ደመቅ አደርገዋለሁ። ለምሳሌ በአማርኛችን ላይ “የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና” ብሎ ቃሉ ሲያልቅ “ና” የምትለው የአማርኛችን ቅንጣት ግልጋሎቷ ምንድር ነው? ወይም ደግሞ “ጳውሎስ ስለ እናንተ ተሰቀለን?” ሲልስ ይህች “ን” ምን እያደረገች ነው? ለምን “ጳውሎስ ስለ እናንተ ተሰቀለ?” ብቻ አይልም ነበር። እንዲሁም እያንዳንዱ ቋንቋ የማይተረጎሙ ቃላቶች አሉአቸው። “ቅንጣት” እንበላቸው/ Particles። እነዚህ ጸሐፊው ሊያስተላልፍ ለወደደው ሐሳብ ግልጽነት ይሰጡታል። ለምሳሌ በግሪክ ቋንቋ «አንድ እንዲህ» አንድ ደግሞ «እንዲያ» የሚል ነገር መናገር ስጀምር “መን….” በሚል ቅንጣት ይጀምርና ከዚያ የተቀረው ሁለተኛውን አንቀጽ መጀመሩን ለማመልከት ደግሞ “ደ…” በሚል ቅንጣት አረፍተ ነገሩን ይጀምራል። እነዚህ አይተረጎሙም ቅንጣቶች እንጂ ቃላቶች አይደሉምና። ይህንን በስብከቴ ይሁን በጽሑፍ ግን “በአንድ እጅ……[እንደዚህ]… በሌላ እጅ….[እንደዚያ]…” ካልኩኝ በበቂ ሁኔታ ሐሳቡን ለአድማጪዬ አስተላልፌለታለሁ። ለምሳሌ፡ «[መን] እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ…[ደ] ከእኔ በኋላ የሚምጣው ግን…» እዚህ ጋር ማቴዎስ “መን” የሚለውን ቅንጣት ተጠቅሟል። ይህቺ ቅንጣት “ቆየኝ እሺ አልጨረስኩም…የሚመጣ ዋና ነገር አለኝ ታገሰኝ” ለማለት ታገለግላለች። በስብከት፤ ግራ ጣቴን ካወጣሁ ይቺን ቅንጣት እየገለጽኳት ነው። ከዚያም በቀኝ ጣቴ ደግሞ ደመቅ አድርጌ «ከእኔ በኋላ የሚምጣው ግን…» በማለት ክርስቶስን እያጎላሁ አብራራሁ ማለት ነው። ግሪኩ ሳልል ግሪኩን ገለጽኩኝ እንደማለት ነው። ይህንን እና የመሳሰሉት በማድርጌ የማነበውን የእግዚአብሔርን ቃል መልክቱን በጥንቃቄ ጨብጬ ለቅዱሱ የእ/ር ህዝብ እንዳስተላልፍ ይረዳኛ። ለአማርኛ አንባቢዎች “የእ/ርን ቃል ለማንበብ የሚወድ ሁሉ ምክሬ ስዋስው ቢያቅለሸልሻችሁም ልመዱት…ጥሩ መድሐኒት ነው» ባይ ነኝ። እነ “ና” እነ “በ’ ወዘተ ትልቅ መለኮታዊ እውነት ይዘዋል። “በእርሱ..ለእርሱ…” የሚሉት መስተዋድዶች «በ» እና «ለ» መጽሀፍ የሚሆን ትንታኔ ውስጣቸው አለ። አንባቢው ዝግ ብሎ ካስተዋለው።
  • ይህንን ካደረግሁ በኋላ፤ የራሴን ትርጉም ከግሪኩ ስዋስዋዊ አወቃቀር አንጻር ከተሰሩ ስራዎች ጋር አመሳከርኩት (ምስሉን ይመልከቱ፡፤ እነዚህ ሁለት ስራዎች በጣም ረድተውኛል)። እያንዳንዱ ቃል ግልጋሎቱ ምንድር ነው? ለአረፍተነገሩ ሙሉ ሐሳብ ምን አይነት አስተዋጾ እያበረከተ ነው? የሚሉትን ጥያቄ እየጠየኩ እና እየመለስኩም ነው ማለት ነው። በምንባቤ ውስጥ ላሉት እያንዳንዱ አረፍተ ነገር እንዲህ አድርጌ ከጨረስኩ በኋላ
  • የንባቡን ጽሑፋዊ ቅንብር እመለከታለሁ (Discourse Analysis)። ይህም በቃልና በአረፍተነገር ደረጃ የተገነዘብኩት ተያይዞ እንዴት በምዕራፋትና በአንቀጻት ደረጃ ተወቃቅሮ «ምን አይነት “መልዕክት” እያስተላለፈ ነው?» የዚህስ መዋቅር አስኳልና እምብርት ምንድር ነው? ይህን ማድረግ ወሳኝነቱ፤ አንዳንድ ጊዜ የምንባቡ ዋና-ዋነኛ የሆነውን መልክት ትተን፤ መልክቱን ለማስተላለፍ በከበቡት አጃቢ ሐሳቦች ላይ ትኩረት አድርገን ቁምነገሩን ስለምንዘነጋ ነው። ይህንን ማድረግ ያንንም አለመዘንጋት ተገቢ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.