
መስቀልና ዙፋንን ያማጠንች ቤተክርስቲያን (መስቀልና ዙፋን – ክፍል 1)
ክራር-ነክ ሙዚቃ መሳሪያዎች በየጊዜው መቃኘት አለባቸው። እያንዳንዱ ክር ትክክለኛ ቅኝቱን እስኪይዝ ድረስ በሁለት ጥግ ተወጥሮ ይቃኛል። የረገበ ክር ዜማ አይደረድርም። አንዷ ክር በግማሽ ወይም በሙሉ ኖታ እንኳ ወጣ ወይ ወረድ ብትል፤ የዜማ መርህ ስለሚጣረስ ጥዑም ቅኔን መደርደር አይችልም። ስለዚህ ተጨዋቹ መሳሪያውን መቃኘት አሊያም ቅኝት የሚያውቅ ሰው ጋር በመውሰድ ማስቃኘት ይኖርበታል።
ቅኝታችን ታድያ ምን ይመስላል?
ልክ እንዲሁ ከላይ በሰፊው እንዳተትን፤ ወንጌላችን በክርስቶስ መምጣትና ዳግም መምጣት ተወጥሮ በትክክል የተቃኘ ቃል ነው። ከዚህ “ውጥረት/tension” የተነሳ “መዳናችን፤ ተስፋችን፤ ልጅነታችን፤ በረከታችን፤ አላማችን፤ ቅድስናችን..ወዘተ…” ልክ እንደ እያንዳንዱ የክራር ክሮች “በክርስቶስ መምጣትና ዳግም ምጻት” ቅኝት ይዘዋል (inaugurated eschatology)። ክርስቶስ ከሰማያዊ ሥፍራ (በአባቱ ቀኝ) ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት፤ በዓለም ዙሪያ ላሉ ህዝቦችና በአየሩ ላይ ላሉ አለቆች ይህ ብዙ ገጽታ ያለውን የማዳን ቃል በታላቅ ዜማ የሚደረድረው አካሉ በትክክል መልዕክቷንና ሕይወቷን በዚህ ውጥረት የቃኘች እንደሆን ብቻ ነው። ወንጌል የሚሰጠን ክርስቶስን ነው (ሮሜ 1:1-4)። እንዲያውም “የተሰቀለ ክርስቶስ/ንጉስ – a crucified Messiah”። ይህ ለአይሁድ መሰናክል ለግሪኮች ደግሞ ሞኝነት ነው። አብሮ የማይሔዱ እውነታዎች ናቸውና። ንጉሥ ይነግሳል እንጂ እንደ ወንጀለኛና እንደ ደካማ ባሪያ አይሰቀልም። ወንጌል ግን ሐይልንና ድካምን፤ ክብርንና ውርደትን፤ ዙፋንና መስቀልን፤ አንድ ያደርጋል። በወንጌል አማካይነት ክርስቶስን በመስቀል ድካም የተመረቀ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አናየዋለንና!
ይህ በመስቀልና በዙፋን የተመጣጠነ ሚዛናዊነትን ካለመጠበቅ የተነሳ፤ ቤተክርስቲያን በታሪኳ ውስጥ ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎች ሲነሱ አይታለች። ይህ ማለት፤ በአንድ እጅ በእውነት ድነናል በሌላ መልኩ ደግሞ ገና ሙሉ በሙሉ መዳናችን አንድ ቀን እንደሚገለጥ በሚዛን አለመያዝ ነው። በእነዚህ ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች ውስጥ፤ ስለ ሦስት አይነት አመለካከቶችን እንዳኛለን፡፡ ሁለቱ የተዛነፉ ሲሆኑ ሦሥተኛዋ ግን የክርስቶስ ሙሽራ ናት። በአዲስ ኪዳን ደብዳቤዎች ላይ እነዚህ ሁለት ጽንፈኛ አመለካከቶች ለትምህርታችን ተጽፈውልናል። ለምሳሌ ያህል አድርገን በተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን ውስጥ እና በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ አማኞችን እንደ ናሙና አድርገን እንውሰድ።
በሽሽት ላይ ያለችው ቤተክርስቲያን! (Under-Realized Eschatology)
ይህ የመጀምሪያው ጽንፈኛ መንፈሳዊነት የመነጨው፤ “ገና ወደ ፊት” በሚገለጠው መዳን ላይ ጤናማ ያልሆነ ትልቅ አጽንዖት አድርጎ “አሁን የተመረቀውን ታላቅ መዳን” ግምት ውስጥ ባለማስገባቱ ነው። እንዲህ ዓይነቷ ቤ/ያን አጉልታ ገና የሚሆነውን ትጠባበቃለች እንጂ፤ አሁን በክርስቶስ ሙታን በመነሳት በተመረቀው መዳን ላይ አትኩሮት አታደርግም። “ኢየሱስ ይመጣል” የሚለውን መልዕክት ጤናማ ባልሆነ መልኩ ትሰብካለች። ይህም ከመደጋገሙ የተነሳ አማኞቿ እጅና እግራቸውን ሰብስበው በፍርሃት ይጠባበቃሉ። ለእርሷ የክርስቶስ ዳግም ምጻዓት፤ ለአሁኑ መንፈሳዊ ሕይወት ብዙ እንደምታ የለውም። አሁን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በሚሰራው የትንሳኤ ጉልበት ላይ “እፍር” የማለት ስሜት የሚሰማት ቤተክርስቲያን ናት። በሃይል የምትናጠቅ አትምስልም። ጥግ ይዛ የክርስቶስ መምጫ የምትጠባበቅ ነች። ከአጋንንት ጋር ባላት ግብግብ ወደ መሃል ገብታ በእ/ር ሐይል በወንጌሉ ቃል ጉልበት ከመፋለም ይልቅ ዳር ይዛ “ማራናት የምትል” ቤተክርስቲያን ናት። አንድ ቀን ቆይ ትላለች። በተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን ውስጥ ግልጽ ሆኖ የሚታየው አንድ ችግር፤ (ወይ የጳውሎስን ትምህርት ካለመረዳት፤ በተለይ ምናልባት በትንቢትና በስህተት ትምህርት ምክኒያት ሊሆን ይችላል፤ 2 ተሰ 2፡2-3) የጌታ መምጫ ደርሷል ተብለው የአሁኑን ኑሯቸውን ያጓጓሉ አማኞች የሚኖሩባት ከተማ ትመስላለች (ምንም እንኳ ምን ያህሉ እንደዚህ እንደነበሩ ለመናገር ቢያዳግትም)። ከዚህ የተነሳ ሊሆን ይችላል እንዳንዶች ጌታ ሊመጣ ነው ተብለው ሥራቸውን አቁመው፤ በድጎማ መኖር የጀመሩና ከሥራ ፈትነታቸው የተነሳ ደግሞ በሰው ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የሚያስቸግሩ አማኞች ያሉባትም ቤተክርስቲያን የሆነችው። ስለዚህም፤
❝በመንፈስ መገለጥ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደ ተላከ መልእክት የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ ፈጥናችሁ ከአእምሮአችሁ አትናወጡ፤ አትደንግጡም። ማንም ሰው በምንም መንገድ አያታላችሁ፤ አስቀድሞ ዐመፅ ሳይነሣ፣ ለጥፋት የተመደበውም የዐመፅ ሰው ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና❞
ስለዚህ በአጭሩ ይህ አይነት አማኝ የበዙባት ቤተክርስቲያን፤ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቶ “አሁን” በግርማው ቀኝ “በተመረቀ መንግሥት” እየሰራ እንደሆን ያልገባት ቤተክርስቲያን ናት። ለዚህች ቤ/ያን የሚሰበክላት ኢየሱስ በክብር “ጌታና ክርስቶስ ሆኖ መሾሙን፤ መቀመጡን” ነው። መምጣቱን የምትጠባበቀው ሸሽቶ በመቀመጥ ሳይሆን፤ በአደባባይ የክርስቶስ ምስክር በመሆን ነው። በአንድ እንጇ መከራና ውርደት በሌላ እጇ ደግሞ ሕይልና ክብር ወጥራ በመጨበጥ። ይህች አይነቷ ጽንፈኛ ቤተክርስቲያን ግን ሥቃይን፤ መከራንና ውርደትን ልክ እንደ ክርስትና “ማረጋገጫ” ምልክት አድርጋ ትወስዳለች። ቃል አጋኖዬ መቼም ግልጽ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ይህም “ወንጌል ያበለጽጋል” የሚለው መርህ “ሐይል ያለ ድካም” እንዳለ ሁሉ “ድካም ያለ ሐይልም” እንዲሁ ጽንፈኛ ነው። የድል ሕይወትና የመከራ ሕይወት ለአዲስ ኪዳን አማኞች በአንድ ጊዜ እውነት ናቸው። ወደ መስቀሉ ተመልክቶ መስቀሉን ተሸክሞ የማይደክም፤ ደግሞስ መስቀሉን ተመልክቶ ሐይልንስ የማይጎናጸፍ ማነ ነው? መስቀልና ዙፋን አይለያዩም። በአንድ እንጇ መከራና ውርደት በሌላ እጇ ደግሞ ሐይልና ክብር በውጥረት አሉ። በእርግጥ ከላይ ያየነውን አይነት ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው የተሰሎንቄ አማኞች፤ በዚህችው ቤተክርስቲያን “ሐይልንና ውርደትን” አመጣጥነው ከያዙ አማኞች መማር በኖረባቸው (1 Th 2:13–14)
ዘራፍ ዘራፍ የምትለዋ ቤተክርስቲያን! (Over-Realized Eschatology)
በአንጻሩ ደግሞ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን አለች። አቤት! አቤት! ይህች ደግሞ ያዙኝ ልቀቁኝ የምትል ሁከት የበዛባት ቤት ነች። ይህች ቤተክርስቲያን ደግሞ አሁን በክርስቶስ በተሰጠን በረከቶች ላይ ትልቅ አጽኖኦት ከማድረጓ የተነሳ ዘላለማዊ ርስቷን አሁን ያደረገች፤ ክርስቶስን መጠባበቅ የዘነጋች እና ገና ኢየሱስ ሲገለጥ በሙላት የምንወርሰውን ርስት “አሁን ሙሉ በሙሉ ወርሻለሁ” ብላ የምታጋንን ነች። “አትባርኩኝ ተባርኪያልሁ” ትላለች። ከዚህ የተነሳ አንዳንዶች “እንደመልአክ ሆነናል (1 ቆሮ. 7:1)” ቢሉ እና “ሙታን ትንሳኤ አሁን ሆኗል…መንፈሳዊ ነው” የሚሉ አማኖች ቢሞሉባት በርግጥ አያስገርምም። ገና የሚፈጸመው ተስፋ፤ ለእርሷ አሁን ነውና። “የዓለምን ሀብት ትማርካለህ…የረገጥከውን ትወርሳለህ….ሕንጻው ያንተ ነው…ብሩና ወርቁ ያንተ ነው…ሳታጠና ፈተና ታልፋለህ…ሳትሰራ ወርቅ በወርቅ ትሆናለህ….የንጉስ ልጅ ስለሆንህ ትበለጽጋለህ” ትላለች። ብልጽግናዋ የመንፈሳዊነቷ ልክ መግለጫ ነው (ሀብታም ነኝ፤ ባለጠጋ ነኝ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና፣ የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም። Re 3:17)። ለዚህች አይነቷ ቤተክርስትያን ለመከራ ሥፍራ የላትም። በህመም ማለፍ ሽንፈት ነው። የንጉስ ልጅ ነህና እንደ ንጉስ ትንቀባረራለህ ባይ ናት። ለቆሮንቶስ የተናገረውን ይህን የሐዋርያውን ምጸት እስኪ ስሙልኝ።
❝አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? አሁን ጠግባችኋል፤ አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል፤ ያለ እኛ ነግሣችኋል፤ እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር❞ 1 Co 4:7–8
ይህች ቤተክርስቲያን ጌታ በመካከሏ ከሰራው አስደናቂ ሥራ የተነሳ ሚዛናዊነቷን አጣች። ጌታ ከመካከሏ ለጥቂት ጊዜ በሃይልና በብዙ የጸጋ ሥጦታ ስለሞላት፤ ያገለገላትን ሐዋርያና አባቷን በንቀት ዓይን መመልከት ጀመረች። ጳውሎስና ጓደኞቹ በመከራና በሕመም ማለፋቸው፤ በመንፈሳዊ ነገር እንደቀዘቀዙ ቆጠረች። አሁን በቅርቡ ወደ ቤተክርስቲያኒቱ በመጡ፤ ከሐዋርያው ላቅ ባሉ፤ “ዘራፍ” በሚሉ፤ ሐዋርያ ሳይሆኑ ሐዋርያ ነን ባሉ ሰዎች (በተለይ 2 ቆሮንቶስ 10-13 ይመ.) የጳውሎስን ሐዋርያነት ማናናቅ ጀመሩ።
❝ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛልና። እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን እናንተ ግን ኃይለኞች ናችሁ፤ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ እኛ ግን የተዋረድን ነን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል። እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና። እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ❞
ጳውሎስ ሊነግራቸው የወደደው ሕይወቱና አገልግሎቱ፤ ልክ እንደ ጌታው “መስቀልንና ዙፋንን” ያማጠነ ሕይወት እንደሚኖር ነው።
❝አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ፣ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም። ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን፦ በብዙ ትዕግሥት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በመታሰር፣ በሁከት፣ በሥራ ብዛት፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመራብ፣ በንጽሕና፣ በዕውቀት፣ በትዕግሥት፣ በቸርነት፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ በእውነተኛ ፍቅር፣ በእውነት ቃል፣ በእግዚአብሔር ኀይል፣ በቀኝና በግራ እጅ የጽድቅ የጦር ዕቃ በመያዝ፣ በክብርና በውርደት፣ በመመስገንና በመሰደብ፣ ኖረናል፤ ደግሞም እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል፤ የታወቅን ስንሆን እንዳልታወቅን ሆነናል፤ ሞተዋል ስንባል እነሆ በሕይወት አለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ ሐዘንተኞች ስንሆን ሁል ጊዜ ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው❞ (2 ቆሮ. 6:3–10)
ይህ የቆሮንቶስ ጉዳይ አሁን ያለንበትን ዘመን ይመስላል። የእምነት-ቃል እንቅስቃሴ በይፋ ከጀመረ ከአንድ ትውልድ በታች ነው። የዚህ አስተምህሮት ትልቅ አባት አድርገው የሚቆጠሩት ከሞቱ ጥቂት ዓመት ጊዜው ነው። የዚህ እንቅስቃሴ አራማጅ የሆኑት ጥቂቶች ግን የክርስቲያኑን ቴሌቪዥን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩት ከመሆኑ የተነሳ የዛሬ 30 ዓመት ይህ ትምህርት የትም አይደርስም ብለው ብዙዎች ቢገምቱም አሁን ትልቅ ሥር ሰዶ መፍትሔ ከየት እንደሚመጣለት የማይታወቅ ችግር ሆኗል። የዚህ እንቅስቃሴ ትልቅ ስህተት ይህ ከላይ ያየነው ጽንፈኝነት ነው። በአሁኑ ላይ ጥልቅ ትኩረት ከመስጠታቸው የተነሳ ብልጽግና እንጂ ክርስቶስ የማይሰበክበት መድረኮች ሆነዋል።[1] ለምሳሌ ያህል ከመሰረታዊ ትምህርታቸው መካከል ሦስቱን እንዳሥሥ፦
- “በቃል ነገሮችን ካለመሆን ወደ መሆን ታመጣለህ…ያዋጅ ቃል” የሚለው እጅግ የሚያሰቅቅ አነጋገር ነው (ምክኒያቱም ምንም ቢደባበስና ከአውዱ የተለየ ጥቅስ ከማምረው እውነት ለማስመሰል ቢሞክሩም ይህ የመለኮትን ሥራ መሻማት ነው።፡እግዚአብሔር ብቻ ነው ተናግሮ የሌለውን ወደ መሆን የሚያመጣው። በኢሳያስ መጽሐፍ ያህዌህ ራሱን ከጣኦታትና ከአሕዛብ አማልክት የለየው በዚህ ሐይሉ ነው “እነዚህን ሁሉ በቃሉ የፈጠረ ማን ነው?”)። በመጽሀፍ ቅዱስ መለኪያ ይሁን በቤተክርስቲያን ታሪክ ማስረጃ፤ ይህ እንቅስቃሴ የተወገዘና ከየትኛውም ቤተእምነት ያሉ የቤተክርስቲያን መሪዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች ያወገዙት አስተምሕሮት ነው። በርግጥ ይህ አስተምህሮት ሥር ከመስደዱ የተነሳ እውነት ቢመስልም ጠለቅ ብሎ ላየው ግን ቅዱሳት መጻህፍትን የሚጣረስ ብዙ ነገር አለው።
- ሌላው ለዚህ አስተምሕሮት መሰረት የሆነው አዋጅ ቃላቸው “እግዚአብሔር በእምነት የሌለውን እንዳለ አድርጎ ይናገራል…ስለዚህ አንተም በእምነት የሌለውን ነገር አድርገህ ተናገር” ባዮች ናቸው። ለምሳሌ ያህል የሚጠቅሱት “በዘፍጥረት 1 ላይ” እ/ር በእምነት እንዴት እንደተናገረ፤ ደግሞ በዘፍጥረት 2 ላይ ቃሉ ከእምነት ቃል ወደ መሆን እንደመጣ እናያለን ይላሉ። በመጀምርያ ይህ አይነት ሐቲት በምንም አይነት መለኪያ ትክክል አይደለም። በተጨማሪ ደግሞ እግዚአብሔር ያምናልን? ማንን ያምናል? እኔና እናንተ ሁሉን ቻዩን አምላክ በክርስቶስ በፈጸመው የማዳን ሥራ ላይ አምነን ድነናል። ከእርሱ በላይ የሚምልበት ማንም ስለሌለ በራሱ አልማለምን? እምነት መታመንና ማመንን ገንዘቡ ያደረገ እንደሆን ነው መጽሀፍ ቅዱሳዊ የሚሆነው። ዝም ብሎ ማመን የኒው ኤጅ ትምህርት ነው። መኪና መኪና መኪና በል መኪና ታገኛለህ። አጋንንታዊ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ነው “በአየሩ ላይ ቃል እንዝራ…ቃላችን ሀይል አለው…ቃላችን አካባቢው ላይ ተጽ ዕኖ ያመጣል” የሚለውን ፉከራ የሰጡን። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በወንጌላት ላይ በክርስቶስ እግር ሥር ተደፍተን “ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል” እንድንል ያደፋፍሩናል። መልሳችን ያለው ሥጋ በሆነው ቃል እንጂ፤ በሥጋ ለባሽ ቃል አይደለም። እነርሱ ግን “እኔ ቃል እናገራለሁ” እንድንል ያደፋፍሩናል።
- በመጨረሻ ሌላው የዚህ እንቅስቃሴ ጽንፈኝነት እግዚአብሔር የሰጣቸው ተስፋ ቃሎች በሙሉ አሁን በሙሉ ይሆናሉ ባዮች ናቸው። ከላይ እንዳየነው እነዚህ ሰዎች “ገና ሊገለጥ ባለው መዳን” ላይ አላተኮሩም። ልክ በሽሽት ላይ ያለችው ቤተክርስቲያን አሁን የተመረቀውን መዳን ጆሮ ዳባ ብላ ገና የሚመጣውን ብቻ እንዳጎላች፤ ይህች ደግሞ በአንጻሩ ሊገለጥ ያለውን ታላቅ መዳን ችላ ብላ አይኗን ያተኮረችው አሁን በሚሆነው ነገር ላይ ነው። “እግዚአብሔር በዚህች ምድር ሳለን ሁሉ እንዲኖረን ይፈልጋል” የሚለው መፎክራቸው ይህንኑ ጽንፈኝነታቸውን ያረጋግጥልናል። ለነርሱ ሰው ሁሉ ሐብታም መሆን ይችላል…አይታመምም…ሁላችን እንፈወሳለን….ሁላችን ጥሩ ጥሩ ቤቶችና ሥራዎች እንይዛለን”። ይህንም ከቅዱስ ቃሉ ጥቅስ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ከዘዳ 28 ወስደው የሚያስተምሩት የበረከትና መርገም አስተምህሮ፤ ብሉይንም እንዲሁም አዲስ ኪዳንንም ጨርሶ ያልተረዳ ነው።
ማጠቃለያ
በተሰቀለ-ክርስቶስ ማመን ለአሕዛብ ሞኝነት ነበር። ምክንያቱም “የተሰቀለ-ንጉሥ” የሚለው ቃል ሲሰሙ ልክ “ርጥበት-አልባ ውቅያኖስ”፤ “ጥልቀት አልባ ጥልቅ” “የማያቃጥል እሳት” እንደማለት ነው! ስሜት አይሰጥም። ግሪኮች ጥበብን ይሻሉ። ስሙ እንደሚያመለክተው ፣ ክርስቶስ ማለት ንጉሥ ሊሆን የተቀባ ማለት ከሆነ ንጉሥ ታድያ መስቀል ላይ ምን ያደርጋል? መስቀል ለአመፀኞችና ለደካሞች ነውና። ግሪኮችና ሮማውያኖች ትሕትናን አይወዱም። በአሳባቸው ትህትና ከድክመት ጋር የተያያዘ ነውና። ትሁት መሆን ፈሪ እንደመሆን ይቆጠራል። ይሁንና የእግዚአብሔር ሞኝነት ከጠቢባን እውቀት ይጠበባል። “በመካከላችሁ ሳለሁ እየሱስ ክርስቶስን ፣ ያውም የተሰቀለውን ፣ እርሱን ብቻ እንጂ ሌላ እንዳላውቅ ወስኜ ነበርና “ (1 ቆሮ. 2:2)።
እግዚአብሔር ያሰበልን ሙላት ሁሉ በዚህ የሚቃረን በሚመስል እውነታ ውስጥ ተካቷል።
❝….ፍፁም የሆነውን የመረዳት ብልጥግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ እተጋለሁ ፤ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በእርሱ ዘንድ ነውና። ማንም ንግግር በማሳመር እንዳያታልላችሁ ይህን እነግራችኋለሁ።❞ ( ቆላ. 2 ፡2-4)
ለዚህ ነው የጳውሎስ መልዕክት የተሰቀለውን ንጉሥ ማዕከል ያደረገው።
❝እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደተቀበላችሁት እንዲሁ በእርሱ ኑሩ ፤በእርሱ ተተክላችሁና ታንፃችሁ፣ እንደተማራችሁት በእምነት ፀንታችሁ ፤ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ❞ (ቆላ. 2:6-7)
በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ “መስቀልና ዙፋንን ያማጠነች” ሦስተኛይቷን ዓይነት ቤተ ክርስቲያን እንመለከታለን። በነገው ዕለት ይወጣል።
(ይህ ጽሑፍ አስቀድሜ ያዘጋጀሁት በጥቅምት 2014 እ.ኤ.አ.)
[1]See Gordon Fee, “The Disease of the Health & Wealth Gospels” Gordon Fee is one of the most respected Pentecostal, biblical scholar and assembly of God ordained minister. I have so much respect for his scholarship and who had so much influence on my earlier theological pursuit. He comments on this movement that the movement hardly understand the New testament to begin with. I fully concur with his comment. The problem is that many Christians who follow their teachings do not know at all that this movement is not a historic Christianity to begin with leave alone, to be biblical and are not acknowledged as such.

