
መስቀልና ኪዳን፡ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት እንዲሰበስባቸው
“በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ። እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ።” (ዮሐ.11:49–53)
የክርስቶስ መስቀል ምን ሥራ ሠራ? ክርስቶስ ከመወለዱ ጀምሮ እስከ መከራው፣ ከሞት ትንሳኤው እስከ እርገቱ፣ እንዲሁም በሰው እጅ ወዳልተሰራችው ቤተ-መቅደስ እስከመግባቱ እና በአብ ቀኝ እስከመቀመጡ ድረስ ምን ተከናወነ ብለን ብንጠይቅ አያሌ ነገሮችን መዘርዘር እንችላለን። ሆኖም ግን ይህንን ሁሉ በአንድ ቃል ብናጠቃልል፤ ክርስቶስ በማንነቱ እና በቃሉ፣ በተለይ በመስቀል ሞቱና በትንሳኤው “አዲስ ኪዳንን” መርቋል። ጌታ ቢረዳኝ፤ በዚህ በሕማማቱ ሰሞን “የክርስቶስ መስቀልና ኪዳን” በሚል ርዕስ ተከታታይ መጣጥፎች ለማቅረብ እሞክራለሁ።
መግቢያ
ስለ “አዲስ ኪዳን” ስንነጋገር፤ “አዲስ” የሚለው ተቀጽላ ቃል የሚያስረዳን ነገር ቢኖር፤ ይህ በክርስቶስ ደም የተመረቀውን ኪዳን መረዳት የምንችለው ከቀደሙት ኪዳናት ጋር በማነጻጸር “ሥምረቱንና ልዩነቱን” ያየነው እንደሆን ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል “ቃል-ኪዳንና ህዝብ” የሚለውን እሳቤ ከዘዳ. 30:1 እና ዮሐንስ 11 እናነጻጽር። ከዚያ በፊት ግን ኪዳን ምን ማለት ነው?
ኪዳን ምን ማለት ነው?
ይህ መጣጥፍ እንዳይረዝምብኝ ኪዳን የሚለው ቃል ባለበት ሁሉ የምናገኘው ቀመር መሰል ድግግሞች በመጠቀም ትርጉሙን ብሰጥ ለዛሬ በቂ ነው። ኪዳን በአንድ እጅ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ፍጥረቱ እና ደግሞ በሌላ እጅ በጸጋ ካዳነው ሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚቀርጽ ቃል ነው። ለምሳሌ ያህል ይህንን ተደጋጋሚ ቀመር እንመልከት
► የእስሪኤላውያን ኪዳን፦ “ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ።” (ዘሌ. 26:11–12 Ex 6:7)
► የአብርሃም ኪዳን፦ “የከነዓን ምድር ሁሉ፥ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ” Ge 17:8
► የዳዊት ኪዳን፦ “እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል (2 Sa 7:14)
► አዲስ ኪዳን፦ “ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል” (Eze 37:27) “ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል..” (ራዕ. 21:7; 10–11)
ስለዚህ በአጭሩ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት “የአምላክና የህዝብ/ የአባትና የልጅ” እንዲሁም ከሕዝቡ ጋር አብሯቸው መኖሩ እና በመካከላቸው መመላለሱን የሚመለከት ቃል ነው። ይህም በመጽሀፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት 1 ጀምሮ እስከ ራዕይ 22 ድረስ የተዘረጋ ጅማት ነው። የኪዳንም ዓላማ
“እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው…እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ…አዳምንም አስወጣው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ” (ዘፍ 2:8፣ 3:8፣ 24)
“የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ (Re 21:3)
ስለዚህ ኪዳናቱ ይህንን ዓላማ ወደ ግብ ለማድረስ የተሰጠ መለኮታዊ አሠራር ነው ማለት እንችላለን።
የእስራኤላውያን-ኪዳንና አዲሱ ኪዳን በዘዳግም 27-30
የእስራኤል ህዝብ የቃል-ኪዳኑን ሕግ በሲና ሲረከቡ እና ይህንንም ኪዳን እንደገና እግዚአብሔር ለሁለተኛው ትውልድ በሞዓብ ምድረ በዳ (በዮርዳኖስ ማዶ) ሲያድስላቸው፤ እሥራኤል “የእግዚአብሔር ሕዝብ” ስለሆነች እንጂ እንድትሆን አልነበረም። ይህም ለኪዳኑ-ሕግ የመታዘዝ ግዴታ የመነጨው፣ በርግጥ እሥራኤል “ሕዝበ-እ/ር” ስለሆነች ነበር። ያህዌህ በጸጋው ከግብጽ ባርነት ነጻ አውጥቶ ወደ ራሱ አምጥቷቸዋልና (ዘጸ 19:4)። ስለዚህም
__“እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብላችሁ አድምጡ፤ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል። ለአምላክህም ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፥ ዛሬም የማዝዝህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን አድርግ” (ዘዳ. 27:9–10)
ለሕጉ መታዘዝ ከአምላካቸው ጋር ያለውን የቃል ኪዳን ግንኙነት የሚንከባከቡበት፣ “ሕዝበ-እ/ርነታቸውን” እና “የተስፋ ርስታቸው” የሚጠብቁበት መንገድ ነበር።
__”ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኃጢአት ምክንያትና ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነው”(ዘዳ. 9:5)
__”እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና” (ዘዳ. 7:7)
ሆኖም ግን ይህ “ኪዳን” እንዲሁም የኪዳኑ ተሳታፊ እሥራኤል ገና ከጅምሩ አንድ ችግር ነበረባቸው።
► (1) እስራኤል “የልብ ችግር” ነበረባት። ለኪዳኑ-የሚታመን ልብ አልነበራት። ኪዳኑ ከእስራኤል የሚጠይቀውን አፍቅሮተ-ያህዌ ማድረግ አልቻለችም።
__”አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” (ዘዳ. 6:5–6)
ሆኖም ግን በተደጋጋሚ የእሥራኤል ልብ የሸፈተው ሌሎች አማልክትን ለማምለክ ነበር። ደንዳና ልብና አንገት ነበራቸው።
__”ዓይኖቻችሁ ያዩአቸውን ታላላቆች ፈተናዎች፥ ታላላቆች ተአምራትና ድንቆች፥ አይታችኋል፤ 4 እግዚአብሔር ግን አስተዋይ ልብ፥ የሚያዩ ዓይኖች፥ የሚሰሙም ጆሮች እስከ ዛሬ ድረስ አልሰጣችሁም” (ዘዳ. 29:3–4)”
__”ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር። ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ። (መዝ..95:10)”
► (2) የሲናው ኪዳን ከያህዌህ ዘንድ በጸጋ የተሰጠ እንዲሁም በራሱ ጻድቅ፤ ቅዱስና መንፈሳዊ ነበር (ዘዳ. 4:8)
__”በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንደማኖራት እንደዚህች ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ፍርድ ያለው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? “
► (3) ሆኖም ግን የኪዳኑ-ሕግ የሰውን ደንዳና ልብ መለወጥ አልቻለም። ከዚህ የተነሳ ይህ ኪዳን በቂና ብቁ አልነበረም። ኋላም ነቢያት ሲናገሩ፦
__”እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። 33ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። (ኤር.31:31–33)”
__አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ” (ሕዝ. 36:26–27)
በእነዚህ የነቢያት ተስፋ ውስጥ የምናየው የቀደመው ኪዳን ሊፈጽም ያልቻለውን ነገር በዚህ በሚታደሰው አዲስ ኪዳን ውስጥ ያህዌህ ያክላል። ከእነዚህ ሁለቱ
► (1) “የድንጋይ ልብ ወደ ሥጋ ልብ” መለወጥ፤ ይህም “የባሕሪ ለውጥን ያሳያል።
► (2) በሰው ልብ ውስጥ ብቃትን እና ሃይልን የሚሰጥ ቅዱስ-መንፈስ ያድራል። እነዚያ አራቱ ፍጡራን ተሸክመውት ከኢየስሩሳሌም መቅደስ ወደ ደብረ-ዘይት ተራራ አኮብኩቦ ከዚያም ወደ ባቢሎን የሸመጠጠው የእ/ር ክብር ተመልሶ በአዲሱ ኪዳን ተሳታፊዎች ሕይወት ውስጥ በክብር ይመለሳል። ሕዝቄል ሲናገር “ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል” (ሕዝ. 37:27) ይላል።
ከዚህ የተነሳ ይህ ኪዳን የሰውን ልብ መለወጥ ባለመቻሉ፤ “የሞት-አገልግሎት…የኹነኔ አገግሎት” አስብሎታል (2 ቆሮ. 3:6-11)። ምንም እንኳ ይህ የሕግ-ኪዳን “ጽድቅ የሆነ ሥርዓትና ፍርድ” ቢሆንም “በድንጋይ ጽላት ላይ የተቀረጸ” እንጂ በኪዳኑ ተሳታፊ ሰው የልብ-ጽላት ላይ ግን የመጻፍ አቅም አልነበረውም። ሕጉ ከሰው ውጪ ያለ የጽድቅ ምሥክር እንጂ ውስጣዊ-ጽድቅን የመፍጠር ኃይል ስላልነበረው ነው። ዛሬም ይህ ሕግ ፍጻሜው ከሆነው ከክርስቶስ (ሮሜ 10፡4) ተነጥሎ ሲነበብ፤ ይህ የኹነኔ አገልግሎት ይቀጥላል። በሰውም ልብ ላይ መጋረጃው ይሸፍናል (2 ቆሮ. 3:15)። ሰው ግን ወደ ጌታ ዘወር ባለ ጊዜ ግን መጋረጃው ይወሰዳል (3፡16-17)። ጳውሎስ አበክሮ የሚነግረን ነገር ምንድር ነው፤ የእግዚአብሔር ህዝብ ለኪዳኑ ታማኝ የሚሆነው ወደ ክርስቶስ ዘወር ሲል እና መንፈስ ቅዱስ ወደ ልቡ ሲመጣ ብቻ ነው። መንፈሱም ከክብር ወደ ክብር የእ/ርን ልጅ እንዲመስሉ ከክብር ወደ ክብር ይለውጣቸውል (3:17-21)። ለገላትያም ቤተክርስቲያን “ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” ሊላቸው የተገደደበት ምክኒያት “በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን?” የአዲስ ኪዳን አማኞች ክርስቶስን በማመን ነቢያት የተነበዩትን ያን የአዲስ ኪዳን ተስፋ ተቀብለዋል፤ የአብርሃም ተስፋ ወራሾች ይሆኑ ዘንድ “ልጆች” ሆነዋል። ማረጋገጫውም የተስፋውን መንፈስ ቅዱስን መቀበላቸው እና በመካከላቸው በሃይል መስራቱ ነው። “6ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ” (ገላ 4:6)
ስለዚህ ወደጀመርንበት እንመለስና፤ የሲናው-ኪዳን ውል በሁለት አካላት መካከል እንደመሆኑ “መለኮታዊው አካል ያህዌህ” እና “ሰብዓዊ አካል እሥራኤል”፤ ለኪዳኑ ስምረት የሁለቱም አካላት ታማኝነት መሰረታዊ ነው። ለምሳሌ የእስራኤልን-ኪዳን ከአብርሃም ኪዳን ጋር ብናመሳስለው (ዘፍ. 15) ግልጽ ይሆንልናል። አብርሃም ያህዌህ የገባለትን “የዘር ተስፋ፤ የርስት ተስፋና ሕዝቦች ሁሉ የሚባረኩበት ዓለም-አቀፍ በረከት ተስፋ” ወራሽ የገዛ ልጁ እንጂ የቤቱ መጋቢ የደማስቆ ሰው ኤሊዓኤዘር እንደማይሆን በተነገረው ጊዜ “አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” ይለናል (15:7)። ግን በ15:8 ላይ አብርሃም “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድወርሳት በምን አውቃለሁ?” ባለ ጊዜ ያህዌህ በተከፈሉት እንስሳት መካከል እየተመላለሰ “18በዚያ ቀን…ለአብራም እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ” ይላል። በዚህ ውል ውስጥ የተስፋውን ቃል ራሱ እግዚአብሔር ወደፊት የሚፈጽመው መሆኑን ያሳያል። ይህ ሲሆን አብርሃም በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ነበር። እንደምታው ግልጽ ነው። ቃሌን ባጥፍ ይህ “የእንሣት ደም የኔ ይሁን” ማለቱ ነው። አብርሃም እንደሆን እምነቱ እንደ ጽድቅ ተቆጥሮለት አርፎ እያንቀላፋ ነው። አብርሃም የጠየቀው ጥያቄ “የገባህልኝን ተስፋ እንድትፈጽም እንዴት አውቃለሁ?” አይደል? በርግጥ የግድ ሰው የሚባል ሃጥያተኛ ፍጡር የኪዳኑ ተሳታፊ እስከሆነ ድረስ ይህ ኪዳን ሊፈጸም አይችልም። ይህ ነው የሲናው ኪዳን ችግር። እንዴት ነው ያህዌህ የገባውን ኪዳን የሚፈጽመው፤ እሥራኤል ታማኝነት የጐደላት ሆና እና ኪዳን አፍራሽ የሆነ እኩይ ተግዳሮት ይዛ? ይህ እስከሆነ ድረስ እግዚአብሔር “ዋሾ” ይባላል፤ ደግሞም በዘፍረት 22 ላይ ለአብርሃም የማለለትን መሃላ ይሻራል። ስለዚህ ውጥረቱ “እግዚአብሔር ጻድቅ ሆኖ (ለኪዳኑ ታማኝ)” ነገር ግን ይህ በኪዳን ከእርሱ ጋር ለተገመደው ተሳታፊ ሃጥያተኛ ሰው የተስፋውን ቃል ወራሽ የሚያደርገው እንዴት ነው? ይህ ጥያቄ ቀጥታ እስከ መስቀል ድረስ ይሚገሰግስና በመስቀል ላይ የሚፈታ ውጥረት ነው (ሮሜ 3፡25-26)። ኪዳን ሁልጊዜም ከተሳታፊው ሰው መታዘዝን ይጠይቃል። ያለመታዘዝ ኪዳን የለም። ለምሳሌ በአዲስ ኪዳን ያለን የተጠራነው “በእምነት ወደ ሆነ መታዘዝ” ነው። ይህ ማለት ክርስቶስን እያመንን ለመታዘዝ በደም የተረጨን እና በመንፈስ ቅዱስ የተቀደስን ነን እንጂ “ግዴታ አልባ” ኪዳን የለንም (here my reader may be aware of the debate on the use of the genitive “obedience of faith” as either: subjective, objective, epexegetical)። ሆኖም ግን ይህ የአብርሃም ተስፋ ከ400 ዓመታት በኋላ ሲፈጸም፤ ቃል አጣፊዋ አስራኤል ቃሉን ከንቱ እንዳታደርግ “የክርስቶስ ደም” መፍሰሱ አይቀሬ ነው። ስለዚህ ለሁለት በተከፈሉት እንሣት መካከል ያህዌህ ብቻውን መመላለሱ እንደ ክርስቶስ አምሳያ እንያለን (ለሁለት የተቆረጠ የሚለው በእብራይስጡ ኪዳን-መሠረተ ለሚለው ጋር ስሙሙነት አለው። ካራት-በሪት ማለት በእብራይስጡ ቃል-በቃል “ኪዳን-ቆረጠ” ማለት ሲሆን ይህ በአማርኛ ኪዳን-ገባ ወይም መሠረተ፤ መረቀ ወዘተ የሚለውን ሐሳብ ያዝላል። ስለዚህ “የእንሣቱ ለሁለት መቆረጥ”፤ “ኪዳን ከመቆረጡ” ጋር ይዛመዳል ማለት ነው።)
የተበተኑት የእግዚአብሔር ሕዝብና እና የኪዳኑ ርግማን
__“የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። (27:26)
በዘዳግም 27-30 ላይ ሙሴ አስቀድሞ ይህ አሁን ከእስራኤል ጋር ያህዌህ የመሠረተውን ኪዳን ከተላለፉ የኪዳኑ መርገም ያገኛቸዋል፡፤ የዚህም መርገም ጫፍ ኪዳኑ መፍረሱ፤ ሕዝቡም መበተኑ ነው።
__“እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፥ እግዚአብሔር በውስጣቸው በሚያኖራችሁ በአሕዛብ መካከልም ጥቂቶች ሆናችሁ ትቀራላችሁ” (ዘዳ. 4:27)
ግን በዘዳግም 30:1 ላይ “በረከቱና መርገሙ፥ በወረደብህ ጊዜ” እንደገና ያህዌህ ተመልሶ ሕዝቡን እንደሚዋጅ ይናገራል:
__”እንዲህም ይሆናል፤ እኔ በፊትህ ያኖርሁት ይህ ነገር ሁሉ፥ በረከቱና መርገሙ፥ በወረደብህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በሚበትንህ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ሆነህ በልብህ ባሰብኸው ጊዜ፥ ወደ አምላክህም ወደ እግዚአብሔር ተመልሰህ እኔ ዛሬ እንደማዝዝህ ሁሉ አንተና ልጆችህ በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ ለቃሉ በታዘዝህ ጊዜ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልሳል ይራራልህማል፤ አምላክህም እግዚአብሔር አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል። ሰዎችህም እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ፈልሰው እንደ ሆነ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፥ ከዚያም ያመጣሃል።” (ዘዳ. 30:1–4)
ይህ የምንሰማውው ቃል፤ ገና እሥራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይገቡ፤ ከተስፋይቱ ምድር ስለ መባረራቸውና ተመልሰው እንደ ገና ወደ ኪዳኑ ስለ መመለሳቸው አስቀድሞ ይመለከታል። ሦስቴ የተደጋገመውን “ጊዜ” የሚለውን ቃል መመልከት ተገቢ ነው።
► (1) በረከቱና መርገሙ በወረደብህ ጊዜ
► (2) በልብህ ባሰብኸው ጊዜ
► (3) ወደ እ/ር ተመልሰህ በፍጹም ልብ ለቃሉ በታዘዝህ ጊዜ።
ሆኖም የብሉይ ታሪክ እንደሚያስረዳን እሥራኤል ይህንን ማስጠንቀቂያ ልብ አላለችም። ኪዳኑንም አቃለለች፤ “መርገምን” በመምረጧ የኪዳኑ መርገም እስኪንጠፈጠፍ ድረስ የሕዝቡ ልብ ቃሉን ማድመጥ አልፈልገም።
__”የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር። 17 ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው…በኤርምያስም አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፤ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ፥ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ፥ ሰንበትን አገኘች” (2 ዜና 36:15–21)
ዘዳግምና በዘመኑ ፍጻሜ የሚመረቀው አዲሱ ኪዳን
በመጀመሪያ ሙሴ ወደ ፊት የተነበየው ትንቢት እግዚአብሔር እንደገና ለአብርሃም የገባለትን ተስፋ የሚፈጽምበት አዲስ ኪዳን ይመሰርታል። በዚህም ሕዝቡን እንደገና ይሰበስባል
__”ይህም ሁሉ በደረሰብህ ጊዜ፥ ስትጨንቅ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፥ ቃሉንም ትሰማለህ። 31 አምላክህ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተውህም፥ አያጠፋህምም፥ ለአባቶችህም የማለላቸውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም” (ዘዳ. 4:30–31)
ሁለተኛ የቀደመው ኪዳን የጎደለውን (የሰውን ልብ የመለወጥ አቅም) አዲሱ ኪዳን ያሟላል (in the new released version 2.0 of the covenant)። ስለዚህ
__”በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል። (ዘዳ. 30:6)
ይህ በሚሆንበት ጊዜ
“ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ወደ ሰማይ ወጥቶ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል በሰማይ አይደለችም። ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ባሕሩን ተሻግሮ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል ከባሕሩ ማዶ አይደለችም” (ዘዳ. 30:12–13)
ነገር ግን ምን ይላል?
“በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” (ሮሜ. 10:8–10)
የቀያፋ ትንቢት፡ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው
በሦስተኛ ደረጃ እና ለማጠቃለል ዳግም ሕዝቡን ለመዋጀት የሚመረቀው አዲሱ ኪዳን ሙሴ በዘዳግም ላይ እንደሚናገረን “አምላክህም እግዚአብሔር አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል።” ይላል። ይህ ኪዳን የሚመረቅበት ቀን የመሰብሰብ ቀን ነው። ይህ የኪዳን ሕዝብ ሲሰብሰብሰ ግን፤ እንደ ቀደመው ኪዳን በሥጋ የአብርሃም ልጆች የሆኑትን ብቻ ሳይሆን ለአብርሃም የተሰጠው አለም አቀፍ በረከት ይህም “በአንተ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ” የሚለውን የእ/ርን ለሕዝቦች ሁሉ ያለውን አጀንዳ የሚፈጽምበት ኪዳን ነው። አይሁድ ከተበትንኑት የሚሰብሰቡት ኪዳን አብረው አሕዝባም በአንድነውት ይሰበሰባልዩ፡፤ ስለዚህ ሆሴዕ ሲናገር “ሕዝቤም ያልሆነውን። አንተ ሕዝቤ ነህ እለዋለሁ፤ እርሱም። አንተ አምላኬ ነህ ይለኛል።” ሆሰ 2:23 በዚህ ወቅት አይሁድ “ሕዝቤ አይደላችሁም ተብለዋል – ሎዓሚ (1:9) ። አህዛብ ድሮውንም ሕዝቡ አልነበሩም። “እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም ተብሎ በተነገረበት በዚያ ስፍራ የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ” (ሆሰ. 2:1)
ስለዚህ በቀያፋ ትንቢት ውስጥ ሐዋርያው ዮሀንስ በክርስቶስ ሞት “የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው “ በማለት የሞቱን ዓላማ ያስረዳናል። “እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ”
ዛሬ በክርስቶስ የምናምን እኛ አሕዛብ የነበርን ከተስፋው ቃል ርቀን፤ ያልተገረዝን አረማውያን የተባልን ሁላችን በሞቱ የተሰበሰብን ህዝቦች ነን። ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች የሆንን፤ በዚህም ዓለም ያለ ተስፋ፤ ያለ እግዚአብሔር ነበርን። (ኤፌ 2:11-12)። በአለም ውስጥ እንደ ብናኝ ጠፍተን ነበርን፡፤ ግን የዛሬ 2 ሺህ አመት ክርስቶስ በመስቀል ሲሰቀል፤ በመስቀሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ እርሱ ልክ ንብ የማር ቀፎን እንዲከብብ በመስቀሉ ላይ ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ ተሰብሰብን! አሜን! ሃሌ ሉያ!

