
መስቀልና ኪዳን፡ የመጨረሻው እራት
[su_quote]እርሱም። ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ [16] እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው (ሉቃስ 22:15-16)[/su_quote]
ይህ እራት እጅግ የከበረ እራት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር
❝ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ [ግን] ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና❞
ይህ የሚያሳየን ይህ የመጨረሻው እራት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ በመረዳትና ተገቢ በሆነ መንገድ የምንቋደሰው፣ ሕይወትና ሞት ያለበት እራት መሆኑን ነው። ይህ እራት በማቴ. ማር. እና ሉቃ. ላይ “የፋሲካ እራት” ሲሆን በዮሐንስ ወንጌል ላይ ደግሞ በተጨማሪ “የስንብትም” እራት ነው። ልክ ይስሐቅ ለልጁ ኤሳው “ሳልሞት ነፍሴ እንድትባርክህ… አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ” (ዘፍ 27:4) እንዳለው ማዕድ በጥንታዊው ዓለም “የስንብት” ሥርዓትም ጭምር ነበር። ሙሴ ህዝቡን ተለይቶ ሲሔድ ለህዝቡ ባርኮትና የኪዳን ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ፤ ክርስቶስም ወደ አባቱ ከመመለሱ በፊት በዮሐንስ ወንጌል ላይ ጥልቅ የሆነ ንግግር ከደ/መዛ. ያደርጋል። “ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር..”
ይህ እራት ግን ደግሞ ትልቅ ኪዳናዊ ምልከታ አለው። ይህ እራት የኪዳን ምረቃ ስነ-ሥርዓት ነበር። በዘጸዓት 24፡8 ላይ የእሥራኤላውያን ኪዳን ሲመረቅ “የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ” እንደሚል፤ ከዚህ በኋላ ክርስቶስ ደሙን አፍሶ ራሱንም መስዋእት አድርጎ በመስጠት አዲስ ኪዳን ይመረቃል፡ ❝ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው❞
ይህ እራት በአራት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ላይ ተጠቅሷል (ማቴ 26:26-29; ማር. 14:22-25; ሉቃ. 22:15-20; 1 ቆሮ. 11:23-26)። እነዚህን በአንድ ላይ ብንመለከት፤ በዚህ እራት ላይ ክርስቶስ አራት ነገሮችን ተናግሯል። የሚከተለው ሰንጠረዥ ተመ.
(1) በእግዚአብሔር መንግሥት… እስከምጠጣበት ቀን ድረስ [ከእንግዲህ] አልጠጣም (ማር. 14:25; ማቴ. 26:28; ሉቃ. 22:20; 1ቆሮ. 11:25)
(2) “እንካችሁ ይህ ሥጋዬ ነው…” (ማር. 14:22; ማቴ. 26:26; ሉቃ. 22:19; 1ቆሮ. 11:24)
(3) ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት (ሉቃ. 22:19; 1ቆሮ. 11:24)
(4) ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። (ማር. 14:24; ማቴ. 26:28; ሉቃ. 22:20; 1ቆሮ. 11:25)
ስለዚህ የመጀመሪያውን ቃል እንመለከት።
ንግግር 1፡ “በእግዚአብሔር መንግሥት… እስከምጠጣበት ቀን ድረስ [ከእንግዲህ] አልጠጣም”
(ማር. 14:25; ማቴ. 26:28; ሉቃ. 22:20; 1ቆሮ. 11:25)
ይህንን እራት ከብሉይ ተስፋ አንጻር፤ ከቀደመው ኪዳን አመራረቅ አንጻርና ከአይሁድ የድግስ በዓላት አንጻር አጠር አድርገን መመልከት እንችላለን።
֍ የእግዚአብሔር ተስፋና ማዕድ
“እራት፤” “ማዕድ” ወይም “ግብዣ” በብሉይ ንጽረተ-ዓለም ውስጥ ትልቅ ኪዳናዊ እንደምታ አሏቸው። ከብዙ ምክኒያቶች መካከል ዋነኛው “ግብዣ/ማዕድ” ኪዳናዊና መሲሃዊ ጉብኝትን ስለሚያንጸባርቅ ነው። ለምሳሌ ኢሳያስ ወደ ፊት እግዚአብሔር ስለ ሚያመጣው ታላቅ ጉብኝት ሲመሰክር
❝የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል…❞ (ኢሳ. 25:6)”
የዚህ የታላቅ ግብዣ ዘይቤያዊ ሥዕል ትርጓሜው ምን እንደሆነ ኢሳያስ ራሱ ሲፈታልን ❝ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና❞ (25:8) ይላል። የዚህ “የተራራ…ግብዣ…” ዕይታ የሚያስተጋባው መለስ ብሎ ወደ ዘጸ 24:1-11 ነው። በዚህ ክፍል ላይ ሙሴ፣ አሮንና ልጆቹ እንዲሁም እሥራኤልን የወከሉ 70 ሽማግሌዎች በእ/ር ፊት ወደ እ/ር ተራራ ይወጣሉ (24:1-8)። በዚያም የሚቃጠል መሥዋዕት ከቀረበ በኋላ “ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ” (24:8) ይላል። በዚህም ደም የእሥራኤላውያን (የሲናው) ኪዳን ተመረቀ። ከዚያም እነዚህ ሰዎች ወደ ተራራው በመውጣት “እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም (24:11)። ኢሳያስ ወደዚህ ክፍል መለስ ብሎ በመመልከት፤ ወደ ፊት ያህዌህ ከሕዝቡ ጋር እንደገና በጽዮን ተራራ በሚመርቀው ኪዳን ‘ታላቅ ማዕድ ያዘጋጃል’ ይለናል። ሆኖም ግን ይህ ማዕድ እንደ መጀመሪያው ኪዳን ሕዝቡን ወክለው የሚቀመጡ “70 የእሥራኤል ሽማግሌዎችን” ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፤ በጽዮን ተራራ ላይ “ሕዝብ ሁሉ (ኮል-ኣም)”…”አሕዛብ ሁሉ (ኮል ጎዪም)” የሚታደሙበት ግብዣ እንደሆነ ኢሳያስ ይነግረናል (ኢሳ 25፡6)። ወይም በአዲስ ኪዳን እንደ ዕብራውያን 12:22-24 አነጋገር፤ “ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት…በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር..የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል…” የድነትን ደስታ ስለተጎናጸፈው ታላቅ የአዲስ ኪዳን ጉባኤ ኢሳያስም አበክሮ ሲነግረን በ25፡9 ላይ ❝በዚያም ቀን…በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል❞ ይላል። በዚህ ታላቅ የያህዌህ ግብዣ ቀን፤ ሞት “የሚዋጥበት” ቀን ነው (ቃሉ “ሞት የሚሰለቀጥበት” ብንልም እንችላለን። ይህ ቃል የአሮን በትር የአስማተኞቹን በትር “ዋጠች” ለማለት ጥቅም ላይ ውሏል። እይታው ሞት ሰውን ሁሉ እንደዋጠ፤ በዚህ ቀን ግን እራሱ ይዋጣል!)። ሲቀጥልም ‘ይህ ቀን እንባ የሚታበስበት’ የድነት ቀን ነው። ታላቅ ድግስ ነው። የተቀደሰ የእግዚአብሄር ድግስ።
እንዲሁ በኢሳ 55:1-2 ❝እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ❞ ብሎ ጥሪ ያቀርባል። ይህ ጥሪ የመጣው መከራ ተቀባዩ የጌታ ባሪያ የሆነው የሥቃይ ሰው ከፈጸመው ሥራ ተከትሎ ነው (ኢሳ. 52:13-53:12)። ይህም ይህ ታላቅ የማዕድ ጥሪ “በነጻ” የሚሸጠው ከዚህ የጌታ ባሪያ ሥራ ምክኒያት እንደሆነ ኢሳያስ እያሳየን ነው። (ዋጋ የተከፈለበት እንጂ ያለዋጋ እንዳለሆነ ኢሳያስ ማመልከቱ ነው ‘ግዙ’ የሚለው = ያለ ዋጋ ግዙ)። ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን ባለመክፈቱ” ይላል ኢሳያስ ነጻ ማዕድ ይቀርባል ይህም ማዕድ 55:3 ላይ “የዘላለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ” ይላል። ስለዚህ ይህ አሁን እያከበርን ካለው የክርስቶስ ራት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለውማለት ነው። የሕማም ሰው ክርስቶስ በፈጸመው ሥራ የተነሳ ታላቅ መዳን ተመርቋል። ይህ መዳን በክርስቶስ ላይ ባለ እምነት በነጻ ተሰጥቶናል። “ኢየሱስም…እንካችሁ ብሉ…ጠጡ!”
֍ የእሥራኤል በዓላትና ማዕድ
በተጨማሪም በብሉይ የምናያቸው የተቀደሱ ማዕዳትና ክብረ በዓላት፤ ለምሳሌ ያህል “የፋሲካ፤” “የቂጣ፤” “የበኩራት በዓል/የበዓለ ሐምሳ፤” እና የዳስ በዓላት ከዚሁ ጋር የሚጋመዱ እውነታዎች ናቸው። እግዚአብሄር ለሕዝቡ ያደረገውን ትድግና ወደ ኋላ መለስ ብለው እንዲያስቡ የሚጋብዙ እነዚህ መታሰቢያዎች፤ በአዲስ ኪዳን “በጌታ ራት” መታሰቢያ ተካተዋል። የዳስ በዓል ላይ ኢየሱስ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ…” በማለት የዚህ በዓል ፍጻሜ ክርስቶስ እንደሆነ እና ይህም ደግሞ ሊፈጽመው ካለው ሥራውና በበዓለ ሃምሳ ቀን ከሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ጋር ተገናኝቷል። እንደዚሁም ጌታ ይህንን የመጨረሻ እራት “የፋሲካ እራት” እንደሆነ እንዲሁም ወንጌል ጸሐፊያት “የቂጣ በዓል” የሚከበርበት ቀን እንደሆን ያሳስቡናል። ከደ/መዛ. ጋር አብሮ ይህንን እራት ሲበላ፤ እነዚህ ሁሉ የብሉይ ዕሳቤዎች በአንድ ላይ መጋጠማቸው ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ደም አዲስ ፋሲካ መርቋል። ይህም ፋሲካ እስከ ሚቀጥለውም መንግሥት ድረስ “ታርደሃልና…” እየተባለ እየተዘመረለት ለዘላለም የሚቀጥል ዝክር ነው! ሃሌ ሉያ! ለመታሰቢያዬ አድርጉት!
֍ ከቀራጮችና ኃጢአተኞች ጋር በላተኛው ክርስቶስ
ይህንን “የግብዣ” መሪ ሃሳብ ይዘን ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ በወንጌላት ላይ በተደጋጋሚ ክርስቶስ ከሰዎች ጋር “ማዕድ” እንደ ቀረበ ይነግሩናል። ይህም ማዕድ ትልቅ መሲሃዊ እንደምታ ነበረው። ከላይ የተመለከትነውን “እ/ር የሚያዘጋጀውን ግብዣ” የወንጌል ጸሐፊያት በሁለት ዘመናት በመክፈል፤ በክርስቶስ አገልግሎትና ሞት እንደተፈጸመ ይነግሩናል። ለምሳሌ ያህል ጌታ በምድራዊ የአገልግሎቱ ወራት ሳለ በተደጋጋሚ ከሰዎች ጋር የተካፈላቸው “ግብዣዎች” ይህንን መሲሃዊ ዘመን እንደፈነጠቀ ማመላከታቸው ነበር። በዓይነተኛነት ለምሳሌ ማርቆስ 2፡15-22ን መጥቀስ እንችላለን። ኢየሱስ በቀራጩ ሌዊ ቤት ገብቶ ማዕድ ሲቀመጥ “ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ (2:15)” (“ጋር” የምትለው ቃል ወሳኝ ናት።) የፈሪሳውያንም ጉርምርምታ “ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው?” ነበር። ፈሪሳውያን በጻድቃንና በሓጥዓን መካከል ያሰመሩት መስመር አንዱ የማዕድ ልዩነት ነበር። ክርስቶስም ሲመልስላቸው “ኃጥያተኞችን” ልጠራ እንጂ በማለቱ በዚህ ገበታ የቀረቡ በንሥሃ የተመለሱ ሐጥያተኞች፤ ህመምተኞች ናቸው። ማርቆስም ቀጠል አድርጎም በ2:17-20 ላይ ጨመር ያደርግና ሌላ ጉርምርምታ ያሰማናል “የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው?” መልሱ በአጭር ቃል “ይህ ወቅት ታላቅ መሲሃዊ ድንግስ ዘመን ስለሆነ ነው። ኢየሱስ ከደ/መዛሙርቱ ጋር በማዕድ “ይፈስክ” ነበር እንጂ አይጾምም ነበር። ምክኒያቱም ሲመልስ ክርስቶስ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም።” የእግዚአብሔር መንግስት አሁን በክርስቶስ ጠብታለች። ነቢያት የተነበዩት ዘመን ደርሷል። አንካሶች እየዘለሉ፤ ሃጥያት ይቅር እየተባለ፤ በሽተኖች እየተፈወሱ፤ ሰዎች ከአጋንንት ነጻ እየወጡ ነው። አሁን የጾም ሰዓት አይደለም። ኢሳያስ የተነበየው የግብዣ ሰዓት ነው። ለምሳሌ ያህል፤ ኤርሚያስ በዘመኑ ከፊት ያለውን የፍርድ ሰዓት እያየ “የተድላ ድምጽና የሙሽራ ድምጽ የማይሰማበት” ይለዋል (ኤር. 7:34፤ 16:9፤ 25:10)። ነቢዩም በአገልግሎቱ ዘመን ሁሉ ሰርግ ቤት፤ ድግስ ቤት እንዳይካፈል በእ/ር ይታዘዛል (ኤር. 16)። በተቃራኒው ጌታ ኢየሱስ ራሱን እና ደ/መዛ. “ሙሽራና ሚዜ” በማለቱ ወደ እነዚህ የብሉይ ክፍሎች በማስተጋባት፤ “የዚህ ሁሉ ፍጻሜ እኔ ነኝ” ማለቱን ያሳየናል። ትንቢተ ዘካርያስም ላይ ኢየሩሳሌም ከፈራረሰች በኋላ አይሁድ የእ/ርን ዳግም ጉብኝት በመናፈቅ የጾም ቀኖችን እንዳወጁ እንረዳለን (ዘካ 8:19)።ያ ጾም አሁን በክርስቶስ መሲሃዊ አገልግሎት መልስ አግኝቷልና “ደ.መዛ. አይጾሙም”። አዲሱ አቁማዳ ተከፍቷል። አዲስ የወይን ጠጅ ተሰጥቷል። ስለዚህ ይህ ግብዣ የክርስቶስን መሲሃዊ አገልግሎት ያሳያል። ሆኖም ግን “ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ”። ክርስቶስ ተመልሶ እስኪመጣ ግን በመካከሉ ላለን እኛ በጾም “ማራናታ!” እንላለን። ይህ ወደ ሚቀጥለው ይወስደናል።
֍ የመጨረሻው የፋሲካ እራት
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይህ “ግብዣ” በአንድ እጅ አሁን በክርስቶስ የተፈጸመ ቢሆንም በሌላ እጅ ወደ ፊት ክርስቶስ ዳግም ሲመለስም የሚከናወን “የበጉ እራት” ድግስ ነው ❝በእ/ር መንግሥት …እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም❞ (ራዕ 19:9, 17–18)። ደግሞም ይህንን ራት በማሰብ ጳውሎስ ሲያሳስበን ❝ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና❞ (1 ቆሮ. 11፡26) ይለናል። በዳግም ምሳቱ ብዙዎች ከምሥራቅ ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በእ/ር መንግሥት ማዕድ ይቀመጣሉ (ማቴ. 8:11)። ወገባችንን ታጥቀን ሙሽራው ሲመለስ በሰርጉ እራት ለመታደብ ዝግጁ መሆን አለብን (12:35–38)። ጽድቅን እየተጠማንና እየተራብን መምጣቱን እንጠባበቃለን (ማቴ. 5:6)።
❝እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም❞ (1 ቆሮ. 5:7–8.) [አንባቢዬ ይህንን ውጥረት እንዲያስተውል እጋብዛለሁ፡ ያለ እርሾ እንዳላችሁ ..አሮጌውን እርሾ አስወግዱ]
እስከዚያው ድረስ “ጽዋውን” በምሳሌ “ከወይኑ ፉት” እያለን ክርስቶስ ስለ ሐጥያታችን ያፈሰውን ደም እናስባለን። ደግሞም በህይወታችን “ከመከራው ፉት” እያልንና ከመካከላችን እርሾን አስወግደን ፋሲካን ያለ ግፍ እናከብራለን። ይህ እራት የከበረ እራት ነው፡፤ እራቱም የሚመጣውን ሐይል አሁን በዚህ ዓለም ላይ የምንቀምስበት እና መመለሱንም የምናውጅበት መንገድ ነው!
❝ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን❞

