
መስቀልና አስተርዕዮተ-እግዚአብሔር
▶️ በስቅለቱ ዋዜማ ስለ መገለጥ በጥቂቱ (Few words on Theological Methodology)
ከሁለት ዓመት በፊት፣ በዚሁ በሕማማቱ ሰሞን፣ መስቀልና ዙፋን በሚል ርዕስ ተከታታይ የሆነ ጽሑፎች አቅርቤ ነበር። መስቀሉ ከመንግሥቱ ጋር ያለውን መስተጋብር፣ ድካም ከኃይል ጋር ወዘተ…ለመዳሰስ ተሞክሯል። በደሙ መንግሥቱ ተመርቃለች። ባለፈው ዓመት እንዲሁ፣ “መስቀልና ኪዳን” በሚል በተከታታይ፣ በክርስቶስ የመስቀል ሥራ እግዚአብሔር አዲስ ኪዳን እንደመረቀ፣ መስቀሉን ከኪዳን አንጻር ተመልክተናል። በደሙ ኪዳን ተመረቀ። በዚህ ዓመት ደግሞ፣ መስቀሉና ሥርየት በሚል ተከታታይ ለመለጠፍ አላማ ነበረኝ። ምንም እንኳ ይህ አላማዬ ግብ ባይመታም። በእነዚህ ሁለት ልጠፋዬ ግን በአጭሩ መስቀሉን ከአስተርዮተ-እግዚአብሔርና ከሥርየት ጋር መመልከት ጀምረናል።
“We can’t talk about God behind his back. It’s crucial that one develops a sense of thinking and speaking in the presence of God” John Webster
“እንዴት?” የሚለው ቃል ብዙ የማይጠየቅና እምብዛም ሥፍራ የማይሰጠው ጥያቄ ነው። በተለይ በእኛ በኢትዮጵያዊያንና በኤርትራዊያን መካከል። እግዚአብሔር እንዴት ይታወቃል? ነገረ መለኮትስ እንዴት ይዋቀራል? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አማኖች እንዴት ይኑሩ?…እንዴት! ብሉይ ወደ አዲስ፣ አዲስስ ብሉይን እንዴት ያብራራዋል? ስለ እግዚአብሔር በድፍረት “እንዲህ ነው” ብለን እንዴት እንናገር! እንዴት! ልብ በሉ “ምን እንናገር” አላልኩም። እንዴት! ሆኖም ግን በነሲብ ይሁን በእውቀት “እንዴት” ለሚለው ጥያቄ መልስ ሳንሰጥ፣ ምንም ነገር ማድረግ አንችልም። «እግዚአብሔር ማን ነው?» ለሚለው ጥያቄ መልስ ከማግኘታችን በፊት፣ የሚቀድመው «እግዚአብሔር እንዴት ይታወቃል» ነው። ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢና ተገቢ መልስ ካላቀረብን፣ ሌላው ሁሉ በጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው።
ከዛሬ 200 ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ‹ቅርጽና ይዘት› የሚሏቸው መርሆች ነበሯቸው (Formal principle and material principle):: በእኔና በአንድ ሞርሞን እምነት ተከታይ መካከል “ኢየሱስየእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ነው” በሚለው አንጣላም። ሁለታችንም በቅርጽ እንስማማለን። የማንስማማው በይዘቱ ነው። እኔ ያንን ስል የማምነውን ሞርሞን አያምንም። በሌላ አነጋገር፤ ሁላችንም “መስቀል መስቀል” ማለታችን ያስማማን ወይም መስቀል ተኮር ያደረገን ሊመስል ይችላል። ኢየሱስን ደጋግመን ስለጠራን፣ ክርስቶስ ተኮር ነን ማለት አይደለም። ጥያቄው “ይህንን ስትል ምን ማለትህ ነው?” “እንዴትስ ታብራራዋለህ?” የሚለው ነው። አንድ ሰው፣ ‹ይህንማ አትጠይቅ! መለያየትን ያመጣል!› ሊል ይችላል። እኔ ደግሞ፤ ድሮውንስ አንድ መቼ ሆንና! በቅርጽ ተስማማን ማለት በይዘት ተስማማን ማለት አይደለምና። ጠያቂው ጥበብ ያለው ይመስላል። ግን በእውነቱ ከሆነ፣ “ውስጡን ለቄስ ብለህ ብቻ ተጓዝ” ማለቱ ነው። ወንጌልን በተመለከተ መሠረታዊ በሆኑት ነገሮች ላይ፣ በቅርጽም በይዘትም መሠረታዊ የሆነ አንድነት (መሰረታዊ የሆነ የሚለው ይሰመርልኝ፣ ምክኒያቱም በሁሉ ረገድ የሆነ ፍጹም ስምምነትን ስለማላወራ) ከሌለን “አንድ” ነን ማለት አንችልም። ክርስቲያናዊ አንድነት “የአዋጅ” ስምምነት ሳይሆን፤ የእምነት ስምምነት ነው። የዚህ ስምምነት ሥር መሠረቱ፣ ስለተሠቀለው ክርስቶስ መሠረታዊ በሆነው “ነገር ላይ” መስማማታችን ነው። ጌታም “አንድ እንዲሆኑ” ብሎ ሲጸልይ፣ እየደጋገመ “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል (ቁ.8 )…ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ (ቁ.14)….ቃልህ እውነት ፤ በእውነትህ ቀድሳቸው (ቁ.17)…የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም (ቁ.20-21)” ይላል። ትኩረቱ “ከአብ ወደ ወልድ ወደ ሐዋሪያቱ” በተላለፈልን መልዕክት ላይ ነው። ጳውሎስም “ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ” ሲል፣ ይህ አንድ ንግግር በምንባቡ አውድ መሠረት “የተሰቀለውን ክርስቶስን” በማመንና በማወቅ ረገድ የሆነ አንድነት ነው። ደግሞም ለጢሞቴዎስ “መልካሙን አደራ ጠብቅ” ሲል፣ በ2ጢሞ 1:9-11 እንደሚያብራራው የወንጌልን ይዘት እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ መገለጡን በቅርጽም በይዘትም በትክክል ለመገንዘብ መጣር አለብን። ስለ እግዚአብሔር “እንዴት” እናስብ? ስለ መስቀሉስ “ምን” እንናገር?
ስለ እግዚአብሔር ስናስብ «በጽንሰ ሃሳብ» መጀመር ራሱን የቻለ አደጋ አለው። ምክኒያቱም እግዚአብሄር ራሱን በጽንሰ ሃሳብ አልገለጠልንምና ነው። እግዚአብሔር ራሱን የገለጠልን «በቃልና በሥራ፣ በድነት ታሪክ ውስጥ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት» ነው። በተለይ ነገረ መለኮትን “በሥልት” ለማቅረብ ስንፈልግ ትልቅ አደጋ በፊታችን የሚጋረጠው ከዚህ የተነሳ ነው። ይህ ማለት ግን ስለ እግዚአብሔር ስናስብ ይሁን ነገረ መለኮትን በዚህ መልኩ ስናዋቅር “ጽንሰ ሃሳብ” አንጠቀምም ማለት ግን ፈጽሞ አይደለም። ፈጽሞ። ትልቁ ጥያቄ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን መገለጥ በዚህ ዓይነት ጽንሰ-ሃሳብ፣ አሊያም በዚህ አገላለጽ፣ ወይም በዚህ ሞዴል ስናቀርብ ይህ አገላለጽ ‹አግባብነት አለው ወይስ የለውም? (does it have biblical warrant or theological precedence)፣ ደግሞስ መሆን አለመሆኑስ የሚዳኘው እንዴት ነው?› የሚሉት ናቸው። ይህ አይነቱ አጠናን፣ በባሕርይው “ሁለተኛ መደብ” ነው። በዚህ መልኩ “ሥልታዊ” ጥያቄዎችን ስንጠይቅ፣ ጥያቄው “ጥቅልና ኢታሪካዊ” (deductive and ahistorical) ነው። ከዚያ በፊት የድነት ታሪክን ቅደም ተከተል ጠብቆ፣ የአስተርዮ ዕድገትን የመመርመርና የማስተፃመር ትንተና ሊቀድም ይገባል። ባለፈው ልጠፋዬ ማስረዳት እንደሞከርኩት፣ “ምን ተጻፈ” ከሚለው እኩል “እንዴት ተጻፈ” የሚለውም ወሳኝ ነው። የመጽሐፉን ይዘት ብቻ ሳይሆን፣ የጽሁፉ አወቃቀርና አቀማመጥ ራሱ መለኮታዊ እቅድ አለው። እንዲህ አይነቱን ጽሁፋዊ ሐቲት፣ ሳናደርግ ወደ ነገረ መለኮታዊ ድምዳሜ መድረስ፣ ሒደቱን ‹እንደማስወረድ› ነው።
ወደ ኋላ ትንሽ እንመለስ። ረቂቅ የሆነን አንድን ነገር ለማብራራት ስንፈልግ የተለያዩ «ሞዴላትን» እንጠቀማለን፡፡ ለዚህ ነው ሰባኪዎች በከተማ ይሁን በገጠር፣ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ላጠናቀቀ ለተማረው ኀይል ይሁን፣ ማንበብና መጻፍ ለማይችለውም ላልተማረው ኀይል፣ መልዕክታቸውን ምሳሌዎችን በመስጠት የሚያብራሩት። ይህ ጥረታቸው ረቂቅ የሆነውን ነገር አድማጩ “እንዲዳሰስው” ለማስቻል ነው። ሆኖም ግን «ሞዴል» በዋነኛነት ደረጃ “ዝንፍ” ነው። የሚገልጸውን ረቂቅ ነገር ለማብራራት ሲል የሚያዛንፈው ሌላ ነገር አለ። ለምሳሌ፡ የለመድነው የምድር ካርታ በርግጥ የተዛነፈ ነው። በጠፍጣፋ ወለል ላይ ተዘርግቶ በትክክል ለማሳየት ሲል፣ ካርታ የምድርን ቅርጽ ያዛንፋል። ይህን ለማየት፡ ድብልብል ኳስን አፈንድተን በወለል ላይ ለመዘርጋት ብንሞክር ግልጽ ይሆንልናል። ክብን ወደ ልሙጥ ወለል መተርጎም ስለማይቻል። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ሞዴል “የሚያብራራውን” ነገር ግልጽ ለማድረግ ሲል፣ የተብራሪውን ሌላኛውን ገጽታ ያዛንፋል። በካርታ ሳይንስ ውስጥ፣ ብዙ ገጽታና መልክ ያላትን ምድር በካርታ ሞዴል ለማስቀመጥ ሲባል፣ ይኽም ውስብስቡን እውነታ ለተወሰነ ግልጋሎት ጥቅም ላይ የሚውል ሞዴልን ለማቅረብ፣ ዝርዝሩን በደፈናው ያቀርባል “[cartography is] an act of generalization to make sense out of an infinitely complex world” ሆኖም ግን የኮምፕዊተር የካርታ ሳይንስ እጅግ ከመርቀቁ የተነሳ (geoinformation science) ከሳተላይትና ከተለያዩ ምንጮች የሚመጡትን “መረጃዎች” (geospatial big data) በሞዴል ለማስቀመጥ፣ ካርታውን የሚነድፉ ኢንጂነሮች፣ ለግልጋሎቱ ሲሉ “ጥሬውን መረጃ\ raw data” ወደ “ሞዴልነት” ለመለወጥ፣ መምረጥ፣ አንዱን ማጋነንና መረጃውን ወደ ምስል መተርጎም ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ‹አንድ ሞዴል ስለ አንድ እውነታ “የሚከስተው ምሥል” በመሠረቱ የተዛነፈ ነው› ማለት ነው። ውስብስቡን እውነታ ከረቀቀ ሁለንተናው ‹በአንድ ጊዜ› ማቅረብ ስለማይችል። ይልቁን፣ “አንድን እውነታ\reality” በሥዕላዊ መንገድ ለማቅረብ፣ ከአንድ በላይ የሆኑና ከተለያየ አንጻር የቀረቡ፣ የተለያዩ ሞዴሎች ያስፈልጋሉ ማለት ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ሞዴል በምስል እንዲከሰት፣ ኢንጂነሩ በፊቱ ያለውን “ጥሬ መረጃ” (Raw Data) መተርጎም አለበት። የመሬትን አቀማመጥ (terrain) “እንዴት በካርታ ይከሰት?” ብቻ ሳይሆን ትርጉም በሚሰጥ መልኩ “እንዴት ይቅረብ?” የሚለውም መሠረታዊ ነው። ከካርታ ሳይንስ ወጥተን ወደ ሕክምና ሳይንስ ስናመራም፤ ልክ የካርታ ሳይንቲስቱ ሞዴል እንደሚቀምር ሁሉ፣ ሳይንሱንም የሚቀምረው ሳይንቲስት አለ። ይህም ሳይንስ ብዙ እንደሚባልለት፣ ንጹሕ ነባራዊ (purely objective) አለመሆኑን ያሳየናል። አንድ “ጥሬ መረጃ” “ምን ማለት ነው?” የሚለውን በሳይንስ አዋቂያን ማኅበረሰብ የሚተረጎምና ውጤቱም በዚሁ ማኅበረሰብ የሚዳኝ ነው። አንድ ሳይንስ “ሳይንሳዊ” መሆን አለመሆኑን የሚዳኝ የሳይንስ ፍልስፍና አለ ማለት ነው። በዘመናዊው የሳይንስ ፍልስፍና፣ ለምሳሌ ያህል፣ “Methodological Naturalism፣” ልዕለ-ፍጥረት የሆነ እውነታ ከሳይንስ ግምገማ ውጪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሳይንስ የማይቀበለው ቅድመ-ግንዛቤ ነው። ይህ ግንዛቤ፣ በዳርዌንያን ፍልስፍና (naturalistic presupposition) ይሁን በዝግ-ዓለም ፍልስፍና (Deism)፣ ‹ልንመረምረውና መርምረን ልናውቀው ከምንችለው ግዑዙ ዓለም ያለፈ ሌላ ልዕልና› የለም ባይ ነው። ይህ ፍልስፍና ለዘመናዊው ሳይንስ መነሻ ፍልስፍናው ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ቅድመ-ግንዛቤ ያዋቀሩት “ሳይንቲስቶች” ለሚመለከቱት ጥሬ መረጃ (raw data) ለሚሰጡት “ትርጓሜም” ጭምር ነው (interpretation of the data)። ከዚህ የተነሳ ሳይንስ በቅድመ ግንዛቤው አስቀድሞ ቅርጽ እንዲይዝ ተገዷል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት የተሰጠን አስተርዮተ እግዚአብሔር ከላይ ከሰጠኋቸው ሁለት ምሳሌዎች ጋር እናመሳስል። እግዚአብሔር ራሱን ገልጦልናል። ራሱንም የገለጠልን በቃልና በሥራ ባከናወነው ትርክት ውስጥ ነው። ይኽም፣ በዋነናነት ደረጃ “አስተርዕዮ” ኪዳናዊ ነው። እግዚአብሔር ስለራሱ የነገረን፣ ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት አማካኝነት ነው። ይህም ግንኙነት ኪዳናዊ ነው፦ ታላቁ ንጉሥ (the suzerain king) በመንግስቱ ውስጥ ካሉ ሁሉ ጋር ያለው “በፍቅርና በታማኝነት\ ኸሰድ-ቨ-አመት” ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ነው። ይህ ግንኙነት ‹አስተርዕዮ ያረገዘ› ግንኙነት እንዲሆን የታቀደ በመሆኑ፣ በግንኙነት ውስጥ የሚከሰቱት ቃሎቹና ሥራዎቹ ስለ እርሱነቱ ይናገራሉ። በግንኙነቱ ውስጥ እግዚአብሔር ለዚያ ትውልድና ለመጪው ስለራሱ እየተናገረ ነው። ከዚህ የተነሳ በአንድ ወቅትና በአንድ ሥፍራ ጌታ የተናገረውና ያደረገው፣ ለመጀመሪያዎቹ ተደራስያን “የተስፋ-እምነት” ግንኙነት መኖሩ ብቻ ሳይሆን (ተሥፋ ሰጥቶ እምነት ጥየቃ)፣ ይህ ግንኙነት ለመጪው ትውልድ፣ ያንንኑ ተስፋ በመፈጸም፣ ለዚህኛው ትውልድ ደግሞ “የፍጻሜ-እምነት” ግንኙነት ያደርጋል (ተስፋ ፈጽሞ እምነት ጥየቃ)።
እዚህ ጋር ቆም ብለን አንድ ነገር እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ፣ መገለጥ (አስተርዕዮ) ያተኮረው፦ (1) በማንነቱና (2) በመለኮታዊ ዓላማው ዙሪያ ነው። መለኮታዊ ማንነቱን እና ፈቃዱን የገለጠልንም “በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ (abstract categories)” አሊያም “በእምነት መግለጫ አንቀጻት” (አንቀጽ 1፣ አንቀጽ 2፣ ወዘተ…እያለ such as Dogmatic Theology) አይደለም። ልድገምና እነዚህ ሁለቱም አስፈላጊና አግባብ ያላቸው የአጠናን ዘዴዎች ናቸው። ግን እግዚአብሔር እንደዚያ ራሱን አልገለጠልንም። በሁለተኛ ደረጃ፣ አስተርዕዮ አስተርዕዮ የሚሆነው፣ ከሥራው በኋላ ተከትሎ የሥራው “ፍቺ” ምን እንደሆነ እግዚአብሔር ራሱ ያብራራ እንደሆነ ነው። አንድን ክንዋኔ እግዚአብሔር ለምን ዓላማ እንዳደረገው ከእግዚአብሔር በስተቀር ሊናገር የሚችል ፍጡር የለም። በርግጥ ሐሳቡ ከሐሳባችን የራቀ ነው። “የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም”! በቃልና በሥራ ያደረገው ሁሉ መለኮታዊ ሥራ ቢሆንም፣ ከሥራው በኋላ ተከትሎ ራሱ እግዚአብሔር ማብራሪያውን ካልሰጠን በስተቀር፣ ሥራው “ሚስጢር” እንጂ “መገለጥ” አይደለም። ቀመሩ ይህንን ይመስላል፦ ቃል\ሥራ + ማብራሪያ = መገለጥ። እሥራኤልን ከግብጽ ካወጣ በኋላ፣ ለምን እንዳወጣት አላማውን በሙሴ በኩል በሲና ተራራ ማብራሪያ ባይሰጥ ኖሮ፣ አላማው ሚስጢር ሆኖ በቀረ። ምክኒያቱም ሕዝብ ከሥፍራ ወደ ሥፍራ መፍለስ በጥንታዌው ዓለም የተለመደ ክስተት ነበር። ደግሞም እግዚአብሔር እሥራኤልን ብቻ አይደለም ያወጣው፣ “እስራኤልን ከግብጽ፣ ፍልስጥኤማውያንን ከከፍቶር፣ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?” (አሞጽ 9:7)። እሥራኤልን ልዩ ያደረጋት የመግቦት ሥራው አይደለም። የመግቦት ሥራው ሲከሰት አይተን እናመሰግናለን እንጂ፣ ከመግቦቱ ጀርባ ያለው ዓላማ እምብዛም አይገባንም። ለምን አንዳንድ ልብ የሚሰብሩ ነገሮች በቅዱሳኑ ሕይወት ውስጥ እንደሚያልፍ ከእግዚአብሔር በስተቀር የሚያውቅ የለም (ምንም እንኳ አንዳዶቻችን ቢቃጣንም)። ክርስቶስን ስናየው ያን ጊዜ እንደታወቅን እናውቃለን። ይህ ሁሉ ትርጉም አልባ አይደለም። ሊሰመርበት የሚገባው፣ እግዚአብሔር ሠራ ማለት፣ ለምን እንደሰራ ካልተብራራ፣ ሚስጢር እንጂ አስተረዕዮ፣ አይደለም።
ኢየሱስ በእንጨት ላይ እንደተሰቀለ፣ ብዙ አይሁዳዊ ወጣቶች ተሰቅለዋል። የሮሙ ንጉሥ ቲቶ፣ የአይሁድ አብዮት በተነሳ ጊዜ (66-70ዓ.ም.) በየቀኑ ወደ 500 መቶ አይሁዳውያን ይሰቀሉ እንደነበር ጆሲፈስ ነግሮናል። ምን አይነት አሰቃቂ ሞት እንደሆነ ይጽፍልናል (Jewish War 7 §203)። የኢየሱስን ሞት ከእነዚህ ምን ለየው? እንዲያውስ ሁለት ወንበዴዎች አብረውትስ ተሰቅለው አልነበረምን? በአንድ እጅ፣ የኢየሱስ ሞት መለኮታዊ እጅ እንዳለበት በክስተቱ መረዳት ይቻላል። አሟሟቱ ስለሞቱ በጥቂትም ቢሆን ተናግሯል። መቶ አለቃው። ወንበዴው። የተገለጠላቸው ነገር ነበር። ሆኖም ግን፤ ከሞቱ በኋላ የአራቱ ወንጌላት ማብራሪያ ባይኖር ኖሮ “ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” ወይም ደብዳቤያት ማብራራሪያ ባይሰጡን “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” “ለምን ሞተ?” የሚለው ከጥቂት በስተቀር፣ ሚስጢር ሆኖ በኖረ።
ለዚህ ነው ሮሜ ሲከፍት (1:1-7) እና ሲዘጋ (16:25-27) ወንጌል “አስቀድሞ የተሰጠ-ተስፋ አሁን የተፈጸመ፣ አስቀድሞ ሚስጢር ሆኖ የነበር አሁን ግን የተገለጠ” የሚለው
“በዘላለማዊ አምላክ ትእዛዝ ሕዝቦች ሁሉ አምነው እንዲታዘዙ፣ በነቢያት
መጻሕፍት አሁን በተገለጠው፣ ላለፉት ረጅም ዘመናት ተሰውሮ በነበረው
ምስጢር መገለጥ መሠረት፣ በአስተማርሁት ወንጌልና በኢየሱስ ክርስቶስ
መሰበክ ሊያጸናችሁ ለሚችለው፣ እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ፣
በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን”
መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢውን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ የታመነ ካርታ/መንገድ ነው። ሆኖም ግን ካርታውን በትክክል ከቅዱስ ቃሉ ማዋቀር የአንባቢው ድርሻ እንደመሆኑ፣ በትክክል ያልተነበበ ካርታ ወደ ገደል እንደሚያመራ በማወቅ፡ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በዚህ ርዕስ ብዙ የምለው ቢኖርም፣ ለአሁን ግን እዚህ ጋር ይብቃኝ።
“The purpose of all theology is to arrive in the presence of God, receive his message and go back into the world with the light of his presence, so that the world may know again that light which lit it up at creation. Jesus has revealed God’s heart. Don’t be satisfied with a swim at the beach. Take up your map and launch out into the deep!”
___Stephan Dempster, “Cartography, Photography and Biblical Theology: Discerning the Big Picture of the Bible” excerpt from his forthcoming book in 2020??

