Articles,  Blog,  ትምህርተ ክርስቶስ,  የአዲስ ኪዳን ነገረ-መለኮት

ልደቱና የእግዚአብሔር ተስፋ ቃሎች (ኪዳንና ትሥጉት)

ሐዋሪያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና” ይለናል (2 ቆሮ. 1:20)። ያለ ኢየሱስ የተስፋ-ፍጻሜ የለም። ማንም ኢየሱስን ዘሎ በቀጥታ የእግዚአብሔርን ተስፋ የሚወርስ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም። ያለ ኢየሱስ የሚጠብቀን “ፍርድና ርግማን” ብቻ ነው። በብሉይ የተሰጡትን ተስፋዎች ሁሉ አንድ አማኝ የሚቀበለው “በክርስቶስ” ውስጥ ነው። ይህንን ለማስረዳት፣ በምናባችን “ማጥለያ” እናስብ። ከላይ የሚጨመረው ዘይት ወደ ጠርሙሱ ጠሎ የሚገባው በማጥለያው ጠባብ አፍ አልፎ ነው። ይህንን ጠባብ አፍ እንደ “ክርስቶስ” አድርገን ብንወስድና ዘይቱን እንደ ተስፋ ቃሎቹ ብንመለከት፣ ጳውሎስ የሚናገረውን እውነታ ያብራራልናል፣ ብዬ አስባለሁ። ለምን ተወለደ? የእግዚአብሔርን ተስፋ እውን ሊያደርግ፤ እግዚአብሔርን እውነተኛ ሊያደርግ ተወለደ። ወረድ ብለን እንደምናየው ኢየሱስ “ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ” ተወለደ (ሮሜ 15:8)።

የአሜሪካኑ 44ኛው ፕሬዚደንት ቦራክ ኦባማ በምርጫው ውድድር ሰዓት፣ “አደርጋለሁ” ብሎ የገባቸው 533 ተስፋዎች ወይም “Campaign promises” ነበሩ። እንደ “ፗሊቲፋክት” ዘገባ ከሆነ፣ ኦባማ ከስምንት ዓመታት የአመራር ቆይታው በኋላ አደርጋለሁ ካላቸው 48.4 ፐርሰንቱን በትክክል ሲፈጽም፣ 27.4 ፐርሰንቱን ደግሞ ከሞላ ጎደል (compromise)፣ የተቀረውን 24.2% ግን ሳይፈጽም ቀርቷል (promise broken)። ኦባማ ሰው እንደመሆኑ መጠን፣ «ተስፋ የገባውን ሙሉ በሙሉ መፈጸም ይችላል» ብለን ስለማንገምት፣ «ይህ አስገራሚ የአመራር ብቃት ነው» ወደ ማለት ድምዳሜ ያደርሰናል።

እግዚአብሔር ግን ሰው አይደለም። በእርግጥ ኢሳያስ ያህዌህ ሕዝቡን ዳግም እንደሚታደግ አስቀድሞ አይቶ፣ ከባቢሎን ምርኮ ባሻገር በፍርድ ሥር የምትማቅቀውን ኢየስሩሳሌምን ሲያጽናና በያህዌህ ታማኝነት ላይ ተመስርቶ ነበረ። የኢሳያስ ትንቢት ሊቅ የሆነው ዖስዋልት (John N. Oswalt) የኢሳ ፵ ትንቢት በሶስት ጥያቄዎች ዙሪያ ላይ እንዳጠነጠነ ይነግረናል። እነርሱም፦ ያህዌህ እንደገና ሕዝቡን ሊታደግ (፩) ፈቃደኛ ነው? (፪) ይችላል? (፫) ያደርገዋል? የሚሉ ነበሩ። ሦስቱም ጥያቄዎች ያነጣጠሩት በያህዌህ ማንነት ዙሪያ ላይ ነው። ያህዌህ «ሊይድነን ይፈልጋል?» ለሚለው ጥያቄ መልሱ አዎንታዊ ከሆነ [አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ]፣ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው፣ “በርግጥ ሊያድነን ይችላልን?” የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ በእግዚአብሔር «ብቃት» ላይ የተመረኮዘ ጥያቄ ነው። አደርጋለሁ ብሎ ተስፋ መስጠት አንድ ነገር ነው። የሰጠውን ተስፋ መፈጸም ‹መቻል› ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ኢሳያስም ሲመልስ፦

____“ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው?…እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ?”

ስለዚህ ያህዌህ ሕዝቡን ለመታደግ ፈቃደኛ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ለመታደግም ሙሉ ብቃት አለው። ይለናል። ግን ደግሞ አንድ ሰው ማድረግ ፈልጎ ያንንም ለማድረግ ብቃት ኖሮት፣ ግን የተስፋ ቃሉ የሚፈጸምበት ሰዓት ሲደርስ “ቃል አባይ” መሆን ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ይህ ሦስተኛው ጥያቄ ‹የታማኝነት› ጥያቄ ነው። ያህዌህ “ታማኝ” ነውን? ለዚህም የአዋጅ ነጋሪው ድምጽ ሲመልስ:-

____“ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች” ይላል።

ሰው ሃላፊ ነው። ሁሉም ነገር ተሸጋጋሪ ነው። ያህዌህ የሰጠው ቃል ግን ዘላለማዊ ነው። አደርጋለሁ እንዳለ ለማድረግ ይችላል። ቃሉም ሊታጠፍ ስለማይችል፤ እንደተናገረው ይፈጸማል። ቃሉ ከምታልፍ ሰማይና ምድር ብታልፍ ይቀላል።

ስለዚህ ያህዌህ የምሥራቹን ቃል “አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ” ብሎ ሲናገር፣ ከላይ የዘረዘርናቸውን ሦስቱንም ጥያዌዎች ሊመልስ ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማዳን ይፈልጋል፣ ሊያድንም ይችላል፤ ሰዓቱም ሲደርስ፤ ቃሉን ሳያጥፍ ያድናቸዋል። ስለዚህ ሰብሰብ ለማድረግ፣ ከኢሳ 40:1 እስከ 41:7 ያለው ክፍል በሦስት አበይት ክፍል ራሱን ይከፋፍላል።

(፩) [40:1-11] የመጀመሪያው ከ40:1-11 ያለው ክፍል ነው። ይህም “የአዋጅ-ነጋሪ” በሚሉ ድምጾች በሦስት ተጨማሪ ንዑስ ክፍሎች ይከፍላል። እነዚህም [ሀ] ታዳጊው ይገለጣል ብለህ ጩኽ (40:3-5)፣ (ለ) ታዳጊው ቃሉ አይታጠፍም ብለህ ጩኽ (40:6-8)፣ (ሐ) ታዳጊው «እረኛና ጦረኛ» ሆኖ ይገለጣል ብለህ ጩኽ (40:9-11)። እነዚህ “ሦስት” አዋጅ ነጋሪ መልክቶች፣ በሰው-አንደበት (40:3) ጀምሮ በመለኮት አንደበት ይጨርሳል (40:5)። ያህዌህ ወደ ምድር ይመጣል። ይህ ተስፋ ራሱ ኢሳያስ “”ምነው ሰማያትን ቀደህ ብትወርድ፧ () ለሚለው የጻድቅ ሰው ጩኸት ምላች ነው። ጥንት ሕዝቡን በምድረበዳ በሴይር ሊገናኛቸው እንደተገለጠ (ዘዳ. 33:2; መሳ. 5:4; መዝ. 68:4) እንደ ገና በክብር ያህዌህ ራሱ ይወርዳል። ይህ የሚመጣው “የእግዚአብሔር ክብር” ግን የሚገለጠውም ለሰው ዘር ሁሉ ነው።

(፪) [40:12-31] የእስራኤል አምላክ ያህዌህ ፈጣሪ አምላክ ነው (40:12-31)። ያህዌህ ሕዝቡን ማዳን ይችላል። ምክኒያቱም እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው። ሁሉም ነገር፤ ይህም በሰማይ ያለው ይሁን በየብስ፣ እንዲሁም በባህር የሚርመሰመሰው ፍጥረት ሁሉ የያህዌህ ፍጡር ነው። እርሱ ብቻ ፈጣሪ ሲሆን፣ ሌላው ነገር በሙሉ የተፈጠረ ነገር ነው (40:12:17)። ይህ ከሆነ ዘንዳ እርሱ ብቻውን ሊመለክ ይገባዋል (40:18-20)። እርሱ ሁሉን የሚቆጣጠርና የሚያስተዳድር ምጡቅ ስለሆነ (40:21–24) የሚስተካከለውና የሚወዳደረው የሌለው ምጡቅና ረቂቅ ነው (40:25–26)። ሆኖም ያህዌህ “ረቂቅና ምጡቅ ነው” ማለት “ሩቅ ነው” ማለት ግን አይደለም (40:27–31)። እርሱ ቅርብ ነው። ከፊቱ የተሰወረ ምንም ነገር የለም። ያህዌህ ሕዝቡን፣ የሰጠወንም ተስፋ አይረሳም።
“ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ። መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም (40:27–28)” ስለዚህ ለእንደዚህ አይነት አምላክ የምንሰጠው ምላሽ “ልባዊ መታመን” ነው (41:31)።

(፫) [41:1-7] በሦስተኛ ደረጃ የእስራኤል አምላክ የታሪክ አራማጅና የአሕዛብ ሁሉ አምላክ ነው። አምላካችን ሁሉን ቻይ ከሆነና ፈቃድ የማይለውጥ እንደሆን ለተስፋ ቃል ወራሾች ካጸናላቸው፣ የተስፋው ወራሾች እነማን ናቸው የሚለው ጥያቄ ተከታይ ጥያቄ ነው። በ41:1 ላይ ጠቅላላ የአሕዛብ ምድር ወደ ያህዌህ ፊት እንዲሰብሰቡና ሙጉቱን እንዲያደምጡ ጥሪ ያደርጋል። ሙጉቱም ያነጣጠረው ያህዌህ አሕዛብን ሁሉ የሚገዛ፣ ነገሥታትን የሚሾምና የሚሽር በመሆኑ ላይ ነው። “ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋላኞችም ዘንድ የምኖር እኔ ነኝ።” ሆኖም ግን ሙጉቱን ያህዌህ ሲያቀርብ፣ አሕዛብ ተያይተውና ተያይዘው ወደ “ጣኦት” ተመለሱ እንጂ ያህዌህን ለማምለክ አልተንበረከኩም (41:6-7)። ስለዚህ ያህዌህ ወደ ቃል-ኪዳን ህዝቡ መለስ በማለት “ባሪያዬ እስራኤል፥ የመረጥሁህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ” ይላል። ኢሳያስ 40-54 ያለውን ሙሉ አውድ መቃኘት ባንችልም፤ ነገር ግን ልክ ያህዌህ የድነትን ተስፋ በመስጠት ጽዮንን እንዳጽናናት (40:1-31) እንዲሁም አሕዛብ የድነትን ማጽናናት ይሰማሉ (41:21–42:17)። ጣኦታት ታሪክን ማቀናበርና ማራመድ አይችሉም። ያህዌህ ግን እርሱ እንደሆን ራሱን ያስመሰክራል (41፡21-24)።

____“ክርክራችሁን አቅርቡ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ማስረጃችሁን አምጡ፥ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። ያምጡ፥ የሚሆነውንም ይንገሩን፤ ልብም እናደርግ ዘንድ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ ዘንድ፥ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፥ የሚመጡትንም አሳዩን። አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ እንደነግጥም ዘንድ በአንድነትም እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ።”

በ41:29 ላይ እና በ42:1 መጀመሪያዎች ላይ ያሉት ሁለት “እነሆ” የሚሉት ቅንጣቶች የሚያሳዩን፣ ያህዌህ የምድር ሁሉ ጌታ ከሆነ (41:1-7) እና ጣኦታት “ነፋስና ኢምንት” ብቻ ከሆኑ (41:21-29)፤ አንደኛ፣ አሕዛብ የያህዌህ በመሆናቸው ወደ እርሱ በንስሃ ሊመለሱ የተገባ መሆኑን ለማሳየት ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ ይህንን አለም አቀፍ ተልዕኮ (አሕዛብን ወደ ያህዌህ የመመለስ ተልዕኮ) ተረካቢው ማን እንደሆን ለማሳየት ነው (42:1-9)። ይህ መልክተኛ ያህዌህ “ባሪያዬ” ይለዋል

____“እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል…አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ…ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ።”

ስለዚህ ይህ የጌታ ባሪያ “ሕዝቡን እስራኤልንና አህዛብን” በአንድ ላይ ገጥሞ ትድግናውን ወደ ብርሃን የሚያወጣ አገልጋይ ነው። በኢሳ 42:10-17 የዚህን ባሪያ የቤዝዎት ሥራ ተከትሎ “ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋና” ይስተጋባል። ምክኒያቱም ድነቱ ዓለምን ሁሉ ስላካለለ።

ስለዚህ የኢሳ 40:1-42:9 ጽሑፋዊ መዋቅር የሚያስረዳን፤ ያህዌህ ሕዝቡን ሊታደግ በክብር እንደሚገለጥ የጀመረው ትረካ፣ በዚህ መንፈሱን በሚያሳርፍበት ‘ባሪያ’ መጠናቀቁ፣ ይህ ባሪያ የያህዌህ ትድግና መሳሪያና መገለጫ መሆኑን ነው። በርግጥ የጌታችንን የኢየሱስ አገልግሎቱን በተመለከተ፤ ሦስቱም ወንጌላውያን ሲጠመቅ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ” የሚለው ሐረግ (ማቴ 3፡17)፣ በተለይ ከፈውስ አገልግሎቱ ጋር ተያይዞ ይህንን የኢሳያስ 42:1-9ን ተስፋ ኢየሱስ እንደፈጸመ ማቴዎስ በቀጥታ ያገናኝልናል (12:16-21)።

“ለምን ተወለደ?” የሚለውን ጥያቄ አንስተን በሦስት መልኩ ለመመለስ እንሞክር። የመጀመሪያን እንመልስና የተቀሩትን በሚቀጥሉት ልጠፋዬ ላዳስስ።በመጀመሪያ የተወለደው የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃል ለመፈጸም ነው። ምድርን ሁሉ፤ አይሁድንና አሕዛብን፤ ሰማይንና ምድርን በአንድነት ከያህዌህ ጋር ለማስታረቅ ተወለደ። ይህም አስቀድሞ የሰጠው ተስፋ ፍጻሜ ነው። እግዚአብሔር ሊዋሽ አይችልም። የሰጠውን ተስፋ ይፈጽማል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር “እውነት” ነው። እውነት የሚለው ቃል፤ የእግዚአብሔን ኪዳናዊ ታማኝነት የሚያጎላ ቃል ነው። እግዚአብሔር “እሙን” ነው። ወልድ ወደ ምድር ሰው ሆኖ ባይመጣ ኖሮ፣ እግዚአብሔር የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች በሙሉ ‘እውን አይሆኑም ነበር። እግዚአብሔር ‘ዋሾ’ ይሆን ነበር። ለዚህ ነው ሐዋሪያው ጳውሎስ

____“ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ደግሞም። ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ ለስምህም እዘምራለሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ፥ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር እውነት የመገረዝ አገልጋይ ሆነ እላለሁ።”

ኢየሱስ ሰው ሲሆን፣ የወረሰው ዘር የአብርሃምን ዘር እንጂ፣ ሶሪያዊ አሊያም ግብጻዊ፣ ወይም ኢትዮጵያዊ አልሆነም። እነዚህንና የተቀረውንም የሰውን ዘር ሁሉ (አሕዛብን) ሊወክል ግን ‘አይሁዳዊ’ ሆነ። ወይም በጳውሎስ አነጋገር ‘የመገረዝ አገልጋይ” ሆነ። ለምን? ምክንያቱን በሁለት “ዘንድ” ብለው በሚያልቁ አረፍተ-ነገሮች ይገልጽልናል። አንደኛ “ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ።” ለአባቶች ሲል ለአብርሃም፤ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ማለቱ ነው። እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ተስፋና በመሃላ ያሰረውን ኪዳን፤ ኋላም ለይስሐቅና ለያዕቆብ አድሶላቸው፤ በእስራኤላውያን ኪዳን (የብሉይ ኪዳን) የመጀመሪያ ደረጃ ፍጻሜውን ካገኘ በኋላ በሙላት በአዲሱ ኪዳን ፈጽሟል። ስለዚህ ክርስቶስ “የመገረዝ አገልጋይ” ሆነ። ለምን? ስለ እግዚአብሔር “እውነት” ሲል። እግዚአብሔር ታማኝ ይሂን ዘንድ። ክርስቶስ ውደ ምድር መጥቶ፣ የአብን ፈቃድ ፈጽሞ ባይመለስ ኖሮ፣ እነዚያ ሁሉ ተስፋዎች ‹ላም አለኝ በሰማይ› ሆነው በቀሩ ነበር። እግዚአብሔርም የተናገርውን ተስፋ መፈጸም ባለመቻሉ፣ በነብዩ ኢሳያስ በኩል ለሕዝቡም ይሁን ለአህዛብ የሰጠው የድነት ተስፋ፣ “እኔ እችላለሁ! አድናለሁ!” ያለው ሁሉ ሳይፈጸም ይቀር ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ በመጀመሪያ ደረጃ “ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር እውነት የመገረዝ አገልጋይ ሆነ እላለሁ” ይላል። ክርስቶስ፣ ያ በኢሳያስ “ባሪያዬ” የተባለው፣ ለሕዝቡ ቃል-ኪዳን፣ ለአሕዛብም ብርሃን በመሆኑ “እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን” ሆኗል። የእኛም እድል ፈንታ “አሜን” ማለት ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር እውነት፤ እግዚአብሔርን ፈቃድና ዓላማ ሊያከናውን፤ እግዚአብሔር ታማኝ ይሆን ዘንድ ተወለደ። አሜን!

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.